Wednesday, March 22, 2023

የአፍሪካ አገሮችን በጅምላ የመውጣት ጥረት የማስቆም የአይሲሲ ፈተና

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኮሶቮና የሩዋንዳ ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀል ትራይቡናሎችን ልምድ መሠረት አድርጎ የተዘጋጀው የሮም ስምምነት፣ እ.ኤ.አ. በ1998 የዓለም አቀፍ ወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) እንዲቋቋም አስችሏል፡፡ ስምምነቱ ከመነሻው ጀምሮ ባደጉና በማደግ ላይ ባሉ አገሮች መካከል ውዝግብ የፈጠረ ነው፡፡ 120 አገሮች ስምምነቱን የፈረሙ ቢሆንም በፍርድ ቤቱ ሥልጣን ላይ ስምምነት አልነበረም፡፡

በሐምሌ ወር 1994 ዓ.ም. ተግባራዊ መሆን የጀመረው የሮም ስምምነት የዓለም አቀፍ ወንጀል ፍርድ ቤት ለዓለም ሰላምና ደኅንነት ሥጋት የሆኑ እንደ ዘር ማጥፋት፣ በሰብዕና ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችንና የጦር ወንጀሎችን የሚፈጽሙ ወንጀለኞችን ሥልጣንን ከለላ በማድረግ ከተጠያቂነት እንዳያመልጡ ለማድረግ መቋቋሙን ይደነግጋል:: አገሮቹ በሮም ስምምነት የመጨረሻ ረቂቅ ላይ እንዳይስማሙ ያደረጋቸው የተፈጻሚነት ወሰኑ መጥበብና መስፋት ነው፡፡ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ወሰኑ ሰፍቶ እንደ ዘር መድልኦ ዓይነት ወንጀሎች እንዲካተቱ ይፈልጉ ነበር፡፡ ያደጉ አገሮች ግን ይህ ለፍርድ ቤቱ አሠራር አይመችም በማለት ሳይቀበሉት ቀርተዋል፡፡

በ1994 ዓ.ም. ሥራ የጀመረው የፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት የመጀመሪያው ዓቃቤ ሕግ አርጀንቲናዊው ሉዊዝ ሞሬኖ ኦካምፓ፣ ለአፍሪካ በጎ አመለካከት የላቸውም ተብለው ይታሙ ነበር፡፡ እሳቸውን የተኩት አፍሪካዊቷ ዓቃቤ ሕግ ፋቱዋ ቤንሱዳ ጋምቢያዊት ሲሆኑ፣ ምናልባትም የአይሲሲን የትኩረት አቅጣጫ ከአፍሪካ ሊያነሱ እንደሚችሉ ተገምቶ ነበር:: ይሁንና የአይሲሲና የአፍሪካ ግንኙነት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ይበልጥ እየተባባሰ ነው የመጣው፡፡ አፍሪካ ላይ ባልተገባ ሁኔታ ትኩረት አድርጓል ተብሎ የሚታማው አይሲሲ፣ በአሁኑ ወቅት እየመረመራቸው የሚገኙት ስምንት ጉዳዮች በሙሉ ከአፍሪካ ናቸው፡፡ በዚህ ጤነኛ ያልሆነ አዝማሚያ ምክንያት የአፍሪካ አገሮች በኅብረት ከአይሲሲ አባልነት ለመውጣት ስትራቴጂ እስከመቅረፅ ደርሰዋል፡፡

ይሁንና የአይሲሲና የአፍሪካ ግንኙነት አይሲሲ ከተቋቋመ በኋላ በነበሩት ጥቂት ዓመታትና የሮም ስምምነት ድርድር ወቅት ጥሩ የሚባል ዓይነት ነበር፡፡ የሮም ስምምነትን ካፀደቁት የመጀመሪያ 60 አገሮች መካከል 17ቱ ከአፍሪካ ነበሩ፡፡ ሴኔጋል የሮም ስምምነትን ለመጀመሪያ ጊዜ እ.ኤ.አ. በ1999 ያፀደቀች አገር ናት፡፡ አሁንም ቢሆን ከፍርድ ቤቱ 124 አባላት መካከል 34 ከአፍሪካ ናቸው፡፡ ይህም ከአውሮፓ ውጪ ትልቁ አኅጉራዊ ስብስብ ነው፡፡ ነገር ግን የፍርድ ቤቱ ሥራ አፍሪካን ብቻ የተመለከተ መሆንና የአፍሪካ ኅብረት ይህን አስመልክቶ የሚያቀርባቸውን ጥያቄዎችና የሚሰጣቸው ውሳኔዎች ግንዛቤ ውስጥ አለመክተቱ፣ አፍሪካውያንን ከአይሲሲ እያራቀ መጥቷል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የተወሰኑ አፍሪካውያን አይሲሲን በዘረኝነት መክሰሳቸውም አልቀረም፡፡ የኒዮ ኮሎኒያሊዝም መሣሪያ አድርገው የሚያዩትም አሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የአፍሪካ አገሮች በኅብረት ከአይሲሲ ለመውጣት ማሰባቸው የሚገርም እንዳልሆነ ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡ በተለይ አፍሪካ ኅብረትና አይሲሲ በሥራ ላይ ያሉ መሪዎችን የወንጀል ተጠያቂነት በተመለከተ ያላቸው ልዩነት፣ እ.ኤ.አ. በ2009 ይፋ ከሆነ በኋላ በነበሩት ዓመታት አዝማሚያው መታየቱን ያመለክታሉ፡፡

የአፍሪካ ኅብረት አይሲሲ በሥራ ላይ ያሉ መሪዎችን በወንጀል ተጠያቂ ለማድረግ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንዲያቆም በይፋ መጠየቁም ይታወሳል፡፡ የሕግ ባለሙያዎችም ልማዳዊ ዓለም አቀፍ ሕግ ይህንኑ እንደሚደግፍ ያመለክታሉ፡፡

የሁለቱ ተቋማት ልዩነት እየሰፋ የመጣውም እ.ኤ.አ. በ2009 አይሲሲ በሱዳን ፕሬዚዳንት በኦማር ሐሰን አል በሽር ላይ የእስር ትዕዛዝ ካስተላለፈው ውሳኔ ጀምሮ ነው፡፡ አይሲሲ በሽርን በዳርፉር የተከሰተውን እልቂት አቀናብረዋል ሲል ይከሳቸዋል፡፡ በሥራ ላይ ያለ መሪ በወንጀል ተጠያቂ ሲደረግ የበሽር የመጀመሪያው ነው፡፡ አይሲሲ እ.ኤ.አ. በ2007 በኬንያ ከተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታንና ምክትላቸውን ዊሊያም ሩቶን በሰብዕና ላይ ወንጀሎችን ፈጽመዋል ብሎ መክሰሱም በአፍሪካ ኅብረት አልተወደደም፡፡ የኬንያ መንግሥት ትብብር ባለማድረጉ ጉዳዩ መቋረጡን አይሲሲ ማስታወቁም ይታወሳል፡፡

ዶ/ር ሰለሞን አየለ ደርሶ ለአኅጉሪቱና ለአፍሪካ ኅብረት ዋነኛ የሰብዓዊ መብት አካል በሆነው የአፍሪካ የሰብዓዊና የሰዎች መብቶች ኮሚሽን በኮሚሽነርነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ለኮሚሽኑ በግጭቶች ውስጥ ስላለ የሰብዓዊ መብት ሁኔታና በድኅረ ግጭት የመሸጋገሪያ ፍትሕና በሰብዓዊ መብት መካከል ስላለው ግንኙነትም የመከታተል ኃላፊነት ተቀብለዋል፡፡

ዶ/ር ሰለሞን ግጭቶች ቀጥለው ባለበት ሁኔታ በሥራ ላይ ያለ መሪን በወንጀል ተጠያቂ ማድረግ ተመራጭ አካሄድ እንዳልሆን ይከራከራሉ፡፡ ‹‹ኦካምፖ በሽር ላይ የእስር ትዕዛዝ የጠየቁት የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ድርድር በማካሄድ ለዳርፉር ቀውስ መፍትሔ ለማምጣት እየሞከረ እያለ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ክሶች ለብሔራዊ ተዋንያን በቂ ውይይት አድርገው ለቀውሱ የፖለቲካና የሕግ መፍትሔ የማምጣት የፖሊሲ ክፍተት እንዳይዘጉ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

የበሽር የእስር ትዕዛዝ አሁንም ቢሆን ሁለቱ ተቋማትን ያላግባባ ዋነኛ ነጥብ ነው፡፡ ‹‹በሽር ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው አዲስ አበባ ላይ ታሰሩ እንበል፡፡ አሁን ዋናው ጥያቄ ከዚያ በኋላ ሱዳን ምን ትሆናለች የሚለው ነው፡፡ ሱዳን ብትበታትንና ብጥብጥ ቢነሳ ኃላፊነት የሚወስደው ማነው? እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ብዙ ጊዜ ግምት ውስጥ አይገቡም፤›› ሲሉ ዶ/ር ሰለሞን ችግሩን ከተለያየ አቅጣጫ ማየት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡

ይሁንና በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ ሕግ በሥራ ላይ ያሉ መሪዎችን የወንጀል ተጠያቂ መሆን ይችላሉ የሚል አቋም እንዳለው አስታውሰዋል፡፡ ‹‹እንዴት የሚለው ግን አሁንም አጥጋቢ ምላሽ አላገኘም፡፡ እስካሁን ድረስ ውሳኔ ያገኙ የአገር መሪዎችን የተመለከቱ የአይሲሲ ጉዳዮች የተከናወኑት መሪዎቹ ሥልጣን ከለቀቁ በኋላ ነው፡፡ የኮትዲቯሩን ሎረን ባግቦንና የላይቤሪያውን ቻርለስ ቴይለርን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በሥራ ላይ ያሉ መሪዎችን ክስ ግን ሕዝቡ ላይ ጉዳት በማያስከትል መንገድ እንዴት ይፈጸማል በሚለው ላይ ግልጽ የሆነ ስምምነት የለም፤›› ብለዋል፡፡

የአፍሪካ አገሮች አይሲሲ ያላግባብ ለይቶ እያጠቃቸው እንደሆነ ደጋግመው ቢናገሩም፣ አብዛኛዎቹን ጉዳዮች አይሲሲ እንዲያያቸው የመሩት ራሳቸው ናቸው፡፡ የኬንያና የኮትዲቯርን ግን አይሲሲ በራሱ ተነሳሽነት የጀመራቸው ናቸው፡፡

የሮም ስምምነት አይሲሲ ያለውን ጉዳዮችን የማየት ሥልጣን በአባል አገሮች ብቻ ሳይሆን፣ አባል ባልሆኑ አገሮች ላይ ጭምር እንዲሆን ያስችላል:: በስምምነቱ አንቀጽ 4 ላይ ልዩ ስምምነት ካለ አባል ባልሆኑ አገሮች ግዛት ውስጥ ፍርድ ቤቱ ሥልጣን ሊኖረው እንደሚችል የተገለጸ ሲሆን፣ በአንቀጽ 12(3) ላይ አባል ያልሆነ አገር የፍርድ ቤቱን ሥልጣን በማመልከቻ መቀበል እንደሚችል ተደንግጓል:: ሆኖም በአንቀጽ 13 ላይ ዓቃቤ ሕግ ጉዳዩ በተባበሩት መንግሥታት ድርድት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት ከተመራለት፣ ማመልከቻ ከአባል አገሮች ከመጣለትና በፍርድ ቤቱ ሥልጣን ሥር ያሉ ወንጀሎች ስለመፈጸማቸው መረጃ ካገኘ ምርመራ መጀመር እንደሚችል መደንገጉ፣ የዓለም አገሮች ኢትዮጵያን ጨምሮ በፍርድ ቤቱ ሥልጣን ላይ የተከፋፈለ አመለካከት እንዲኖራቸው አድርጓል::

የሁለቱ ተቋማት ግንኙነት እንደሻከረ ሲያዘግም ቆይቶ እ.ኤ.አ. ጥር 2017 ቢደርስም፣ በወቅቱ የተሰጠው የአፍሪካ ኅብረት ውሳኔ ግን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚለያዩ አስመስሎ ነበር፡፡ ‹‹ከአይሲሲ መውጫ ስትራቴጂ›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀው የውሳኔ ሐሳብ የአፍሪካ አገሮች በኅብረት እንዲወጡ በማለም የተረቀቀ ነው፡፡ እርግጥ ነው ሰነዱ አስገዳጅነት የሌለው በመሆኑ አገሮቹ በተናጠል ውሳኔ መስጠት ይችላሉ፡፡ በሰነዱ ላይ ናይጀሪያ፣ ላይቤሪያ፣ ሴኔጋልና ኬፕ ቨርዴ ልዩታቸውን ወድያው አስመዝግበው ነበር፡፡ ማላዊ፣ ታንዛኒያ፣ ቱኒዚያና ዛምቢያ ደግሞ ሰነዱን ለማጥናት ተጨማሪ ጊዜ ጠይቀዋል፡፡

በተጨማሪም ይህ የአፍሪካ ኅብረት ውሳኔ የመጣው ቡሩንዲ፣ ጋምቢያና ደቡብ አፍሪካ ከአይሲሲ እንደሚወጡ በይፋ ከገለጹ በኋላ ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ ከአይሲሲ ጋር ጥሩ ግንኙነት የነበራት ቢሆንም፣ እ.ኤ.አ. በሰኔ 2015 ለአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ደቡብ አፍሪካ የሄዱትን በሽርን ባለማሰሯ ውጥረት ውስጥ መግባቷ ይታወሳል፡፡

የአገሮቹና የአፍሪካ ኅብረት ውሳኔዎች ተደምረው የአፍሪካ አገሮች በጅምላ ከአይሲሲ ሊወጡ ይችላሉ የሚል ከባድ ሥጋት ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም፣ የቅርብ ሁኔታዎች ጉዳዩ እየቀዘቀዘ እንደመጣ ያመለክታሉ፡፡ እንደ ቡርኪና ፋሶ፣ ቦትስዋና፣ ጋናና ሴራሊዮን ያሉ አገሮች ከአይሲሲ መውጣትን ተቃውመዋል፡፡ ደቡብ አፍሪካና ጋምቢያ ደግሞ የቀድሞ ውሳኔያቸውን ከልሰዋል፡፡ የአፍሪካ አገሮች በአይሲሲ ላይ ያላቸው ቅሬታ ግን ቀጥሏል፡፡

 

አይሲሲ ከተቋቋመባቸው ዓላማዎች ዋነኛው ተጠያቂነትን ማስፈን ነው፡፡ አፍሪካ በአይሲሲ ላይ ያለው ቅሬታ አግባብነት የሌለውና የተጋነነ መሆኑን አንዳንዶች ይጠቅሳሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የአይሲሲ እንቅስቃሴዎች አፍሪካ ላይ ያተኮሩት በአኅጉሩ የሚፈጸሙት ወንጀሎች ከሌሎች አካባቢዎች ስለማይነፃፀሩ ነው የሚል መከራከሪያ ሲቀርብ ይስተዋላል፡፡ አይሲሲም ራሱን የሚከላከለው ለተጠቂዎች ፍትሕ ከመስጠት የዘለለ ዓላማ እንደሌለው ነው፡፡   

አይሲሲ ከሕግ ተቋምነት ይልቅ የፖለቲካ ተቋምነቱ ያመዝናል በማለት የሚከራከሩ አካላት፣ አይሲሲ ከተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ጋር ያለው ግንኙነት መዋቅራዊ ችግር እንደፈጠረበት ያመለክታሉ፡፡ እርግጥ ነው አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩሲያና ህንድን የመሳሰሉ ታላላቅ የፖለቲካ ኃይሎች የአይሲሲ አባል አይደሉም:: በአይሲሲ አመሠራረት፣ ዓላማ፣ ቅርፅ፣ አደረጃጀትና የሥራ ውጤቶች ላይ በአባላቱም ሆነ አባል ባልሆኑ አገሮች የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ይገኛሉ::

ይህ ባህሪው አይሲሲን በበርካታ አወዛጋቢ ሁኔታዎች የተሞላ ተቋም አድርጎታል:: አብዛኛዎቹ አባል ያልሆኑ አገሮች የአይሲሲ ዓቃቤ ሕግ የምርመራና ክስ የማዘጋጀት ሥልጣን ገደብ የሌለውና ለፖለቲካ ፍላጎቶች ማሟያ ሊውል ይችላል የሚል ፍርኃት አላቸው:: ቻይናና ሩሲያ የአይሲሲ አሠራር የአገሮችን ሉዓላዊነት ሊሸረሽር ይችላል የሚል ሥጋት አላቸው:: አሜሪካና ህንድ አይሲሲ ለብሔራዊ ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓታቸው ቦታ የሚሰጥ አለመሆኑን ይተቻሉ:: አሜሪካ በተጨማሪም በመላው ዓለም ለተለያዩ ዓላማዎች በተሰማሩ ወታደሮቿ ላይ ወደፊት ሕጋዊ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱ አይሲሲ ሁኔታዎችን ማመቻቸቱን ትቃወማለች::

ፍርድ ቤቱ ሥልጣን ያለው በአገሮች ላይ ብቻ ሳይሆን በግለሰቦች ላይ፣ ይባስ ብሎም በሥልጣን ላይ ያሉ የአገር መሪዎች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሠራተኞችና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ መሆኑንም ትቃወማለች:: ዓቃቤ ሕጉም ምርመራ የሚጀምረው ከሕግ ጋር በተያያዘ ምክንያት ብቻ መሆኑ በቂ እንዳልሆነም ታስረዳለች:: የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ሊጠየቅ የሚገባው ምርመራ እንዲጀመር ዓቃቤ ሕጉን እንዲመራ ብቻ ሳይሆን፣ አስፈላጊ ከሆነ ምርመራዎች እንዲቆሙ ጭምር መሆን እንዳለበትም ትጠቁማለች::

ቻይና በበኩሏ የፍርድ ቤቱ ሥልጣን አባል በሆኑ አገሮች ላይ ብቻ እንዲወሰን ትፈልጋለች:: እንደ ህንድ ሁሉ ቻይና የአገር ውስጥ ግጭቶች በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ሊታዩ እንደማይገባም አቋም ይዛለች:: የትንኮሳ ወንጀል በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት መታየቱም የተመድ የፀጥታው ምክር ቤትን ኃይል እንደሚያዳክምም ቻይና ታምናለች:: ህንድ ከፍርድ ቤቱ ጋር በተያያዘ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት የተሰጠው ሥልጣን ፍትሐዊ አለመሆኑን፣ ይህም የፀጥታው ምክር ቤት አባል የሆኑትና ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ያላቸውን የፍርድ ቤቱ አባላት ያልሆኑትን እንደ አሜሪካ፣ ቻይናና ሩሲያ ያሉ አገሮች እንደነሱው አባል ያልሆኑት አገሮች ላይ ምርመራ እንዲጀመር የመወሰን ሥልጣን እንዲኖራቸው መደረጉ፣ ፍትሐዊ ያልሆነና በተመድ ቻርተር ላይ ያልተሰጠን ሥልጣን የፀጥታ ምክር ቤቱ እንዲኖረው ማድረጉን ትተቻለች::

በፀጥታው ምክር ቤት ላይ የሚቀርበው ክርክር ጥቂት አገሮች የዓለምን የፖለቲካ ሁኔታ ከመቆጣጠራቸውና ከዓለም አቀፍ ሕግ ክፍተት ጋር የተያያዘ ፖለቲካዊ ክርክር ነው:: ከዚያ ውጪ ዓለም አቀፍ ወንጀሎች በብዛት እየተፈጸሙ ያሉት ወይ አፍሪካ አልያም መካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ነው በማለት አንዳንዶች ይከራከራሉ:: የተመድ የፀጥታ ምክር ቤትና የአይሲሲ ዓቃቤ ሕግ ከሚቀርቡላቸው ከእስራኤል፣ ከሶሪያ፣ ከሩሲያና ከአሜሪካ ጋር የተያያዙ ጥቆማዎች መካከል አንዱም ለውይይት አለመቅረቡ ተቋሙ ሁለት ዓይነት አሠራር ተከትሏል ለማለት እንደሚያስችል ግን ይቀበላሉ::

እንደ ፕሮፌሰር ማኩዋ ሙቱዋ ያሉ ምሁራን ደግሞ አይሲሲ እስካሁን አፍሪካ ላይ ብቻ የተመረጡ ጉዳዮችን ማየቱ ተቋሙን ለመቃወም በቂ አለመሆኑን ይናገራሉ:: ፕሮፌሰሩ አፍሪካ ላይ ብቻ መተኮሩ ሳይሆን መታየት ያለበት፣ የሥራው ጥራትና ትክክለኛነት ጭምር መሆን እንዳለበት ያስረዳሉ::

ኦካምፓ በጥቅምት ወር 2000 ዓ.ም. 2,889 የወንጀል ጥቆማዎች ቀርበውላቸው ነበር:: ወንጀሎቹ በመላው ዓለም በ139 አገሮች ውስጥ የተፈጸሙ ነበሩ:: ነገር ግን ምርመራ የተደረገው በአራት የአፍሪካ አገሮች ብቻ ነው:: ከ1994 ዓ.ም. በኋላ የተፈጸሙ ወንጀሎችን የማየት ሥልጣን ያለው አይሲሲ ዓይኑን ለምን አፍሪካ ላይ ብቻ አደረገ? በእስራኤል፣ በፍልስጤም፣ በሶሪያ፣ በሩሲያ፣ በእንግሊዝ፣ በአሜሪካ፣ በአፍጋኒስታንና በመሳሰሉ አገሮች ዜጎች አማካይነት በአፍሪካ የተከሰተው ዓይነት አሰቃቂ ወንጀል አልተፈጸመምን? በርካታ ተንታኞች እነዚህ ወንጀሎች ምርመራ እንዳይደረግባቸው ያደረገው በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት የሚሽከረከረው የኃይል ፖለቲካ መሆኑን ይቀበላሉ::

አይሲሲ በራሱ የማሰር ሥልጣን የለውም:: የእስር ትዕዛዝ የተላለፈባቸው ወንጀለኞች በአባል አገሮቹ እንዲያዙለት ትብብር ይጠይቃል:: አል በሽር የእስር ትዕዛዝ ከተላለፈባቸው በኋላ ኢትዮጵያን ጨምሮ ኤርትራን፣ ሊቢያን፣ ግብፅን፣ ሶማሊያን፣ ኳታርን፣ ሳዑዲ ዓረቢያንና ደቡብ አፍሪካን የመሳሰሉ አገሮችን ጎብኝተዋል:: ሆኖም እስካሁን አሳልፎ የሰጣቸው የለም:: ይህም በሥልጣን ላይ ያለ መሪ በኃላፊነት ሊጠየቅ አይገባውም ከሚለው ጽንሰ ሐሳብ ጋር በተገናኘ ስለመሆኑ በርካታ ኤክስፐርቶች ይስማማሉ:: ፍትሕ ሁሌም ሰላምን አያሰፍንም በማለት የሚከራከሩ አፍሪካዊያን፣ የአፍሪካ የፍትሕ አረዳድ ከምዕራባዊያኑ ለየት ባለ መንገድ ከበቀል ይልቅ ለድርድርና ለይቅርታ የቀረበ በመሆኑ፣ በአይሲሲ እንዲመሩ ከመጠየቅ የራሳቸው ምርጫ የሆነ አይሲሲ መሰል ተቋም እንዲፈጥሩ፣ የእውነትና የስምምነት ኮሚሽን እንድያቋቁሙ፣ ይቅር እንዲባባሉ፣ አልያም አገር በቀል የሆነ የግጭት ማስወገጃ ሥርዓት እንዲቀርፁ ነፃነት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ይጠይቃሉ::

አይሲሲ ከዚህ ትችት ራሱን ለመከላከል በሚመስል ሁኔታ በቅርቡ በጆርጂያ፣ በፍልስጤምና በአፍጋኒስታን ላይ ምርመራ ጀምሯል፡፡ ይህ አይሲሲ ዓለም አቀፋዊ ባህሪውን ለማረጋገጥ አስፈላጊ ቢሆንም፣ አሁን በእጁ ላይ ያለውን የአፍሪካ ጥያቄ መመለሱን እርግጠኛ መሆን እንዳለበት ብዙዎች ያሳስባሉ፡፡

ይሁንና አፍሪካ በአይሲሲ ላይ ትክክለኛ ጥያቄ ቢኖረውም የራሱን ጥያቄዎች በቅድሚያ መመለስ ይኖርበታል፡፡ ለአይሲሲ ምርመራ በር የሚከፍቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ከማስወገድ ጀምሮ ለችግሮች ተዓማኒና አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት የምችል  የፍትሕ ሥርዓት መገንባት ተጠቃሽ ውስጣዊ መፍትሔዎች ናቸው፡፡ በመሠረቱ አይሲሲ ብሔራዊ የፍትሕ ሥርዓትን የሚደግፍ ተቋም እንጂ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍትሕ የሚሰፍንበት ተቋም ሆኖ አልተዋቀረም፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -