Tuesday, July 23, 2024

የሰብዓዊ መብት አያያዝ ችግር እስከ መቼ እሹሩሩ ሲባል ይኖራል?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት አራት የፖለቲካ ድርጅቶች የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢሕአዴግ) ብለው ባቋቋሙት ፓርቲ የምትመራ አገር ነች፡፡ በ1983 ዓ.ም. የደርግ መንግሥት ከወደቀና እንደ ሶቭየት ኅብረት ከተፈረካከሰ በኋላ የተቋቋመው ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት፣ ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ ለአምስተኛ ጊዜ በ2007 ዓ.ም. ባካሄደው አገራዊ ምርጫ የሕዝብ ተወካዮችን ምክር ቤት መቀመጫ ሙሉ በሙሉ በማሸነፍ የአምስት ዓመት የሥልጣን ባለቤትነቱን አረጋግÚል፡፡

ከአፍሪካ ኅብረት የተውጣጣ ቡድን የምርጫውን ሒደት ታዝቧል፡፡ ቡድኑ የተካሄደው ምርጫ ፍትሐዊና ሰላማዊ ነው ብሎ ቢገልጽም፣ በተቃራኒው የምርጫውን ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ ያስገቡ ወገኖች ነበሩ፡፡ ያም ሆነ ይህ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ በሚባል ደረጃ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መቀመጫ ወንበር ከአጋር ድርጅቶቹ ጋር በመሆን ሙሉ በሙሉ በመያዝ በትረ ሥልጣኑን ተቆናÚል፡፡

የኢሕአዴግ ሙሉ በሙሉ አሸናፊነት የተበሰረበት ጊዜ ዓመታትን ሳያስቆጥር ብዙ እክሎች ገጥመውት እንደበርና እነዚህ ችግሮች አሁንም ድረስ እንዳልተፈቱ ይታወቃል፡፡ ኢሕአዴግ በ2007 ዓ.ም. ምርጫ ውጤት መሠረት በትረ ሥልጣኑን ይዞ በነደፈው ፖሊሲና ስትራቴጂ አገሪቱን በመምራት ብዙ ርቀት ሳይጓዝ በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ክልሎች ሕዝባዊ ሁከትና ብጥብጥ ተነስቶ አገሪቱን አደጋ ላይ ጥሏት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡

ከሐምሌ 2008 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ መስከረም 2009 ዓ.ም. በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች በተቀሰቀሱ ሁከቶች፣ እንዲሁም በደቡብ ክልል በጌዴኦ ዞን ብሔርን መነሻ አድርጎ በተከሰተ ግጭት የ669 ሲቪሎችና የፀጥታ አስከባሪዎች ሕይወት ማለፉን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡ ከተጠቀሱት የሟቾች ቁጥር 495 ያህሉ ሕይወታቸው ያለፈው በኦሮሚያ ክልል በተነሳው ብጥብጥ እንደሆነ ኮሚሽኑ ሚያዚያ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት አስታውቋል፡፡

በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተቀሰቀሰውን ግጭት አዘል ተቃውሞ በመመርመር ሪፖርት ያቀረበው ኮሚሽኑ፣ የግጭቱና የተቃውሞው መሠረታዊ መንስዔ ከሆኑት መካከል አንዱ የዜጎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ችግር እንደሆነ ጠቁሟል፡፡

የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ሕዝቡን በሚመሩበትና በሚያስተዳድሩበት ወቅት የመብት ጥሰት በማካሄዳቸው፣ ለተቃውሞው እንደ አንድ መንስዔ ሆኖ ቀርቧል፡፡

በዚህ ሁከትና ግጭት የተነሳ በሚሊዮን የሚቆጠር ንብረት እንደወደመ የጠቀሰው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሪፖርት፣ ለዚህ ችግር መነሻ የሆኑ የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ለሕግ እንዲቀርቡ ሲልም አሳስቧል፡፡

የኢትዮጵያን ሰብዓዊ መብት አያያዝ በተመለከተ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተለያየ ይዘት ያላቸው ሪፖርቶች በተለያዩ ጊዜያት ይወጣሉ፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ በተለይ በምሥራቅ አፍሪካ ሰላምና ደኅንነት እንዲሰፍን እያከናወነችው ያለው ሥራ ከፍተኛ መሆኑን የሚጠቅሱት ባለሙያዎች፣ በአገር ውስጥ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ እስካሁን ድረስ ችግሮች እንዳሉ ይጠቁማሉ፡፡

ከአውሮፓ ኅብረት ጀምሮ እስከ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተቋም ድረስ ብዙ ክሶች ቀርቦባታል፡፡ በተለይም ከሐምሌ 2008 ዓ.ም. ወዲህ በአገሪቱ ተቀስቅሶ በነበረው ሁከትና ብጥብጥ የተነሳ መንግሥት የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ጥሷል በሚል፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሌሎች ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በኢትዮጵያ ላይ ወቀሳ ሰንዝረዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ከሐምሌ 2008 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች መነሻ ምክንያትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በገለልተኛ አጣሪ እንዲመረመር ለኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ ይኼን ጉዳይ በማስመልከት ከቢቢሲ ጋር ቆይታ የነበራቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ኢትዮጵያ ምርመራውን በራሷ አቅም ማካሄድ እንደምትችል በመጥቀስ የተመድን ጥያቄ ውድቅ አድርገዋል፡፡

የሰብዓዊ መብት አያያዝን ለማጣራት ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ቡድን በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ተዘዋውሮ እንዲያጣራ ለጠየቀው ጥያቄ ፈቃድ እንደተነፈገው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ዛይድ ራአድ ሁሴን ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ተናግረዋል፡፡ ኮሚሽነሩ ባለፈው ዓመት በሁለቱ ክልሎች በተቀሰቀሰው አለመረጋጋት ምክንያት ቢሮአቸው በአገሪቱ ተከስቶ የነበረውን ሁከትና ብጥብጥ፣ እንዲሁም ከዚህ ጋር ተያያዞ የጠፋውን የሰው ሕይወት ለማጣራት በተደጋጋሚ ጊዜ ለኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄ ቢያቀርብም፣ እንዳልተፈቀደለት ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽነሩ በሕግ ጥላ ሥር ያሉ ዜጎች አያያዝ ላይ ኢትዮጵያ ትኩረት ሰጥታ እንድትሠራም አሳስበዋል፡፡

በሕግ ጥላ ሥር ያሉ ታራሚዎች አያያዝ ላይ ክፍተቶች እንዳሉ ብዙ ጊዜ ሲነገር ይደመጣል፡፡ በቁጥጥር ሥር ውለው በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎች የተፋጠነ ፍትሕ እንደማያገኙም እንዲሁ፡፡ በእነዚህና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች የተነሳ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና የሰማያዊ ፓርቲ ሰሞኑን መግለጫ አውጥተው ነበር፡፡ እንደ ፓርቲዎቹ መግለጫ፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ታራሚዎች ሊከበርላቸውና ያለምንም ችግር ተፈጻሚ ሊሆንላቸው የሚገባውን የሕገ መንግሥት ድንጋጌ እየጣሰ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 21/22 መሠረት በሕግ ጥበቃ ሥር ያሉ ዜጎች ከትዳር ጓደኞቻቸው፣ ከቅርብ ጓደኞቻቸው፣ ከሃይማኖት አባቶቻቸው፣ ከሐኪሞቻቸውና ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር የመገናኘትና እንዲጎበኗቸው ዕድል የማግኘት መብት እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡ ሕጉ ይኼን ቢፈቅድና ቢያዝም የፓርቲዎቹ አመራሮች የታሰሩባቸውን በርካታ አባላት ለመጠየቅ ወደ ቂሊንጦ ሄደው መከልከላቸውን ተናግረዋል፡፡ የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት በ2009 ዓ.ም. መስከረም ወር ላይ ባወጣው መግለጫ ይኼንን ሐሳብ ይጋራዋል፡፡ የታሰሩ ዜጎች በዘመዶቻቸውና በአማካሪ ግለሰቦቻቸው እንዳይጎበኙ ከማድረግ ባሻገር፣ በእስረኞች አያያዝ ላይ ጉድለቶች እንዳሉ ጠቁሟል፡፡

 የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የወቅቱ ፕሬዚዳንት ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) ይኼንን ሐሳብ ይጋሩታል፡፡ እንደ እሳቸው አባባል፣ በታሰሩት ወገኖች ላይ የሚፈጸመው ግፍና በደል ሕገ መንግሥቱን የጣሰና ሊታለፍ የማይችል ጉዳይ እንደሆነ አስምረውበታል፡፡ የፍትሕ አካላት የሚባሉትን ፖሊስና ሌሎችንም ጨምሮ በእስረኞች አያያዝ ላይ እስካሁን ሊቀርፉዋቸው ያልቻሉ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፣ መንግሥት በሰብዓዊ መብት አያያዝ በተለይም በታራሚዎች ላይ ያለው አሠራር ኋላ ቀር እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

መኢአድና ሰማያዊ ፓርቲ እንደሚሉት፣ በእስር ላይ የሚገኙ አባሎቻቸው የሚያስፈልጓቸውን ቁሳቁስ ይዘው ለመጎብኘት ሲሄዱ የጥበቃ አባላትና ኃላፊዎች እንዳይገቡ እንደከለከሏቸው ገልጸዋል፡፡ ክልከላ የተደረገው በጥበቃዎቹ ወይም በኃላፊዎቹ መሆንና አለመሆኑን ለማረጋገጥ የማረሚያ ቤቱን አስተዳደር በደብዳቤ መጠየቃቸውን የገለጹት ፓርቲዎቹ፣ ምንም ዓይነት ምላሽ ባለማግኘታቸው ድርጊቱ ሆን ተብሎ በአባሎቻቸው ላይ እንግልት ለማድረስ ታስቦ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ይኼንን ሐሳብ ይጋሩታል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ይኼንን ድርጊት እየፈጸመ ያለው በሁለቱ ፓርቲ አባሎች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎች በሕግ ጥላ ሥር ባሉ ዜጎች ላይም እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የሕግ ባለሙያ ደግሞ በአሁኑ ወቀት መንግሥት በጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ ሆኖ ብዙ ችግሮችን ለመፍታት ደፋ ቀና እያለ ቢገኝም፣ ጉዳያቸው በሕግ ጥላ ሥር ሆኖ እየታየ ያሉ ዜጎችን አያያዝ በተመለከተ ሰፊ የሆነ ችግር እንዳለ ይስማማሉ፡፡ በማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የታሰሩ ዜጎች በዘመዶቻቸውና በጠበቆቻቸው እንዲጎበኙ ሕግ ቢፈቅድም፣ ተፈጻሚ እንደማይሆን ይጠቅሳሉ፡፡ በተለይ በሕመም ላይ ያሉ እስረኞች የተለየ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባ ቢሆንም እስካሁን ግን እንደሌለ ይገልጻሉ፡፡

አቶ ሙሼ በበኩላቸው መንግሥት የታራሚዎችን ንፅህና፣ ጤንነትና ሌሎች መሠረታዊ ጉዳዮችን የሟሟላት ግዴታ እንዳለበት ጠቁመው፣ ይኼ ግን ተግባራዊ ሲሆን እንደማይታይ ይናገራሉ፡፡ መኢአድና ሰማያዊ ፓርቲም በዚሁ ጉዳይ ላይ በሚደረገው ሕገወጥ ክልከላ ምክንያት በሕመም ላይ ያሉ የታሰሩ አባሎቻቸውን መጠየቅ እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ ከመኢአድ አቶ አወቀ አባተና መልካሙ ገበየሁ፣ ከሰማያዊ ፓርቲ ደግሞ አቶ አበባው ሰጠኝና አቶ ሉሉ መካሻ በመደብደባቸው ለሕመምና ለስቃይ መዳረጋቸውን፣ በቂ ሕክምና ባለማግኘታቸውም ሕይወታቸው አደጋ ላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የፓርቲዎቹ አመራሮች እየተፈጸመ ነው ያሉትን የሕገ መንግሥት ድንጋጌ ጥሰት በሚመለከት ሪፖርተር የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች አስተያየት እንዲሰጡ ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካ መግለጻችን ይታወሳል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሕግ ባለሙያው፣ የችግሩን ሥር መስደድ አመላካች ጉዳይ እንደሆነ ይስማማሉ፡፡

 በሕገ መንግሥቱ እንደሰፈረው ዜጎች መረጃ የማግኘት መብት እንዳላቸው ቢደነግግም፣ የታራሚ ቤተሰቦች ስለታራሚ ወገኖቻቸው መረጃ ለማግኘት የሚያደርጉት ጥረት አለመሳካቱ፣ የሕገ መንግሥቱ ተፈጻሚነት ክፍተት አንዱ ማሳያ ነው ይላሉ፡፡

የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳዳር የፍትሕ አካል ሆኖ ማንኛውም ጥፋት ያጠፋም ያላጠፋም፣ በወንጀል የተጠረጠረም ያልተጠረጠረም የሕግ ፍርድ እስኪያገኝ ድረስ በማረሚያ ቤት ሆኖ ጉዳዩን እንደሚከታተል የሚገልጹት ዶ/ር ጫኔ፣ ይኼንን ለማሟላት ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች እንዳሉ ይጠቅሳሉ፡፡

ሰው ሰው በመሆኑ መከበር የሚገባውና ድብደባና ስቃይ እንዳይደርስበት ሕጉ እንደሚከለክል ይናገራሉ፡፡ ይኼን ለማስፈጸም ደግሞ ዓቃቤ ሕግ ሕጎች በአግባቡ መተርጎማቸውን እያረጋገጠ፣ እነዚህ እስረኞች በአግባቡ መያዛቸውንና የሕግ ከለላ መስጠት እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡  

አሁን ባለው የአፈጻጸም ሥርዓት ግን ሕጉ በሚገባ እንዲከበር የማይጥሩ፣ ወገንተኛ የሆኑ፣ በራሳቸው ስሜት የሚጓዙ፣ ፍርድ የሚያጣምሙ፣ ወይም ደግሞ የፍትሕ አንቀጾችን በተገቢው መንገድ ማስቀመጥ የማይችሉ አቅም የሌላቸው፣ ከዚያም በላይ ሌሎች ነገሮችን ማሟላት የማይችሉ፣ እንደሆኑ ዶ/ር ጫኔ ይገልጻሉ፡፡ ዓቃቤ ሕግ ከምንም በላይ ኃላፊነት መውሰድ የነበረበት ቢሆንም እየወሰደ እንዳልሆኑ ይናገራሉ፡፡

የሕግ ባለሙያው ይኼንን ሐሳብ ይጋሩታል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ሕጉ እንዲከበር ከማድረግ ይልቅ በተቃራኒው ተፈጻሚ እንዲሆን እስኪመስል ድረስ እየሠራ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ አቶ ሙሼ ደግሞ በአሁኑ ወቅት የፍትሕ አካላት የሚባሉት ከታራሚዎች ገንዘብ በመቀበል የፍትሕ ሥርዓቱ እንዲዛባ እያደረጉ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡

አገሪቱ ደሃ ብትሆንም እንኳ አንድ ታራሚ ማግኘት የሚገባውን መብት ማግኘት እንዳለበት የሚገልጹት አቶ ሙሼ፣ በዚህ ዙሪያ ሰፊ ሥራ መከናወን እንደሚገባው ይጠቁማሉ፡፡ ዶ/ር ጫኔ እና የሕግ ባለሙያው ደግሞ በኢትዮጵያ አስፈጻሚው አካልና የፍትሕ አካሉ በሥልጠናና በተለያዩ ዘዴዎች ራሳቸውን በማብቃት፣ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሥርዓቱ መሻሻል እንዳለበት ይስማማሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ ተላላፊ በሽታ እንኳን ቢነሳ ታራሚ ዜጎች ሊተርፉ እንደማይችሉ ነው፡፡ የሕግ ባለሙያው ይኼን ሐሳብ እንደሚጋሩትና ጉዳዩ ከዚህም በላይ ግዝፈት እንዳለው ይጠቁማሉ፡፡ ያጠፋ ሰው እንደ ሰው የማይቆጠርበት ጊዜ ላይ ደርሰናል ባይ ናቸው፡፡ አቶ ሙሼ በበኩላቸው፣ አንድ ዜጋ ማረሚያ ቤት ሲገባ፣ ያንን ዜጋ ብቁ አድርጎ የማውጣት ኃላፊነት የመንግሥት ቢሆንም የሚደረገው ግን ከዚህ የተገላቢጦሽ ነው ይላሉ፡፡

ማረሚያ ቤቶች ራሳቸው ለታሰሩ ዜጎችን በሕጉ መሠረት ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ ሲገባቸው፣ የታሰሩ ዜጎችን ሰብዓዊ መብት ከመጠበቅ ይልቅ የስለላ ሥራ ይሠራሉ የሚሉት የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ሰዎችን ከውጭ አሰማርቶ የሚያስደበድብ የማረሚያ ቤት አስተዳደር ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው በማለትም ይሞግታሉ፡፡ ጉዳዩ ከዚህም አለፍ ብሎ የማረሚያ ቤት ሠራተኞች የእስረኞችን አያያዝ በተመለከተ  የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሚያዚያ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት ላይ፣ በአዳሚ ቱሉ ማረሚያ ቤት 14 ሰዎች ሊያመልጡ ሲሞክሩ በጥበቃ ኃላፊዎች መገደላቸው ሕግን ያልተከተለ፣ አላስፈላጊና ተመጣጣኝ እንዳልነበር ገልጿል፡፡ ይኼ የሚያመለክተው ደግሞ ማረሚያ ቤት አስተዳደር በታራሚ ዜጎችን ሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ክፍተቶች እንዳሉበት አንዱ ማሳያ ነው ሲሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

በእስር ላይ ያሉ ዜጎች አካላቸው እየጎደለና ሰብዓዊ መብታቸው እየተገፈፈ እንደሆነ የሚናገሩት ዶ/ር ጫኔ ታራሚው በተፈጥሮ ያገኛቸውን ሰብዓዊ መብቶች የሚጋፉና በዚች አገር ለምን ተፈጠርኩ እስከሚል የሚማረር እስረኛ እንዳለ ይላሉ፡፡ የሕግ ባለሙያው በበኩላቸው፣ በመደብደብ እጃቸውን አጥተው፣ አካላቸው ጎድሎ የሚታዩ እስረኞች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ ይህ ደግሞ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲባልና ሲነገር የነበረ እንዲሁም በአገሪቱ ላይ ብዙ ኪሳራ ያደረሰ ቢሆንም፣ አሁን መንግሥት ጥልቅ ተሃድሶ ብሎ ወደ እንቅስቃሴ ከገባ ወዲህ ሊፈታውና ሊያሻሽለው እንዳልቻለ ይጠቅሳሉ፡፡

የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በሚያዚያ ወር ላይ ባቀረበው ሪፖርት ሊጠየቁ ይገባቸዋል የተባሉ ወገኖች ዕርምጃ ሲወሰድባቸው ሕዝቡ ማየት ይፈልጋል የሚሉት የሕግ ባለሙያው፣ ይህ ካልሆነ ግን ሕዝብና መንግሥት ሆድና ጀርባ ሆነው እንደሚኖሩ አጠያያቂ አይደለም ይላሉ፡፡ ነገር ግን ሕዝብ አሁንም ወደ ከዚህ ቀደም ዓይነቱ ረብሻና ሁከት ውስጥ መግባቱ የማይቀር እንደሆነም ሥጋታቸውን በማከል፡፡

የአንድ አገር የዕድገት መለኪያ አንዱ ጉዳይ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ደረጃ እንደሆነ የሚናገሩት የሕግ ባለሙያው፣ አገሪቱ በአሁኑ ወቅት በኢኮኖሚው ዘርፍ የተሻለ እንቅስቃሴ እያስመዘገበችና በአፍሪካ ደረጃ ስሟን ከፍ እያደረገች ቢሆንም፣ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ግን ይኼንን ጉዳይ ጥላሸት እየቀባው እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ጥሰቶችን መከላከልና መጠበቅ የሚገባው ዓቃቤ ሕግ እንደሆነ የሚገልጹት ዶ/ር ጫኔ፣ ይኼንን ለመከላከል ዓቃቤ ሕግ ፈቃድና ፍላጎትም እንደሌለው ይገልጻሉ፡፡ የሕግ ባለሙያው በበኩላቸው፣ እንደዚህ ዓይነት ሥራዎች በኢትዮጵያ የተወገዙ ይመስል እንቅስቃሴ አይታይባቸውም በማለት የዶ/ር ጫኔን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡

እንደህ ዓይነት የመብት ጥሰቶች ሊፈቱና መፍትሔ ሊደረግላቸው የሚገባው በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እንደሆነ የሚገልጹት አቶ ሙሼ፣ ኮሚሽኑ ቁርጠኛ መሆን አለበት ይላሉ፡፡ የታሰሩ ዜጎች በማረሚያ ቤት የሰብዓዊ መብቶቻቸው ተከብሮ እንዲኖሩ ኢትዮጵያ የተቀበላቻቸውና ሕግ አድርጋ የምትመራባቸው ዓለም አቀፍ ሕጎች ሳይቀሩ ቢያስገድዱም፣ የተፈጻሚነት ደረጃቸው ዝቅተኛ እንደሆነ የሚናገሩ ወገኖች አሉ፡፡

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ደሃ ታራሚዎች ሰብዓዊ መብቶቻቸው እንዲከበርላቸው ሲባል መንግሥት ራሱ ጠበቃ እንዲያቆምላቸው ሕጉ ቢያስገድድም፣ መንግሥት ጠበቃ አቁሞላቸው የሚከራከሩ ወገኖች እንደሌሉ ዶ/ር ጫኔ ይናገራሉ፡፡ ዓለም አንድ መንደር እየሆነችና ሥልጣኔው ከጫፍ እስከ ጫፍ እየተቀጣጠለ ባለበት በዚህ ዘመን፣ ኢትዮጵያ በዚህ ጉዳይ ኋላ ቀር እንደሆነች የሕግ ባለሙያው የአቶ ሙሼን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡

ልጆቿን በላይቤሪያ፣ በሩዋንዳ፣ በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በኮንጎ፣ በኮሪያና በሌሎች ዓለም አቀፍ ግዳጆች ላይ ያሰማራች አገር፣ በዚህም የተነሳ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ የመፍጠር አቅሟ ከፍ እያለ በመጣበት ዘመን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሥርዓቱ እንደገና ሊፈተሽ እንደሚገባው የሕግ ባለሙያው ይናገራሉ፡፡

ታራሚ ዜጎች፣ በነፃነት በመናገራቸውና በመጻፋቸው የታሰሩ ጋዜጠኞችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ስላሉ መንግሥት በዚህ ላይ ሰፊ ሥራ ማከናወን እንዳለበት የሚናገሩ ባለሙያዎች እዚህም እዚያም ይደመጣሉ፡፡

አንድ ታራሚ በትንሹ ሊያገኝ የሚገባውን በዘመዶቹ፣ በጠበቆቹና በቤተሰቦቹ የመጎብኘትና የመጠየቅ መብት  መነፈግ የለበትም የሚሉት ዶ/ር ጫኔ፣ መኢአድና ሰማያዊ ፓርቲዎች ለታሰሩ አባሎቻቸው ስንቅ ይዘው ለመጠየቅ በሄዱበት ወቅት መከልከላቸው በጣም እንዳሳዘናቸው ይገልጻሉ፡፡ ጉዳዩ አዲስ እንዳልሆነ የሚናገሩት የሕግ ባለሙያው፣ መንግሥት ጆሮ ያልሰጠው አሳሳቢ ጉዳይ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ደግሞ መንግሥትንና ሕዝብን ወደ ዳግመኛ ቅሬታ ውስጥ ሊያስገቡ እንደሚችሉ የሚናገሩት የሕግ ባለሙያው፣ አስቸኳይ መፍትሔ ሊበጅለት እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡

እነዚህንና መሰል የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመከላከል ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ምን እንደሆነ ማወቅ እንዳለበት የሚናገሩት ዶ/ር ጫኔ፣ በማረሚያ ቤት ውስጥ በኃላፊነትም ሆነ በፈጻሚነት ለሚሠሩ ወገኖች ተከታታይ ሥልጠና በመስጠት መንግሥት ከስህተታቸው እንዲታረሙ ማድረግ እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡

በሕግ ጥላ ሥር የሆኑትም ሆኑ ሌሎች ዜጎች ሰብዓዊ መብቶቻቸው ተከብሮ፣ ጥፋተኛ የሆኑ ካሉም ጉዳያቸው ሕጉ በሚያዘውና በሚፈቅደው ብቻ ተዳኝተው የሚኖሩባት አገር እንድትሆን መንግሥትና ኅብረተሰቡ በጋራ መሥራት እንዳለባቸው አስተያየት ሰጪዎች ጠቁመዋል፡፡ የታሰሩ ዜጎችን ጉዳይ በሕግ አግባብ በመፍታት አገሪቱ አሁን ካለችበት ድህነት ማውጣት ተገቢ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ይኼንን ወደ ተግባር ለመቀየር ደግሞ የመንግሥትን ቁርጠኝነት የሚፈልግ ጉዳይ እንደሆነ በመጠቆም፡፡

አቶ ሙሼ፣ ‹‹ማረሚያ ቤቶች የታራሚዎችን ሰብዓዊ መብት ለማክበርና ለማስከበር ብቁ አይደሉም፡፡ ስለዚህ መንግሥት በዚህ ላይ እጁን በማስገባት የታራሚዎችን ሁለንተናዊ መብት መጠበቅና ማስጠበቅ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው፤›› ይላሉ፡፡

በሕግ ጥበቃ ሥር ያሉ ዜጎችን አያያዝ በተመለከተ መረጃ እንዲሰጡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር) ተጠይቀው፣ ‹‹በአሁኑ ወቀት በእስረኞች አያያዝ ላይ የተነሳውን ቅሬታ ለመመርመር ባለሙያዎቻችን ማረሚያ ቤት አስተዳደር ሄደው ጉዳዩን እያጣሩ ስለሆነ፣ ሥራቸውን ሲያጠናቅቁ ውጤቱን ይፋ እናደርጋለን፡፡ አሁን በምርመራ ላይ በመሆናችን መረጃ ልንሰጥ አንችልም፤›› ብለዋል፡፡    

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -