Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የተቀዛቀዘ የኢኮኖሚ ዕድገት ከ550 ሚሊዮን በላይ ሕዝቦችን ወደ ተባባሰ የድህነት አዘቅት ሊጥል እንደሚችል ተመድ ይፋ አደረገ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የደሃ አገሮችን የልማት ጥያቄዎች ለማሟላት በዓመት እስከ ሦስት ትሪሊዮን ዶላር ያስፈልጋል

ከሁለት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ የተስተናገደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፋይናንስ ለልማት ጉባዔን ወቅታዊ ሁኔታ የገመገመው የተመድ ግብረ ኃይል፣ ድህነትና ረሃብ ከዓለም ይጠፋሉ ተብለው በሚጠበቁበት እ.ኤ.አ. በ2030 ከ550 ሚሊዮን በላይ ሕዝቦች ለዚሁ ችግር ተጋላጭ ሊሆኑ የሚችሉበት አዝጋሚ የኢኮኖሚ ዕድገት እየተመዘገበ መሆኑ ሥጋት እንዳሳደረበት ተመድ ይፋ አድርጓል፡፡

ድህነት ከዓለም እንደሚጠፋ ተስፋ በሚደረግበት ወቅት ከግማሽ ቢሊዮን በላይ ሕዝቦች በድህት አረንቋ ውስጥ ለመኖር እንደሚገደዱ ሥጋቱን የገለጸው ተመድ፣ በሥሩ የሚገኙ ኤጀንሲዎችን በማስተባበር፣ ግብረ ኃይል አቋቁሟል፡፡ የበይነ ኤጀንሲዎቹ ሪፖርት እንደሚያመለክተው በመቶ ሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሕዝቦች በድህነት አረንቋ ውስጥ መውደቅ ሰበብ እንደሚሆን የተፈራው የዓለም ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከዓመት ዓመት አዝጋሚነቱ በመባባሱ ነው፡፡

በተመድ የዚህ ዓመት የፋይናንስ ለልማት ሪፖርት መሠረት ታዳጊ አገሮች እጅጉን ተጎጂዎች ከሚባሉት ውስጥ እንደሚመደቡ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድና የልማት ጉባዔ ተቋም (UNCTAD) ምደባ መሠረት ከ44 ያህል ያለደጉ ወይም በማደግ ላይ ካሉ አገሮች ውስጥ ከ30 በላይ የሚገኙት በአፍሪካ በመሆኑ፣ በእነዚህ አገሮች ውስጥ የሚታየውን ዘገምተኛ ለውጥ ይበልጥ ሊጎዳው እንደሚችል ተመድ ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ አስፍሯል፡፡ በትንበያዎች መሠረት በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ይኖራል ተብሎ የሚጠበው የዓለም ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከሦስት በመቶ አይልጥም፡፡ የዓለም ንግድ እየተቀዛቀዘ መምጣጡ ደግሞ በሸቀጦች ዋጋ መውደቅ ሲደቆሱ የቆዩትን ደሃ አገሮች ይበልጥ አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚጥል ከመፈራቱም ባሻገር፣ ላለፉት አምስት ዓመታት ሲጓዝበት ከመጣው የሁለት በመቶ አማካይ ዓመታዊ ዕድገት በተጨማሪ ካቻምና የአሥር በመቶ ቅናሽ ማስመዝገቡም ሥጋቱን አባብሶታል፡፡

ይህንኑ ተከትሎም የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ አገሮች የቱንም ያህል ድህነትን ለመዋጋት ቢነሱ፣ ለዚሁ የሚረዱ እንቅስቃሴዎችን ቢያደርጉ፣ ሉላዊነትን መሠረት ያደረጉ ለውጦችና የቴክኖሎጂ ዕድገቶች ቢመዘገቡም፣ አሁንም ግን የምግብ ዋስትና ችግር፣ የውኃ አቅርቦት እጥረት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ግጭቶችና ሌሎችም ግዙፍ ፈተናዎችን ለውጦችን እየተገዳደሩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

ካቻምና አዲስ አበባ ያስተናገደችውን ሦስተኛውን ፋይናንስ ለልማት ጉባዔን መነሻ ያደረገው የተመድ ሪፖርት፣ ከጉባዔው ወዲህ የታዩትን ለውጦች የሚፈትሽ ነው፡፡ በአዲስ አበባው ጉባዔ ወቅት 17ቱን የተመድ ዘላቂ የልማት ግቦች ለማሳካት፣ ብሎም የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመቅረፍ እስከ 1.5 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ይፋ ተደርጎ ነበር፡፡ ይህ ገንዘብ ባላደጉት አገሮች ውስጥ ብቻ የሚታየውን ክፍተት የሚጠቁም ሲሆን፣ በመላው ዓለም ያለው የመሠረተ ልማቶች አለመሟላት ችግር ከሦስት እስከ አምስት ትሪሊዮን ዶላር ይገመታል ይላል፡፡

በመሆኑም እንዲህ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት አስቸኳይ የረዥም ጊዜ ኢንቨስትመንት እንዲደረግ የሚጠይቀው ተመድ፣ የዓለም የኢኮኖሚ መቀዛቀዝን ሊያነሳሱ የሚችሉ እንቅስቃሴዎች እንዲደረጉ አሳስቧል፡፡

ከአምስት ሺሕ በላይ ታዳሚዎች የተገኙበት የካቻምናው የአዲስ አበባ የፋይናንስ ለልማት ጉባዔ፣ እ.ኤ.አ. እስከ መጪው 2030 ድረስ የሚዘልቁት የልማት አጀንዳዎች ይፋ የተደረጉበት፣ 17ቱን የልማት ግቦች ለማስፈጸምም የሚጠይቀው የፋይናንስ መጠን በድብስብሱ እስከ ሦስት ትሪሊዮን ዶላር መሆኑ የተገለጸበት ነበር፡፡ ከዚህ ባሻገር በስብሰባው ወቅት ድሆች ወይም ታዳጊ አገሮች ራሳቸውን መደጎም እንዲጀምሩ የተጠየቀበት መድረክ እንደነበርም ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ከፍተኛ ታቃውሞ በተደመጠባቸው፣ የዓለም የሲቪክ ማኅበራት ድምፃቸውን ካሰሙባቸው ነጥቦች መካከልም ያደጉ አገሮች ኩባንያዎች በታዳጊ አገሮች ላይ የሚያደርሱት የታክስ ማጭበርበር፣ የትርፍ ማሸሽ ተግባራት እንዲሁም የገንዘብ ስወራ ወንጀሎች መፍትሔ እንዲሰጥባቸው የጠየቁበት አግባብ ይታወሳል፡፡

በትልልቅ ድንበር ተሻጋሪ ኩባንያዎች አማካይነት ከአፍሪካ አገሮች በዓመት እስከ 70 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ እንደሚሸሽ ጥናቶችን ይጠቁማሉ፡፡ በቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ተቦ ምቤኪ የሚመራው የአፍሪካ ከፍተኛ ፓነል፣ በዚሁ በድንበር ተሻጋሪ ኩባንያዎች አማካይነት ከአፍሪካ አሥር ዋና ዋና አገሮች እየተሰወረ እንደ ስዊዝ ባንክ ባሉ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የሚጋዘው ገንዘብ በትንሹ ከ70 እስከ 100 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል፡፡ ከአሥሩ ዋና ዋና ተጠቂ አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ የምትመደብ ሲሆን፣ በየዓመቱም እስከ 15 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ በኩባንያዎች አማካይነት እያጣች እንደምትገኝ የፓናሉ ጥናታዊ ሪፖርት አመላክቷል፡፡

እንዲህ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ ተመድ ጥብቅ አሠራሮችን መከተል እንደሚገባው የሲቪክ ማኅበራቱ ጠይቀው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ምንም እንኳ በተመድ ሪፖርት መሠረት ለታዳጊ አገሮች የልማት ጥያቄዎች ሦስት ሚሊዮን ዶላር ያህል ገንዘብ ያስፈልጋል ቢልም፣ እንደ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳንና የመንን የመሳሰሉ ያሉ ከፍተኛ የድርቅ እንዲሁም የረሃብ አደጋ ያንዣበባቸው አገሮች ለደረሰባቸው የምግብ እጥረት ቀውስ ያገኙት ምላሽ ደካማ ሆኖ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ በሁለት ተከታታይ ዓመታት ውስጥ ከ18 ሚሊዮን ያላነሰ ሕዝብ ለአስቸኳይ የምግብ እጥረት ቢጋለጥም፣ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተገኘው ምላሽ ቀዝቃዛ መሆኑ ሲዘገብ ቆይቷል፡፡ በዚህ ዓመት ከ7.8 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለዕለት ደራሽ ዕርዳታ በመጋለጡ ከ950 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ ይፋ ተደርጓል፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች