Saturday, December 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ አስተዳደር ልዩ የሊዝ ጨረታ በቅርቡ እንደሚያወጣ አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት ልዩ ጨረታ ለማውጣት ዝግጅት መጠናቀቁን፣ ለዚህ አገልግሎትም ሦስት ቦታዎችን መረከቡን አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጀማል አልይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ልዩ ጨረታ ሰፋፊ መሬቶችን የሚፈልግ ስለሆነ ከሰው ንክኪ ነፃ አድርጎና መሠረተ ልማት አሟልቶ የማቅረብ አቅም ይጠይቃል፡፡

      ‹‹በማስፋፊያም ሆነ በመልሶ ማልማት ሥፍራዎች ሰፋፊ ቦታዎችን ማዘጋጀት አስቸጋሪ ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን ልዩ ጨረታ ለማውጣት እየተዘጋጀን ነው፡፡ እስካሁን ሦስት ቦታዎችን ተረክበናል፤›› ሲሉ አቶ ጀማል ገልጸዋል፡፡

      የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዓመት ሁለት ጊዜ ልዩ ጨረታ የማውጣት ዕቅድ ነበረው፡፡ ነገር ግን እስካሁን ድረስ የወጣው በ2007 ዓ.ም. እና በ2008 ዓ.ም. ሁለት ጊዜ ብቻ ነው፡፡ የ2009 በጀት ዓመት ሊጠናቀቅ ከሁለት ወራት ያነሰ ጊዜ ብቻ ቢቀረውም፣ ልዩ ጨረታው ግን እስካሁን አልወጣም፡፡

አቶ ጀማል እንዳሉት አስተዳደሩ የመሬት አቅርቦቱ እንዲሻሻል ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ መመርያ በመስጠቱ፣ የበጀት ዓመቱ ሳይጠናቀቅ ልዩ ጨረታው ይወጣል፡፡

 

የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ ኅዳር 2004 ዓ.ም. የወጣው አዋጅ በተግባር ላይ ከዋለ በኋላ አገለግሎት የሚሰጡ ግንባታዎች የሚስተናገዱት በልዩ ጨረታ ነው ቢባልም፣ በመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ዕቅድ መሠረት ልዩ ጨረታ እየወጣ ባለመሆኑ አልሚዎች እየተስተናገዱ አይደለም፡፡

      ለአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ለባለ ኮከብ ሆቴሎች፣ ለስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች፣ ለግዙፍ ሞሎችና ለሪል ስቴት ግንባታዎች ቦታ የጠየቁ ባለሀብቶች ጥያቄ እየተስተናገደ ባለመሆኑ፣ ባለሀብቶች በመጉላላታቸው  ዕቅዳቸውን ለማቋረጥ መገደዳቸውን እየገለጹ ነው፡፡

      ለኢንዱስትሪዎች፣ ለመንግሥት፣ ለማኅበራትና ለሃይማኖት ተቋማት  ፕሮጀክቶች በስተቀር በምደባ መሬት ማቅረብ ቆሟል፡፡ በተለይ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ለመገንባት የሚፈልጉ ባለሀብቶች መስተናገድ የሚችሉት በልዩ ጨረታ ብቻ መሆኑ ተገልጿል፡፡

      ነገር ግን የአዲስ አበባ ከተማ ሁለት ጊዜ ብቻ ነው ልዩ ጨረታ ያወጣው፡፡ ‹‹ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለማካሄድ ቦታ በድርድር ሊቀርብ ይገባል፡፡ ነገር ግን ድርድር ለጊዜው ቢቀር እንኳ፣ የልዩ ሊዝ ጨረታ በተደጋጋሚ ቢወጣ አማራጩን ማየት ይቻል ነበር፤›› ሲሉ ለባለ ኮከብ ሆቴልና ለሆስፒታል ግንባታ ቦታ ጠይቀው መስተናገድ አልቻልኩም ያሉት፣ የአርትሜስ ካፒታል ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መሠረት መኰንን ገልጸዋል፡፡

አርትሜስ በአዲስ አበባ ከተማ በሁለት ቢሊዮን ብር ካፒታል ሆቴልና ሆስፒታል ለመገንባት 40 ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት እንዲሰጠው ጠይቆ ነበር፡፡ ነገር ግን ቦታ ከተዘጋጀለት በኋላ በሊዝ አዋጁ ምክንያት መስተናገድ እንደማይችል ተገልጾለታል፡፡

‹‹ለከተማው ትልቅ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ፕሮጀክቶች ቢሆኑም፣ ልንስተናገድ አልቻልንም፤›› ሲሉ አቶ መሠረት ገልጸው፣ ‹‹ልዩ ጨረታውም በወቅቱ የማይወጣ፣ ሲወጣም በቁጥር አነስተኛ ቦታዎች ብቻ የሚወጡ በመሆናቸው፣ እንዲሁም በግንባታው ተሳትፎ የሌላቸው ደላሎች ዋጋ የሚሰቅሉ ስለሆነ ጉዳዩን የከፋ አድርጎታል፤›› ሲሉ አቶ መሠረት አስረድተዋል፡፡

በመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ሥር የሚገኘው የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት፣ የሊዝ አዋጁና የሊዝ አዋጁን ለማስፈጸም የወጡት ደንብና መመርያዎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ለመገንባት ጥያቄ ያቀረቡ ባለሀብቶችን ለማስተናገድ የሚቻልበት መንገድ በግልጽ አለማስቀመጣቸውን በመግለጽ፣ ማብራሪያ እንዲሰጠው ጥቅምት 2 ቀን 2006 ዓ.ም. መጠየቁን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

      የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ ቁጥር 271/2007 በፌዴራል ደረጃ የፀደቀ በመሆኑ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዚህ ላይና ሌሎች አላሠራ ባሉ የአዋጁ አንቀጾች ላይ ማሻሸያ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡

      የቤቶችና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ከአዲስ አበባና ከሌሎች ክልሎች የቀረቡለትን ቅሬታዎች መሠረት በማድረግ፣ የሊዝ አዋጁን ለማሻሻል እንቅስቃሴ መጀመሩ ይነገራል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች