Wednesday, September 27, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የግልጽነት መጥፋት ብልሹ አሠራሮችን እያስፋፋ ነው!

ግልጽነት ለመረጃ ፍሰት፣ ለሥራዎች መቀላጠፍ፣ ለቁጥጥርና ክትትል፣ ለውጤታማነትና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚረዳ መርህ ነው፡፡ ግልጽነት ሲኖር የኃላፊነት ስሜት ይፈጠራል፡፡ ተጠያቂነትን ያላብሳል፡፡ በየትም አገር ቢሆን መንግሥትም ሆነ የግል ድርጅት፣ የትምህርት ተቋምም ሆነ የጤና፣ የሙያ ማኅበራትም ሆኑ የተለያዩ አደረጃጀቶች አሠራራቸው ለሕዝብ ግልጽ መሆን አለበት፡፡ ኃላፊነትና ተጠያቂነትም እንዲሁ፡፡ በተለይ ደግሞ የመንግሥት አሠራር ግልጽ መሆን አለበት፡፡ የመንግሥት አሠራር ግልጽ መሆን ያለበት በሕግ ተጠያቂነት ስላለበት ብቻ ሳይሆን፣ የሚያወጣቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በቀጥታ በአገር ላይ ተፅዕኖ ስላላቸው ነው፡፡ ይህ ግልጽነት ደግሞ ብቃት ባላቸው አመራሮችና ሠራተኞች አማካይነት ተግባራዊ ሲደረግ የተዝረከረኩ አሠራሮች ይወገዳሉ፡፡ በኃላፊነትና በተጠያቂነት ስሜት ስለሚሠራም ሕግ ይከበራል፡፡ አሁን ግን በብዙ ሥፍራዎች በግልጽነት መጥፋት ብቻ ብልሹ አሠራሮች እየተስፋፉ ነው፡፡

የመንግሥት አሠራር ግልጽነት ሲጎድለውና የሹማምንቱ የተጠያቂነት ወሰን በማይታወቅበት ሁኔታ ውስጥ፣ የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ይደፈጠጣሉ፡፡ ለዜጎች መቅረብ ያለባቸው መሠረታዊ አገልግሎቶች ይስተጓጎላሉ፡፡ ፍትሕ ማግኘት ብርቅ ይሆናል፡፡ በመንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የመስተናገድ መብት ይጣሳል፡፡ አንድ ሙሰኛ ወይም ደንታቢስ በያዘው ጉዳይ ምክንያት ዜጎች ለብዙ ጊዜ ይንከራተታሉ፡፡ አቤቱታ ሲያሰሙ በአግባቡ አዳምጦ የሚመልስ አይኖርም፡፡ ችግሮች እየተደራረቡ ይሄዱና ብሶት ሲገነፍል ከመራወጥ ይልቅ፣ በሕጉ መሠረት ኃላፊነትን መወጣት ከብዷል፡፡ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተመሥርተው ምሬት ሲያቀርቡ ብልሹ አሠራሮች መንስዔ መሆናቸውን ማን ያስተባብላል? በበርካታ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ አገራቸውን የሚወዱና የሕዝብ አገልጋይነት መንፈስ ያላቸው በርካታ ዜጎች የመኖራቸውን ያህል፣ ወሳኝ የሆኑ ኃላፊነቶችን ይዘው ሕዝብ የሚያስለቅሱ ደግሞ በብዛት አሉ፡፡

ያለንበት ዘመን መረጃ በብርሃን ፍጥነት ከአንዱ ወደ ሌላው የሚተላለፍበት ነው፡፡ ከዚህ ፈጣን ግስጋሴ ጋር እኩል መራመድ ፈተና የሆነባቸው፣ ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን ሲያቅታቸው በራቸውን ዘግተው ችግር ይፈጥራሉ፡፡ ብቃት ስለሌላቸውና በራሳቸው ስለማይተማመኑ ከመሥራት ይልቅ ማደናቀፍ ይቀናቸዋል፡፡ የሚሠሩ ከሆነ ግን ግልጽ መሆን አለባቸው፡፡ ኃላፊነትና ተጠያቂነትም ይኖርባቸዋል፡፡ ግልጽነትን፣ ተጠያቂነትንና ኃላፊነትን የሚሸሹት እንቢ በማለት ነው፡፡ ሠርተው ማሠራት ስለማይችሉ ይደበቃሉ፡፡ የሚሠራውን ደግሞ ጠልፈው ይጥላሉ፡፡ በተለያዩ መዋቅሮች ውስጥ ተሰግስገው ብልሹ አሠራሮችን ያስፋፋሉ፡፡ ብዙ ጊዜ የሚጠየቁት ወይም ካሉበት ኃላፊነት የሚነሱት በርካታ ጥፋቶችን ካደረሱ በኋላ ስለሆነ፣ በሕዝቡ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ምሬት ይፈጠራል፡፡ በዚህም ሳቢያ ሕዝብና መንግሥት ይጋጫሉ፡፡ ጥቂቶችን ለመከላከል ብቻ ሲባል ሕዝብ ጥላቻ ውስጥ እንዲዘፈቅ ይደረጋል፡፡ መንግሥት ተዓማኒነቱን ያጣል፡፡

ግልጽነት ለመንግሥት፣ ለገዥው ፓርቲ፣ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ለግል ድርጅቶች፣ ለግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ ለፍትሕ አካላት፣ ለሙያ ማኅበራት፣ ለሚዲያ፣ ለትምህርትና ለምርምር ተቋማት፣ ወዘተ. በጣም አስፈላጊ መርህ ነው፡፡  እዚህ አገር ውስጥ እንደ ልማድ አስረው ከሚጎትቱ ችግሮች መካከል አንደኛው የግልጽነት አለመኖር ነው፡፡ መንግሥትም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የእዚህ መጥፎ ልማድ እስረኞች ናቸው፡፡ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ መንግሥት ድረስ ድብቅነት ይበዛል፡፡ መልካም ከሚባሉ ጉዳዮች ውጪ የሚያጋጥሙ ሌሎች ክስተቶች ይድበሰበሳሉ፡፡ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ወሳኝ በተባሉ ጉዳዮች ላይ በግልጽነት አይወያዩም፡፡ ባልና ሚስት መሀል ጭምር ክፍተቶች አሉ፡፡ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ደግሞ ግልጽነት ብርቅ ነው፡፡ በመረጃ ዕጦት ወይም መዛባት ምክንያት ከእውነታዎች ይልቅ ሐሜቶችና አሉባልታዎች የበላይነት የሚይዙት፣ ግልጽነት በጎደለው ኅብረተሰብ ውስጥ መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡

ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት ባለመቻሉ ብቻ ዕርዳታ ለተጎዱ ወገኖች ጊዜውን ጠብቆ አይደርስም፡፡ የአቅርቦት ችግር ሳይኖር መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ለሕዝቡ በአግባቡ አይሠራጩም፡፡ በድንገተኛ አደጋ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች በመንግሥት የተገባላቸው ቃል ተፈጻሚ አይሆንም፡፡ በአሁኑ ጊዜ በበርካታ ሥፍራዎች ቸልተኝነት ከመቼውም ጊዜ በላይ አብቧል፡፡ የሚቆጣጠር የበላይ አካል የለም ወይ እስኪባል ድረስ ኃላፊነትን በአግባቡ አለመወጣት ባለመቻሉ ብቻ፣ በየቦታው በጣም የሚያሳፍሩ ድርጊቶች ተንሰራፍተዋል፡፡ ግብር ከፋዩ ሕዝብ አገልግሎት ተስተጓጉሎበት ቅሬታ ሲያቀርብ፣ ይህ ቅሬታ ነገ ወዴት ያመራል የሚል ሐሳብ የሌላቸው በዝተዋል፡፡ በየቦታው ራሳቸው ላይ ትንንሽ ዘውዶች የደፉ ሹማምንት ማንንም ሳይፈሩ በአደባባይ ጉቦ ይቀበላሉ፡፡ ካልተሰጣቸው ደግሞ ያንገላታሉ፡፡ ብልሹ አሠራሮችን በማስፈን የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማትን የደላላ መፈንጫ አድርገዋል፡፡ ፍትሕ ፍለጋ የሚባዝኑ ዜጎች እንባቸውን የሚያብስላቸው አጥተው ሲብሰከሰኩ ደንታ የማይሰጣቸው ሞልተዋል፡፡ ችግሩ ፈንድቶ ነውጥ ሲነሳ ግን ጣት ለመቀሰር አንደኛ ናቸው፡፡ በዚህ ሥልጡን ዘመን ለሕዝብም ለአገርም የማይመጥኑ በየቦታው ተኮልኩለው አገር ሲያተራምሱ ማየት ይቆጫል፡፡

አገሪቱን በጣም እየጎዱ ካሉ ችግሮች መካከል አንዱ የግልጽነትና የተጠያቂነት መጥፋት ነው፡፡ የዘር፣ የሃይማኖት፣ የባህል፣ የቋንቋ፣ የፖለቲካ አመለካከትና የመሳሰሉ ልዩነቶች ባሉበት አገር ውስጥ ግልጽነት ከሌለ እንዴት ልዩነቶችን ማቻቻል ይሞከራል? በማንኛውም ጊዜና አጋጣሚ ችግሮች ሲያጋጥሙ መፍትሔው ማፈላለግ የሚቻለው ግልጽነት ሲኖር ነው፡፡ አቅዶ ለውጤት መብቃት የሚቻለው ግልጽነት ሲኖር ነው፡፡ ሥራን በአግባቡ መርቶ ለዕድገት መብቃት የሚቻለው ግልጽነት ሲኖር ነው፡፡ ግልጽነት ለሕግ የበላይነት መስፈን፣ ለዴሞክራሲ መዳበር፣ ለሰብዓዊ መብት ጥበቃ፣ ለሐሳብና ለንግግር ነፃነት፣ በሰላማዊ መንገድ ታግሎ በምርጫ ሥልጣን ለመያዝ፣ በአገር ግንባታ ተሳትፎ ለማድረግና አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ወሳኝ ነው፡፡ ግልጽነት በሌለበት ሌብነት፣ ሕገወጥነት፣ ማናለብኝነት፣ ግዴለሽነትና አምባገነንነት ይንሰራፋሉ፡፡ አገሪቱ በትክክለኛ ጎዳና ላይ እንድትራመድ ከተፈለገ ሕዝብ፣ መንግሥትና ይመለከተናል የሚሉ አካላት በሙሉ ግልጽነት እንዲሰፍን ይረባረባሉ፡፡ ግልጽነት የጎደለው አገር የአጥፊዎች መፈንጫ ከመሆኑም በላይ፣ ብልሹ አሠራሮችን ያስፋፋል!    

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...

ማን በማን ላይ ተስፋ ይኑረው?

በአንድነት ኃይሉ ችግሮቻችንን ለይተን ካወቅን መፍትሔውንና ተስፋ የምናደርግበትን ማወቅ እንችላለን፡፡...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት...

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...