Sunday, September 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቀን ገቢ ግምት ባለመሠራቱ የአዲስ አበባ የንግድ ሥርዓት ፍትሐዊነት እንደተዛባ ተጠቆመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከ2003 ዓ.ም. ወዲህ በአዲስ አበባ ያለው የንግድ ሥርዓት ፍትሐዊነት የጎደለው መሆኑ ተጠቆመ፡፡ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የአዲስ አበባ ታክስና ፕሮግራም ሥራዎች ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ነፃነት አበራ ዓርብ ግንቦት 11 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፣ በአዲስ አበባ የቀን ገቢ ግምት ሳይሠራ ለሦስት ዓመታት በመዘግየቱ  በንግድ ሥርዓቱ ላይ የፍትሐዊነት ችግር እንደፈጠረ ገልጸዋል፡፡

እንደ ወ/ሮ ነፃነት ገለጻ፣ የቀን ገቢ ግምት መካሄድ የነበረበት በየሦስት ዓመቱ እንደሆነ ሕጉ ቢያዝም፣ ከ2003 ዓ.ም. ወዲህ የገቢ ግምት ሥራ ባለመሠራቱ ነጋዴውን የበይ ተመልካች አድርጎት ቆይቷል፡፡ በ2003 ዓ.ም. የቀን ገቢ ግምት ተሠርቶላቸው ወደ ንግድ ሥርዓቱ የገቡ አካላት ተገቢውን ግብርና ታክስ ለመንግሥት እየከፈሉ ቢሆንም፣ ከዚያ ወዲህ ወደ ንግድና ኢንቨስትመንት ሥርዓቱ የተቀላቀሉ አካላት ግን በዚህ ሥርዓት ሳይካተቱ መቆየታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ሳቢያ በነጋዴው መካከል የፍትሐዊነት ጥያቄ ሲነሳ እንደቆየ የጠቆሙት ምክትል ዳይሬክተሯ፣ በ2009 ዓ.ም. የሚደረገው የቀን ገቢ ግምት እነዚህን የፍትሐዊነት ጥያቄዎች ሊፈታ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

ሚያዚያ 17 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የተጀመረው የቀን ገቢ ግምት ሥራን በተመለከተ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮና በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አማካይነት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተጠቆመው፣ በአሁኑ ጊዜ የቀን ገቢ ግምት ማካሄድ ያስፈለገው አሁን ያለውን የኢኮኖሚ ዕድገት ያገናዘበ አማካይ የቀን ገቢ ግምት በማጥናት እያንዳንዱ ነጋዴ ደረጃውን እንዲያውቅ፣ በደረጃው መሠረትም የሚጣልበትን ግብርና ታክስ እንዲከፍል ለማድረግ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፎይኖ ፎላ ከዚህ በፊት የነበረው የገቢ አሰባሰብ ሥርዓት ክፍተት እንደነበረበት ጠቁመው፣ ይህንን ክፍተት ለመሙላትም ባለፉት አምስት ዓመታት ጥናቶች ሲካሄዱ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡ አሁን እየተደረገ ያለው የቀን ገቢ ግምት ከዚህ በፊት ወደ መረጃ ሥርዓቱ ያልገቡ ነጋዴዎችን በማስገባት፣ ተገቢውን ግብርና ታክስ ለመሰብሰብ እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዲላሞ ኦቶሬ በበኩላቸው፣ የዘንድሮው የቀን ገቢ ግምት ሥራ ካለፉት ዓመታት በዝግጅትና በአደረጃጀት እንደሚለይ ጠቁመዋል፡፡

አሁን እየተደረገ ያለው  የቀን ገቢ ግምት ሥራ ከነጋዴው አቅም በላይ ግብርና ታክስ በመጫን አላስፈላጊ የሆነ ገቢ ለመሰብሰብ አይደለም የሚሉት ወ/ሮ ነፃነት፣ ይህን ሥራ ለማከናወን ከሚያዚያ 17 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ 1,904 ገማች አባላት ወይም 469 ቡድን ተሰማርቷል ብለዋል፡፡ አሁን ያለው የቀን ገቢ ግምት ሥራ 50 በመቶ እንደደረሰ የጠቆሙት ምክትል ዳይሬክተሯ፣ ወደ ሥራው ሲገባ ችግሮች አጋጠጥመው እንደነበር አልሸሸጉም፡፡

የገማች አባላትን ሥነ ምግባር በተመለከተ ለቀረበው ጥያቄ ወ/ሮ ነፃነት ሲመልሱ፣ ከዚህ በፊት ከነጋዴው ጋር እየተመሳጠሩ የቀን ገቢ ግመታውን ያስተጓጎሉ ባለሙያዎች ነበሩ ብለዋል፡፡ ዘንድሮ ግን እነዚህንና መሰል ድርጊቶችን ለመከታተል ያመች ዘንድ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡ ይህንንና ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት መመርያ የተዘጋጀ መሆነን የጠቆሙት ምክትል ዳይሬክተሯ፣ በመመርያው ላይ የንግዱ ማኅበረሰብ ማድረግ ያለበትን ዝግጅት፣ መረጃ እንዴት መስጠት እንዳለበት፣ ሳይሰጥ ቢቀር በምን አግባብ ሊዳኝ እንደሚችልና የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸው ገማች ኮሚቴዎች ሊወሰድባቸው ስለሚገባ ዝርዝር ዕርምጃዎች በመመርያው መቀመጡን አስረድተዋል፡፡

እስካሁን በተደረገው የቀን ገቢ ግምት ሥራ የተፈጠሩ ችግሮች ምን እንደሆኑ የተጠየቁት ኃላፊዎቹ፣ ነጋዴው ትክክለኛ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆን፣ ዘግቶ መጥፋት፣ መረጃ ሊሰጡ የማይችሉ ሕፃናትን ማስቀመጥና ሸቀጦችን መሰወር ዋነኛ ችግሮች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ የሚጠቀሙ ነጋዴዎች ለምን በዚህ የቀን ገቢ ግምት ውስጥ መካተት እንዳለባቸው የተጠየቁት ወ/ሮ ነፃነት፣ በአዲስ አበባ የደረጃ ‹‹ሀ›› እና የደረጃ ‹‹ለ›› ግብር ከፋዮች የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ገዝተው እንዲጠቀሙ መመርያው እንደሚያስገድድ አስታውቀዋል፡፡ በዚህ መሠረት አብዛኛዎቹ የገዙ ቢሆንም፣ በትክክል እየተጠቀሙበትና ደረሰኝ ቆርጠው እየሰጡ እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች