Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ዓረቢካን የመሰለ ቡና ለዓለም ከሰጠን እኛ ለምን ሳይንሱን አንመራውም››

የጅማ ዩኒቨርሲቲ የቡና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር፣ ገዛኸኝ በሬቻ (ዶ/ር)

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የግብርና እና የእንስሳት ሕክምና ኮሌጅ በበመምህርነትና በተመራማራነት ማገልገል ከጀመሩ 16 ዓመታትን ያስቆጠሩት ገዛኸኝ በሬቻ (ዶ/ር)፣ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የቡና ምርምር ተቋም (International Institute of Coffee Research At Jimma University) መሥራችና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ዶክተር ገዛኸኝ ከ19 ዓመታት በፊት በጅማ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ የፕላንት ሳይንስ ተማሪ ነበሩ፡፡ ከዚያ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሆርቲካልቸር፣ ማስተርስ ዲግሪያቸውን ደግሞ በኦርጋኒክ ፋርሚንግ፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ በቡና ዘረመል ላይ ሰርተዋል፡፡ በአገሪቱ ስላለው የቡና ምርት ሁኔታና የተቋሙን እንቅስቃሴ በተመለከተ ሻሂዳ ሁሴን ዶክተር ገዛኸኝን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ተቋሙ የተመሰረተበት አላማ ምንድነው?

ዶ/ር ገዛኸኝ፡- እንደሚታወቀው ጅማ የቡና መገኛ ቦታ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክም ትልቁ የቡና ማሳ በጅማ ነው የሚገኘው፡፡ በአጠቃላይ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የቡና መገኛ እንደሆነ ነው የሚታወቀው፡፡ አጋጣሚው ዩኒቨርሲቲው በቡና ላይ ትኩረቱን አድርጎ ቢሠራ ጥሩ ስም የሚያሰጠው እንደሆነ አምኖ ከሰኔ 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በቡና ላይ ትኩረቱን ያደረገ የቡና ዓለም አቀፍ የምርምር ተቋም አቋቋመ፡፡ ቀደም ሲል ዩኒቨርሲቲው ላለፉት 40 ዓመታት በቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ላይ በስፋት ሲያሠለጥን ቆይቷል፡፡ ይህን የምርምር ተቋም እንዲቋቋም ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ በቂ የሠለጠነ  የሰው ሀብት አለው፡፡ ቡና እንደሌሎቹ ሰብሎች አይደለም፡፡ ቡና ብዙ ነገር ነው፣ ቡና ኢኮኖሚ ነው፣ ቡና አንትሮፓሎጂ ነው፣ ቡና ከኢኮ ሲስተም ጋር ትልቅ ቁርኝት አለው፣ ቡና ከቱሪዝም ጋር ይገናኛል፡፡ ዩኒቨርሲቲውም በቡና ላይ አሥር የዶክትሬት ዲግሪ ፕሮግራሞች መስጠቱም በቡና ላይ የሚሠሩ በቂ ባለሙያዎች እንዲኖሩን አድርጓል፡፡ እኔም የዶክትሬት ዲግሪዬን የሠራሁት በቡና ላይ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው የተለየ ነገር መፍጠር የሚችለው በዚህ በአረንጓዴ ወርቅ በቡና ላይ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ አጋሮቻችንም ይህንኑ ነው የሚሉት፡፡ ቡና በአንድ የሙያ ዘርፍ ብቻ የሚሠራ አይደለም፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለሙያዎችና የትምህርት ዘርፎች በዩኒርሲቲው መኖራቸው ደግሞ መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ ቡናን ለማጣጣም ቡና መቆላት፣ መፈጨት አለበት፡፡ በዚህ ውስጥ ብዙ የኬሚካል ሪአክሽኖች አሉ፡፡ ለቡና ጣዕም የሚሰጡ በርካታ ይዘቶች አሉ፡፡ እነዚህን የሚያጠና ኦርጋኒክ ኬሚስትሪ በመሆኑ ከተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ጋር ያገናኘዋል፡፡ ግብርና ላይ ብቻ ተመሥርቶ የሚሠራ ሳይሆን ከሌሎች የሙያ ዘርፎች ጋር የሚያገናኘው በመሆኑና እነዚህ የሙያ ዘርፎች እዚሁ ዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው የምርምር ተቋሙ እንዲቋቋም ሌላው የተመቸ አጋጣሚ ነው፡፡ በቡና ዘረመል ሀብት ላይ ያሉት የተለያዩ ሥጋቶች በንጥረ ነገር ይዘቱ ላይ ሊፈጥሩ የሚችሉትን ችግር በተመለከተ ምርምር አድርገናል፡፡ ለምሳሌ ጫካዎች ሲመነጠሩ በቡና ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ እንደሚፈጥር፣ ምርምር አድርገን የጥበቃ ስትራቴጂ ዲዛይን አዘጋጅተናል፡፡

ሪፖርተር፡- የጥበቃ ስትራቴጂውን ቢያብራሩልን

ዶ/ር ገዛኸኝ፡- በኢትዮጵያ ሁሉም ቦታ ቡና አለ፡፡ የቡና ዘረመል ሀብትን ለማስጠበቅ በአገሪቱ ሁሉም ቦታ ላለው የቡና ምርት ጥበቃ ማድረግ አይቻልም፡፡ ትልቁ የቡና ዝርያና ብዝኃነት የሚገኝበት ቦታ ግን መጠበቅ አለበት፡፡ ስለዚህ ያ ቦታ የትነው? የሚለው መለየት አለበት፡፡ ቦታው ከተለየ በኋላ ደግሞ በምን ዓይነት መልኩ በማን መጠበቅ አለበት? ምን ዓይነት ጥቅምስ መገኘት አለበት? የሚሉትን ያካተተ ነው ስትራቴጂው፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት በቡና ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ የሚገኙ በሽታዎች የትኞቹ ናቸው? በተደጋጋሚ ጊዜ በመከሰት ምርት የሚያጠቁትስ የትኞቹ ናቸው?

ዶ/ር ገዛኸኝ፡- በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በስፋት የነበረ አሁንም በከፊል ያለ ኮፊቤሪ የተባለው የቡና በሽታ ነው፡፡ አንዳንዴ ገበሬዎች ኮሌራ ይሉታል፡፡ ይህ ቡናን በጣም በማጥቃት የሚታወቅ ነው፡፡ ሌላውና በጣም አስቸጋሪው ኮፊ ዊልት ዲዚዝ ነው፡፡ ይኼ በሽታ አንዴ ከተከሰተ አይድንም፡፡ ያለው አማራጭ ወደ ሌላ እንዳይዛመት ግንዱን ነቅሎ ማቃጠል ነው፡፡ ሌላው ኮፊ ሊፈረስት የምንለው ነው፡፡ ይሄ በሽታ ለአገሪቱ በተለይም ካለው የአየር ለውጥና ከሙቀቱ ጋር ተዳምሮ ትልቅ ሥጋት ሆኗል፡፡ ከዚህ ቀደም እንደ ቴፒና በበቃ ባሉ ዝቅተኛ ቦታዎች ላይ ብቻ ነበር እንደችግር ይታይ የነበረው፡፡ አሁን ግን ወደ ሌሎቹ የቡና አብቃይ ቦታዎች በስፋት እየታየ ያለ ሌላው ሥጋት ነው፡፡ በዓለም ደረጃ ግን አንደኛ ሥጋት ነው፡፡ ለምሳሌ ከዓመት በፊት 34 በመቶ የሚሆነው የኮሎምቢያ ቡና በዚህ በሽታ ምክንያት እንዲወገድ ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- የኮፊ ሊፈረስት በሽታ መገለጫው ምንድነው?

ዶ/ር ገዛኸኝ፡- በቅጠሎች ጀርባ ላይ የሚታይ ዝገት የመሰለ ነገር ነው፡፡ ይህ ዝገት መሳይ ነገር እየሠፋ ሲመጣ ቅጠሎች ይረግፋሉ፡፡ ምግብ የሚሠራው የአጠቃላይ ምርቱን ሕይወት የሚደግፈው ቅጠሉ ረገፈ ማለት ደግሞ በቂ ፍሬ እንዳይሰጥ፣ ቡናው እንዲደርቅ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በጊዜ መፍትሔ ካልተሰጠው እንደ ኮፊ ዊልት ግንዱን ሊያደርቀው ይችላል፡፡ ነገር ግን በሽታውን ለመከላከል ኬሚካል መርጨት ይቻላል፡፡ ከአየር ለውጥ ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም በቡና ላይ ብዙም ለውጥ አያመጡም የሚባሉ አሁን ግን ከፍተኛ ችግር እያስከተሉ ያሉ ተባዮችም አሉ፡፡ ብሎች ሊፍ ማይነር የሚባለው ተባይ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ነው፡፡ አሁን ከአየር ለውጥ ጋር ተያይዞ በስፋት እየተከሰተ ይገኛል፡፡ በተለይ ከዓመት በፊት በቡና ላይ ከፍተኛ ችግር አስከትሎ ነበር፡፡ ሁለተኛው አንቴስቲያበግ ነው፡፡ አንቴስቲያበግ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ በስፋት ይታያል፡፡ ሌላው ኮፊቤሪቦረር የሚባል በሌላው ዓለም ትልቅ ችግር እየፈጠረ ያለው ተባይ ነው፡፡ በእኛ አገር ወደ እነ ቴፒና በበቃ አካባቢ ይታያል፡፡ ወደ ሌላ አግሮ ኢኮሎጂም እየመጣ ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ ከአየር ንብረቱ ጋር ተያይዞ በተባዮችና በሽታዎች ለቡና ትልቅ ሥጋት እየሆኑ መተዋል፡፡ ስለዚህ የቡና ጥናት፣ የቡና እንክብካቤ አያያዝ ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ለቡና የሚያሠጉ የበሽታ፣ የተባዮች፣ የአረም እንደዚሁም ተለዋዋጭ የሆነው የአየር ንብረት በቡና ምርት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ሳይቀር ነው የምናጠናው፡፡ አንደ ምሳሌ የምጠቅሰው በጅማ ዞን ውስጥ ሰንጠማ በሚባል አካባቢ ያደረግነው አንድ ጥናት አለ፡፡ ቦታው ከዚህ በፊት ከፍተኛ ዝናብ የሚያገኝ ቦታ ነው፡፡ ስለዚሀ የአየር ለውጥ በእርግጥ ለቡና ሥጋት ነው ወይ? እየተከሰተ ያለ ነገርስ ነው ወይ? በቡና ተባዮችና በሽታዎች ላይ ምን ዓይነት ለውጥ እየፈጠረ ይገኛል በሚል ቀደም ተብሎ የተደረገ አንድ ጥናት አለ፡፡ በጥናቱ መሠረት በአካባቢው ለሚቀጥሉት 30 ዓመታት የሙቀት መጠን በሦስት ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይጨምራል፡፡ የዝናቡ መጠን ግን አሁን ባለበት መጠን ነው የሚቀጥለው፡፡ ይኼ ደግሞ ለቡና ከፍተኛ ችግር ነው፡፡ ቡናው ከሚፈልገው በላይ አንድ ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሙቀት መጨመር በራሱ ትልቅ ችግር ነው፡ በሌላ በኩል ሙቀቱ ለአንዳንድ ተባዮች አመቺ ሁኔታን ይፈጥል፡፡ ለዚህ መፍትሔ የሚሆኑ ሥራዎችን ፕሮጀክት ቀርፀን በገበሬው ማሳ የላይ እየሠራን እንገኛለን፡፡ የተለያዩ የቡና ዝርያ ያላቸውን ማለትም የውኃ እጥረትና በሽታን የመቋቋም አቅም ያላቸው ዝርዎች በአየር ለውጥ በሚጠቁ ቦታዎች ላይ እንዲተከሉ የችግኝ ማፍላትና  ተከላ እንዲካሄድ እያደረግን እንገኛለን፡፡ በሌላ በኩል የአየር ለውጥ የቡና ምርት ላይ ችግር እንዲከሰት የሚያደርግ  ከሆነ ለማኅበረሰቡ ኑሮውን የሚደግፍበት አማራጭ መፍጠርም ግድ ነው፡፡ በዚህ መሠረት የአካባቢው ማኅበረሰብ በንብ ማነብ እንዲሠማራ ተደርጓል፡፡ የምግብ አቅርቦትን በተመለከተም በቀላሉ በበሽታ ማይጠቁ የበቆሎ ዝርያዎች በአካባው እንዲስፋፉ አድርገናል፡፡ ከዚህም ሌላ ለቡና ጥበቃ የሚሆኑ የተለያዩ አገር በቀል ዛፎችን የመትከል ዘመቻም እንጀምራለን፡፡ ይህም የአየር ለውጥ በአካባቢው ላይ የሚፈጥረውን ተፅዕኖ ከወዲሁ መከላከል የሚያስችል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ተቋሙ በሽታን የሚከላከሉ ችግኞችን አፍልቶ ለገበሬው በማሠራጨት ረገድ ትልቅ ክፍተት እንዳለበት አርሶ አደሮች ያማርራሉ፡፡ በዚህ ላይ የእርሶ አስተያየት ምንድነው?

ዶ/ር ገዛኸኝ፡- በቂ ዘር አባዝቶ ለገበሬዎች በማሠራጨት በኩል ትልቅ ክፍተት አለ፡፡ በዚህ ውስጥ ብዙ ባለድርሻዎች አሉ፡፡ የምርምር ተቋም ተመራምሮ ያገኘውን አንድ መነሻ ዘር ለባለድርሻ አካል ይሰጣል፡፡ ነገር ግን አብሮ የመስራቱ ነገር በጣም የላላ ነው፡፡ እንደዚህ ያሉ የምርምር ተቋማት ምርምር ውጤቶችን በባለቤትነት ማስፋፋት ያለበት ግብርና ሚኒስቴር ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲ፣ በምርምር ተቋማትና በግብርና ቢሮዎች በኩል ያለው ግንኙነት ላይ ትልቅ ክፍተት አለ፡፡ ተናቦ በመሥራት ረገድ ትልቅ ችግር አለ፡፡ ገበሬዎቹ የሚያነሱት ነገር በጣም ትክክል ነው፡፡ ገበሬዎች አለማቋረጥ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ለምሳሌ አንድ አዲስ ቴክኖሎጂ ለግብርና ይረዳል ብዬ ለገበሬው ጥዬለት ብመጣ ዋጋ ለውም፡፡ ከቴክኖሎጂው ጋር ልናስተዋውቀው፣ ልናስተምረው ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ልንሰጠው ይገባል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ አጠገቡ የግብርና ባለሙያ አለ፡፡ ነገር ግን ተገቢውን ነገር እያደረጉ ነው? እኔ እጠራጠራለሁ፡፡ ቡና ላይ ለውጥ አልመጣም በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን በጀት ዓመት ቡና ላይ ለማስመዝገብ የተያዘውን ዕቅድ 50 በመቶው እንኳን ማሳካት አልተቻለም፡፡ ይህ የሚያሳየው ሁሉም ባለድርሻ አካል ተናቦ አለመሥራቱን ነው፡፡ ትልቅ ክፍተት ነው፡፡ እኛ ግን እንደ አንድ ተቋም የተወሰኑ ዘሮችን አባዝተን ለተወሰኑ ገበሬዎች በዓመት እንሠጣለን፡፡ ነገር ግን በጣም ጥቂት ነው፡፡ እንደ መንግሥት በስፋት ሊኬድበት የገባል፡፡ ግብርና ሚኒስቴር ጉዳዩን በባለቤትነት ሊሠራበት ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ምን ያህል የተሻሻሉ ዝርያዎችን ማውጣት ችሏል?

ዶ/ር ገዛኸኝ፡- አንድ ዝርያ ለማውጣት በትንሹ ከአሥር እስከ አሥራ አምስት ዓመታት ይፈጃል፡፡ በድሮ ኮንቬንሽናል ብሪዲንግ ደግሞ እስከ 30 ዓመታት ያስፈልጋል፡፡ በጣም ረዥም ጊዜ ይፈጃል፡፡ ነገር ግን አንድ ችግር ሲከሰት ለችግሩ የአጭር ጊዜ፣ የመካከለኛ የረዥም ጊዜ ስትራቴጂ ይቀመጣል፡፡ በሽታው ሲከሰት  ከነበሩት ዝርያዎች ውስጥ በሽታውን መቋቋም ሚችሉ መኖራቸውን ማረጋገጥና ከተገኙ በሁለትና ሦስት ዓመት ውስጥ ወደ ሥራው መግባት ነው፡፡ ሌላው በአጭር ጊዜ ሊጠናቀቅ የሚችል በሽታውን መቆጣጠር የሚችል ኬሚካል ካለ ፍተሻ ማድረግ ነው፡፡ በሌላ አገር ጥቅም ላይ የሚውሉ ኬሚካሎችን ማስገባት ይቻላል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ቡና ኦርጋኢክ (የተፈጥሮ) ቡና ነው፡፡ ገበሬዎቻችን ያንን ያህል ኬሚካል እንዲጠቀሙ አናበረታታም፡፡ ስለዚህ ተፈጥሯዊ የሆኑ የመከላከያ ዘዴዎችን በመጠቀም በሽታውን እንዲከላከሉ ይደረጋል፡፡ ይሁንና ችግሩ እየገዘፈ የሚሄድ ከሆነ ምርቱን ማጣት ስለሌለብን ወደ ኬሚካሉ ልንሄድ እንችላለን፡፡

ሪፖርተር፡- የቡናን ደኅንነት በባህላዊ መንገድ እንዴት ማስጠበቅ ይቻላል?

ዶ/ር ገዛኸኝ፡- ጥሩ ምግብ ካገኘ ንፅህናው ከተጠበቀ በቂ ነው፡፡ በጣም ሲታፈን፣ ከፍተኛ ጥላ ሲኖር፣ የአየር እርጥበቱ እየጨመረ ይመጣል፡፡ ይህም ለአንዳንድ በሽታዎች መከሰት አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ለምሳሌ ከቡና ላይ ጥላን በማሳሳት ፀሐይ እንዲገባና ነፋስ እንደ ልብ እንዲዘዋወር ማድረግ የቡና ምርትን ከበሽታ የሚከላከሉበት አንዱ ባህላዊ ዘዴ ነው፡፡ ከግንዱ ላይ የሚወዳድቁ ቅጠሎችም ሳይነሱ መቅረት የለባቸውም፡፡ ተባዮችም በጣም ካልበዙ በስተቀር በእጅ ለቅሞ ማንሳት ይቻላል፡፡ ዋናው ክትትል ማድረግ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ተደራሽነታችሁ በጅማ ዙሪያ የተወሰነ ነው ወይስ በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች?   

 ዶ/ር ገዛኸኝ፡- እኛ ሁሉም የቡና አካባቢዎች ላይ ሄዶ ለመሥራት ነው ዕቅዳችን፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን ተመሳሳይ ሥራ ከሚሠሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ነው የምንሠራው፡፡ ይህም በቡና ዙሪያ ከባድ ተፅዕኖ መፍጠር እንድንችል ያደርገናል፡፡ ቡናን በተለይም ዓረቢካን  የመሰለ ቡና ለዓለም ከሰጠን እኛ ለምን ሳይንሱን አንመራውም የሚል ራዕይ ነው ያለን፡፡

ሪፖርተር፡- የቡና መገኛ አገር የሆነቸው ኢትዮጵያ ከቡና ማግኘት የሚጠበቅባትን ጥቅም እያገኘች አይደለም ይባላል፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተየያየት ምን ይመስላል? ምክንያቱስ ምንድነው ይላሉ?

ዶ/ር ገዛኸኝ፡- ይህ ሰፊ ነው፡፡ ቡናን ለብዙ ዘመናት ስናመርት የቆየን ነን፡፡ ነገር ግን የምናመርትበት መንገድ ኋላ ቀር ነው፡፡ ሁለተኛና ትልቁ ነገር እኛ ከቡና ማግኘት ያለብንን ጥቅም የማናገኝበት ምክንያት ባለው የጥራት ችግር ነው፡፡ በዓለም ላይ እጅግ ተፈላጊ የሆነውን ዓረቢካ ቡና እናመርታለን፡፡ ነገር ግን በሚፈለገው መጠን ጥራቱን ጠብቆ መላክ ላይ ክፍተት አለ፡፡ የቡና ግብይቱ ላይም ራሱን የቻለ ትልቅ ችግር አለ፡፡ የአንድ አካባቢ ቡናን ከሌላው ጋር የመቀላቀል ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ የጅማ ቡናን ከይርጋ ጨፌ ጋር የመቀላቀል ችግር አለ፡፡ የጅማ ቡና ራሱን የቻለ ጣዕም አለው፡፡ የይርጋ ጨፌም ራሱን የቻለ ጣዕም አለው፡፡ በሚቀላቀሉበት ጊዜ በጥራቱ ላይ ችግር ይፈጥራል፡፡ የይርጋ ጨፌን ቡና ለሚፈልግ ዓለም አቀፍ ደንበኛ የተቀላቀለው ሲላክ ላይቀበል ይችላል፡፡ ሌላው ዋናውና ትልቁ ችግር ቡናችንን ብራንድ አድርገን አንልክም፡፡ ቡናችን በሚመረትበት አካባቢና በጣዕማቸው ብራንድ አድርገን አለመላካችን ማግኘት የሚገባንን ጥቅም እንዳናገኝ አድርጎናል፡፡ ከዚህም ሌላ ላለፉት በርካታ ዓመታት እሴት ሳንጨምር አረንጓዴ ቡና ነው ምንልከው፡፡ አሁን ብቅ ብቅ የሚሉ እሴት ጨምረው የሚልኩ ድርጅቶች  አሉ፡፡ መንግሥትም በዚህ ዙሪያ ለሚሠሩ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ማድረግ ጀምሯል፡፡ ቡናን እሴት ጨምረን አለመላካችን ትልቅ ችግር ነው፡፡ ሌላው ጉዳይ የቡና ጥራት እዚያው ማሳ ላይ ነው የሚጀመረው፡፡ ማሳ ላይ የተሻለ እንክብካቤ፣ ንጥረ ነገር አግኝቶ ካላደገ የምርት ጥራቱ ላይ ችግር ይፈጠራል፡፡ አዘገጃጀቱ አጫጫኑ ሁሉ በጥራቱ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ በዚህ ረገድ ትልቅ ችግር አለ፡፡ ስለዚህም ነው መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ አገሪቱ በቡና ተጠቃሚ እንድትሆን እየሠራ ያለው፡፡ የእኛ ተቋምም ይኼንን አገራዊ ንቅናቄ ጥናት በሚያስፈልግበት ቦታ በጥናት፣ ሥልጠና በሚያስፈልግበት ቦታ ሥልጠና በመስጠት የራሳችንን አስተዋጽኦ ለማድረግ እየሠራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አገሪቱ በቡና ምርት ምን ያህል  እምቅ አቅም አላት? መጠቀም የተቻለውስ በምን ያህል ነው?

ዶ/ር ገዛኸኝ፡- በአገሪቱ ወደ ቡና ማሳነት መለወጥ የሚችሉ በጣም ብዙ ቦታዎች አሉ፡፡ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ በአማራ ክልል ለቡና ምርት የተመቹ ቦታዎች አሉ፡፡ ዝቅተኛ ቦታዎችን ሳይቀር መስኖን በመጠቀም ቡና አምራች ማድረግ ይቻላል፡፡ ነገር ግን አገሪቱ ያላትን አቅም 50 በመቶ ያህል እንኳ ጥቅም ላይ ማዋል አልተቻለም፡፡ ይህን ለማድረግ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል፡፡ በዓለም ላይ አንደኛ ቡና አቅራቢ አገር ብራዚል ነች፡፡ ከብራዚል ቀጥሎ ከዛሬ 27 ዓመታት በፊት ቡና ማምረት የጀመረችው ቬትናም ነች፡፡ ኢትዮጵያ ላለፉት ሦስትና አራት ዓመታት በአምስተኛ ደረጃ ላይ ነው የምትገኘው፡፡ በሚቀጥሉት አምስት አመታት ቬትናምን ከቦታዋ ለማንሳት ዕቅድ ተይዟል፡፡ የገበያ ድርሻችንን ወደ አሥርና 15 በመቶ ለማድረስም ታስቧል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓመት 390,000 ሜትሪክ ቶን ቡና ነው ወደ ውጭ የምንልከው፡፡ ከአምስት ዓመታት በኋላ ወደ 1,000,000 ለማድረስ ነው የምንሠራው፡፡ ይህንን ለማድረግ ብዙ መሥራት ያለብን የቤት ሥራዎች አሉ፡፡ የቡና ምርታማነትን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ከዝርያ መምረጥ፣ ከእንክብካቤ መሥጠት፣ ከበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ጀምሮ ብዙ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ጥራቱን ጠብቆ ማዘጋጀት፣ እሴት ጨምሮ መላክ ከተቻለ፣ ከተሳካልን ደግሞ ይኼ የጅማ፣ ይኼ የሊሙ እያልን መላክ ከቻልን ከቡና ማግኘት የሚገባንን ጥቅም ማግኘት እንችላለን፡፡   

  

 

 

 

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...

የልጅነት ሕልም ዕውን ሲሆን

‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚል በብዙዎች ዘንድ የሚዘወተር አባባል አለ፡፡ አባባሉ የተጎዳን ሰው ለመርዳት፣ የወደቁትን ለማንሳት፣ ያዘኑትን ለማፅናናት፣ ከገንዘብ ባሻገር ቅንነት፣ ፈቃደኝነት፣...

በርካታ ሐኪሞችን የሚፈልገው የጨቅላ ሕፃናት ሕክምና

በኢትዮጵያ የጨቅላ ሕፃናት ሞትን ለመቀነስ ባለፉት አሠርታት የተሠሩ ሥራዎች ለውጥ አምጥተዋል፡፡ ሆኖም በጨቅላ ሕፃናት ሕክምና ዘርፍ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ከነበረው ቢሻልም፣ የጨቅላ ሕፃናት...