Friday, July 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ከፍተኛ አደጋ ያደርሳሉ ባሏቸው ተሽከርካሪዎች ላይ የዓረቦን ጭማሪ እያደረጉ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የትራፊክ አደጋ በማስከተል በግንባር ቀደምትነት እየተመዘገቡ ከሚገኙ ተሽከርካሪዎች መካከል ጃፓን ሠራሾቹ ቪትዝና ያሪስ ሞዴሎች፣ እንዲሁም የቻይናውን ሲኖትራክ መነሻ በማድረግ የመድን ኩባንያዎች በሚሰበስቡት የዓረቦን ክፍያ ላይ ጭማሪ እያደረጉ እንደሚገኙ ታወቀ፡፡

 

በአገሪቱ ከሚገኙ 17 የመድን ዋስትና ሰጪ ተቋማት የተወሰኑት የዓረቦን ሽያጫቸው ላይ ክለሳ በማድረግ ጭማሪ ማድረግ የጀመሩ ሲሆን፣ ክለሳ ለማድረግ ዝግጅት ላይ የሚገኙ እንዳሉም ሪፖርተር ካነጋገራቸው ኩባንያዎች ለማወቅ ተችሏል፡፡

የተሽከርካሪዎች አደጋን በተመለከተ ኩባንያዎቹ በጋራ ባካሄዱት የሞተር ግምገማ ጥናት መሠረት ቪትዝና ያሪስ አውቶሞቢሎች፣ እንዲሁም ሲኖትራክ የጭነት ተሽከርካሪዎች ከፍተኛ አደጋ እያስከተሉ እንደሚገኙ በመለየት ከፍተኛውን የመድን ሽፋን ክፍያ እንዲከፍሉ ለማድረግ መገደዳቸውን ከአዋሽ፣ ከኦሮሚያና ከኒያላ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡

በዚህ ሳቢያም አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ ካለፈው ጥር ወር 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በተሽከርካሪዎች ዓረቦን ክፍያ ላይ እስከ ሦስት እጥፍ የሚደርስ ጭማሪ አድርጓል፡፡ ኒያላና አፍሪካ ኢንሹራንስ ኩባንያዎችም ተመሳሳይ ጭማሪ ማድረጋቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሌሎቹም የመድን ድርጅቶች ጭማሪ ለማድረግ እየተዘጋጁ እንደሚገኙ ተሰምቷል፡፡

የኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ በበኩሉ በተመሳሳይ ምክንያት ባለፈው ዓመት ጭማሪ ያካሄደ በመሆኑ፣ በዚህ ዓመት ግን ምንም የተለየ ዕርምጃ እንደ ማይወስድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ኃላፊ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የዓረቦን ክፍያ ከመነሻው አነስተኛ በመሆኑ ምክንያት ለሞተር ዘርፍ ከሚከፈለው የመድን ካሳ ክፍያ አኳያ የማይመጣጠን በመሆኑ፣ ኪሳራ እየገጠማቸው እንደሚገኑ ኩባንያዎቹ ሲናገሩ ቆይተዋል፡፡ ከሞተር ኢንሹራንስ የሚሰበስቡት ዓረቦን አነስተኛ በመሆኑ ትርፋማ ባያደርጋቸውም፣ ከልዩ ልዩ የኢንቨስትመንት ምንጮች የሚያገኙት ትርፍ በዘርፉ ለመቆየት ዋስትና እንደሆናቸውም ኩባንያዎቹ ይናገራሉ፡፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዓረቦን ክፍያን በተመለከተ አማካይ ተመን ባለመቀመጡ ሳቢያ፣ እንዲሁም ከተሽከርካሪዎች አደጋ መብዛት ጋር ተዳምሮ የሞተር ኢንሹራንስ ከፍተኛ ችግር እንደሚታይበት የሚገልጹ አሉ፡፡

ለተሽከርካሪዎች የመድን ሽፋን የመስጠት ግዴታ በሁሉም ኩባንያዎች ላይ የተጣለ ቢሆንም፣ ከተወሰኑ ተሽከርካሪዎች ሞዴሎችና ከመለዋወጫ ዕቃዎች ጋር በተያያዘ በየጊዜው የሚከሰተው አደጋ እየጨመረ መምጣቱን በመጥቀስ ይከራከራሉ፡፡ በዘርፉ እየተነሱ ካሉ የአደጋ መንስዔዎች መካከል ለአብነት የሚጠቀሰው እንደ ቪትዝ ያሉ ተሽከርካሪዎች በቶዮታ ኩባንያ ሲመረቱ፣ በአብዛኛው መሪያቸው በስተቀኝ በኩል ተደርጎ ነው፡፡ ይሁንና በዱባይና በሌሎች አካባቢዎች መሪዎቹን ወደ ግራ በማዞር አገር ውስጥ ማስገባት የተለመደ ተግባር ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች በሕግ አስገዳጅ የሆኑ መሥፈርቶችን፣ የተመረቱበትን ዘመን ጨምሮ በሕገወጥ መንገድ መሪ በማስቀየር ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቡ አስመጪዎችና አሽከርካሪዎችም ለትራፊክ አደጋው መባባስ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ፣ በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ የሚሠሩ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡

በአንፃሩ የትራፊክ ደኅንነት ባለሙያዎች ግን እንዲህ ያለውን ድምዳሜ ለመያዝ ጥናት ላይ የተመሠረቱ ትክክለኛ መረጃዎች መቅረብ እንዳለባቸው በመግለጽ፣ በተለይም የተሽከርካሪዎች መሪ ስለዞረ ብቻ አደጋ እያደረሱ ነው ብሎ ለመናገር እንደሚያስቸግር ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች