Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዓለምኢራንን ያገለለው የዶናልድ ትራምፕ የመካከለኛው ምሥራቅ ጉብኝት

ኢራንን ያገለለው የዶናልድ ትራምፕ የመካከለኛው ምሥራቅ ጉብኝት

ቀን:

ሥልጣን በተቆናጠጡ በ120ኛ ቀናቸው የመጀመሪያውን የውጭ ጉዞ በሳዑዲ ዓረቢያ ያደረጉት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ በሳዑዲ ጉብኝታቸው ትልቅ ሥፍራ የሰጡት ሽብርተኝነትን መዋጋት ነው፡፡

ሽብርን ከእስልምና ጋር በማያያዝ ፈርጀዋል፣ የሰባት ሙስሊም አገሮች ዜጎች ለተወሰነ ጊዜ አሜሪካ እንዳይገቡ (ሁለት ጊዜ በፍርድ ቤት ታግዷል) የሚያስችል ሰነድ ፈርመዋል ተብለው በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና በተለያዩ አገሮች ውግዘት የደረሰባቸው ትራምፕ፣ በሳዑዲ ዓረቢያ በነበራቸው ቆይታ ለዓለም ሥጋት የሆነውን ሽብርተኝነት ለመዋጋት የዓረብ አገሮች መሪዎች ከአሜሪካ እንዲተባበሩ ጠይቀዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ሙስሊሞችን ከሽብር ጋር በመፈረጅ የሚታወቁት ትራምፕ፣ ዛሬ ደግሞ ጣታቸውን በኢራን ላይ ብቻ ቀስረዋል፡፡

ከኑክሌርና ከባለስቲክ ሚሳይል ጋር በተያያዘ ከኢራን ጋር አይጥና ድመት የሆነችው አሜሪካ፣ በኢራን ላይ የተለያዩ ማዕቀቦችን ስታስጥል ኖራለች፡፡ አሁን ደግሞ ጨዋታው የኑክሌር ብቻ ሳይሆን ኢራን ሽብርን ትደግፋለች የሚልም ሆኗል፡፡

- Advertisement -

ለሽብርተኞች የገንዘብ ድጋፍና ለምልመላና ለመኖሪያ አመቺ ምኅዳር የፈጠረችን  አገር በግልጽ ሳይናገሩ ሽብርን መዋጋት አይቻልም በማለትም፣ ‹‹ኢራን በዓለም የሚታየው ሽብር መናኸሪያ ነች፤›› ሲሉ ኮንነዋል፡፡

በሳዑዲ ዓረቢያ ለተሰባሰቡ 55 የዓረብና ሌሎች የሙስሊም አገሮች መሪዎችም ሽብርተኞችን ከማኅበረሰባቸው፣ ከማምለኪያ ሥፍራቸውና ከአካባቢያቸው እንዲያስወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በምረጡኝ ቅስቀሳቸውም ሆነ ሥልጣን ከያዙ በኋላ እንደ ሳዑዲ ዓረቢያው ዓይነት መደበኛ፣ የተሳካና ጠንካራ ንግግር አድርገው አያውቁም የተባሉት ትራምፕ፣ ‹‹ጭካኔ ብልኃት አይደለም፣ ወንጀል ነፃነትን አያጎናጽፍም፤›› ሲሉም የሃይማኖት መሪዎች ሽብርተኝነትን ሊዋጉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ቀስቃሽ በሆነ ንግግራቸው፣ ‹‹ሽብርተኞችን አስወጧቸው፣ ከማኅበረሰባችሁና ከእምነት ሥፍራዎቻችሁ አስወጧቸው፡፡ የሽብርን መንገድ ከመረጣችሁ ሕይወታችሁ ባዶ ይሆናል፣ ሕይወታችሁ ያጥራል፣ መንፈሳችሁም የተወገዘ ይሆናል፡፡ ጀግኖች ንፁኃንን አይገድሉም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ሽብር አምላክን አያመልክም፣ የሚያመልከው ሞትን ነው፤›› ብለውም  ጽንፈኝነትን ለመዋጋት ለሚደረገው ጥረት፣ አሜሪካ የመካከለኛው ምሥራቅ መሪዎችን ትደግፋለች ብለዋል፡፡

በሳዑዲ ዓረቢያ በተካሄደው የዓረብ ሙስሊሞችና የአሜሪካ ጉባዔ ላይ አጽንኦት የተሰጠው ሽብርን መዋጋትና በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላምን ማስፈን ሲሆን፣ ይህን ጅማሮም ‹‹ታሪክ የሚያስታውሰው›› ብለውታል፡፡

የሽብርን ተግባር ለማስቆም ‹‹የፍፃሜው መጀመሪያ አሁን ነው›› በማለትም በቀጣናው አይኤስንና ሌሎች ፅንፈኛ ቡድኖችን በገንዘብ የሚደግፉትንም ኮንነዋል፡፡

አንድ በሚያደርጓቸውና በሚጋሯቸው የደኅንነት ጉዳዮች አሜሪካ የመካከለኛው ምሥራቅን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗን ገልጸው፣ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮችም የሁሉም ጠላት የሆኑትን ሽብርተኞች ለማንኮታኮት አሜሪካን ብቻ መጠበቅ እንደሌለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

ትራምፕ ሳዑዲ ዓረቢያ በገቡ ዕለት በአሜሪካና በሳዑዲ ዓረቢያ መካከል የተፈረመውን የጦር መሣሪያ ግዥ ስምምነት በማስታወስም፣ ሳዑዲ ዓረቢያ በቀጣናው ደኅንነትን ለማስጠበቅ ለምትጫወተው ሚና ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል፡፡

አሜሪካ ለዘመናት የገነባችውን ስደተኞችን የመቀበል ባህል የሸረሸሩትና በአሜሪካ ስደተኞች ላይ አሉታዊ አቋም ያላቸው ትራምፕ፣ እሳቸው አገራቸው ላይ ካላቸው አቋም በተለየ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ስደተኞችን እንዲቀበሉም አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ ‹‹ቀጣናው አዳዲስ ስደተኞች የሚመጡበት እንጂ የአካባቢው ዜጎች ከቀዬአቸው ለቀው የሚሰደዱበት መሆን የለበትም፤›› ብለዋል፡፡

የሽብር ጉዳይ ሲነሳ፣ በምዕራቡና በሙስሊሙ ዓለም መካከል ያለ ግጭት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ሽብር በአብዛኛው የሚያያዘውም ከሙስሊሞች ጋር ነው፡፡ ይህ የተሳሳተ አመለካከት ነው በማለት የሚሞግቱ ቢኖሩም፣ ትራምፕ ሥልጣን በያዙ በመጀመሪያው ወር ውስጥ ካሳለፏቸው ውሳኔዎች ውስጥ ሽብርን ከአሜሪካ ለመግታት፣ የሰባት የሙስሊም አገር ዜጎች አሜሪካ እንዳይገቡ ማገድ ይገኝበታል፡፡

ሆኖም ሽብርን መዋጋት በምዕራብና በሙስሊሙ ዓለም መካከል እንደሚደረግ ጦርነት ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት አጽንኦት በመስጠት፣ ‹‹አሜሪካ የአሜሪካውያንን የአኗኗር ዘይቤ በሌሎች ላይ የመጫን ፍላጎት የላትም፡፡ እኛ እዚህ የተገኘነው እንዴት እንደሚኖር፣ እንዴት እንደሚሠራና እንዴት እንደሚመለክ ለማስተማር ወይም ለመንገር ሳይሆን፣ ሁላችንም የተሻለ ሕይወት እንዲኖረን በጋራ እሴቶቻችንና ፍላጎቶቻችን ላይ መሠረት ያደረገ ትብብር ለመፍጠር ነው፤›› ብለዋል፡፡

ትራምፕ ይህን ሲሉ ኢራንን ከሽብርተኞች ጎራ ፈርጀው ነው፡፡ ምንም እንኳን የኢራንና የአሜሪካ ፍጥጫ ይበልጡኑ ከኑክሌር ማበልፀግ ጋር የተያያዘ ቢሆንም፣  አጀንዳ ያደረጉት የኢራንን ሽብር ጠንሳሽነት ነው፡፡ ‹‹በቀጣናው ላለው አለመረጋጋት ኢራን ኃላፊነቱን ትወስዳች፡፡ የኢራን መንግሥት ጅምላ ጭፍጨፋን በግልጽ የሚሰብክ ነው፤›› ሲሉም ለጉባዔው ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡

ኢራን በበኩሏ የትራምፕ የመካከለኛው ምሥራቅ ጉብኝት ለይስሙላና ከሳዑዲ ዓረቢያ ከ300 ቢሊዮን ፓውንድ በላይ የሚያገወጣ የንግድ ስምምነት ለመፈጸም ነው ብላለች፡፡ ትራምፕ ኢራንን የዓለም አቀፍ ሽብር መናኸሪያ  ናት ብለው በተናገሩ በሰዓት ውስጥ ምላሽ የሰጡት የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጃቫድ ዛሪፍ፣ ‹‹ለትራምፕ የማይነጥፍ ወተት  የምትሰጥ ላም›› ብለው በገለጿት ሳዑዲ ዓረቢያ በተካሄደው ጉባዔ የትራምፕ መገኘት፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ከቴህራን (ኢራን) ባላንጣ ከሆነችው ሳዑዲ ዓረቢያ ገንዘብ ለማለብ እንደሆነም በመግለጽ፣ አሜሪካ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር ያደረገቻቸውን የ480 ቢሊዮን ዶላር ስምምነቶች ጠቁመዋል፡፡

የኢራን ፕሬዚዳንት ሐሰን ሮሃኒም ዳግም በተመረጡ ማግሥት፣ የትራምፕ የሳዑዲ ዓረቢያ ጉብኝት ከዕይታ ያለፈ አይደለም ብለዋል፡፡

ትራምፕ የአሜሪካ ወዳጅ በሆነችው ሳዑዲ ዓረቢያ በደረሱበት ዕለተ ቅዳሜ ግንቦት 12 ቀን 2009 ዓ.ም. ከሳዑዲ ዓረቢያው ንጉሥ ሳልማን ጋር 110 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ የጦር መሣሪያ ሽያጭ ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን፣ ይህም ኢራን በሳዑዲ ዓረቢያ ላይ እያሳደረች ያለውን ጫና ለማለዘብ ነው ተብሏል፡፡

አልጄዚራ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬክስ ቲሊርሰንን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ የጦር መሣሪያ ግዥ ስምምነቱ ኢራን በሳዑዲ ዓረቢያ በሁሉም ድንበሮች  የፈጠረችውን ሥጋት ለመከላከል ነው፡፡

የአሜሪካና የሳዑዲ ዓረቢያን የቆየ ወዳጅነት ለማጠናከር ያግዛል በተባለው የትራምፕ ጉብኝት፣ ከጦር መሣሪያ ሽያጭ ስምምነት በተጨማሪም በሁለቱ አገሮች በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ የተባሉ በጠቅላላው ከ380 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ የንግድና ኢንቨስትመንት ስምምነቶች ተፈርመዋል፡፡

የአሜሪካው ጄኔራል ኤሌክትሪክ ኩባንያም በዕለቱ 15 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የንግድ ስምምነት መፈራረሙን አስታውቋል፡፡

የስምንት ቀናት የውጭ ጉብኝታቸውን በሳዑዲ ዓረቢያ የጀመሩት ትራምፕ በቀጣይ ያቀኑት ወደ እስራኤል ነው፡፡ ወደ እስራኤል ያቀኑት ኢራን ከኑክሌር ጦር መሣሪያ ጋር ተያይዞ እየፈጠረች ያለውን ጫና አስመልክተው ኢራንን በማስጠንቀቅ ነበር፡፡

ትራምፕ ከእስራኤል ፕሬዚዳንት ሪዮቭን ሪቭሊን ጎን በመሆን በእየሩሳሌም ለሚገኙ ጋዜጠኞች እንዳሉት፣ ኢራን የኑክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤት መሆን  የለባትም፡፡

በአሜሪካና በእስራኤል መካከል ያለውን ትስስር በማጉላትም፣ አሜሪካና እስራኤል የረዥም ጊዜ ወዳጆች ብቻ ሳይሆኑ ታላቅ ወዳጆችና አጋሮች መሆናቸውንና ሁሌም ጎን ለጎን እንደሚቆሙም ተናግረዋል፡፡

በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል ያለው አለመግባባት በሰላም እንዲፈታ እንደሚያደርጉ ከምርጫ ቅስቀሳ ጀምሮ የተናገሩት ትራምፕ፣ ምንም እንኳን ለሁለቱ አገሮች አንዱ  የፀብ መንስዔ እስራኤል በምሥራቅ እየሩሳሌም የምታደርገው የሠፈራና የቤት ግንባታ ፕሮግራም ቢሆንም፣ እዚህ ላይ አስተያየት ሳይሰጡ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው አለመግባባት በሰላም መፈታት እንዳለበት አስምረውበታል፡፡ እንዴት? የሚለውን ግን አልገለጹም፡፡

‹‹እስራኤላውያንና ፍልስጤማውያን ወጣቶችና ሕፃናት በሰላማዊ ሥፍራ ማደግ ይገባቸዋል፡፡ ህልማቸውን ለማሳካትም ብዙዎችን ከቀጠፈው ግጭት ነፃ ሆነው ማደግ አለባቸው፤›› ሲሉም በሁለቱ ወገኖች መካከል የሰላምን አስፈላጊነት ሰብከዋል፡፡

ትራምፕ በብራሰልስ የቡድን ሰባት አገሮች ጉባዔን የሚካፈሉ ሲሆን፣ ቫቲካንና ሲሲሊም የጉዟቸው መዳረሻ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...