Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊድንገተኛ ሕክምናው

ድንገተኛ ሕክምናው

ቀን:

የሰዎች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ እንዲሁም ከማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጋር ተያይዘው ለሚከሰቱ ድንገተኛ የጤና እክሎች ፈጣንና ቀልጣፋ የሕክምና አገልግሎት መስጠት ወሳኝ ቢሆንም፣ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ አገሮች ቀላል አይደለም፡፡

በኢትዮጵያ በተለይ ከትራፊክ አደጋ ጋር ተያይዞ ለሚከሰቱ ድንገተኛ አደጋዎች በመንግሥትም ሆነ በግል ሆስፒታሎች የመጀመሪያ ዕርዳታ የሚሰጥበት ሥርዓት  የተዘረጋ ሲሆን፣ ይህ ግን በአገር አቀፍ ደረጃ እንደሚጠበቀው እንደማይተገበር በተለያዩ መድረኮች ተገልጿል፡፡

የድንገተኛ ሕክምና አሰጣጥ ቀድሞ ከነበረበት እየተሻሻለ ቢሆንም፣ በተለይ አዲስ አበባ ለእሳት፣ ለመኪና አደጋና ለሌሎችም ድንገተኛ አደጋዎች ተጋላጭ ከመሆኗ አንፃር በድንገተኛ ሕክምና ዙሪያ ተግዳሮቶች አሉ፡፡ የሕክምና ባለሙያና የአምቡላንስ አቅርቦት ዕጥረቶች፣ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

 በአዲስ አበባ በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች የድንገተኛ ሕክምና የመጀመሪያ ዕርዳታ የሚሰጥበት አሠራር ቢኖርም፣ በከተማዋ ከሚደርሱ ድንገተኛ አደጋዎች ግማሽ ያህሉን የሚያስተናግደው በተለይ ለድንገተኛ አደጋዎች ተብሎ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ሥር የሚተዳደረው የአዲስ አበባ በርን፣ ኢመርጀንሲ ኤንድ ትራውማ (አቤት) ሆስፒታል ነው፡፡

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ሥር የሚገኘው የአዲስ አበባ በርን ኢመርጀንሲ ኤንድ ትራውማ (አቤት) ሆስፒታል በተገኘንበት ወቅት፣ አዳራሹና ቅጥር ግቢው በታካሚዎች ተጨናንቋል፡፡  ታካሚዎቹም በመኪና አደጋ፣ በእሳት ቃጠሎ፣ በድብደባና  ተያያዥ በሆኑ አደጋዎች የተጎዱ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል የተወሰኑት በቅብብሎሽ (ሪፈር) ከሌላ ሆስፒታል የመጡ ሲሆኑ፣ አብዛኞቹ ግን በተጠቀሱት አደጋዎች ተጎድተው  በታክሲ፣ በቤት መኪናና በአምቡላንስ ዕርዳታ በቀጥታ ወደ ሆስፒታሉ የመጡ ናቸው፡፡

የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ገሊላ መንግሥቱ እንደሚሉት፣ ለሕክምና ከሚመጡት ታካሚዎች መካከል አብዛኞቹ በመኪና አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆኑ፣ በመጠኑም ቢሆን የእሳት ቃጠሎ ተጎጂዎችም ይመጣሉ፡፡ ብዙዎቹ ከአዲስ አበባ፣ በከፊል ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል የሚመጡ ናቸው፡፡

አዲስ አበባ ውስጥ ከሚደርሱት ልዩ ልዩ አደጋዎች መካከል ግማሽ ያህሉን የሕይወት ማዳን ሥራ የሚያከናውነው ይህ ሆስፒታል መሆኑን ዶ/ር ገሊላ አመልክተው፣ ሥራው የተወሰነውም ባሉት 250 አልጋዎች ብቻ  እንደሆነ፣ ከታካሚዎች ብዛት አንጻር ሲታይ የአልጋ ችግር እንዳለ፣ ይህን ችግር ለመወጣት  ሆስፒታሉን ማስፋፋት ብቻ ሳይሆን ይህን መሰል አገልግሎት የሚሰጡ  የሕክምና ተቋማትም መስፋፋትና ማደግ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

የአቤት ሆስፒታል የኢመርጀንሲ፣ የኒሮሰርጀሪ፣ የኦርቶፔዲክስ፣ የፕላስቲክ ሰርጀሪና የፎረንሲክ ስፔሻሊቲ አገልግሎቶች የሚሰጥ ቢሆንም፣ የስፔሻሊስቶች ወይም የልዩ ሐኪሞች ዕጥረት እንዳለ ገልጸዋል፡፡ ይህንንም ችግር ለማቃለል ከፕላስቲክ ሰርጀሪ በስተቀር በሌሎች የሕክምና መስኮች የድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞች በማካሄድ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ሆስፒታሉ እየተገለገለበት ያለው ሕንፃ በኪራይ ሲሆን፣ ከሁለት ወይም ከሦስት ዓመት በኋላ የራሱ የኢመርጀንሲ ኮምፕሌክስ ሕንፃ ያሠራል፡፡ ለዚህ የሚውል መሬት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል አካባቢ ያገኘ ሲሆን፣ የሕንፃውም ዲዛይን በመጠናቀቅ ላይ እንደሆነ ዶ/ር ገሊላ አመልክተዋል፡፡

አቶ ኤፍሬም በቀለ የሆስፒታሉ የጤና መረጃ ቅንብርና ፍሰት አስተባባሪ በቀን  እስከ 50 ሕሙማን በድንገተኛ መጥተው እንደሚታዩ፣ ከእነዚህም መካከል እስከ 80 በመቶ የሚሆኑት ትራውማ ኬዝ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ይህም ማለት በመኪና አደጋ፣ በድብደባ፣ በመውደቅና በመሳሰሉት አደጋዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆኑ፣ የቀሩት 20 በመቶ ደግሞ ከቀዶ ሕክምና ችግር ወይም ከሕክምና ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ በትራውማ ኬዝ ከተያዙት አደጋዎች መካከል  የመኪና አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው 50 ከመቶ ያህሉ ናቸው፡፡

ሆስፒታሉ  በአንድ ጊዜ እስከ 50 የሚጠጉ ሕሙማን ማስተናገድ የሚችል የድንገተኛ ክፍል ሲኖረው፣ ለሕክምና ከሚመጡት መካከል እስከ 40 በመቶ  የሚሆኑትም ተኝተው የሚታከሙ፣ 60 በመቶው ደግሞ ለ24 ሰዓት ሕክምና አግኝተው የሚሸኙ ናቸው፡፡

ድንገተኛ ሕክምና ላይ አተኩሮ አገልግሎት ከሚሰጠው አቤት ሆስፒታል በተጨማሪ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ በዳግማዊ ምኒልክ፣ በየካቲት 12 እና በጤና ጣቢያዎች በተጓዳኝ የሚሰጥ ቢሆንም፣ በዘርፉ የአምቡላንስና የሕክምና ባለሙያ ዕጥረት እንዳለ ይነገራል፡፡

በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የድንገተኛ ሕክምና ኬዝ ቲም  ባለሙያ ሲስተር የኔነሽ ግርማ እንደሚሉት፣ ቢሮው ድንገተኛ ሕክምናን ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ ቢሆንም ዘርፉ ገና ይቀረዋል፡፡

ለድንገተኛ አደጋ ምላሽ የሚሰጥ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ሆኗል ባይባልም፣ ቢሮው የባለሙያ ሥልጠና በመስጠትና በስሩ የሚገኙ ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች በቁሳቁስ እንዲደራጁ ለማድረግ  እየሠራ ነው ብለዋል፡፡

ለድንገተኛ አደጋ የሚውሉ አምቡላንሶች ዕጥረት መኖሩን በማስታወስም፣ እያንዳንዱ ወረዳ አምቡላንስ እንዲኖረው ለማድረግ እየተሠራና ቢሮውም 50 አምቡላንስ ጠይቆ ምላሽ እየጠበቀ እንደሚገኝ አክለዋል፡፡

ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የ2009 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርቱን ለተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት እንደገለጸው፣ አስቸኳይ ዕርዳታ የሚፈልጉ የጤና እክሎችን የሚያክሙ የጤና ተቋማት እያደራጀ መሆኑን፣ በተለይ በሆስፒታሎች በድንገተኛ ሕክምና ማለትም በቃጠሎ፣ በመመረዝና በሌሎች አፋጣኝ ምላሽ የሚሹ  ሕክምናዎችን ለማሻሻል እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ