Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትኢትዮጵያ ቡና በአገር ውስጥ አሠልጣኞች ብቃት እምነት ማጣቱን ገለጸ

ኢትዮጵያ ቡና በአገር ውስጥ አሠልጣኞች ብቃት እምነት ማጣቱን ገለጸ

ቀን:

  • የቀድሞውን ሰርቢያዊ አሠልጣኝ መልሶ ቀጠረ

  ከተመሠረተ አራት አሠርታትን እያስቆጠረ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ በአገር ውስጥ አሠልጣኞች የሙያ ብቃት እምነት እያጣ መምጣቱን አስታወቀ፡፡ ዓምና ያሰናበታቸውን ሰርቢያዊ ድራጎን ፖፓዲችን ለ2010 የውድድር ዓመት በድጋሚ የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ አድርጎ ቀጥሯል፡፡

ክለቡ ባለፈው ሰኞ ግንቦት 14 ቀን 2009 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሆቴል በሰጠው መግለጫ፣ ለቀድሞው ሰርቢያዊ አሠልጣኝ ቅድሚያ የሰጠው ከአገር ውስጥ አሠልጣኞች ጀምሮ ቡድኑ በአሁኑ ወቅት ለሚጠበቀው ውጤት ትክክለኛውን ሰው ማግኘት ባለመቻሉ እንደሆነም አስታውቋል፡፡ በኢትዮጵያ ቡና ታሪክ የመጀመሪያው የውጭ አሠልጣኝ እንደነበሩ የሚነገርላቸው ፖፓዲች፣ ቀደም ሲል ለስንብታቸው ምክንያት ሆኖ ሲደመጥ የነበረው የዕውቀትና የብቃት ጉዳይ ሳይሆን፣ ከግል ባህሪ ጋር በተገናኘ እንደነበርም የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ገልጸዋል፡፡ የአሠልጣኙን ወርኃዊ ክፍያ አስመልክቶ የክለቡ የውስጥ ጉዳይ በመሆኑ ምንም ዓይነት ማብራሪያ እንደማይሰጡ ጭምር የቦርድ ሰብሳቢው አስረድተዋል፡፡

ክለቡ የቀድሞውን አሠልጣኝ በድጋሚ የመቅጠሩ ዜና ይፋ ከመሆኑ አስቀድሞ በቡድኑ በተጨዋችነትና አሠልጣኝነት የሚታወቀው ካሳዬ አራጌን ጨምሮ የበርካታ የአገር ውስጥ አሠልጣኞች ስም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ተያይዞ ሲነሳ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ በነዚህና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ያጠነጠኑ በርካታ ጥያቄዎች በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ተነስተዋል፡፡

ከአሠልጣኝ ድራጎን ፓፓዲች ስንብትና ድጋሚ ቅጥር ጀምሮ ክለቡ በወሰደው እያንዳንዱ ውሳኔ ምክንያታዊ እንደነበር ያስረዱት የቦርድ ሰብሳቢው፣ በተለይ ከካሳዬ  ጋር ተያይዞ ለተነሳው ጥያቄ እንደ ክለብ የበላይ ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን፣ በግል ቢሯቸው ሳይቀር ከግለሰቡ ጋር መነጋገራቸውን ተናግረዋል፡፡ በእሳቸውና በካሳዬ መካከል የተደረገው ውይይት የቀድሞው ተጫዋችና አሠልጣኝ ከዓመታት ቆይታ በኋላ ኢትዮጵያ ቡናን ለማሠልጠን ፍላጎቱ ከሆነ ለኃላፊነቱ በሚያበቃው የሙያ ብቃትና ችሎታ ላይ እንደተነጋገሩም ገልጸዋል፡፡ በወቅቱ የደረሰበት ስምምነትም ኃላፊነቱን በትክክል መወጣት ይችል ዘንድ እንዲማርና ለዚያም ክለቡ የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያደርግለት ተነጋግረው መለያየታቸውን በመግለጽ ጭምር ነው ያስረዱት፡፡

በአገር ውስጥ አሠልጣኞች የሙያ ብቃት ዙሪያ ለተነሳው ጥያቄ ኃላፊው፣ ‹‹እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ኢትዮጵያ ቡና ከእንግዲህ በምንም መልኩ ከኢትዮጵያውያን አሠልጣኞች ጋር እንደማይደራደር፣ ምናልባት ፍላጎት ካለው ደግሞ እንደሌሎቹ የሙያ ዘርፍ አሠልጣኞቻችንም ከጊዜው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ሊያራምዳቸው የሚችለውን ዕውቀት እንዲኖራቸው ማድረግ ከቻሉ ብቻና ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም የስምንተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በአግባቡ ማለፍ አለማለፋቸው ሳይረጋገጥ ‹‹ኢንስትራክተር›› የሚል ትልቅ የሙያ ማዕረግ የተሰጣቸው ሰዎች ያሉባት አገር ውስጥ መኖራችንን መዘንጋት ያለብን አይመስለኝም፡፡ እግር ኳሱ እንዲያድግና እንዲለወጥ ከሆነ ፍላጎታችን በአሁኑ ወቅት እየተሰጠ ያለው የአገር ውስጥ ሥልጠና ጭምር መፈተሽ ይኖርበታል፤›› በማለት ነው ያስረዱት፡፡

በክለቡ ሰርቢያዊ አሠልጣኝ የሚከተሉትን የሥልጠና ፍልስፍና የማይቀበሉ ተጨዋቾች እንዳሉም ከተነሱት ጥያቄዎች ውስጥ ተጠቃሽ ነው፡፡ ለዚህም ኃላፊው፣ ‹‹እንደነዚህ የመሰሉ ሌሎችም በርካታ የክለቡን ህልውና የሚፈታተኑ አሉባልታዎች በተለይም በሶሻል ሚዲያው እንደሚናፈሱ እናውቃለን፡፡ ኢትዮጵያ ቡና ተቋም እንደመሆኑ እግር ኳሱ በተለይም በአሁኑ ወቅት በምን ደረጃ እንደሚገኝ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ይህም ሲባል በአንድ ክለብ ውስጥ የተጫዋች ኃላፊነትና የአሠልጣኝ ኃላፊነት ምን እንደሆነ ጭምር ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ክለቡ የዋና አሠልጣኝነቱን ኃላፊነት ለሰርቢያዊ አሠልጣኝ ሲሰጥ ተጨዋቾች የአሠልጣኙን ፍልስፍና ‹ይቀበሉታል? አይቀበሉትም?› የሚል ቅድመ ሁኔታ የሚያስተናግድበት አንዳችም ጉዳይ አይኖርም፤›› ብለዋል፡፡  

አሠልጣኝ ድራጎን ፖፓዲች በበኩላቸው፣ ‹‹በግሌ መታየት አለብኝ ብዬ የማስበው እንደ አንድ የጦር መሪ ነው፡፡ ተጨዋቾች የምሰጣቸውን ሥልጠና ማክበርና መቀበል የሙያው ሥነ ምግባር እንጂ፣ የፍላጎት ጉዳይ አይደለም፡፡ ሥራዬን አከብራለሁ፡፡ ሥራቸውን ማክበር ደግሞ የተጫዋቾች ኃላፊነት ነው፤›› ብለው በኢትዮጵያ ቡና ውስጥ በነበራቸው ቆይታ የአንዳንዶቹን ስም በመጥቀስ ምንም ዓይነት ችግር እንዳልነበራቸው ጭምር  ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...