Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሒልተን ሆቴል አስተዳደርና የሠራተኛ ማኅበር እየተወዛገቡ ነው

የሒልተን ሆቴል አስተዳደርና የሠራተኛ ማኅበር እየተወዛገቡ ነው

ቀን:

በሒልተን ሆቴል አስተዳደርና በሠራተኞች ማኅበር መካከል የተፈጠረው ውዝግብ ቀጥሏል፡፡ የውዝግቡ ምክንያት የሠራተኛ ማኅበሩ ጠቅላላ ጉባዔ ለማድረግ ጥሪ ማድረጉ ነው፡፡

ሚያዝያ 16 ቀን 2009 ዓ.ም. እና ግንቦት 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በማኅበሩ ሊቀመንበር አቶ አብርሃም አበበ ተፈርሞ በወጣው ደብዳቤ፣ የሠራተኛ ማኅበሩ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔ ለማድረግ ፈቃድ እንዲሰጥ በመጠየቁ፣ የሆቴሉ አስተዳደር ጥያቄውን ተቀብሎ ፈቅዶ ነበር፡፡

ነገር ግን ሆቴሉ ግንቦት 10 ቀን 2009 ዓ.ም. በሆቴሉ የሰው ኃይል ዳይሬክተር ወ/ሮ አዳኑ ታፈሰ በተጻፈ ደብዳቤ፣ ግንቦት 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ሊደረግ የነበረው ስብሰባ መሰረዙን አስታውቋል፡፡

በደብዳቤው መሠረት የስብሰባ ፈቃዱ የተሰጠው ለሆቴሉ ሠራተኞች ብቻ ሆኖ ሳለ፣ ማኅበሩ ግን በስብሰባው ላይ ጋዜጠኞች፣ የመንግሥት አካላት፣ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን፣ የቱሪዝም ሆቴሎችና ጠቅላላ አገልግሎት ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን የጋበዘ ስለሆነ፣ ይኼንን ማስተካከል ካልተቻለ የተሰጠው የስብሰባ ፈቃድ ይሰረዛል፡፡

ይህ ሆን ተብሎ ሠራተኛው በነፃነት እንዳይናገርና በደሉን እንዳይገልጽ የተደረገ ዕርምጃ ነው ሲሉ የማኅበሩ ኃላፊዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ከአሁን ቀደም በሆቴሉና በማኅበሩ መካከል በደመወዝ ጭማሪና በሠራተኞች ጥቅማ ጥቅም፣ በዝውውርና በዕድገት ላይ ጭቅጭቅ መነሳቱ ይታወሳል፡፡

እስከ ቅርብ ወራት ድረስ ግማሽ ክፍለ ዘመንን ያስቆጠረውና በአሁኑ ጊዜ 630 ሠራተኞች የሚያስተዳድረው የሒልተን ሆቴል መነሻ ደመወዝ 600 ብር ነበረ፡፡ የመጨረሻው የደመወዝ እርከን ደግሞ 6,853 ብር ነው፡፡ ከደመወዝ እርከን ጋር በተያያዘ ሠራተኞቹ ባነሱት ጥያቄ ሚያዝያ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ላይ ማስተካከያ ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት ከ15 በመቶ እስከ 25 በመቶ ጭማሪ ተደርጓል፡፡

ነገር ግን ይኼ ማስተካከያ ለሠራተኞች የማይጠቅምና እነሱም እንዳልተስማሙበት የማኅበሩ አባላት ይገልጻሉ፡፡ ሆቴሉ ከደመወዝ ጋር በተያያዘ ወጥ የሆነ አሠራር የለውም ይላል ማኅበሩ፡፡ ‹‹ችግራችን እንዲፈታ የጠራነው ይኼ ጠቅላላ ጉባዔ ሠራተኛው ተገኝቶ ችግሩን በግልጽ እንዲናገርበት የታለመ ነው፤›› ሲሉ አቶ አብርሃም አስረድተዋል፡፡

‹‹መሰብሰባችንም መሠረታዊ ሕገ መንግሥታዊ መብታችን ነው፤›› ሲሉም አቶ አብርሃም ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ሪፖርተር የሆቴሉን ኃላፊ ክላውዝ ስቴነር ለማናገር የሞከረ ቢሆንም፣ በሕዝብ ግንኙነት ጽሕፈት ቤት በኩል ስብሰባው መፈቀዱን ብቻ እንደሚያውቁ ተናግረዋል፡፡

እስካሁን ሆቴሉ ግንቦት 10 ቀን 2009 ዓ.ም. የጻፈውን ደብዳቤ የሚሽርና ስብሰባው እንዲካሄድ የሚፈቅድ ደብዳቤ አለመጻፉን ማኅበሩ አክሎ ገልጿል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...