ህዳሴ የተሽከርካሪዎችና የማሽነሪ ገበያ አክሲዮን ማኅበር በአዲስ አበባ ከተማ 250 ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት እንዲሰጠው፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጥያቄ አቀረበ፡፡
አክሲዮን ማኅበሩ በመሀል አዲስ አበባ ሁለት ባለአራት ኮከብ ሆቴሎች፣ አምስት ሺሕ ሱቆች፣ ስምንት ሺሕ ተሽከርካሪዎችን የሚይዝ የመኪና ማቆሚያ፣ የመኖሪያ አፓርታማዎች፣ ሬስቶራንቶችና የፋይናንስ ተቋማት የሚገለገሉባቸው ግዙፍ የገበያ ማዕከል ለመገንባት ዕቅድ ይዟል፡፡
እነዚህ ትልልቅ ዕቅዶች ተግባራዊ ለማድረግ ሦስት ቢሊዮን ብር የሚያስፈልግ ሲሆን፣ እስካሁን 2,692 አክሲዮኖችን መሸጡን የአክሲዮን ማኅበሩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንማው አበራ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ማኅበሩ ይህንን ግዙፍ የገበያ ማዕከል ግንባታ ለማካሄድ ከፌዴራልና ከአዲስ አበባ ከተማ ኃላፊዎች ጋር መምከሩን፣ ፕሮጀክቱ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ተቀባይነት በማግኘቱ ልዩ አገራዊ ፋይዳ ባላቸው ፕሮጀክቶች መስተንግዶ መሠረት እንዲስተናገድ እንዲፈቀድለት፣ የመሬት ጥያቄውን በቅርቡ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ማቅረቡ ታውቋል፡፡
አክሲዮን ማኅበሩ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትን ውሳኔ እየተጠባበቀ መሆኑን አቶ አንማው አስረድተዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለዚህ ፕሮጀክት ይሁንታ ከሰጠና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ድሪባ ኩማ ከተቀበሉት፣ ፕሮጀክቱ ዕውን የሚሆንበትን ቦታ በመሀል አዲስ አበባ በመልሶ ማልማት አካባቢዎች ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ይህ ፕሮጀክት ዕውን ሲሆን ለ35 ሺሕ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጠር፣ የኩባንያውን መመሥረት አስመልክቶ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኩባንያው መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ደረጀ መኮንን ተናግረዋል፡፡
አክሲዮን ማኅበሩ የተመሠረተው አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የሆኑ ስብሰባዎች በሚስተናገዱባትና የአፍሪካ መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ የሚካሄደው ንግድ የተበታተነ በመሆኑ፣ ይህንን ግዙፍ የገበያ ማዕከል ከአፍሪካ አንዱና ዋነኛ የማድረግ ህልም መሰነቁን ማኅበሩ ገልጿል፡፡
በአዲስ አበባ ዘመናዊ የሆነ የተሽከርካሪና ማሽነሪ ግብይት ማዕከል እጥረት መኖሩን፣ አዲስ አበባ ከኒውዮርክና ከጄኔቫ ቀጥላ ሦስተኛዋ የዓለም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እምብርት መሆኗን ታሳቢ በማድረግ፣ አክሲዮን ማኅበሩ ሲመሠረት በቅድሚያ አሳካዋለሁ ብሎ የተነሳው የተሽከርካሪና የማሽነሪ ግብይትን ዘመናዊ ማድረግ ቢሆንም፣ ይህ ዓላማ ሳይቋረጥ በቅድሚያ የከፋ ችግር የሚስተዋለው ዘመናዊ የሆነ ሁለገብ የገበያ ማዕከል አለመኖሩ ስለሆነ እዚህ ላይ ትኩረት እንደተደረገ የማኅበሩ መግለጫ ያወሳል፡፡
‹‹በአፍሪካም ሆነ በዓለም በታላቅነቱ ተጠቃሽ የሚሆን ታላቅ የገበያ ማዕከል የመገንባት ዕቅድ ተቀባይነት አግኝቷል፤›› ሲል የአክሲዮን ማኅበሩ መግለጫ ያስረዳል፡፡