Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መውረድም መውጣትም ይጨንቃል?

እነሆ መንገድ ከኮተቤ ወደ መገናኛ። ጅምር መንገድ ማለቂያ የሌለው ዛሬም እያነሆለለ እያዳፋ ያስጉዘናል። አጥፊና አልሚ ያለ ቀጠሮ ይገናኛል። ሰው ያለ ቢጤው ሊውል ባላሰበው ሊሠለጥን ልራመድ ብሎ መንገድ ያምናል። መንገድ እንዳመሉ የመጣ የሄደውን ሲያንገዋልለው ውሎ ሲያድር ያለ ቀለሙ ቀለም፣ ያለ ስሙ ስም እየሰጠ የሚሸኘው ብዙ ነው። ብዛትና ጥራት በተምታቱበት በዚህ በእኛው ጎዳና ደግሞ እንዳመጣለት የሚያወራው፣ የሚያስበው የሚያስነጥሰውና ካገኘው ጋር እየተላተመ ከተፈጥሮ አደጋ እኩል የኅብረተሰብን የሐሳብ ፍሰት ያውካል። ለምሳሌ እዚህ ታክሲያችን ውስጥ መጨረሻ ወንበር የተሰየመ አንድ ወጣት፣ “እስኪ ቴዲን አድርጉልን። ሌላ ሙዚቃ መክፈት ክልክል ነው…” እያለ ይደነፋል። “ሙዚቃ ቤት መሰለህ እንዴ የገባኸው? የሾፌሩን የመዘወርና የዘፈን ምርጫ መብት መቃወም ክልክል ነው፤” ይለዋል ወጠምሻው ወያላ። “አገር ከዕውቀት ተጣልታ በዜማ ብቻ የምታስብበት ጊዜ ላይ እንድረስ?” ይላሉ ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየሙ አዛውንት። “ምን እናድርግ አባት እነሱ ናቸዋ ሁላችንን እንባ እንባ እያስባሉ አንጎራጓሪ ያደረጉን፤” ትላቸዋለች ከጎናቸው። ጉድ በሉ እንግዲህ፡፡

‹‹ማንጎራጎርና መጎርጎር ማንን ሲጠቅም አየሽ? የጎረጎረም ዘንዶ አወጣ፣ ያንጎራጎረም  ጎብጦ ቀረ። ቀና ነው እንጂ የሚበጅ፤” ሲሏት፣ “እኮ በየት በኩል? አሳዩንና ቀና እንበል። ቀና ስንል የምናየው ቀባሪ ቡጢና አፈር ደፊ አካፋ ነው። ማለቴ ጉልቤና ጉልበቱ ነው የተቆጣጠረን። በዚያ ላይ ደግሞ…” ብላ ዕቃ እንደጠፋት እመቤት ቀልቧ ሲበታተን፣ “እኔ ልጨርስላት . . .  በዚያ ላይ ደግሞ በአገሩ ባህልና ወግ መሠረት የሚደመጥና የሚሰማው የሰከነ ሐሳብ ሳይሆን የሚዋዥቅ መሬት ያልረገጠ የስሜት ማዕበል ነው። በአገራችን የሰከነ ነገር ይወደዳል ከተባለ ቡና ብቻ ነው፤” ሲላቸው ያ መጨረሻ ወንበር ላይ የተቀመጠ ወጣት አዛውንቱ፣ “ድሮም ከእናንተ ጋር መጫወቴ?” ብለው ፊታቸውን አዞሩ። የዙረቱ አታካችነት አልበቃን ብሎ ደግሞ በዚህ ፀሐይ በረባ ባረባው ሙግት ሰለቸን አቦ!

“ሞልቷል ሳበው፤” አለ ወያላው ሳናስበው ዘሎ ወደ ታክሲያችን እየገባ። “ምን ይሞላል ብለህ ነው የዚህ ዓለም ነገር?” ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጡ አዛውንት ናቸው የሚያናግሩት። “አይዞን ‘ፋዘር’! አንድ ቀን ዓለምም ብትሆን እንደዚች ታክሲ መሙላቷ አይቀርም፤” አላቸው። “በሕዝብ ብዛት ነው? ይቀልዳል እንዴ ይኼ?! እንኳን ዓለም ካርድ ወደ ሞባይላችን መሙላት አልችል ብሎናል። በዝተን በመባዛት ካልሆነ ችግርን አቃለን ሰላምና ደስታን ለዓለም ሕዝብ ማዳረሱን እርሳው፤” አሉት አንዴ በመስኮቱ አሻግረው ወደ ውጭ እየተመለከቱ፣ አንዴ ደግሞ ወደ ወያላው ዞረው ዓይን ዓይኑን እያዩ። “ታዲያ ምን ተሻለ ይላሉ?” አላቸው ሾፌራችን። የወያላውን ተግባቢነት ለመንጠቅ ይመስላል። የዘመኑ ሰው በውድድር ስም የማይነጣጠቀው ነገር የለም አይደል? “ምን ይሻላል? ጊዜን ከዚህ የበለጠ ለመታዘብ ዕድሜ መለመን! በቃ ሌላ ምንም የሚሻል ነገር የለም። መልካም አስተዳደር፣ ፍትሕ፣ ዴሞክራሲ… ልመናው ላይ ውኃ፣ ኔትወርክ፣ መብራት፣…  ልመና ከመደረብ ውጪ የመጣልን አዲስ ነገር ምን አለ?” አሉት። ሾፌራችን ሳቀ።

“መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲያችን መሥራት እንዲጀምር ቢያንስ መፍትሔ የለዎትም?” ቢላቸው አጠገባቸው የተቀመጠ ወጣት ተራቸውን ሳቃቸውን ለቀቁት። “አይ አንተ ምነው አንተን ባደረገኝ! ያልተነካ አቤት ግልግል ሲችልበት እኮ?” እያሉ አሽሟጠጡት። ወጣቱ ግራ ተጋብቶ አፈረና ዝም አለ። ወያላው ነገሩን እንደገና አንስቶ፣ “ነገራችን ሁሉ መቆራረጥ በበዛበት ዘመን ምድር ላይ ለመኖር ምን ዕድሜ አስለመንዎ?” አላቸው። “የለም! ርስት ልለምን ኖሯል? ያውም በሊዝ የገባ መሬት? ኧረ እንዴት ተቀለደ እናንተ! አንደኛዬን መንኜ ለነፍሴ የሰማይ ቤት ርስት አልለምንም?” አሉትና ያልተጠየቁትን መለሱ። ያልተጠየቁትን መመለስ (መልስ ከተባለ) በእሳቸው እንዳልተጀመረ አብዛኞቻችን በማወቃችን የከፋ ተቃውሞ ሳይገጥማቸው ቀሩ። “ይቅርታ ‘ፋዘር’ አስቆጣሁዎት መሰለኝ?” ብሎ ሳይጨርስ፣ “ወይድ ቀጣፊ! ወትሮም ተደራጅተሽ ስታበቂ ሰውን ክፉ ለማናገር እሳት መጫር ሙያ መስሎሻል አዳሜ? ቆይ ግድ የለም!” ብለው አፈጠጡበት። ወያላው ቀልቡ ተገፎ አመዱ ሲቦን ትዕይንቱ ዘና ያደረጋቸው ተሳፋሪዎች ይሳሳቃሉ። መንገድ የማያሳየን የለም! 

ታክሲዋ ጉዞዋን ቀጥላለች። በብዛት ከተደረደሩ ጥቅሶች መካከል አንዱዋን አስተውሎ ያነበበ ወጣት መናገር ጀመር። ‘ፍጥነት ዕድሜን ያሳጥራል እንጂ ጊዜን አይቆጥብም’ ትላለች። ገርሞት ፈገግ እንዳለ፣ “እኔ እኮ የማይገባኝ አሁን ይኼ ጥቅስ ለእኛ ነው መለጠፍ ያለበት? ወይስ ለሹፌሩ?” ብሎ ጠየቀ። “ኧረ ተወኝ ወንድሜ!” ይላል አጠገቡ የተቀመጠው ተሳፋሪ በሰለቸ ድምፀት። ወያላው በግልምጫ እያየው በምርቃናው የምናብ ሜዳ ላይ ወጣቱን የተናነቀው መስሏል። “ወይ ይኼ ምርቃና? ስንቱን ጀግና አደረገው?” ይላል ይኼን የሚያስተውል። የሚስቀው ይስቃል። ወዲያው ዋናው ርዕሰ ጉዳይ ተመልሶ ተነሳ። ወጣቱ፣ “በጣም እኮ ነው የሚገርመው? ‘ብልሹ አሠራርን በማስወገድ ጠንካራ የልማት ሠራዊት እንፍጠር’ ተብሎ የሚለጠፈው ለእኛ። ‘ለሙስና እጅ አንሰጥም’ ተብሎ የሚለጠፈው ለእኛ። መቼ ይሆን ሁሉም የራሱን ጉድፍ ማጥራት የሚጀምረው?” ተጀመረ እንግዲህ።

አሁንም አጠገቡ የተቀመጠው፣ “ህም ድረቅ ቢልህ! ልፋ ቢልህ! ሰሚ ያለ መስሎሃል?” ይለዋል። “ወሬ! ወሬ! ኧረ ወሬ ጠላሁ!” ሲል ወያላው እንደ መወናጨፍ ይቃጣዋል። “የመጣ የሄደው ዝም ብሎ ሲቀደድ. .  . . አንተ ምን አለብህ የምቀዳው እኔ?” ብሎ ሾፌሩን ይተነኩሰዋል።  ሾፌሩ ግራ እንደመጋባት እያለ፣ “ታዲያ መሥራት ካልቻልን፣ መብላት ካልቻልን፣ ቢያንስ ማውራት መቻል የለብንም?” ይለዋል በስፖኪዮ እያየው። “እውነት ነው! ስናወራ ነው የሚያምርብን፤” ቀጥሏል ወጣቱ። በዚህ መሀል ነበር፣ “መንግሥት ይኼን እየሰማ እንቅልፍ ይወስደዋል?” ብሎ የጠየቀውን ፍለጋ ጥቂት ደቂቃ ዝምታ ሰፍኖ የቆየው። አንዳንዴ እኮ መተንፈስን የመሰለ ምን አለ?

“ወንድሜ እዚህ አገር ስንዝር ለመራመድ ግንብ ማፍረስ እንደሚጠበቅብህ አልነግርህም። ቢሮክራሲው፣ ዳኛው፣ አስተዳዳሪው እኛን ማገልገል ሳይሆን ዓላማቸው የሚስለው እኛ እንድናገለግላቸው ነው። ማን ወዶ ይሰንፋል? ማን መማር ይጠላል? ማን ማትረፍ ይንቃል? ግን ሁሉንም እንዳይሆን የሚያደርገው አጥር ነው። እናም በዚህ መሀል እኔ ለአገሬ ምን አደረግኩላት ብዬ ላስብ? ወይስ እንዴት ብዬ ልዝረፍሽ?” ሲል ብዙም ሊከራከረው የፈለገ አልነበረም። በልቶ ለማደር ማሰብም እንደ አስተዋፅኦ ይቆጠር ይሆን? ምን ይታወቃል ጊዜው የኑሮ ውድነት ነው እኮ! የአገር ነገር ሲነሳ ሁሌም  ቢሆን ምሳጤ አይጠፋም። ሁሉም በየራሱ ህሊና ጅረት ይሆናል። ግራ ቀኝ እያየ አንዳንዴም ፊት ለፊት፣ ብቻ በዝምታ ያስባል። ኑሮ አንዳንዴ እንደሚታክተን አዕምሮን ማሰብ ቢታክተው፣ ከተማችን የዕብዶች መናኸሪያ መሆኗ ባላጠያየቀ ነበር።

“አይ አንቺ አገር መቼ ይሆን በልቶ ማደር ልጆችሽን በሐሳብ አዙሪት እየናጠ መድፋቱን የሚተዋቸው?” እያሉ አንድ አዛውንት ተሳፋሪ ሲገቡ፣ ያወራነውን ሳይሰሙ እንዲያ ማለታቸው እያስገረመን ተመለከትናቸው። ለካ ከመንገዱ ዳር ምንም እህል ባለመቅመሱ ምክንያት በቁመቱ ልክ የተጋደመ ስኳር በሽተኛ ዓይተው ኖሯል። በሽተኛውን ቀና አድርገው ሚሪንዳ ለማቅመስ የሚሞክሩ መንገደኞች ይረባረባሉ። “ምናለበት ከውድቀት በፊት ብንረባረብ?” ቢል አንድ ተሳፋሪ፣ “እውነት ነው። ይኼኔ አንድ ጉርሻ ማግኘት ባይችል ነው፤” ብሎ አጠገቡ ያለው መለሰ። አመላችን ሆኖ ካለቀ መድረስ ይቀናናል። ‘አቅርቡኝ ጠይቁኝ ብዬ ስለፈልፍ ሰሚ ስላጣሁኝ፣ በድኔን አትንኩት ስሞት አትቅበሩኝ’ ያለው ማን ነበር?

ወደ መገናኛ ተቃርበናል። አንዱ ስማርት ፎኑን ቦግ አድርጎ አብርቶ የሆነ ነገር እያየ ይስቃል። አጠገቡ የተቀመጠች፣ ‹‹እኛም እንሳቃ፤›› ትለዋለች። ‹‹አንዱ ምን ብሎ ፖስት ቢያደርግ ጥሩ ነው? ነፍሰጡር ሚስቴ ካልጠፋ ነገር ስብሰባ አማረኝ ትለኛለች። እባካችሁ ጥሩ የስብሰባ ማዕከል ጠቁሙኝ። እውነት ይሁን ውሸት እንጃለቱ…›› ይላታል። ‹‹እውነቷን ነው። የሥራ ሰዓት በስብሰባና በግምገማ እየተቃጠለ ደመወዝ በሚገኝባት አገር ከዚህ በላይ ምን ሊያምራት ይችላል?›› ብላ አጠገቤ ያለችው ጮኸች። ‹‹የአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ይዘሀት ሂድ አትለውም ታዲያ? ምን ትጠብቃለህ?›› ይላል መጨረሻ ወንበር ከተሰየሙት አንዱ። ‹‹አሪፍ ሐሳብ። እንዲያው የዘንድሮው ስብሰባ መሪ ሐሳብ ሴቶች ላይ አነጣጥሯል እየተባለ ነው። ግን ብቻ…›› ብላ ከወይዘሮዋ ጎን የተሰየመችው ወጣት በእንጥልጥል ተወችው።

‹‹ጨርሺው እንጂ…›› ሲሏት ወይዘሮዋ፣ ‹‹አልወለድም ቢልስ ልጁ?›› ብላን አረፈችው። ድርሰት አደረግሺው እንዴ እህት? ፅንስ እኮ ነው…›› አላት ጎልማሳው የሚላት ጠፍቶት። ‹‹ምን ይታወቃል ዘንድሮ? ትናንት ድርሰት ነው የተባልነው ነገር ዛሬ ገሃድ ሆኖ እያየን ነው። እንዲያው ብቻ በአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ላይ እናቱ በሆዷ ይዛው ሲታደም የሚሰማው ነገር ቢያስደነግጠው . . . ማለቴ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ተጎትቶ ቢሰማ አፍ አውጥቶ አልወለድም ሊል ይችላል። ያለፉት ወራት ብዙ ሺሕ የአፍሪካ ልጆች በረሃ አቋርጠው በሊቢያ ወደ አውሮፓ ለመግባት ሲጥሩ የሚገጥማቸው አስከፊ ነገር በካሜራ ሲቀረፅ ሰንብቷል። ስደትን ምርጫው ያደረገ ትውልድ በዚህ አኅጉር ላይ ተነስቷል። ከዚህ የበለጠ የሙሉ ጊዜ መወያያ ችግርና ሁሉን ዳሳሽ የሆነ ርዕሰ ጉዳይ አይኖርም። መፈክሩም ስደት ይቁም ‹ስደት ይብቃ፣ አፍሪካን ለአፍሪካውያን፣ ወዘተ› ሊሆን በተገባ ነበር። በፆታም ሆነ በምንም ነገር ከመከፋፈላችን በፊት ማናችንም ሰው መሆናችን ይቀድማል። ታዲያ ይኼ አልወለድም አያስብልም? ያስብላል?›› ብትል መልስ አጣን። ሌላው ቀበል አድርጎ፣ ‹‹ከአፍሪካ አልፈን የዓለም የጤና ተቋምን በቁጥጥራችን ሥር ያደረግን ቀን ይኼው ጉድ እንዳይደገም እንጂ ሌላውስ ሌላ ነው…›› ሲል ወያለው ‹መጨረሻ› ብሎ በሩን ከፈተው። ከፈረሱ ጋሪው በቀደመባት አኅጉር ደግሞ ዓለምና ጤናዋ ምን ምን ይጠብቁብን ይሆን! የሚል ፅንስ ድምፅ ሲሰማን መውረድም መውጣትም ጨነቀን።  መልካም ጉዞ!  

 

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት