Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየመልካ ቁንጥሬ ሙዚየም ዳግም ሥራ ሊጀምር ነው

የመልካ ቁንጥሬ ሙዚየም ዳግም ሥራ ሊጀምር ነው

ቀን:

 በዕድሳት ላይ የሚገኘው የመልካ ቁንጥሬ የቅድመ ታሪክ መካነ ቅርስ ሙዚየም ከወር በኋላ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ተገልጿል፡፡ ከወራት በፊት ዕድሳቱ የተጀመረው ሙዚየሙ አስፈላጊ ግብዓቶችን በማሟላት ላይ እንደሚገኝና ከወር በኋላ ዳግም ወደ ሥራ እንደሚመለስ የመልካ ቁንጥሬ ቅድመ ታሪክ መካነ ቅርስ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ተሰማ ተናግረዋል፡፡ በዓለም ለ40ኛ፣ በኢትዮጵያ ለ15ኛ ጊዜ የተከበረውን  ዓለም አቀፍ የሙዚየም ቀን ምክንያት በማድረግ መካነ ቅርሱ ሲጎበኝ እንደገለጹት፣ አራት ክፍሎች ያሉት ሙዚየሙ በአንድ ሚሊዮን ብር እየተደረገለት ያለው ዕድሳት እየተገባደደ ይገኛል፡፡

      የመልካ ቁንጥሬ የቅድመ ታሪክ መካነ ቅርስ (ፕሪሒስቶሪክ አርኪዎሎጂካል ሳይት) ሙዚየም የመጀመርያው ክፍል የአፍሪካ የቅድመ ታሪክ መረጃ ሙዚየም      (አፍሪካን ፕሪሒስቶሪክ ኢንፎርሜሽን ሙዚየም) በአፍሪካ ውስጥ ትልልቅ ሥራ የሠሩ ታዋቂ አርኪዎሎጂስቶች፣ ጂኦሎጂስቶችና ሌሎችም የዘርፉ ባለሙያዎችን ያስቃኛል፡፡ ከነዚህም ድንቅነሽ (ሉሲ)ን ያገኟት ዶናልድ ጆንሰንና በመልካ ቁንጥሬ ቀደምት ሰዎችና እንስሳት የእግር ዱካ (ፉት ፕሪንት) ያገኘችው ሜሪ ሊኪና ቤተሰቦቿ ይጠቀሳሉ፡፡

በሙዝየሙ ከቀደሙ የድንጋይ መገልገያዎች ጀምሮ የመካከለኛው ዘመን የድንጋይ መገልገያዎችም ይገኛሉ፡፡ በአገሪቱ ያሉ ስድስት በዘርፉ ተጠቃሸ የሆኑ የቁፋሮ ቦታዎች (አርኪዮሎጂካል ሳይትስ) ሐዳር፣ ኦሞ ስምጥ ሸለቆ፣ ባሌ ጋደብ፣ መካከለኛው አዋሽ፣ ሞጆና ድሬዳዋ የዋሻ ውስጥ ሥዕሎች የተገኙበት ለገ ኦዳን የሚያሳይም ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሁለተኛው ክፍል የጂኦሎጂና ቮልካኖሎጂ ሲሆን፣ መልካ ቁንጥሬ ከሚገኝበት ሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባልጩ ከሚባለው የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ የነበረበት አካባቢ የተሰበሰቡ ሹል መገልገያ ድንጋዮች የሚገኙበት ነው፡፡  ሦስተኛው ክፍል ስለ ፖሊአንትሮፖሎጂ ማለትም የሰው ልጅ በዝግመተ ለውጥ ሒደት ዛሬ ያለበት እንዴት እንደደረሰ የሚያሳይ ነው፡፡ አራተኛው መልካ ቁንጥሬ የሚባለውና በመካነ ቅርሱ ካሉ የቁፋሮ ቦታዎች የተሰባሰቡ የእንስሳት ቅሪተ አካሎችና የእጅ መሣሪያዎች የሚገኙበት ነው፡፡

አቶ ተስፋዬ እንደሚናገሩት፣ በሙዚየሙ የተሰበሰቡት ቁሳቁሶችና ቅሪተ አካሎች ጉዳት እንዳይደርስባቸው በአግባቡ የሚቀመጡበትና ለዕይታም ምቹ የሚሆኑበት መደርደሪያ ተሠርቷል፡፡ ‹‹በአዲስ መልክ የተሠሩት መደርደሪያዎች የሚበላሹ ነገሮች እንዳይኖሩ ይረዳሉ፡፡ መደርደሪያዎቹን ለማስገባት፣ ሙዚየሙን ለማደስ፣ ታፔላ ለመለጠፍና ለአጠቃላይ ዕድሳቱ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት የአንድ ሚሊዮን ብር ድጎማ አድርጓል፤›› ሲሉም ያስረዳሉ፡፡ የሙዚየሙ ታድሶ መከፈት መካነ ቅርሱን ለጎብኚዎች ምቹ እንደሚያደርግም ይጠበቃል፡፡

ኃላፊው እንደሚሉት፣ ተፈጥሮ ከነበረው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ የጎብኚዎች ቁጥር ዘንድሮ ቢያሽቆለቁልም፣ መካነ ቅርሱን ለመጎብኘት የዘርፉ ተመራማሪዎችና ሌሎች ግለሰቦችም ይሄዳሉ፡፡ መልካ ቁንጥሬን ለማስተዋወቅ በሕዝብ ግንኙነት ክፍል በኩል በበራሪ ወረቀቶችና በተለያዩ መንገዶች መረጃ እንደሚያሰራጩ ይናገራሉ፡፡ በዚህም የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች፣ ቱሪስቶች እንዲሁም ተመራማሪዎች ወደ አካባቢው ይጓዛሉ፡፡ ‹‹የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች በብዛት ይመጣሉ፡፡ በዓመት እስከ አሥር ሺሕ ጎብኚዎች መካነ ቅርሱን ይጎበኛሉ፤›› ይላሉ፡፡

መካነ ቅርሱ አሁንም ጥናትና ምርምር የሚካሄድበት መሆኑና በየወቅቱ አዳዲስ ግኝቶች ይፋ መደረጋቸው የቦታውን ዕውቅና ይጨምሩታል፡፡ ኃላፊው እንደምሳሌ የሚጠቅሱት በዓለም አቀፍ ደረጃ ገና ይፋ ባይደረግም በአካባቢው የቀደምት ሰዎችና እንስሳት የእግር ኮቴ ዱካ/አሻራ (ፉት ፕሪንት) መገኘቱን ነው፡፡ ከጣሊያን ሳፔንዛ ዩኒቨርሲቲ በቦታው ተገኝተው ጥናት የሚሠሩ  ተመራማሪዎች ያሉ ሲሆን፣ የእግር ዱካ መገኘቱ ትልቅ ዜና በመሆኑ ይፋ ሲደረግ የጎብኚዎች ቁጥር ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

መልካ ቁንጥሬ የቅድመ ታሪክ መካነ ቅርስ ብቸኛው በግልጽ የሚታይ (ኦፕን ኤር ሙዝየም) በመያዙ ይታወቃል፡፡ መካነ ቅርሱ ከሆሞኢሬክተከ ታሪክ ጋር የሚገናኝ ሲሆን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ መቆም የቻለውን የሰው ዝርያ ሆሞኢሬክተስ ቅሪተ አካል፣ የድንጋይ መሣሪያዎች፣ እሳት ያነደዱበት ቦታና የጉማሬ ቅሪተ አካል ይገኝበታል፡፡ ላለፉት አምስት አሠርታት የምርምር ውጤቶች መነሻ በመሆን የሚጠቀሰው መካነ ቅርሱ፣ ወደ 65 የቁፋሮ ቦታዎች አሉት፡፡

በአፍሪካ ከታንዛኒያው ኦልዱቫይ ጎርጅ ቀጥሎ የሚገኝ ኦፕን ኤር ሙዝየም ሲሆን፣ ከሌሎቹ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለየ የቅድመ ታሪክ ሙዚየም ነው፡፡ ‹‹የድንጋይ መገልገያዎች፣ የእንስሳት፣ የሰዎችና የዕፀዋት ቅሪተ አካሎች የሚገኙበት በመሆኑ ከሌሎች የቁፋሮ ቦታዎች በበለጠ ለጥናትና ምርምር የተመቸ ነው፤›› ይላሉ ኃላፊው፡፡

ከ65 የቁፋሮ ቦታዎች ጎምበሬ የተባለውን አቶ ተስፋዬ ያስጎበኙን ሲሆን፣ ቦታው የ1.7 ሚሊዮን ዓመት ታሪክ ያለው ነው፡፡ የሆሞኢሬክተስ መኖሪያ አካባቢ ከቅሪተ አካሎችና መገልገያ ቁሳቁሶች ጋር ይጎበኛል፡፡ ግንቦት 12 ቀን 2009 ዓ.ም. አካባቢውን በጎበኘንበት ወቅት በቁፋሮ ቦታው ፕላስቲክ ተጥሎ ተመልክተናል፡፡ የብዙ ዓመታት ታሪክ ያለው ሥፍራ በተገቢው መንገድ መያዝ አይገባውምን? በሚል ከሪፖርተር የቀረበውን ጥያቄ ኃላፊው ሲመልሱ፣ ለቦታው ጥበቃ እንደሚደረግና ጎብኝዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መልዕክት ቢተላለፍም አንዳንዴ ታዳጊዎች ባለማወቅ ቆሻሻ እንደሚጥሉ ተናግረዋል፡፡ ታዳጊዎቹ ጎብኝተው ሲጨርሱ በየቀኑ ፅዳት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ ቦታው ኦፕን ኤር ሙዝየም በመሆኑ መሸፈን ስለማይቻል ንፅህናውን መጠበቅ ላይ እንደሚሠሩም አክለዋል፡፡ መካነ ቅርሱ በ100 ሺሕ ካሬ ሜትር ስፋት የታጠረ ሲሆን፣ የቁፋሮ ቦታዎቹ በቋሚ እንጨትና ጣሪያ (ከአራቱም አቅጣጫ ክፍት የሆነ) ተከልለዋል፡፡

የሙዚየም ቀንን ያስታከከው ጉብኝት ከመልካ ቁንጥሬ በተጨማሪ ጥያ ትክል ድንጋዮችና አዳዲ ማርያም ቤተ ክርስቲያንንም ያካተተ ነበር፡፡ በዩኔስኮ (በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት) መዝገብ ላይ ከሠፈሩት ቅርሶች መካከል ጥያ ትክል ድንጋዮች ይገኙበታል፡፡ በቦታው ከ700 እስከ 900 ዓመታት ያስቆጠሩ የነገሥታትና ጦረኞች መካነ መቃብሮች ያሉ ሲሆን፣ 41 ቁም ድንጋዮች ይገኛሉ፡፡ ባለ አምስት ሜትሩ ትልቅ ትክል ድንጋይ ከዕድሜ ብዛት ተሰብሮ ከፊሉ ለጥናትና ምርምር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ይገኛል፡፡

ከትክል ድንጋዮቹ አንዱ ወደ ጎን በመዚየሙ የብረት ድንጋይ ተደርጎለታል፡፡ የጥያ ትክል ድንጋዮች አስጎብኚ አቶ ሲሳይ ዋቅጂራ እንደሚናገረው፣ ድንጋዮቹ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ጥላ (ሼድ) ይደረጋል ቢባልም እስካሁን የተሠራ ነገር የለም፡፡ አካባቢውን በጎበኘንበት ወቅት መሬት ላይ የሚገኙ መካነ መቃብሮች ጎብኚዎች ሲረማመዱባቸውና የቆሙትን ትክሎችም ሲነካኳቸው አስተውለናል፡፡ ‹‹ቅርሶቹን መንካት ክልክል ነው›› የሚል መግለጫ በመካነ መቃብሩ መግቢያ ከመለጠፍ ባለፈ ቅርሶቹ እንዳይነኩ የሚከላከል አካል አልነበረም፡፡

በመካነ መቃብሩ አቅራቢያ ግንባታው በ2006 ዓ.ም. ተጀምሮ በ2008 ዓ.ም. የተጠናቀቀው ሙዚየም ይገኛል፡፡ ሆኖም ሙዝየሙ በአሁን ወቅት ያለአገልግሎት ተቀምጧል፡፡ አስጎብኚው እንደሚለው፣ በመካነ መቃብሩ ከቅሪተ አካሎች ጋር ተቀብረው የተገኙ የሸክላ ቁሳቁሶችና ጌጣ ጌጦች እንዲሁም የጉራጌን ባህል የሚገልጹ ቁሳቁሶች ሲሟሉ ሙዚየሙ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል፡፡ የሙዝየሙ ግንባታ ቢጠናቀቅም ወደ ሥራ አለመገባቱ የብዙዎች ጥያቄ መሆኑን ገልጾ፣ ሥራ እንዲጀምር በየአቅጣጫው ግፊት እየተደረገ መሆኑን አስረድቷል፡፡

በክልሎች የሚገነቡ ሙዝየሞችን በተመለከተ ጥያቄ ሲነሳ ይህ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ከሙዝየሞቹ የቅርስ ስብስቦች ጀምሮ፣ ቅርሶቹ ስለሚያዙበት መንገድና ሙዝየሞቹ በሚሰጡት አገልግሎት ዙሪያ ያሉ ችገሮች ይነሳሉ፡፡ ሙዚየም የሌላቸው አካባቢዎች ብዙ ከመሆናቸው ባሻገር ሙዚየም ተገንብቶ ተገቢውን አገልግሎት የማይሰጡም አሉ፡፡  ባለፈው ሳምንት ዓለም አቀፍ የሙዚየም ቀንን ምክንያት በማድረግ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አዳራሽ በተደረገ ውይይትም የክልል ሙዚየሞች ትኩረት እንደተነፈጋቸው ተመልክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...