Wednesday, September 27, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ለጤናማ ሥርዓት ግንባታ ሐሳብ ይዋጣ!

ለአገር ሰላም፣ መረጋጋት፣ ዕድገት፣ ብልፅግና፣ እንዲሁም ለሕዝብ የተሟላ እርካታ ሲባል ጤነኛ የሆነ ሥርዓት መገንባት መቼም ቢሆን የማይታለፍ መሠረታዊ ጉዳይ መሆን አለበት፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሚከናወኑ አፍራሽ ድርጊቶች ደግሞ ለጤና አልባ ሥርዓት መደላድል ይሆናሉ፡፡ አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያስፈልጋታል ሲባል በዴሞክራሲ መመዘኛ ብቁ የሆነ ቁመና መኖር አለበት ማለት ነው፡፡ ይህ ዕውን ይሆን ዘንድ ደግሞ በሕግ የበላይነት ላይ የተመሠረተ ጤናማ የሥርዓት ግንባታ ሒደት መጀመር አለበት፡፡ ይህ ዓይነቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው ደግሞ ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል ሲሆኑና እኩል ተጠያቂነት ሲኖርባቸው ነው፡፡ ዜጎች ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በፈቃዳቸው እንዲመሠረት ዕውቀትን የተመረኮዘ ግንዛቤ ሊፈጠርላቸው ይገባል፡፡ እነሱም በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ኃላፊነታቸውን መወጣት መብታቸውም ግዴታቸውም ይሆናል፡፡ በዚህ ዓይነቱ አካሄድ ደግሞ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ይከበራሉ፡፡ በዚህ መሠረት የሚገነባ ሥርዓት መሠረቱ ጠንካራ ይሆንና የአገር ሰላምና ዕድገት አስተማማኝ ይሆናል፡፡

ዜጎች በገዛ አገራቸው አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲራመዱ ከሚያደርጓቸው መሠረታዊ ከሚባሉ ጉዳዮች መካከል ዋነኛው የሕግ የበላይነት መከበር ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ሲከበር ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመሰብሰብ፣ የመደራጀትና በነፃነት ለመምረጥም ሆነ ለመመረጥ የሚያስችላቸው ዕድል በጣም የሰፋ ይሆናል፡፡ ይህ ዓይነቱ የተቀደሰ ሐሳብ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ የሲቪክ ማኅበራት እንደ እንጉዳይ መፍላት አለባቸው፡፡ አገራቸውንና ሕዝባቸውን በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል የተዘጋጁ፣ የማንም ተላላኪ ያልሆኑ፣ በሕግ ብቻ የሚመሩና ተጠያቂነት ያለባቸው ሲቪክ ማኅበራት ሲኖሩ የዜጎች ንቃተ ኅሊና ይዳብራል፡፡ በአሉባልታ ላይ የተመሠረቱ ሳይሆኑ በመረጃና በማስረጃ የዳበሩ አስተሳሰቦች ይንሸራሸራሉ፡፡ ያኔ የተለያዩ ሐሳቦች በነፃነት የሚስተጋቡበት ሥርዓት ዕውን መሆኑ በገቢር ይረጋገጣል፡፡ አሁን በየቦታው የሚታየው የሌሎችን ሐሳብ ደፍቆ የራስን ማቀንቀን ሙዚየም ይገባል፡፡ ከዚህ ቀደም የተፈጸሙ አጓጉል ድርጊቶች ለታሪክ ድርሳንነት ይተላለፋሉ፡፡ የዘመናት ቁስሎች ሽረው አዲስ ምዕራፍ ይጀመራል፡፡

ከላይ እንደ መንደርደሪያ የተነሱ በኩረ ሐሳቦች ዕውን ይሆኑ ዘንድ መጀመሪያ የተዘጋጋው የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳ መከፈት አለበት፡፡ ሰላማዊና ሕጋዊ የፖለቲካ ትግሉ አሁን እንደሚታየው የቀልደኞች መጫወቻ ሳይሆን፣ ለአገራቸው ከሚታሰበው በላይ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉ ወገኖች የሚሳተፉበት መሆን ይገባዋል፡፡ አገራቸውን በተለያዩ የሙያ መስኮች የሚያገለግሉ ወገኖች በነፃነት ያደራጁዋቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ብርታትና ጥንካሬ አግኝተው የሚፈለግባቸውን ሚና እንዲጫወቱ፣ ደጋፊ ወይም አባል መሆን የሚፈልጉ ዜጎች ያለምንም መሸማቀቅ እንዲሳተፉባቸው ሲደረግ የአገሪቱ የወደፊት ተስፋ ይለመልማል፡፡ ‘ፖለቲካና ኮረንቲን በሩቁ’ የሚባለው የፍርኃት ቆፈን ውስጥ የሚያስገባው አባባል ተረት ይሆናል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው የሕዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ በተግባር ሲረጋገጥና በሕግ የተደነገጉ መብቶች ሥራ ላይ ሲውሉ ብቻ ነው፡፡ በዚህ ዓይነቱ ቀና መንገድ ላይ መረማመድ የሚቻለው ደግሞ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከማንም በፊት ቁርጠኛ መሆን ሲችል ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በተለያዩ ምክንያቶች የተገፉ ዜጎች፣ ምሁራንና የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሠለጠነ አኳኋን ለዚህ በጎ ጅምር እንዲነሳሱ ይረዳል፡፡

እከሌ ከእከሌ ሳይባል እስካሁን ለነበሩ ችግሮችና አሳዛኝ ድርጊቶች ራስን ከመውቀስ ጀምሮ የተለያዩ ጠቃሚ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡ ማዶ ለማዶ ሆኖ ሲወጋገዙ መኖር ምንም የፈየደው ነገር የለም፡፡ ሌላው ቀርቶ ላለፉት 26 ዓመታት በፖለቲካው መስክ የተከናወኑ ድርጊቶች ስህተትን በሌላ ስህተት ለማረም ከመፍጨርጨር ውጪ ምን ተገኘ? ጽንፍ ይዞ አሰቃቂ በሆኑ ቃላት ከመወራረፍ በላይ ምን ተደረገ? ንፁኃን ዜጎችን የሚማግዱ አላስፈላጊ መስዋዕትነቶችን በተለያዩ ጊዜያት ከመፈብረክ ያለፈ ምን የረባ ነገር አለ? ሌላው ቀርቶ በቅርቡ አገሪቱን ጭንቅ ውስጥ የከተታት ነውጥ ሲፈጠር የፖለቲካ ኃይሎች ሚናስ እዚህ ግባ የሚባል ነበር? በማኅበራዊ ሚዲያዎች ግለሰቦች አገርን ሲያተራምሱ የፖለቲከኞች ፋይዳስ ታይቷል? ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል የሚታወቀው የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች እሰጥ አገባ ለዚህ ትውልድ ካልጠቀመ፣ በነበረበት ሁኔታ መቀጠሉ ረብ የለውም፡፡ ይልቁንም ለአዲስ ምዕራፍ መዘጋጀት ይበጃል፡፡

አገሪቱን እየመራ ያለው መንግሥት ችግሮቹን ማወቁ አንድ ነገር ሆኖ፣ ነገር ግን ባለህበት እርገጥ ዓይነት አካሄዱን ማቆም አለበት፡፡ በመጀመሪያ ሌላው ቢቀር በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና ያገኙ መሠረታዊ የሚባሉ መብቶች እንዲከበሩ ያድርግ፡፡ እነዚህ መብቶች ሲከበሩና ሕዝብ የሚፈልገው ሥራ ላይ ሲውል ሌላው ዕዳው ገብስ ነው፡፡ ሥልጣን ላይ መውጣትና መውረድ በሕዝብ ነፃ ፍላጎት ብቻ መሆኑን ከልቡ ይመን፡፡ ለዚህም ምርጫን ነፃና ፍትሐዊ የሚያደርጉ አሠራሮች ተግባራዊ እንዲደረጉ ይጣር፡፡ በቁጥጥሩ ሥር ያሉት በግብር ከፋዩ ሕዝብ በጀት የሚተዳደሩ ሚዲያዎች የሐሳብ ብዝኃነትን ያስተናግዱ፡፡ ከአድሎአዊ አሠራር ይላቀቁ፡፡ ሥልጣን በኃይል ወይም በጉልበት እንደማይያዝ የሚደነግገው ሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ምርጫዎች የሕዝብ ይሁንታን ማግኘት ሲጀምሩ አስተማማኝ ሰላም ይሰፍናል፡፡ ዴሞክራሲ በእርግጥም ሥርዓት ይሆናል፡፡ ከዚህ ቀደም የደረሱ በደሎች ሁሉ ለታሪክ ይተዋሉ፡፡ በሌላ በኩል በተቃውሞው ጎራ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች ራሳቸውንና ደጋፊዎቻቸውን አደብ አስገዝተው ለዴሞክራሲ ታዛዥ ይሁኑ፡፡ ‘ከእኔ በስተቀር…’ የሚባሉ ፉከራዎቻቸውን ፋይል ዘግተው ለሐሳብ ነፃነት ይሟገቱ፡፡ በሐሰተኛ ታሪኮችና ድርሳናት ላይ ተንጠልጥለው የሌለ ነገር እያወሩ የጤናማ ሥርዓት ግንባታን አያደናቅፉ፡፡ ለሕጋዊና ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ይዘጋጁ፡፡ ያኔ በእርግጥም የተበለሻሸው ሁሉ ይስተካከላል፡፡ የሕዝብ ምኞት ዕውን ይሆናል፡፡

የአገር ጉዳይ የሚያገባቸው ማለትም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ በሲቪክ ማኅበራት፣ በሃይማኖት ተቋማት፣ በንግድ፣ በእርሻ፣ በቴክኖሎጂ፣ በሕክምና፣ በተለያዩ አደረጃጀቶችና በመሳሰሉት የሚሳተፉ ዜጎች አለን ይበሉ፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ለአገራቸው ክብር፣ ዕድገትና ብልፅግና አስተዋጽኦ ይኖረናል የሚሉ ሁሉ በቀና መንፈስ ይቅረቡ፡፡ ይህንን ማድረግ ሲቻል መቀራረብ፣ መነጋገርና መደራደር ችግር አይሆንም፡፡ እስካሁን ድረስ በሰፊው ሲስተጋቡ የቆዩ አፍራሽ ነገሮች ሥፍራ አይኖራቸውም፡፡ ከመሰዳደብና ከመወጋገዝ ምንም ጠብ አይልም፡፡ ለአመፅና ለውድመት ከሚዳርጉ አስከፊ ተግባራት ውስጥ መውጣትና አዲስ ምዕራፍ መጀመር የወቅቱ ዓላማ መሆን አለበት፡፡ የአገርን ክብር እያንቋሸሹ አንድነቷን ለመናድ ሕዝብ የሚከፋፍሉ ከንቱዎችም ባረጁና ባፈጁ ፕሮፓጋንዳዎች ወጣቱን አያደንቁሩ፡፡ ኢትዮጵያዊነትን እየዘለፉ አገርን ለማድማት መሞከር ፋይዳ የለውም፡፡ ይህንን ኩሩ ሕዝብ በዘርና በሃይማኖት መለያየት አይቻልም፡፡ የሞከሩትም አልተሳካላቸውም፡፡ ከምንም ነገር በላይ የአገር የጋራ ጉዳይ ሊያሳስብ ይገባል፡፡ አገር ሰላም የምትሆነው በመግባባት ላይ የተመሠረተ የሐሳብ ልዩነት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ገንቢ ሐሳቦች ደግሞ ይበረታታሉ፡፡ ልዩነትን እያጦዙ አገርን ለማጥፋት መገዳደር ግን ኋላቀርነት ነው፡፡ አገር የሚጠቅማት ጤናማ ሥርዓት መገንባት ነው፡፡ ለጤናማ ሥርዓት ግንባታ ሐሳብ ማዋጣት ይቅደም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...

ማን በማን ላይ ተስፋ ይኑረው?

በአንድነት ኃይሉ ችግሮቻችንን ለይተን ካወቅን መፍትሔውንና ተስፋ የምናደርግበትን ማወቅ እንችላለን፡፡...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት...

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...