Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትታሪክን በመቆልመም ለወገንተኛ ፖለቲካ ፍላጎት እንዲገብር ማድረግ ለዚህ ዘመን አይመጥንም

ታሪክን በመቆልመም ለወገንተኛ ፖለቲካ ፍላጎት እንዲገብር ማድረግ ለዚህ ዘመን አይመጥንም

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ ታሪክነት ሲታተት የነበረው ነገር ዛሬ ትልቅ ጥያቄ ምልክት ውስጥ የወደቀ እንደመሆኑ፣ ይህ የዛሬው ወቅት የተለዩ ሥራዎችን ይሻል፡፡ ምንም ምንጭ ሳያሳውቁ የተሸጠሸጠ ነገር ለዚህ ወቅት ምንም ያለማዋጣት ያህል ነው፡፡ ከመስመር መስመር የምንጮችን ስሞች በድፍኑ መደቅደቅም ብቻውን ለአንባቢ የሚያስተማምን ነገር በመስጠት በኩል የሚያበረክተው ነገር የለም፡፡

ቁም ነገሩ ለምስክርነት የሚበቁ መረጃዎች መሥፈራቸው ነው፡፡ ዛሬ የሚያስፈልገው አንድ የታሪክ ጉዳይን የሚመለከቱ ተደጋጋፊና የሚጣሉ መረጃዎች እየተጋጠሙ የሚመዛዘኑበት፣ የማያፈናፍኑ ማስረጃዎች ከአጠራጣሪ የሚለዩበት፣ በመረጃዎች ደካማነትና ማነስ ላይ ሎጂካዊ ፈትል ተጨምሮ ምናልባት እንዲህ ሆኖ ይሆናል ሊባሉ የሚችሉትና ግምት ለመስጠት የሚያስቸግሩ የተለዩበት ትንታኔ ነው፡፡ አንባቢ ከጸሐፊው ጋር እርግጡንና አጠራጣሪውን አብሮ እንዲፈርድ የሚያስችለው የዚህ ዓይነት ሥራ ነው፡፡ ለሕዝብ በሚቀርቡ ሥራዎች ዘንድ ዛሬ ያለው ዋና ጉድለትም እዚህ ላይ ነው፡፡

ለምሳሌ አምስትና ስድስት መቶ ዓመታት ስላለፋቸው የታሪክ ጉዳዮች እከሌ እንዳለው እየተባለ ወይም በድፍኑ ምንጩ (በቅንፍ/በቁጥር) ተጠቁሞ ይተረካል፡፡ የምንጩ ዘመን ሲታይ የአሥራ ዘጠነኛው ወይም የሃያኛው ክፍለ ዘመን ጸሐፊ ይሆናል፡፡ ጸሐፊው ይህን የቅርብ ምንጭ ለምን ተጠቀመ? ለምን አመነው? አንባቢ ምን ይዞ ይመንለት? ምንም፡፡ መልስ ይጠፋል፡፡ በዚያ ላይ አመኔታ ከመለመን በማይሻል በዚህ ዓይነት የመረጃ ምንጭ ላይ ተመሥርቶ ቋጥኝ የሚያህል ትርጓሜ (ትንታኔ) ይሰጣል፡፡

ቀደምት ጸሐፊዎችን በአድሏዊነት እየነቀፉ ግን ከአድሏዊነት አለመራቅ ሌላው ዓይን ያወጣ አሳፋሪ ችግር ነው፡፡ የዓለም አገሮች የታሪክ ጉዞ በየትም ሥፍራ ሚዛን ጠብቆ ሂያጅ ሆኖ አያውቅም፡፡ የመገዛዛት ሒደት አሸናፊነትንና የኃይል የበላይነትን እንጂ ተራን ተከትሎ አያውቅም፡፡ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ግንባታ ከአገሪቱ መጠሪያ ጭምር ከሰሜን ወደ ደቡብ የተካሄደ የመስፋትና የማስገበር ጉዞ (ግን የተወሳሰቡ ከሁለት አቅጣጫም የአካባቢዎች የመዋዋጥ ትንንቅና የሕዝቦች እንቅስቃሴ የነበሩበት) መሆኑ አያስገርምም፡፡

በዚህ የተዛነፈ አካሄድ ውስጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እንደ ማንኛውም ገዢ ሃይማኖት የተስፋፊዎቹ የርዕዮተ ዓለም ተቋም ሆና ሠርታለች፡፡ ነግሥታትን በማስወደስ፣ ዘመቻ በመባረክ፣ አብሮ በመዝመት ተሳትፋለች፡፡ የአስገባሪነት ጥቅም ተካፍላለች፣ ታሪክ ጽፋለች፣ ገድል ጽፋለች፡፡ የጽሑፍ ሀብቶቿን በቁም ጸሐፊዎቿ እያባዛች አንዱ ዘንድ ቢቃጠል ሌላ ሥፍራ እንዲገኝ አድርጋ አቆይታለች፡፡ ለነገሥታት ውድ ንብረቶች አስተማማኝ መቀመጫም እሷው ነበረች፡፡ ይህን ያህል በሰፋ ሚና ውስጥ አሻራዋ ቢበዛ፣ ራሷን ከኢትዮጵያ ምንነት ለይቶ ለማየት ብትቸገር፣ ለኢትዮጵያ ባንዲራ ክርስቲያናዊ ትርጓሜ ብትሰጥ፣ ምኒልክ ይህንኑ ትርጓሜ ቢያውጁ (አህመዲን ጀበል፣ 2003 ገጽ 23፡፡)  የጉድ ሥራ አይሆንም፡፡ ገዢ ርዕዮተ ዓለሞች ያላደረጉት በኢትዮጵያ ምድር አልተደረገም፡፡ እንደ የርዕዮተ ዓለሙ ዓይነት በክርስቶስ ልደት ላይና በሂጂራ ላይ ተመሥርቶ መቁጠር መጥቷል፡፡ የመስቀል ቅርፅ፣ ጨረቃና  ኮከብ፣ ጎራዴ፣ ማጭድና መዶሾ ሁሉ የባንዲራ ዓርማ ሆነዋል፡፡ የኦሮሚያ የዛሬ ዓርማ ቀለማት ከኦሮሞ ነባር ባህልና አተያይ ጋር የተያያዘ ተምሳሌታዊ ሥር አላቸው፡፡

ኦርቶዶክስ ክርስትና የኢትዮጵያ መለያና መታወቂያ ሆኖ በተሾመበት በዚያ አፄያዊ የአስገባሪነት ዘመን ውስጥ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ መነኮሳት በጻፏቸው ታሪኮች ለእምነታቸው ወገንተኛ መሆን የተልዕኳቸው ተፈጥሮ ነው፡፡ የሌላ ሃይማኖት ተከታዮች (እንቢ ያሉት እየተፈጁ) ወደ ክርስትና መግባታቸውን የጽድቅ ሥራ፣ በክርስትና ላይ ይህ ሲፈጸም ደግሞ የኩነኔ (የሃይማኖት መጥፋት) ወይም የፍርጃ ጊዜ አድርጎ ከማየትና ከመተርጎም ሊያመልጡ የሚችሉበት ጊዜ አልነበረም፡፡ በዚያን ጊዜ የአህመድ ኢብን ኢብራሂምን የድል ዘመቻዎች በኢትዮጵያና በክርስትና ላይ የተነሳ ጦርነት፣ የጥፋትና የቅጣት ዘመን አድርገው ለምን ጻፉ ብሎ መብከንከን መቃዠት ይሆናል፡፡

ዕውናዊ አስተሳሰብ የህሊና ለውጥ ባላስከተለባቸው ኅብረተሰቦች ውስጥ ክንዋኔዎች የሚብራሩትና እንቆቅልሾች የሚፈቱት በእምነት አማካይነት ነው፡፡ ህልሞችና ድርጊቶች የመለኮታዊ ደግና መጥፎ ሥራ መከሰቻና ማመልከቻ ሆነው ይወሰዳሉ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስም በአገራችን የዕለት ተዕለት ኑሮ ቅጥ አምባር የታጣላቸውን ነገሮች መፍቻ ሆኖ እያገለገለ ያለው እምነት ነው፡፡ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን ውስጥ ክፉና ደግ ውጤት ያመጣሉ የሚል ትርጉም የምንሰጣቸው ምልኪዎች አሉ፡፡ አንድ ሰው እክል አጋጥሞት ከአገር አቋራጭ የአውቶቡስ ጉዞ ቢተጓጎልና ያ አውቶብስ ቢገለበጥ የሰውየው መቅረትና መትረፍ የእግዜር ሥራ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ያላንዳች ሕመም ወደ ሞት የሄደ ከፃድቅ ሊቆጠር እንደሚችል ሁሉ ብዙ በሕመም መሰቃየት “ምን ኃጢያት ቢኖርበት ነው” የሚል አተረጓጎም ይጠራል፡፡ ታማሚው በደል የሠራ ወይም ፆም የማያከብር ከሆነማ የቅጣቱ ምክንያት የታወቀ ያህል ነው፡፡ የበሽታ ወረርሽኝንና ችጋርን ከኃጢያትና እግዜርን ከመርሳት የመጣ ቅጣት አድርጎ መተርጎምም የተለመደ ነው፡፡ መጥፎ ህልም አሳይቶኛል ብሎ መሥጋት/ከመንገድ መቅረት፣ ደግ ህልም አይቻለሁ ብሎ የተቃና ዕድል መጠበቅ ቀደም ባለው ጊዜ በተለይ የተለመደ ነበር፡፡

በተራው ሰው ደረጃ ይህንን ያህል ለማለት ከተቻለ፣ ለፃድቅነት የቀረቡ ለምዕመናን ንስሐና ደኅንነት መግቢያ በር የሆኑ፣ እስከ ንጉሥ ድረስ መገዘትና መፍታት የሚቻላቸው (ቃላቸው በጥርጣሬ የማይታይ) መነኮሳት ምን ያህል ያልተገደበ የትርጓሜና የንግርት ሥልጣን እንዳላቸው መገመት ነው፡፡ የሚያስሞግስ ባህርይና አድራጎት ያሳዩ ሰዎች በሆኑት ላይ ያልሆኑት፣ በሠሩት ላይ ያልሠሩት እየተጨማመረ ማንነታቸው አፈ ታሪክ አከል ይሆናል፡፡ በጊዜያት ውስጥ እየተራገበ የተገነባው የአፄ ቴዎድሮስ፣ የአለቃ ገበረ ሃናና የቅርቡ የኮምጬ አምባው ሰብዕና ከእውነተኞቹ ሰዎች አለልክ የናረ ነው፡፡ በሃይማኖትም በኩል በመስቀላቸው ፈዋሽነት በፆም ፀሎታቸው የሚሞገሱ፣ የወደፊቱ የሚታያቸውና ቃላቸው መሬት ጠብ የማይል የሚባልላቸው፣ የሠሩት እየተባዛና ጭማሪ እየወለደ ታምር የሚወራላቸው የእምነት ሰዎች ዛሬም ድረስ አሉ፡፡

ገድሎች በዚህ ዓይነት ሒደትና በመነኮሳት ያልተገደበ የመንፈስ ሥልጣን መሀል የበቀሉ ከመሆን አያመልጡም፡፡ በዶ/ር አያሌው ሲሳይ የአገው ሕዝቦችና የዛጉዌ ሥርወ መንግሥት ታሪክ ውስጥ በተጠቀሱ የገድል ጽሑፎች፣ ሥርወ መንግሥትን ከዛጉዌ ዘሮች ወደ ዳዊት ዘሮች የመለሰው እግዚአብሔር ግብሩና አስተሳሰቡ ሰዋዊ ሆኖ መቀረፁን እናስተውላለን (227 – 37)፡፡ ከተክለ ፃድቅ መኩሪያ የኢትዮጵያ ታሪክ ከአፄ ልብነ ድንግል እስከ አፄ ቴዎድሮስ ውስጥ የተጠቀሰው የገድል ጽሑፍ እግዚአብሔር የአፄ ልብነ ድንግልን ጥጋብና እብሪት ሊያበርድ “ግራኝን” ማስነሳቱን፣ ልብነ ድንግል ተፀፅቶ እግዚትነ ማሪያምን ቢለምን በራዕይ ታይታውና በመኃሪነቷ ልመናውን ሰምታ ንስሐ እንዲገባ እንዳዘዘችው፣ ሥጋው ተሰዳ ብትሞትም ነፍሱ ደስታን እንደምታገኝ እንደነገረችው እናነባለን (37 – 38)፡፡ ይህን ያህል መለኮታዊ ንግግርን/ቃል ኪዳንና ንግርትን እስከ መደርደር የመጠቀ ብዕር  ምድራዊ ክንዋኔዎች ላይ ፈጠራ መጨማመር እንደማይሳነው ማስተዋል አይከብድም፡፡ (በገድሎች ውስጥ የሚታየውን የሰማያዊ ኃይላት ተሳትፎ ሆን ብሎ የተጻፈ የእብለት ድርሰት አድርጎ ማቅለል እውነቱ ዘንድ የሚያደርስ አይመስለኝም፡፡ ጸሐፊው “ተገልጦለት”ም ሆነ ከቃላዊ ቅብብል ወስዶ የሚጽፈውን ራሱ ሳያምንበት አይቀርም፡፡ ጳጳስ ከግብፅ ማሾም ሳይቋረጥ ለረዥም ጊዜ የቆየው በረሃብና ቸነፈር መቀጣት ይከተላል ተብሎ ስለታመነም ነበር፡፡)

ዞሮ ዞሮ በቤተ ክርስቲያን ትምህርት የተቀረፁ ሰዎች የሚጽፏቸው ዜና መዋዕሎችም ውስጥ ዋናው ባለታሪክ (ንጉሡ) በጀብዱ ሥራው በእግዜር የሚመራ/የሚጠበቅ መሆኑ እንዳለ ሆኖ እንጀራው ከንጉሡ የሆነ፣ የጻፈውን ለንጉሡ አንብቦ ማሳረምና በአጻጻፍ አስደስቶ መሸለም ተግባሩ የሆነ፣ የንጉሥ ሽንፈትና ድል የራሱም ዕጣ የሆነ የዜና መዋዕል ጸሐፊም በገለልተኛነት ሊጽፍ አይችልም፡፡ ንጉሡ የጠላውን እየጠላ፣ የሚፋለመውን እየተፋለመ (እየኮነነና እያክፋፋ) ቢጽፍ ግዳጁ እንጂ ውርደቱ አይሆንም፡፡

ሃይማኖትና ታሪክ ጸሐፊነት ሳይቀር የማንበርከክና ያለመንበርከክ ትንንቅ ተሳታፊ በነበረበት የቀድሞ ዘመን ውስጥ ያለውን አድሎአዊነት አይቀሬነት ያለስሜታዊነት ማስተዋል፣ ሥራዎቹን ክዶና ንቆ ከመተው ፋንታ ውሸትና እውነቱን በተለያየ ዘዴ አበጥሮ ለመለየት አንጀትና ዓይን እንዲኖረንና ያለንበት ዘመን የጣለብንን ኃላፊነትም እንድናጤን ይረዳናል፡፡  

በዛሬው ጊዜ ታሪክ ራሱን ችሎ በሥነ ምግባር የሚሠራ፣ እውነት ላይ ለመድረስ የሚካሄድ የዕውቀት መስክ የሆነበትን ዘመን ዘግይተንም ቢሆን የመቀላለቀል ወጉ የደረሰን እንደመሆኑ የጥፋት ማማሃኛ አይኖረንም፡፡ ታሪክን ለመንግሥታዊ ፕሮፓጋንዳ፣ ለብሔርተኛ ወይም ለትምክህተኛ ፍላጎት እንዲገብር ማድረግ፣ ታሪክንና ሃይማኖትን መቀላቀል ከዛሬው ዘመን ታሪክ አጻጻፍ ውጪ ነው፡፡

የትርፍ ጊዜ ጸሐፊም ሆንን የሙሉ ጊዜ፣ የታሪክ ሙያተኛም ሆንን ኢሙያተኛ፣ ታሪክን አጥንተን ለመጻፍ ከተነሳን የመጀመርያው ሥነ ምግባር ማንኛንውንም ነገር ክፍት በሆነ አዕምሮና ገለልተኛ በሆነ ስሜት የመቅረብ ዝግጅት ነው፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የሚታሰሱና የሚበረበሩ የመረጃ ምንጮችን ብዛትና ዓይነት የተሟላ እውነት ላይ በመድረስ ዓላማ መምራት፣ በመረጃ ብርበራ ሒደት ውስጥም በወገናዊነትና በባይተዋርነት የተጻፉትን በቅጡ መለየት፣ ምንጮች ውስጥ ለሚያጋጥሙ ስሜቶች (ጥላቻዎች፣ ስድቦች፣ ሙገሳዎች) አለመበገር፣ (ከተበገሩ ለመታወርና ወደ አድሏዊነት ለመንከባለል ይጋለጣልና) የመረጃዎችን ዋጋ ለእኛ በመጣም አለመጣማቸው ሳይሆን ትክክለኛ በመሆን አቅማቸው መመዘን፣ በወገንተኛነት በተጻፉ ጽሑፎች ውስጥ (ለምሳሌ የጦርነት) ስለወገን ጥንካሬና ስለጠላት ድክመት የተነገሩ ነገሮችን በጥንቃቄ መፈተሽ፣ በቀጥታ ከመሸናነፍ ግብግብ ጋር ያልተያያዙ ለውሸትና ለማጋነን ያልተመቹትን ከሚመቹት መለየት፣ አህመድ ኢብን ኢብራሂም ምንኩስናውን አፍርሶ ከሙስሊም ሴት ከተገናኘ መነኩሴ የተወለደ (የኃጢያት ልጅ) አድርጎ በሚያቀርብ ዓይነት የፕሮፓጋዳ ሥራ አለመጭበርበር፣ በአንፃሩ ስለ“ወገን” ድክመትና ስለ“ጠላት” ጥንካሬ ለተሰጡ ምስክርነቶች ደግሞ የመታመን ብልጫ መስጠት አግባብ ነው፡፡

በዚሁ ዓይነት አንዱ ዘንድ የተገኘ መረጃ ደጋፊ ካለው ማጣራት፣ ከ“አሉ” ባይ የጽሑፍ መረጃ ወደ “አየሁ” ባይ የጽሑፍ መረጃ ማለፍ፣ የዓይን ምስክር መረጃም ውስጥ ከወሬ (ከስሚ)፣ ከእግረ መንገድ ልብታና አብሮ ከመሰንበት የተገኘውን ለይቶ ለማጤን መሞከር፣ ስለደብዳቤ መጻፍና ስለመሰል ክንዋኔዎች የሚሰጡ ትረካዎችን የተቻለውን ያህል ከሰነዶቹ ጋር ማገናዘብና ማጎዳኘት፣ የቃል መረጃን በመጠቀም ጊዜም በመረጃው አሰባሰብ ላይ በሰጪና በተቀባይ መካከል በሚኖር የመተማመን ቀዳዳ ምክንያት ሊመጣ ለሚችል እብለትና ጭማሪ/ቅናሽ ልዩ ትኩረት መስጠት፣ ይህን መሰሉን ችግር ለመቀነስ የቃል መረጃው ከተለያዩ ሥፍራዎች የመገኘቱን መጠንና ቀደም ባለ ጊዜ ስለቃል መረጃው በጽሑፍ የተመዘገቡ ነገሮች መኖር አለመኖራቸው ግምት ውስጥ ማስገባት ይጠበቃል፡፡ በመተንተን ጊዜም የአሳማኝ መረጃ እጥረት/ዕጦት ያለባቸውን የታሪክ ጉዳዮች በተመለከተ ከማድበስበስ፣ ከመሸምጠጥ ወይም ግምትን እውነት አስመስሎ ከመሙላት መቆጠብ፡፡ አጠራጣሪውን፣ አልፈታ ያለን እንቆቅልሽና መላምታዊ የሆነውን ከተረጋገጠው ለይቶ ማሳየት ግድ ነው፡፡

እነዚህን የመሳሰሉ ጥንቃቄዎች ተወስዶም ታሪክ ሒሳብ ባለመሆኑ የማያዳግም ሥራ አይገኝም፡፡ ጉድለቶችና የትንታኔ ልዩነቶች ከሰው ሰው መኖራቸው አይቀርም፡፡ ታሪክ የሚጣራው የአንዱን ትንታኔ ሌላው እያበራየው፣ አንዱ በሌላው ላይ እያከለ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት አካሄድ በቀድሞ የታሪክ አጻጻፍ የተሠሩ ብልሽቶችን ማቃናት፣ የተገፋው፣ የጠለሸው፣ የደበዘዘውም ሆነ የተጋነነው ትክክለኛ ምንነቱ እንዲታይ ማድረግ የዛሬ ኃላፊነት ነው፡፡ ሆኖም ግን የትናንት ዓይነት ብልሽቶች ዛሬም እየተደገሙ ማወካቸው አልቀረም፡፡ ነባር ከሆነ ወይም ወረት ካገኘ አቋም ጋር ለመስማማት ሲባል ወይም በቀደመ ጊዜ የተወረወሩ የንቀትና የዘለፋ ስሜቶችን በአፀፋ ለመበቀል ሲባል ወይም አስቀድሞ ተወስኖ ላለቀ መደምደሚያ ማስረጃ እየጠቀሱ (የምርምር መልክ እያስያዙ) መሸጥሸጥ፣ የታሪክ ዕውቀት ከማበርከቱ ይልቅ ማደንቆሩ ይበልጣል፡፡

ለታሪክ ጥናት ቅርብ የሆነ  ሰው በጥንታዊ መዛግብት ጥናት ማስትሬት ዲግሪ ያገኘ በቀድሞው የታሪክ አጻጻፍ ውስጥ የነበረውን አድሏዊነት የተቸ ሰው፣ የ19ኛውን ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ይዞ አውሮፓውያንን በመሻማት የተካሄደውን የኢትዮጵያን የግዛት ጥቅለላ መገባደጃ ሒደት የሙስሊሞች “ህልውና” የተደፈጠጠበትና በአውሮፓውያን “ሞግዚትነት” የተፈጸመ አድርጎ ሲጽፍ (አህመዲን ጀበል፣ 2003፣ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ከ615 – 1700 ገጽ 23) ከአፄ ዘርአያዕቆብ ጋር ሲታገል የነበረው ሡልጣን ሺሃቡዲን “ከደቡብ ሞቃዲሾ እስከ ሰሜን ኤርትራ . . . የሚዘልቅ ጠንካራ ኢስላማዊ መንግሥት የማቋቋም ዓላማ ነበረው” ባለበት አፉ (167)፣ አለፍ ብሎ (ገጽ 207 ላይ) “ከደቡብ ወደ ሰሜን ዘምቶ “ካልገዛኋችሁ!” ያለ አልነበረም” በማለት የ”ግራኝ ገዢነት እንዳልነበር ሲሸመጥጥ፣ ስለሰሜኖቹም ወደ ደቡብ የመዝመት ምክንያቱ ‹‹ክርስቲያኖቹ ሊገዙ የተፈጠሩ›› እንደሆኑ ማመናቸው አድርጎ ሲያቀርብ ሰውየው የሚናገረውን ነገር ያውቀዋል ወይ ያሰኛል፡፡

ወገናዊ አጻጻፍን የሚተች ርዕስ ለመጽሐፉ የሰጠው ታቦር፣ (የውገና ድርሰቶችና የታሪክ እውነቶች፣ ታቦር ዋሚ 2006) በዋናነት ስለገዳ የሚያወራውን የአባ ባህርይን ጽሑፍ ተስፋፊዎች የኦሮሞንና የደቡብን ግዛቶች በወረራ ሕጋዊ ለማድረግ (ኦሮሞዎች ከውጪ የመጡ ናቸው፣ አሁን ያሉበት መሬት ከ16ኛው ክፍለ ዘመን በፊት የእኛ ነበር ለማለት) በብዕር ስምና በታሪክ ስም ያዘጋጁት ተረት አድርጎ ይሰርዘዋል (ገጽ 128)፡፡ ዶ/ር ላጵሶ ድሌቦ ኦሮሞ በጠባብ ጎጥ ይኖር የነበረ፣ አዋማዊ እምነት የሚከተል ከብት አርቢ፣ ወዘተ ብሎ ስለመጻፉ ጠቅሶ ለጥላቻ ማስረጃ ያደርገዋል (136)፡፡ በንግሥተ ሳባ ታሪክ ላይ የተመሠረተውን ሰለሞናዊ ዘርነት ከነገሥታት ወደ ሕዝብ አሻጋግሮ “. . . ጥቂቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ የዕብራውያን ዘር፣ የተመረቁና የበላይ ሲደረጉ አብዛኞቹ ደግሞ የተረገሙና የበታች የተደረጉት ግብፃውያን በፈጠሩት የተረት ሰነድ . . . ” እያለ ጽፏል (187)፡፡ ገጽ 259 ላይ ያስቀመጠው ብያኔማ አተላላቁ! “ስለንግሥት ሳባ ታሪክ፣ ስለዮዲት፣ ስለጥንቱ የኢትዮጵያ ግዛት ስፋት፣ ስለዛጉዌ ነገሥታት አወዳደቅ፣ ስለ ይኩኖ አምላክ ሥልጣን ላይ መውጣት፣ ስለክብረ ነገሥትና ፍትሐ ነገሥት፣ ከዘርዓ ያዕቆብ እስከ አፄ ገላውዴዎስ ድረስ ስለነበሩ ነገሥታት ታሪክ፣ ስለኦሮሞ ሕዝብ ታሪክ፣ ስለኢትዮጵያን ሙስሊሞች ታሪክ፣ ስለፈላሻዎች ታሪክ፣ ወዘተ ያላንዳች ማስረጃ በደብተራዎች ተጽፈው በታሪክ ስም ሲተላለፉ የመጡ ተረቶች ናቸው፡፡” ሳያንጓልሉ ወደ ቆሻሻ ቅርጫት፡፡

ድርቢ ደምሴ የአማራን፣ የትግሬን፣ የጉራጌንና የሐረሪን ሴምነትና ኩሽነታቸውን ንቀውና ሰርዘው የሰለሞን (የእስራኤል) ወይም የዓረብ ዘር ነን ከማለት የመጣ ያደርጋዋል (Dirribi, Oromo Wisdom in Black Civilization 2011፤374)፡፡

የተዳፈኑ እውነቶች ደራሲዎች (መርዕድ ታዬና ደረጀ ጃገማ 2005) “ኢትዮጵያ” አቢሲኒያውን ከኩሾች የሰረቁት ታላቅ ስም ብለው ሲቆጩ (80-1)፣ ድሪቢ ደግሞ ግሪኮች ለማንቋሸሽ የሰጧቸውን “የተቃጠለ ፊት” የሚል ትርጉም ያለውን ባዕድ ስም የአገር መጠሪያ ማድረግ አሳፋሪ ነው ይለዋል (የተጠቀሰው፣ 379)፡፡ ግሪኮቹ ለማንቋሽሽ የሰነዘሩት ቃል መሆኑን፣ ጥቁረትን የሚገልጽ ቃልም “አሳፋሪ” መሆኑን ድሪቢ ነው የሚያውቀው፡፡ ያም ሆነ ይህ በብሉይ የሰው የዘር ሐረግ መሠረት የጥቁሮች ትውልድ ከካም ልጅ ጋር የተገናኘበትን “ኩሽ” ኢሃይማኖታዊ በሆነ ትርጓሜ እየተገለገሉ፣ የ“ኢትዮጵያ”ን ለአገር ስምነት መብቃት ጥቁርነትን በሚገልጽ ነባር ትርጉሙ ማራከስ፣ ወይም ስሜን ተነጠቅሁ የሚል ሌላ አገር በሌለበት፣ አንድ ሺሕ ተኩል ዓመታት በላይ ካለፈ በኋላ ተነስቶ ስለስም “ስርቆት” ማውራት፣ ምን ክፋት ልሥራ ካልሆነ በቀር ምን ሊሆን ይችላል!

“ኢቶፒስ” አክሱማውያኑን ጨምሮ ለአካባቢው አፍሪካዊያን የዋለ ስም እንደነበር ሁሉ፣ አክሱማውያን ከግሪኮች ጋር ቅርርብ ነበራቸውና መጠሪያውን ከቃል ልማድ ተቀብለው ወደ አገር መጠሪያነት አዙረውት ይሆናል፡፡ አክሱማውያኑ ብሉይ ኪዳንን የተረጎሙት የኢብራይስጡን “ኩሽ” ወደ “ኢቶፒስ/ኢቶፒያ” ከለወጠ የግሪክኛ ትርጓሜ ከሆነም (ጌታቸው ኃይሌ፣ አንዳፍታ ላውጋችሁ  2006፣ ገጽ 253) ከቃል ልምድ ባሻገር  ሃይማኖታዊ ምክንያትም ስሙን ለመጠቀም ያስቧቸው ይሆን ይሆናል፡፡ (በግሪክ የተጻፈው የኢዛና የድንጋይ ጽሑፍ ላይ የአክሱማዊያንን መንግሥት ለመግለጽ የዋለው ‹ኢትዮጵያ› በግዕዝ በተጻፉ የድንጋይ ጽሑፍ ላይ አለመደገሙ፣ የሐበሻ ንጉሥ መባሉ፣ (ተወልደ ትኩእ፣ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክ 2004 ገጽ 14-15)  አክሱማውያኑ ‹ኢትዮጵያ›ን በስምነት መጠቀም ገና መጀማመራቸው እንደነበር የሚጠቁም ይመስላል፡፡)

ሃይማኖትን መሠረት በማድረግ እነ “ደብረ ዘይት”፣ “ሆሳዕና” የሚባሉ የሥፍራ ስሞች በአገራችን ውስጥ እንደወጡ፣ ዛሬም ከእምነት ጋር በስሜት ለመቀራረብ ለልጆቻችን ከእምነት መጻሕፍቶቻችን ውስጥ ስሞች እንደምንመዝ፣ ተመሳሳይ ነገር ጥንት መደረጉ ምን ያስደንቃል!

ድርቢ ሃይማኖት መቀየር ማንነትን መቀየር ነው (51)፣ የሴም ሃይማኖቶች መስፋፋት ለኦሮሞም ለሐበሾችም ባርነት ነው (432፣434) ብሎ እስከ ማወጅ ፅንፍ ይሄዳል፡፡ በዚህም የክርስቲያንና የሙስሊም ኦሮሞነትን ጎደሎ ኦሮሞነት ያደርገዋል፣ ማለትም ወደ ኋላ ተመልሶ ታሪክን በማረም ይህንን የተጓደለ (የታጣ) ማንነት የማስተካከል ተግባር ይደቅናል፡፡ ለዋቄፈታ እምነት ያደረገው ከስብከት የማይተናነስ አሞካሽነትም የዚሁ የማንነት እርማት እንቅስቃሴ አካል መሆኑ ነው፡፡ የዋቄፈታ እምነትን መከተልም ማስፋፋትም ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው፡፡ ከዋቄፈታ ውጪ መሆንን ኦሮሞነትን ማጣት አድርጎ ማየት ግን አደገኛ ፅንፈኝነት ነው፡፡

በእሱ መንገድ ከተሄደ ከመካከለኛው ምሥራቅ የበቀሉትን የክርስትናና የእስልምና እምነቶች ዛሬ በአራቱም ማዕዘን የተቀበሉ የዓለም ሕዝቦች ሁሉ ማንነታቸው ጎድሏል ማለት ነው፡፡ ለእነሱ ምን ይመክር ይሆን? እስልምና በዓረቦቹ ውስጥ ጭምር የተስፋፋው ነባር እምነቶቻቸውን “ማንነታቸው”ን በስብከትም ሆነ በጎራዴ አስጥሎ ነው፡፡ ዓረቦቹስ ማንነታቸውን ለማስመለስ ወደ ጥንቱ ጣዖት አምልኮ ይመለሱ? የጥንቶቹም እምነቶች ከዓረብነት ጋር እንዳልተፈጠሩ ሁሉ ዋቄፈታም ከኦሮሞነት ጋር አብሮ አልተፈጠረም፡፡ ሁሉ ነገር ልውጠት አመጣሽ ነው፡፡ እና የት ጋ ነው ማቆሚያው?

የሚይዙ የሚጨብጡትን ያጡት የተዳፈኑ እውነቶች ደራሲዎች በአንድ በኩል ወደ ጠቢቡ ሰለሞን ሄደች የምትባለውን ንግሥት ከመረዌ የተገኘች ያደርጋሉ (ገጽ 38 -9)፡፡ በሌላ ጎን አቡጊዳ ከ”አቡገዳ”፣ አክሱም ከ”አካሱማ” ላሊበላ ከ“ኢላሊ በላ” ግንኙነት ሳይኖረው አይቀረም እያሉ ኦሮሞአዊ አሻራንና ቀደምት ነዋሪነትን እስከ ሰሜን ድረስ እያመለከቱ (154)፣ በተቃራኒው ሮማውያንን ጭምር ወክሎ በመረዌ ላይ ኢዛና ያካሄደው ወረራ “እስከ አሁን ያለ ከልጅ ልጅ የዘለቀና ማቆሚያ ያጣ ቁርሾ በሴማውያኑና በኩሻውያኑ መካከል እንዲኖር ምክንያት ሆነ” ይላሉ (85)፡፡ ድሪቢም አሰፋ ጃላታን ከጀርባው አድርጎ፣ ‹‹እኛ የኩሽ ሕዝቦች የራሳችን ሃይማኖት፣ ቀን አቆጣጠርና የአስተዳደር ሥርዓት አለን፣ … ራሳቸውን ነጭ ነን ከሚሉ ጋር የምንጋራው ታሪክም ሆነ የዘር አመጣጥ የለንም፡፡ እነሱ ‹እኛ ከእስራኤል ወይ ከዓረቢያ የመጣን ሴማዊያን ነን፣ የመጣነውም ጥቆሮችን ልንገዛ እንጂ ጥቁር አደለንም፣ ጥቁሮች እርጉምና ሰይጣን ናቸው› ይላሉ›› ብሎ ያውጃል፡፡ (ትርጉም የእኔ) (‘We do not have such a history and do not share common history and ancestry with the dependent that claim to be whites. They allegedly claim: ‘we are semitic and we came from Israel or Arebia, we came to rule over blacks but we are not blacks; blacks are evil and devil.’” (Dirribi 2011; 427-8)).

ይህ ‹አዋጅ›፣ “የአክሱም ሥልጣኔ መሠረት ከዓረቢያ የፈለሱ ሕዝቦች” እየተባለ ሲጻፍልንና ስንማር የኖርነው ታሪክ፣ በክርስትና እምነት ብሉይ ውስጥ የተነገረለት የእስራኤል ሕዝብ በእግዜር የተመረጠ መሆን የሚፈጥረው አዘንባይነት፣ የአፄዎች ከይሁዲዎች ጋር የዘር ሐረግ አለን ባይነት፣ እነዚህ አንድ ላይ በሴምም ሆነ በኩሽ ተናጋሪዎች ህሊና ላይ ያሳረፉትን ተፅዕኖ አንድ ላይ በሴሞቹ ላይ አነጣጥሮ ከኩሽና ከአፍሪካ ጋር የማቃቃር ያህል ጎጂ ነው፡፡ የማጋነንና መራራ የስሜት ሙላት እንደዚህ ዓይነት ጥፋት ውስጥ ይጥላል፡፡ ይህን መሰሉ መራራነት ለኦሮሞም ሆነ ለድሪቢ የሚበጅ ነገር አያስገኝም፡፡

ከውግዘትና ቂም ከመለፈፍ የማይርቁ ድምዳሜዎችን እየጠቀስን መደርደር እንቀጥል ብንል መጽሐፍ አይበቃንም፡፡ እነዚህን መሳይ አስተሳሰቦች በእንግሊዝኛና በአማርኛ ከመቅረብ አልፈው በፓርቲ አስተሳሰብነት ብቅ ለማለት ችለዋል፡፡ ውስጥ ለውስጥ እየተዛመቱ ህሊና ማሻከራቸውም አይቀርም፡፡ ከዚህ ቀደም የተፈጸሙ ግራ ያጋቡ ጭካኔዎችና ቁጣዎችም ከሚያቃቅሩ አስተሳቦች ጋር የተያያዘ ንክኪ እንዳላቸው መገመት አይከብድም፡፡ እነ ድሪቢ የዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ተቀባዮች እንጂ አመንጪዎች አይደሉም፡፡ የታሪክ ምርምር ባለሙያዎች ምን እስኪፈጠር እንደሚጠብቁ ግራ ይገባል፡፡

ዛሬ ሊገኙ በሚችሉ መረጃዎች የኢትዮጵያን ሰሜናዊና ደቡባዊ ሕዝቦች የታሪክ ተራክቦ አካሄድ በየፈርጁ በጥልቀት ተረድቶ መጻፍ በራሱ ከባድ ሥራ ሆኖ እያለ፣ በስሜታዊነት ጫፍና ግምት ይዞ መገምደል ከተጨመረ የረባ ፍሬ ማሳየት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከኢትዮጵያ የታሪክ ጉዳዮች ውስጥ እንደ ጦር የሚፈራውና ከሁሉም በበለጠ የመግባባት ችግር ያለበት የኦሮሞ ጉዳይ ነው፡፡ ኦሮሞ ቅኝ ውስጥ ነው የሚለው አመለካከት በታሪክ ጥናት ዘንድ እንድንቆጥር ማስቸገሩ ገና አልተቋረጠም፡፡ ቅኝ ገዢነት በተፈጸመባቸው ሥፍራዎች ውስጥ ቅኝ ገዢዎቹ ቅኝ ገዢነታቸውን ተጠራጥረው አያውቁም፡፡ ተገዢዎቹም ቅኝ ውስጥ ነን ወይስ አይደለንም የሚል ግራ መጋባትና ክርክር ተፈጥሮባቸው አያውቅም፡፡ በእኛ ሁኔታ ግን “ቅኝነቱ” የመነጠል ፖለቲካ የወለደው በመሆኑ አወዛግቧል፡፡ መነጠልን በማሳካት ዓላማ ታሪክ ተቆልምሟል፡፡

ታሪክ ቆልማሚዎቹና ቅኝ ተገዛን ባየቹ ምንም ቢሉ ግን ሕዝብ ውስጥ በቅኝ ገዢና በቅኝ ተገዢነት መፋጠጥ እንደምን እንደሌለ (በአንድ አገር ሰውነት ተያይቶ ለምን እንዲሚኖር)፣ ማርክሲስት ነን ከሚሉት አንስቶ እስከ ብሔርተኞች ድረስ በኢትዮጵያዊነት ቅጥር ግቢ ውስጥ የፖለቲካ ትግል ያደረጉበትና እያደረጉ ያሉበት ታሪክ በኢትዮጵያ እንዴት ሊከሰት እንደቻለ፣ ከቀደምት ክፍለ ዘመናት ጀምሮ እስከ ምኒልክና ኃይለ ሥላሴ ድረስ “ሰለሞናዊ” ነን የሚሉ “ቅኝ ገዢዎች” እንደምን ከ”ቅኝ ተገዢ” ጋር የተቀላቀለ ዘር ሊኖራቸው እንደቻለ፣ እንደምንስ “ቅኝ ተገዢዎቹ” የየጁ መሳፍንት በ“ቅኝ ገዢዎቹ” ሥልጣነ መንግሥት ላይ የክፍለ ዘመን ሦስት ሩብ ያህል ሊገዙ እንደቻሉ፣ በተወሰኑ አወቅን ባዮች ኦሮሞዎች ውስጥ የሚሽከረከረው ይህ ዓይነቱ የቅኝ ተያዝን አስተሳሰብ ለምን በሲዳማ፣ በሐድያ፣ በከምባታ፣ በወላይታ፣ በአፋር፣ ወዘተ ትምህርት ቀመሶች ዘንድ ሥር እንደሌለው፣ በአጠቃይ በቅኝ ገዢና ተገዢ መሀል ሆኖ የማውያቅ ነገር ለምን በኢትዮጵያ እንደሆነ ማስረዳት አይችሉም፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን የገዢነትና የተገዢነት ታሪክ ሳያዛቡ የማቅረብ ተግባር የትኛውንም የፖለቲካ ሙሌትና አጥር ማለፍን ይጠይቃል፡፡ ታሪክ ለመጻፍ ብዕር ባነሱ ቁጥር፣ ኦሮሞ ከየት እንደመጣ የማሳመን ጥያቄ ዛሬ ያለ ይመስል፣ ከእስያ/ማደጋስካር፣ ከወደ ባሌ፣ ወዘተ በሚሉ ጉዳዮች ላይ መሽከርከር፣ በዘለፋዎች እየበገኑ እነ አባ ባህርይ፣ አለቃ ታዬና አለቃ አፅሜ፣ ወዘተ ላይ ወገራ ማካሄድ ያታከተ ነገር ሆኗል፡፡

ኦሮሞ ከውጭም ሆነ ከባሌ መጣ ባይነትና የአባ ባህርይ ድርሰትን የኦሮሞን መብት ለመንሳት የተቀናበረ ሴራ በማድረግ እየተደጋገመ የሚወረወር ክስ ከጥንቆላ አይሻልም፡፡ የአባ  ባህርይን ድርሰት የከፈተ ሰው የሚያገኘው ሴራ ሳይሆን የ16ኛውን ክፍለ ዘመን የኦሮሞን ግዙፍ እንቅስቃሴ ጥቃቴ ብሎ ያረረ መነኩሴን ነው፡፡ ያውም ብሽቀትና ዘለፋ እያፈተለከበትም ቢሆን ስለኦሮሞ ሥርዓተ ኑሮ የሚተርክ፡፡ በመዝሙሩም ሰርፀ ደንግል አኀዛብን ሁሉ ይገዛ ዘንድና የጭንቅ ሞገድ ፀጥ እንዲል የሚለምን መሆኑ (ጌታቸው ኃይሌ፣ የአባ ባህርይ ድርሰት 1997፤ ገጽ 40) በሰርፀ ድንግል ዘመን የተጻፈ ነው ብሎ ለመገመት የሚያስችል ነው፡፡ ኦሮሞ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን በፊት በመሀል ኢትዮጵያ “ለመኖሩ” ማስረጃ እንዲሆን በቅርብ ዘመን የተቀናበረ ሰነድ አድርጎ መፍረድም የሚያስገኘው ትርፍ የለም፡፡ ምክንያቱም ከ16ኛው ክፍለ ዘመን በፊት ኖሬ ነበር ባይነት መብት እንደማያስመልስ ሁሉ፣ ከ16ኛ ክፍለ ዘመን ጀምሮ መኖር ባለመብትነትን አይቀንስም፡፡ የአባ ባህርይ ድርሰት ናፒየር እጅ የገባበትን (የተጠቀሰው፣ ጌታቸው ኃይሌ ገጽ 36፡፡) 19ኛ ክፍለ ዘመን የተጻፈበትም ጊዜ አድርገን ብንወስድ እንኳ ይቅርና በዚያ ጊዜ እነ አለቃ ታየ ስለኦሮሞ በጻፉበት ወቅትም “ሴራ” የሚያሳስብ የኦሮሞ የመብት (የነፃነት) ጥያቄ አልነበረም፣ ትንቢት ታያቸው ካልተባለ በቀር፡፡ በዚያ ላይ ምኒልክ ወሮ የተቆጣጠረው ብዙ ሕዝቦችን እንደመሆኑ ኦሮሞን ለይቶ ከውጭ መጣ ወይም ከ16ኛ ክፍለ ዘመን በፊት በመሀል ኢትዮጵያ አልነበረም የሚያስብል የሴራ ሰነድ ለማዘጋጀት የሚያበቃውን ምክንያት፣ ከዚህም የሚገኘውን የፖለቲካ ጥቅም ቁልጭ አድርጎ ማስቀመጥ ይገባል፡፡

መውጫ የሌለው የዚህ ዓይነት ተንኮል አነፍናፊነት ውስጥ ከመትረክረክ ይልቅ እርባና ያላቸውን ማስረጃዎች በመልቀም ላይ ማተኮር ያስፈልጋል፡፡ መሐመድ ሐሰን አባ ባህርይን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅሟል፡፡ (Mohammed Hassen፣ 1994 The Oromo of Ethiopia a History 1570-1860)  ስለገዳ በማጥናት ረገድ ልዩ ሥፍራ ያለው አስመሮም ለገሰ በዘለፋ ሳይጋረድ “ኦርጅናሌ (በቀጥተኛ ግንዛቤ የተገኙ) የሚመስሉ” መረጃዎችን አጢኗል (Asmarom 2006፤ Oromo Democracy 99)፡፡ በዚያው ገጽ ላይ ደ’ ኣባዲ (d’ abbadie) እና አፅሜ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማለቂያ ላይ የመዘገቡት በ20ኛው ክፍለ ዘመን ቦረና ውስጥ ከታየው ጋር ተመሳሳይ ስለመሆኑ መስክሯል፡፡ ስለኦሮሞ የውጊያ ሥልት አባ ባህርይ የሰጠውን ምስክርነትም “እጅግ ሁነኛው ማስረጃ” ብሎ ይገልጸዋል (46)፡፡ እሸቱ ኢረና አንዳች ስሜታዊ ንቁሪያ ውስጥ ሳይገባ ኦሮሞ ከ16ኛ ክፍለ ዘመን በፊት በመካከለኛው ኢትዮጵያ እንደነበር ለማሳየት ከአለቃ ታዬ መረጃ ወስዶ ለመጠቀም ችሏል፡፡ (እሸቱ ኢረና የኦሮሞ ታሪክ ከጥንት – 1890 መጨረሻ  2001፣ 41-2)

ከዚህ እስከዚህ ግዛቴ ብሎ በድንበር መገደብ ባልነበረበት፣ ፍላጎትና የኃይል ብልጫ እስከተገናኙ ድረስ ይዞታ ማስፋት በነበረበት ጊዜ የሆነውን ሁሉ በዛሬ ብሔረተኛ ብሌን “ነፃ ግዛት”፣ “ነፃነት”፣ “የቅኝ ወረራ” እያሉ መግለጽ ሌላ ማነቆ ነው፡፡ “የ16ኛ ክፍለ ዘመን የኦሮሞ እንቅስቃሴ ቀድሞ በወረራ የተያዘበትን ሥፍራ እንደገና የማስመለስ የነፃነት እንቅስቃሴ ነበር” ባይነትም (አባገዳ ወርቅነህ ገዳ ሥርዓትና የተደበቀው የኦሮሞ ሕዝብ ታሪክ፣ (2003) ታቦር (2006) ወዘተ) ታሪክን በትክክለኛ ገጹ የማያሳይ ከሓርነት ትግል የተወለደ ፖለቲካዊ ሥሌት ነው፡፡ መሐመድ ሐሰን በትክክል እንደገለጸው፣ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የኦሮሞ በገፍ ወደ ላይ መንቀሳቀስ በክርስቲያናዊና በእስላማዊ መንግሥታት በጦርነት መጠፋፋት ምክንያት መንገድ የቀናው ክስተት ነው (Mohammed  1994፡20) ፡፡ ግስጋሴው “የቀድሞ ይዞታ በማስመለስ” የተገደበ አልነበረም፡፡ እናርያን ወግቷል (49)፡፡ አጋጅ ባጣበትና ሊያግዱ የሞከሩትን በኃይል በበለጠበት ሥፍራ ሁሉ በየአቅጣጫው ትግራይ ድረስ ተሠራጭቷል፡፡ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ወረራ ኦሮሞ ከቦታው ተነቅሎ ባሌ ድረስ እንደተገፋ ሲወራም ለምን በነበረበት እንዲገብር ሳይደረግ እንደቀረ፣ በሥፍራው ማን እንደተተከለና እነ ሐድያ፣ ወላይታ፣ ከምባታ፣ ወዘተ የት እንደነበሩ/ከየት እንደመጡ ወይም ለምን በነበሩበት እነሱ እንደቆዩ ማስረዳት ግድ ይላል፡፡

ኦሮሞ ከ16ኛ ክፍለ ዘመን በፊት ሸዋ ላይ እንደነበር ለማስተማመን ይደረግ የነበረውም ክርክራዊ ርብርብ የኦሮሚያ ካርታን የመቅረፅ ፖለቲካዊ ሥራ ነበር፡፡ የተሟላ የታሪክ ጥናት እነዚህን ከመሳሰሉ ፖለቲካዊ ሒሳቦችም ሆነ ከደረቁ አሮጌ እሳቤዎች ወጥቶ በሰፊው ዓይንን መክፈት፣ ከደቡብ እስከ ሰሜን መረጃዎችን መፈለግ፣ የአርቢነት፣ የአራሽነትም ሆነ የገዢነት ገጽታዎችን ከነ መስተጋብራቸውና ትሩፋታቸው መመርመር ይጠይቃል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...