የጋምቤላ ክልል መንግሥት በገቡት ውል መሠረት አላለሙም በማለት የ269 ኢንቨስተሮችን መሬት መንጠቁ ተቃውሞ በማስነሳቱ፣ ጉዳዩን በድጋሚ ለማጣራት 13 አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቋመ፡፡
ቅዳሜ ግንቦት 5 ቀን 2009 ዓ.ም. በጋምቤላ ከተማ በተካሄደው ስብሰባ ከክልሉ መንግሥት፣ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ ከኢትዮጵያ ሆርቲከልቸርና ግብርና ልማት ባለሥልጣን፣ እንዲሁም ከጋምቤላ ክልል የእርሻ ኢንቨስተሮች ማኅበር የተውጣጣ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡
ኮሚቴው የእርሻ ኢንቨስተሮቹን የሥራ እንቅስቃሴ ያለበትን ደረጃና ያላለሙ ኢንቨስተሮች በምን ምክንያት ሊያለሙ እንዳልቻሉ ከመረመረ በኋላ፣ ለክልሉ መንግሥትና በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለሚገኘው የኢኮኖሚ ዩኒት ሪፖርት አድርጎ ውይይት እንደሚደረግበት ታውቋል፡፡
በጋምቤላ ክልል የተንሰራፋውን ችግር ለመፍታት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ተጠንቶ ሰኔ 2008 ዓ.ም. የቀረበውን ሪፖርት፣ የጋምቤላ ክልል መንግሥት ፕሬዚዳንት የካቲት 2009 ዓ.ም. በ269 ኢንቨስተሮች ላይ የወሰዱትን ዕርምጃና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጥር 2009 ዓ.ም. ለሰፋፊ እርሻዎች ብድር የሚሰጥበትን አዲስ መመርያ የጋምቤላ ክልል የእርሻ ኢንቨስተሮች በግዮንና በካፒታል ሆቴሎች በተካሄዱ ስብሰባዎች፣ እንዲሁም በተገኘው መድረክ ተቃውመዋል፡፡
ከኢንቨስተሮቹ በኩል ጠንከር ያለ ተቃውሞ የገጠመ በመሆኑ፣ ችግሩን ለመፍታት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሥር በዶ/ር አርከበ ዕቁባይ የሚመራው የኢኮኖሚ ዩኒት ጉዳዩን እንዲፈታ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡
ዶ/ር አርከበ በእርሻ ኢንቨስትመንት ያለውን ችግር ለመፍታት 20 አባላት ያሉት ኮሚቴ ያቋቋሙ ሲሆን፣ ይህ ኮሚቴ በፋይናንስና በተለይ ኢንቨስተሮቹ በብዛት በሚያመርቱት የጥጥ ግብይት መስክ ያለውን ችግር ለመፍታት የተለያዩ ዕርምጃዎች በመውሰድ ላይ ይገኛል፡፡
በመሬት ይዞታ ላይ ያለውን ችግር ለመፍታት ደግሞ በጋምቤላ ክልል መንግሥት ኃላፊነት 13 አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሞ፣ የመጀመሪያ ስብሰባውን በማካሄድ ማጣራቱን ጀምሯል፡፡
ኮሚቴው እስካሁን በደረሰባቸው ግኝቶች ላይ ዓርብ ግንቦት 11 ቀን 2009 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ውይይት ማድረጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በጋምቤላ ክልል በእርሻ ኢንቨስትመንት የተንሰራፋውን መጠነ ሰፊ ችግር ለመፍታት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኮሚቴ አደራጅቶ ጥናት በማስጠናት ሰኔ 2009 ዓ.ም. ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
በተካሄደው የግብርና ኢንቨስትመንት ጥናት ላይ በመመሥረት ባለሀብቶችን በደረጃ በመፈረጅ ውጤታማ የሆኑትን የማበረታታት፣ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን የመደገፍና ልማት ላይ ባልሆኑት ደግሞ የማስተካከያ ዕርምጃ መወሰድ እንዳለበት ታምኗል፡፡
በዚህ መሠረት በመሬት ልማት፣ በካምፕ አደረጃጀት፣ በእርሻ መሣሪያና በሥራ ዕድል ፈጠራ በተሰኙ መመዘኛዎች 451 ባለሀብቶች ተመዝነው 49 በጣም ጥሩ፣ 38 ጥሩ፣ 68 መካከለኛ፣ 1 አጥጋቢ፣ 27 ደካማ፣ 269 ደግሞ በጣም ደካማ ተብለው ተፈርጀዋል፡፡
በዚህ መሠረት በክልሉ መንግሥትና በሚመለከተው የፌዴራል ግብርና ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ በኩል በጣም ጥሩ ከተባሉት ሃያ ማበረታቻ፣ 68 የመጀመሪያ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ 27 የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ እንዲሁም ደካማ ተብለው የተፈረጁት 269 ባለሀብቶች ውላቸውን በማቋረጥ ያላለሙትን መሬት የመንጠቅ ዕርምጃ እንዲወሰድ በጥናቱ ላይ ተቀምጧል፡፡
በዚህ መሠረት የጋምቤላ ፕሬዚዳንት አቶ ጋትሉዋክ ቱት በ269 ኢንቨስተሮች ውል በማቋረጥ ዕርምጃ ወስደዋል፡፡
ነገር ግን የጋምቤላ ኢንቨስተሮች ከመሠረቱ ጥናቱ ሙሉ ያለመሆኑንና በባለሀብቶች ላይ ያለውን ችግር ያላገናዘበ ነው በማለት ተቃውመውታል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተጠናው ጥናትም ቢሆን በመሬት የይዞታ ካርታ መደራረብ በመኖሩ ባንኮች የፈቀዱትን ብድር እንኳ ያለመልቀቃቸው፣ በጋምቤላ ክልል አመራሮች የሚታይ የመልካም አስተዳደርና ኪራይ ሰብሳቢነት መኖሩ፣ በክልሉ ከፍተኛ የእርስ በርስ ግጭትና አለመረጋጋት፣ የሰላም ዕጦት፣ የአካባቢው ኅብረተሰብ ተጠቃሚነት የሌለና ሥርዓት አልበኝነት የተንሰራፋ መሆኑ ተገልጾ እያለ፣ ለእርሻ ሥራ መቻኮል አግባብ አይደለም በማለት ኢንቨስተሮቹ ተቃውመዋል፡፡
የጋምቤላ ክልል መንግሥት ዕርምጃ ከወሰደ በኋላም የኢንቨስተሮቹ ተቃውሞ የቀጠለ በመሆኑ፣ መንግሥት ዘግይቶም ቢሆን ተቃውሞውን በመስማት በድጋሚ ማጣራት እንዲደረግ ወስኗል፡፡
ሪፖርተር ባለፈው ዓርብ ሌሊት ማተሚያ ቤት እስከገባበት ድረስ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ስብሰባ በመቀመጣቸው አስተያየታቸውን ማካተት አልቻለም፡፡ ይሁንና የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ጋትሉዋክ ጉዳዩ ያልተቋጨ በመሆኑ አስተያየት ከመስጠት እንደሚቆጠቡ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡