Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቡና አምራቾች ይዘንና ዘመናዊ ገበያ አቋቁመን ከፍና ዝቅ ማለታችን ተቀባይነት እንደሌለው ደምድመናል››

አቶ ኤርሚያስ እሸቱ፣  የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ለመፍጠር ታስቦ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በዋናነት የቡና ግብይትን በማከናወን ይታወቃል፡፡ የኤሌክትሮኒክስ ግብይትን በማስረፅ ተጠቃሽ ሆኖ እየሠራ ያለው ይህ ተቋም፣ ወደ ዘጠነኛ ዓመቱ እየተሸጋገረ ነው፡፡ የቡናን ያህል አይሁን እንጂ እንደ ሰሊጥ ያሉ ሌሎች ምርቶችን በዚህ ግብይት ሥርዓት ውስጥ እንዲያልፉ እያደረገ ነው፡፡ መንግሥት የተሻለ የቡና ምርትና  የቡና ግብይት ሥርዓት ለመዘርጋት ያስችላል የተባለውን ‹‹የቡና ሪፎርም›› በማድረግ ላይ ነው፡፡ ከሰሞኑ ግን ይህ ‹‹ሪፎርም›› የምርት ገበያውን ህልውና ይነካል ተብሎ አስተያየቶች ከየአቅጣጫው እየተሰሙ ነው፡፡ ይህ ሪፎርም የምርት ገበያውን ህልውና ይነካል የሚለውን በተመለከተ፣ ምርት ገበያው እያደረጋቸው ስላሉ እንቅስቃሴዎች፣ እንዲሁም ተቋሙን የሚመለከቱ ሌሎች ጉዳዮች ላይ በመንተራስ ዳዊት ታዬ የኢትዮጵያ ምርት ገበያን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት እየመሩ ያሉትንና በዚህ የኃላፊነት ቦታ ከሁለት ዓመት ተኩል በላይ የቆዩትን አቶ ኤርሚያስ እሸቱን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ለማስፈን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተቋቋመ ወደ ዘጠኝ ዓመታት እየተቆጠሩ ነው፡፡ እርስዎ ደግሞ ይህንን ተቋም በመምራት ከሁለት ዓመት ተኩል በላይ ቆይተዋል፡፡ ኃላፊነቱን ከተረከቡ በኋላ ምን ተከናወነ? ምንስ ተሠራ ብለው ያምናሉ? ለውጦች አሉ?

አቶ ኤርሚያስ፡- በቆየሁባቸው ጊዜያት ውስጥ ከቀን ወደ ቀን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የነበሩና የተከማቹ የቆዩ አሠራሮችን ዘመናዊ የማድረግና ሥራውም በሙሉ ገጽታው እየተስተካከለ ሄዷል፡፡ በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ መቶ በመቶ ግብይቱን ወደ ኤሌክትሮኒክ የግብይት ማዕከል አሸጋግሯል፡፡ የዚህ ዓላማው ከግብይት ሥርዓቱ ጋር ተያይዞ እጅ በእጅ መነካካቱ የሚያመጣቸው ብዙ ክፍተቶች፣ ልዩነቶችና አምባጓሮዎች መቶ በመቶ አፅድተን እየሄድንበት ነው፡፡ ለምሳሌ በፊት በዓመት የግብይት ወቅት ውስጥ እስከ አንድ ሺሕ የሚደርሱ ክሶች ወይም የሕግ ክፍተቶችን እንመረምር ነበር፡፡ አሁን ግን ይህ በጣት በሚቆጠር ጉዳዮች ወርዷል፡፡ ምክንያቱም ግብይቱ መቶ በመቶ በጣት አሻራና በፊርማ ስለሚያልፍ፣ በፊት ለክርክርና ለምርመራ የሚያጋልጡትን ሥርዓቶች እየፈታን ሄደናል፡፡ በተመሳሳይ የክፍያና የሥልጠና ሥርዓቱ ወደ ዘመናዊ ግብይት የማስገባቱ ሒደትም በተጠናከረ ሁኔታ ቀጥሏል፡፡ በፊት በግልጽ ገበያ ላይ የመጨባበጥ ልምድ የነበረው ገበያ ፈጻሚ፣ አሁን ሠልጥኖ ‹ሰርቲፋይድ› ሆኖ መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ በኤሌክትሮኒክስ ገበያ የመገበያየት አቅም ገንብተናል፡፡ ሌሎች በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ከሁለት ዓመታት ወዲህ ወደ ሰባት የሚሆኑ ግንባታቸውን እያካሄድን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት ግንባታዎችን ነው ያካሄዳችሁት?

አቶ ኤርሚያስ፡- የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ማዕከሎች ናቸው፡፡ ግንባታው ክልሎችን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ በሐዋሳ፣ በነቀምትና በሁመራ የጀመርናቸውን የኤሌክትሮኒክ ግብይት መፈጸሚያ ማዕከሎች መቶ በመቶ ግንባታዎችን አጠናቀን ግብይቱን ለመጀመር እየተዘጋጀን ነው፡፡ በጅማ፣ በአዳማና በጎንደር ደግሞ የኤሌክትሮኒክ ግብይት መፈጸሚያ የማዕከሎቹ ግንባታዎች በማገባደድ ላይ ናቸው፡፡ የእነዚህ ማዕከሎች ግንባታና ሥራ መጀመር ወደ ክልሎች ያለንን ተደራሽነት ይጨምረዋል፡፡ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ገበያ ለመፈጸም ያለውን ውጣ ውረድ በተወሰነ ደረጃ ያስቀራል፡፡ ምርቱ ከሚገኝበት ቦታ በቅርብ ገበያውን ለመፈጸም ያስችላል፡፡ ከዚህ ባሻገር በምርት ገበያችን ብዙ የውጭና የውስጥ አሠራሮችን የፈተሽንበትና ማሻሻያዎችን ያደረግንበት ጊዜ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ የሚመሩትን ምርት ገበያ እንዲህ ቢገልጹትም ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚሰነዘሩት ግን የምርት ገበያው እንቅስቃሴ ስለመዳከሙ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አጠቃላይ የቡና ግብይትንና ከቡና ጋር የሚያያዙ ጉዳዮችን ለመለወጥ የተጀመረው ‹‹የቡና ሪፎርም›› የኢትዮጵያ ምርት ገበያን አሠራር ያዳክማል፣ ይቀይራል እየተባለ ነው፡፡ የቡና ሪፎርሙና የእናንተ ጉዳይ ምን ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል? እንደሚባለው በትክክል ሪፎርሙ የምርት ገበያውን ቅርፅ ይለውጣል?

አቶ ኤርሚያስ፡- እንግዲህ በአንዳንድ ሚዲያዎች ሲጻፍና አንዳንድ ሰዎች ሪፎርሙን ሲሰሙ የሚሰጡት አስተያየት ላይ መሠረት የተደረገ ሊሆን ይችላል እንጂ፣ ምርት ገበያው የሚዳከምበትና የተዳከመበት ሁኔታ የለም፡፡ መንግሥትም ከጊዜ ወደ ጊዜ ዘመናዊ የገበያ መድረክ ሆኖ የሚቀጥል መሆኑን የሚያውቀው ነው፡፡ በአገር ደረጃ ትልቅ እሴት ይሆናል የሚል እምነት ነው ያለው፡፡ በፖሊሲ ዙሪያም ያለው ይህ ነው፡፡ እርግጥ አሁን ቡና ከፍተኛ ሪፎርም ላይ ነው፡፡ ሌሎች ሪፎርም የሚፈልጉ ወደዚያ ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ምርት ገበያው አንድ ዘመናዊ የገበያ መድረክ ነው የሚለውም ነገር መዘንጋት የለበትም፡፡ ኅብረተሰቡ የሚፈልጋቸውን የምርት ዓይነቶች ቆም ብለህ ብታይ፣ ጤፍ ምርት ነውና ይፈለጋል፡፡ ዘይት፣ ስኳርና የመሳሰሉ በርካታ ምርቶችም አሉ፡፡ እነዚህ በዘመናዊ የገበያ ሥርዓት ውስጥ እስካልገቡ ድረስ ሁልጊዜ  በምንሰማቸው ችግሮች ውስጥ ያልፋሉ፡፡ ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡ የምርት ብልሽት፣ ጥራት፣ ደረጃና እጥረት የመሳሰሉት የሚቀረፉት ዘመናዊ ገበያ በሚኖርበት ጊዜ ነው፡፡ ጅምላ ንግዱን ወይም የመጀመሪያ ደረጃ ገበያውን ከሁለተኛ ደረጃ ገበያው የሚያገናኝ ድልድይ ነው፡፡ ስለዚህ የዘመናዊ ገበያን ጠቃሚነት ቆም ብሎ ማየት ያሻል፡፡ ሪፎርሙ ምርት ገበያውን የሚያዳክምና የሚያፈራርስ ሳይሆን ገበያው ለአርሶ አደሩ የተለያዩ አማራጮችን የሚከፍት ነው፡፡ በዚህ አማራጭ ውስጥ የምርት ገበያው አንዱና አንኳር አማራጭ ሆኖ ተወዳዳሪ ሆኖ ይቀርባል፡፡ ምርት ገበያውን የሚያሳንስ ነገር ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡

ሪፖርተር፡- ሪፎርሙ ምርት ገበያውን ተወዳዳሪ ያደርገዋል ሲባል ምን ማለት ነው? ሌሎች ተመሳሳይ ሥራ ሊያከናውኑ የሚችሉ ይኖራሉ ማለት ነው?

አቶ ኤርሚያስ፡- ሌላ ተቋማት ይኖራሉ ማለት ሳይሆን፣ አርሶ አደሩ በሌሎችም አማራጮች ምርቱን የመሸጥ ዕድል ይኖረዋል፡፡ ለምሳሌ አንድ አልሚ ምርቱን ኤክስፖርት ማድረግ ቢፈልግ፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ውስጥ ሳይገባ በቀጥታ ለዓለም አቀፍ ገዥ የመሸጥ ዕድል ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ በተመሳሳይ ከአልሚም አንድ ደረጃ ተሂዶ ሥርዓቱን የሚያሟላ አቅራቢ ቢሆንና አዋጭ ሆኖ ካገኘውና ያንን የኤክስፖርት ወጪውን ሸፍኖ ኤክስፖርት ለማድረግ አቅም ካለው፣ ያንን ገበያ የሚያገኝበት ሁኔታ ካለም ይህም አማራጭ ይኖራል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በምርት ገበያ የሚመጡት የምርት ዓይነቶችና መጠኖች ይኖራሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ አማራጭ ገበያ እንዲያገኙ ዕድል ይፈጥራል፡፡ ለምሳሌ በቡና ሪፎርም ላይ በአትኩሮት እየሠራን ያለነው፣ የኢትዮጵያ ቡና በጣም ጥራት ያለው ከመሆኑ የተነሳ፣ በስፔሻሊቲ ገበያ ላይ ለመወዳደር ከፍተኛ ዕድል አለው፡፡ ነገር ግን ዕድሉን መጠቀም አልቻለም፡፡ ያልቻለበትን ምክንያት ወደ ውስጥ ገብተን መንዝረን ስንመለከተው፣ ከሌሎች የቡና ሪጅኖች የሚመጡ ቡናዎች ምርት ገበያ ውስጥ ገብተው ስለሚቀላቀሉ ነው የሚል እንደ ምክንያት ተነስቷል፡፡ አሁን የሁሉንም ቡና አመጣጡ እንዲታወቅ የሚል አንድምታ አለን፡፡ ስለዚህ ሁሉም ቡና እንዲህ ሆኖ እንዲሸጥ ሪፎርሙ ያስገድዳል፡፡ በተመሳሳይ  ስፔሻሊቲ ቡና ስላለኝና በጣም ጥሩ ዋጋ ስለማገኝ ቀጥታ ኤክስፖርት ማድረግ እችላለሁ ካለ፣ ጥሩ ዋጋ የሚባለውን መነሻ አስቀምጦ ወደ ውጭ ገበያ እንዲያገበያይ ዕድል የመፍጠር ሁኔታ ይኖራል ማለት ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ስለዚህ እዚህ ስፔሻሊቲ የሚባለው ምርት ላይ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ምንም ዓይነት አስተዋጽኦ የለውም ማለት ነው?

አቶ ኤርሚያስ፡- ምንም ሚና አይኖረንም፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ መሠረት በሪፎርሙ መሠረት ከቡና ግብይት ጋር ተያይዞ እናንተም የተለየ አሠራር ይኖራችኋል ማለት ነው? እናንተ የማታገበያዩት ቡና አለ ማለት ነው?

አቶ ኤርሚያስ፡- ትክክል፡፡

ሪፖርተር፡- ግን በእናንተ በኩል የሚያልፈው የቡና ምርት መጠን ምን ያህል ይሆናል? ስፔሻሊቲ ተብሎ ሊላክ የሚችለውስ?

አቶ ኤርሚያስ፡- በጣም ትንሽ ነው፡፡ የዓለም ገበያን በምንመለከትበት ጊዜ በጣም ጠንካራ ተወዳዳሪነትን ይሻል፡፡ ገበያ ከፍተኛ የአደጋ ሥጋትን የመሸከም አቅምን ይሻል፡፡ እንድንወዳደር ያስገድደናል፡፡ ስለዚህ አማራጭ መኖሩ አንዳንድ ጊዜ ወደ ኮንትሮባንድ እንዳይገባ ያግዛል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሳይፈልጉ ባልሆነ ዋጋ እንዲሸጡ የሚያስገድደውን አጋጣሚ ማጥፋት እንፈልጋለን፡፡ እንደ አማራጭ ያንን በር መክፈቱ ለአርሶ አደሩ ወይም አቅም ላላቸው ጥሩ በር ይከፍታል፡፡ ግን በስኬል ስታየው እንዲህ ባለው ዓለም ቀፍ ፕሮቶኮል ውስጥ ለመወዳደ በአሥር ጆንያ ገበያ ከተገኘ ስፔሻሊቲ ስለሆነ እሰየው ነው፡፡ በኮንቴይነር ካላደረግክ አያዋጣም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በጥቃቅን ደረጃ ውድድር እንዲኖር በር ይከፈታል ማለት ነው፡፡ እዚህም ላይ አቅም ያላቸው ተወዳዳሪዎች እንዲፈልቁና ሕገወጥ አሠራሮች እንዲቀሩ ያደርጋል፡፡ በመጠን ደረጃ  በቀጥታ ይላካል ተብሎ የሚገመተው ከአምስት እስከ አሥር በመቶ የማይበልጥ ነው፡፡ ግፋ ቢል 15 በመቶ ቢሆን ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- በምርት ገበያው በኩል ሳይሆን በቀጥታ ምርቶቻቸውን መላክ የሚችሉት ስፔሻሊቲ ተብለው የሚለዩት ብቻ ናቸው? ወይስ ከስፔሻሊቲ ውጪ ያሉ የቡና ምርቶች በቀጥታ ሊላኩ ይችላሉ?

አቶ ኤርሚያስ፡- እኛ የዚህን ጥናታችንን አካሄድ ስንመለከተው በቀጥታ ኤክስፖርት ማድረግ ያዋጣል ተብሎ የሚታመነው ስፔሻሊቲ ያላቸው ቡናዎችን ነው፡፡ ምክንያቱም ስፔሻሊቲ እጥፍ ድርብ የሆነ ዋጋ አለው፡፡ ጥራት ያለው የኢትዮጵያ አንድ ኪሎ ቡና በ20 ወይም በ30 ዶላር ሊሸጥ ይችላል፡፡ እኛ ደግሞ እያየን ያለነው ከዚህ የበለጠ ነው፡፡

ሪፖርተር፡-፡- ከዚህ የበለጠ ሲሉ?

አቶ ኤርሚያስ፡- ከዚህ የበለጠ ያየነው ያቺ ቡና ተቆልታ እንድትሸጥ እንፈልጋለን፡፡ ስፔሻሊቲው ሳይሆን ኖርማል የሚባለው የኢትዮጵያ ቡና ጥራቱን ጠብቆ ተቆልቶ ኤክስፖርት ቢደረግ፣ አንዱን ኪሎ የተቆላ ቡና እስከ 40 ዶላር ድረስ መሸጥ ይቻላል፡፡ ስለዚህ ታች ላይ በሩ ቢከፈት መጠኑ አምስትና አሥር በመቶ መሆኑ ሳይሆን፣ ከስፔሻሊቲ ቡና ዓይነት ውጪ በአማካይ የምናገኘው ሦስት ዶላር ነው፡፡ አሥር በመቶ መጠን አለው የምንለው ቡና እስከ 40 ዶላር ድረስ መሸጥ ይቻላል፡፡ ከዚህ አንፃር አሥር በመቶው እንኳ ቢወጣ 90 በመቶው ጥሬ ቡና ከሚያመጣው፣ የተቆላው ቡና ተወዳዳሪ የሚሆን የውጭ ምንዛሪ ሊያመጣልን ይችላል፡፡ ስለዚህ ምርት ገበያው አማራጩ አሁንም አለው፡፡ ግዴታ አይደለም፡፡ ከፈለገ ራሱ ካልፈለገም በምርት ገበያው ላይ ቡና ሊያመጣ ይችላል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም በአማራጭ የሚደረገው ግብይት እሴት ከመጨመርና የውጭ ምንዛሪ ከማስገኘት ባሻገር፣ በቡና ጥራት ላይ እንድንወዳደር በር ይከፍትልናል፡፡ እታች አርሶ አደሩ ለጥራት እንዲተጋም ያበረታታል፡፡ ቡናን ቆልቶና ፈጭቶ ለመላክ የሚያስችል ሰፊ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ አሁን እኮ ይህንን ሥራ ለመሥራት ወደ አምስት የሚሆኑ ኩባንያዎች ፈቃድ ወስደዋል፡፡ ይህ የሆነው በዚህ በሪፎርም ዝግጅት ወቅት ነው፡፡ ሌሎችም ለመግባባት እየተዘጋጁ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ትልቅ ጉዳይ የበለጠ እያሰብንበት ነው፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ደግሞ ለመጀመርያ ጊዜ ኤክስፖርት ስታንዳርድ የሆነ ቡና ከምርት ገበያው እዲገዙ ተፈቅዷል፡፡ ይህ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡

ሪፖርተር፡-፡- ከገለጻዎት መረዳት የቻልኩት ከሰሞኑ በተለያዩ አቅጣጫዎች እየተሰማ እንዳለው በአዲሱ ሪፎርም ምክንያት ምርት ገበያው ይፈርሳል የሚባለው ነገር ትክክል አይደለም?

አቶ ኤርሚያስ፡- በፍፁም ትክክል አይደለም፡፡ እስካሁን ምርት ገበያው የማያገበያየው  አሥር በመቶ የማይሞላውን ቡና ነው፡፡ እንዲያው ቢበዛ 15 በመቶ ድረስ ሊሄድ ይችላል፡፡ አብዛኛው ቡና አሁንም በእኛ በኩል ነው የሚገበያየው፡፡

ሪፖርተር፡- የእናንተን ደጃፍ ሳይረግጡ በቀጥታ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡትን ስፔሻሊቲ ቡናዎች በትክክል ስፔሻሊቲ መሆናቸውን ማን ይቆጣጠራል?

አቶ ኤርሚያስ፡- ስፔሻሊቲ ቡናዎች ላይም አማራጮች አሉ፡፡ አሁን ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ ከገባ የወራት ዕድሜ ያለው ቢሆንም፣ ከፍተኛው ሥራ ያለው በዚህ ባለሥልጣን ላይ ነው፡፡  ከታች እስከ ላይ ድጋፍ ያደርጋል ተብሎ ትልቅ ኃላፊነት የተሰጠው ለቡናና ሻይ ባለሥልጣን ነው፡፡ ምርት ገበያው እኮ ታች ወርዶ ጥራት ላይ ይህንን ሥሩ፣ ይህንን አትሥሩ አይልም፡፡ የመጣውን ቡና ደረጃ እያወጣለት ለግብይት አቅርቦ ሻጭና ገዥን ማገናኘት ነው፡፡ ሌሎች ሥራዎችን ለማከናወን ዋነኛ ባለቤት ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ነው፡፡ ልማቱንም ገበያውንም የሚመራው እሱ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በነገራችን ላይ ይህንን ሪፎርም ለማምጣት በተከታታይ የቡና ባለድርሻዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር አድርገውት በነበረው የውይይት መድረክ ላይ፣ እንደ ችግር ካቀረቡዋቸው ጉዳዮች አንዱ የምርት ገበያውን አሠራር የሚመለከት ነው፡፡ በምርት ገበያው ላይ የተለያዩ ቅሬታዎች ቀርበውበታል፡፡ አሉ ያሉዋቸውንም ጉድለቶች በተለያዩ መንገዶች ገልጸዋል፡፡ እናንተ ለእነዚህ ቅሬታዎች የሰጣችሁት መልስ ምንድነው? ችግሮቹንስ ፈታችኋል?

አቶ ኤርሚያስ፡- እንዲያው ይህንን ነገር ለማስረዳት አንድ ምሳሌ ልጥቀስ፡፡ አንድ ምግብ ቤት ገብተህ ጥሩ ምግብ ተዘጋጅቶት በጥሩ አቀራረብ ቀርቦ፣ ምግቡ ጨው ከሌለው ትዝ ብሎን ልናገር የምንችለው ምግቡ ጨው የለም በማለት መናገር ነው፡፡ በምርት ገበያው ላይ የሚነሳው ነገር እንዲህ ይመስለኛል፡፡ የምርት ገበያው የሚያከናውናቸው በጣም ብዙ ሥራዎች አሉ፡፡ መተኪያ የሌላቸው ሥራዎች ናቸው፡፡ ምርት ይቀበላል፣ ለተቀበለው ምርት ደረጃ ያወጣል፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ የሚጎድል ነገር ካለ ኃላፊነቱን የሚወስደው ምርት ገበያው ነው፡፡ ከዚያም ምርቱን ያገበያያል፡፡ ካገበያየ በኋላ ከሻጭ ወደ ገዥ የባለቤትነት መብቱን ያሸጋግራል፡፡ ይህን ሁሉ ኃላፊነት ወስዶ በየቀኑ ማገበያየት ትልቅ ሥራ ነው፡፡ በአብዛኛው እንዲህ ዓይነት አቤቱታዎች ሲመጡ ጫፍ ላይ አንዱን ነገር ብቻ መዞ የመያዝና ገበያው ላይ የሚፈጠሩትን ነገሮች አጉልቶ የማስታወስ ነገር አለ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ  ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ትዕዛዝ መሠረት እኛም አባል ሆነን አቅራቢዎችና ገዥዎች፣ ሻጮችና ኤክስፖርተሮች፣ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን፣ ንግድ ሚኒስቴርና ሁሉም የቡና ባለድርሻ አካላት ያሉበት ሰፊ ውይይትና ምክክር ተደርጓል፡፡ በሁሉም ምክክር መድረኮች ሄደን መጨረሻ ላይ የተስማማንበት ነገር፣ የኢትዮጵያ ምርት ሚና መተኪና የሌለው መሆኑ ነው፡፡ በጣም ያስፈልገናል፡፡ ችግሮቹን ማረምና ማስተካከል ነው ያለበት የሚል የጋራ ስምምነት ነው ያደረግነው፡፡ በዚህ የጋራ ስምምነት መሠረት ነው ይኼ ሪፎርም ተቀርፆ ወደ ሕግ ማውጣትና ወደተለያዩ የሥራ ለውጦች እየተዘጋጀን ያለነው፡፡ ስለዚህ በምርት ገበያ ግብይት ውስጥ ያልጣፈጠው ጨው የቱ ጋ ነው? ሲባል ምርት መቀላቀሉ ላይ ነው፡፡ ምርት መቀላቀሉ ተጠያቂነትን አጥፍቷል የሚል አስተያየት ነው የቀረበው፡፡ የእኔ ምርት ከሌላ ሰው ምርት ጋር ተቀላቀለ በሚል መንፈስ፣ ኪሎው ተጓደለ፣ ጥራቱ ተዛባ፣ ጥሩ ተደርጎ የተዘጋጀ ምርት ይዘቱን ጠብቆ እንዲወጣ አላረጋገጠም የሚለውን ቅሬታ እኛ ተቀብለናል፡፡ ስለዚህ በሪፎርሙ እነዚህን ለማስተካከል ነው እየሄድን ያለነው፡፡ መፍትሔ ነው ያስቀመጥነው፡፡ ስለዚህ ባለድርሻ አካላቱ አጨብጭበው ተቀብለውታል፡፡ ስለዚህ ይህንን መሬት ላይ ካወረዳችሁልን የእኛ ጥያቄ ተመለሰልን ማለት ነው ብለው ነው ያስቀመጡት፡፡

ሪፖርተር፡- ከሰሞኑ የለውጥ ሒደት ጋር ተያይዞ ሌላ ብዥታ የፈጠረው ምርት ገበያው ቡና ለማገበያየት በየዕለቱ መነሻ ዋጋ ሊያደርግ ነው የሚል ነው፡፡ ቀድሞ መነሻ ዋጋ ያስቀምጥ ነበር፡፡ ከዚያ እንዲቀር ተደረገ፡፡ አሁን ደግሞ መልሶ ሊጀምር ነው እየተባለ ነው፡፡ በጨረታ ላይ ዋጋ መነሻ ማስቀመጡ ደግሞ ተገቢ አይደለም የሚል አስተያየት ይሰነዘራል፡፡

አቶ ኤርሚያስ፡- በመጀመሪያ ደረጃ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋጋ አውጥቶ አያውቅም፡፡ ይህ አስተያየት የተሳሳተ ነው፡፡ ይህ መታረም አለበት፡፡ ምርት ገበያው በፍፁም ዋጋ አውጪ ሆኖ አያውቅም፡፡ ምርት ገበያችን የሚያደርገው በዕለቱ የነበረውን የገበያ ዋጋ ይመለከትና የመዝጊያ ዋጋ የሚባል ነገር አለ፡፡ በዚያ መነሻነት የሚቀጥለው የገበያ ቀን ጤናማ የሆነ አካሄድ እንዲኖረው በሆነ ርቀት ውስጥ እንዲሄድ ይቆጣጠራል፡፡ ይመለከታል፡፡ የዛሬ ገበያ በአማካይ በ100 እና በ150 በመቶ ሄዶ ወይም በአማካይ 125 በመቶ ነበር ብሎ ለአብዛኛው ገበያ ፈጻሚ ያስተላልፋል፡፡ ምክንያቱም ሁሉም የዛሬ ገበያ በአማካይ ዋጋው ይህንን ያህል ከሆነ፣ ነገ ገበያው በዚህ ርቀት ውስጥ ይሆናል ብሎ መተንበይ አለበት፡፡ አደጋውን መቆጣጠር አለበት፡፡ ሁሉም በዓለም ላይ የሚሠሩ ምርት ገበያዎች እንደዚህ ናቸው፡፡ በቅርቡ እንኳን አንድ የቻይና ምርት ገበያ ለሁለት ቀናት ተቋርጦ ነበር፡፡  

ገበያው ከሆነ ሥርዓት ውስጥ ጥሶ ሲሄድ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ያሉ ተዋንያንን እንዳለ ስለሚጎዳ ገበያውን የማስቆም ሁሉ መብት አለው ማለት ነው፡፡ የእኛም ምርት ገበያ በተመሳሳይ ነው የሚሠራው፡፡ ገበያው ከዚያ ርቀት ውስጥ ሲወጣ ገታ ያደርገዋል፡፡ ምክንያቱም የማይገመቱ ወይም አብዛኛው ገበያ ውስጥ ያለው ኅብረተሰብ ያልሰማው መረጃ፣ በተወሰኑ ሰዎች ዘንድ ባለ መረጃ ገበያን የማጦዝ ዓይነት ባህሪ ካለው የመቆጣጠር ኃላፊነት አለው፡፡ ለዚህ አንድ ምሳሌ ልስጥህ፡፡ ሁል ጊዜ በየወሩ መጨረሻ ላይ በነዳጅ ማደያዎች ሠልፍ ታያለህ፡፡ አሽከርካሪዎች ገና ለገና ነገ ዋጋ ይለወጣል ብለው ስለሚሠጉ ተሠልፈው ለሊት ይገዛሉ፡፡ የእኛ ተልዕኮ ያንን ዓይነት መሠለፍ በየቀኑ ገበያችንን እንዳይጎዳብን ነው፡፡ በየቀኑ ጤናማና አሳታፊ የሆነ ግብዓት እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ስለዚህ እኛ የመዝጊያ ዋጋ ሊስታችንን እንጭናለን (ፖስት) እናደርጋለን፡፡ አሁን ያብራራሁት ነገር እንዳለ ሆኖ፣ የዓለምን ገበያ የእኛ ገበያ ፈጻሚዎች እንዲረዱ እንፈልጋለን፡፡ የዓለምን ገበያ ታሳቢ በማድረግ በእኛ ገበያ ለመገበያየት እንዲረዳቸው የኒዮርክን የቡና ዋጋ ወይም የናይጄሪያንና የቻይናን የሰሊጥ ዋጋና የመሳሰሉትን እንጭንላቸዋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ሌላው ጉዳይ ደግሞ የመጋዘን አገልግሎቱን ይመለከታል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ምርት ገበያው የመጋዘን አገልግሎቱንም አንድ ላይ ይሠራ ነበር፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት የመጋዘን አገልግሎት ከምርት ገበያው መነጠል አለበት ተብሎ ራሱን ችሎ ተቋቋመ፡፡ አሁን ደግሞ እንዲዋሀድ ተወሰነ፡፡ ለምን?

አቶ ኤርሚያስ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም አቤቱታዎች ሲቀርቡ የነበረው የመጋዘን አገለግሎት ላይ በጣም ብዙ ችግር ስላለ ነው፡፡ የመጋዘን አገልግሎቱ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ መነጠል አለበት የሚሉ የባለድርሻ አካላት ግፊት ነበር (በወቅቱ እኔ አልነበርኩም)፡፡ እኔ ከመምጣቴ በፊት የተደረገው ዓለም አቀፍ መነሻ የሚያመላክተው የመጋዘን ሥራ ለብቻው በመነጠል መካሄዱ ተመራጭ ነው የሚል አመለካከት ነበር፡፡ የመጋዘን አገልግሎት እንዲለይና ራሱን ችሎ እንዲሠራ አቅጣጫ ተሰጥቶ፣ በዚህ መሠረት ላለፈው አንድ ዓመት ያህል የመጋዘን አገልግሎቱ ተነጥሎ ለብቻው እንዲሠራ ተደርጎ ነበር፡፡ አሁን ግን ሪፎርሙን ስናስብ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ይዘን አንዱ ቦግ ብሎ የወጣው፣ እኛ ገና እንጭጭ የሆነ የግንባታ ደረጃ ላይ መሆናችን ነው፡፡ ምክንያቱም የውጭዎቹ በዚያን ጊዜ የተወሰደው እነሱ መጋዘን ኦፕሬት የሚያደርጉት ከብዙ ዓመታት ልምድና ብዙ የመጋዘን አገልግሎት ከገነቡ በኋላ ነው ይህንን ያደረጉት፡፡ እኛ ገና መንደርደርያው ላይ ቶሎ ብለን አጨናጋፊ ነው የሚል ነገር ወሰድን፡፡

ስምንት ዓመት ሳይሞላው የመጋዘን አገልግሎቱ ተገንጥሎ መውጣቱ ተጨማሪ ወጪ እንዲጠይቀን አድርጓል፡፡ ተነጥሎ መሥራቱ የእሴት ሰንሰለታችን በዓለም ተወዳዳሪ እንዳይሆን፣ የማኔጅመንት መጪው ራሱ ተወዳዳሪ እንዳይሆን የሚያደርሰው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ ያንን ወጪ በምርት ገበያው አካተን ብንቀለብሰው  በቀላሉ ተወዳዳሪ እንድንሆን ያደርጋል ወደሚል መግባባት ላይ ተደረሰ፡፡ ማኔጅመንቱ ደግሞ አንድ ሆኖ ያለውን የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት (አሁን ጥሩ መሠረተ ልማት አለው) ይህንን መጠቀም ይችላል፡፡ እንደ አዲስ ኢንቨስት ከማድረግ ባለው ሥርዓት ውስጥ ማስኬዱ ውጤታማ ያደርጋል የሚል ሐሳብ ነው ከባለድርሻ አካላት ያገኘነው፡፡ ስለዚህ የመጋዘን አገልግሎቱን መቀላቀል አሁን የሚታሰበውን ለውጥ ለማምጣት ትልቅ ሚና ይኖረዋል ተብሎ በመታመኑ የተወሰደ ዕርምጃ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ሪፎረም ጋር ተያይዞ አዳዲስ አሠራሮች ይመጣሉ፡፡ አሁን ለምሳሌ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣንና ከቡናና ሻይ ባለሥልጣን ጋር የሚኖው ግንኙነት ምን ዓይነት ይዘት ይኖረዋል? ተጠሪነታችሁስ?

አቶ ኤርሚያስ፡- በጣም ግልጽ መሆን ያለበት የአሠራር ሥርዓታችንን የሚነካ ብዙ ነገር የለም፡፡ ምርት ገበያ ከዚህ በፊት ሲዋቀርም ከምሥረታው ጀምሮ ለንግድ ሚኒስቴር ሪፖርት ያደርጋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ በሚዲያዎች ላይ የምርት ገበያና የምርት ገበያ ባለሥልጣን የሚባለው እየተቀያየረ ይገለጻል፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ገበያችን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባንኮችን እንደሚቆጣጠር ሁሉ የገበያውን ሥርዓት የሚቆጣጠር አካል ነው፡፡ አስፈላጊና ገለልተኛ አካል ነው፡፡ ምክንያቱም ምርት ገበያ ከገበያተኞች ጋር የሚፈጠሩትን ልዩነቶችና  የሁሉንም ጥቅም ጠብቆ የማስኬድ ኃላፊነት አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን በፊት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ከሚሆን ሁለቱም ምርት ገበያው ቡና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን ለአንድ ሚኒስቴር (ለንግድ ሚኒስቴር) ሪፖርት ቢያደርጉ ተባለ፡፡ አዲሱ ነገር ይህ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ተጠሪነቱ ለእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የሚቀጥል ነው፡፡ ስለዚህ ምንም የተነካካ ነገር የለም፡፡

ሪፖርተር፡- ከሪፎርሙ ምን ይጠበቃል? የቡና ገበያ ወርዷል፡፡ ይህንን ያሽቆለቆለ አፈጻጸም ለማንሳት ያስችላል?

አቶ ኤርሚያስ፡- በመጀመርያ ቡና ወርዷል የሚለው አመለካከት ሙሉ ለሙሉ ትክክል አይደለም፡፡ አሁን የስምንት ወራት ትንተና ስንሠራ በዚህ ዓመት በምርት ገበያችን የተሸጠው ቡና ከፍተኛ ነው፡፡ ዋጋውንም ስናየው ከዓለም ገበያ የተሻለ ዋጋ ነው የምናገኘው፡፡ ያው የኢትዮጵያ ቡና ተፈላጊ በመሆኑ ጥሩ ዋጋ አለ፡፡ ስለዚህ ቡናችን በጣም ወርዷል የሚለው ነገር መቶ በመቶ ትክክል አይደለም፡፡ በቡና ገበያ ሥርዓታችን ውስጥ ችግሮች አሉ በሚለው ላይ ተስማምተናል፡፡ ቡናችን በሚፈለገው ፍጥነት እያደገ አይደለም፡፡ ዕድገቱ በጣም ትንሽ ነው፡፡ ሁለት በመቶ፣ አምስት በመቶ ከፍ ዝቅ ይላል፡፡ ሌሎች አገሮች ግን የቡና ምርታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ ችለዋል፡፡ የቬትናምና የኮሎምቢያ ቡና ገበያ በከፍተኛ ሁኔታ አድጓል፡፡ የኢትዮጵያ ቡና በጣም ተፈላጊ ሆኖ ሳለ ዕድገቱ አነስተኛ ነው፡፡ እንደ ሌሎቹ ከፍተኛ የሆነ ዕድገት የታየበት ባይሆንም፣ መጠነኛ ዕድገት ግን አለው፡፡ አሥር በመቶ፣ 15 በመቶ አላደገም፡፡ ከሌሎች አገሮች ጋር ለመወዳደር ዕድገታችን በዚያ ልክ መፍጠን አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ወርዷል የምንለው እኮ ከቡና የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ እያሽቆለቆለ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ምን ያሳያል?

አቶ ኤርሚያስ፡- እንዳልኩህ ነው፡፡ የኢትዮጵያን የአሥር ዓመታት የኢትዮጵያን የቡና ወጪ ንግድ ብትሠራ የአንድ ቢሊዮን ዶላር የቡና ገበያ ነው ያለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከድርቁም ጋር ተያይዞ በአማካይ 750 ሚሊዮን ዶላር፣ 800 ሚሊዮን ዶላር ይገኛል፡፡ ዝቅ ሲል 600 ሚሊዮን ዶላር ይገኛል፡፡ ዞሮ ዞሮ ይህ ጥሩ ነው እያልኩ አይደለም፡፡ ይህንን ሁሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቡና አምራቾች ይዘንና ዘመናዊ ገበያ አቋቁመን ከፍና ዝቅ ማለታችን ተቀባይነት እንደሌለው ደምድመናል፡፡ ችግሩ ተወዳዳሪ የሆኑ የቡና አብቃይ አገሮች እጅግ ከፍተኛ ተወዳዳሪ ለመሆን በአሥርና በ15 ዓመት በመቶ እያደጉ ነው፡፡ የእሴት ሰንሰለት ወጪያቸውን በጣም ቀንሰው በጥራት ጭምር እየተወዳደሩና እያደጉ ጥለውን እየሄዱ ነው፡፡ ስለዚህ ከእነሱ ጋር ለመወዳደር ምርታማነታችንና ጥራታችንን ማሳደግ አለብን፡፡ እሴት ጨምሮ የመሸጥ ሥራ ላይ ብዙ መረባረብ አለብን፡፡ እስካሁን አላደረግነውም፡፡

ሪፖርተር፡- እሴት ጨምሮ በመሸጡ ላይ ተስፋ አለ?

አቶ ኤርሚያስ፡- አንድ ምሳሌ ልስጥህ፡፡ ቅድም እንዳልኩህ ቡና ቆልተውና ፈጭተው ኤክስፖርት የሚያደርጉ ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች በሁለት ወራት ከመጡ፣ በአንድ ዓመት ውስጥ ብዙ ይመጣሉ፡፡ እዚህ ላይ መታሰብ ያለበት ቆልተንና ፈጭተን የምንልከው ቡና ጥሬ ቡና ልከን ከምናገኘው የእጥፍ እጥፍ ገቢ የሚያስገኝ ነው፡፡ እዚህ ላይ በብርታት መሥራት አለብን፡፡ ማገዝ አለብን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማስተላልፈው መልዕክት የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ያለበቂ ምክክርና ውይይት እንዳይፀድቅ ነው›› አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም፣  የሕግ ባለሙያ

አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም በዳኝነትና በጥብቅና ሙያ ለረዥም ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ከአምስተርዳም ዩኒቨርሲቲ በሕገ መንግሥትና አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ  ጠበቆች ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ...

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት...

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም....

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...