Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሸቃቢ ሚዛኖች

ሸማቾች ምሬት ከሚያሰሙባቸው በርካታ የግብይት ችግሮች አንዱ በወስላታ ሚዛኖች የሚፈጸምባቸው ማጭበርበር ነው፡፡ አምስት ኪሎ ሽንኩርት አስመዝነው የገዙ የቤት እመቤት እንደው ለምናልባቱ በማለት ትክክለኛነቱ በተረጋገጠ ሚዛን ሲያስመዝኑ፣ አራት ወይም ሦስት ተኩል ሆኖ የሚገኝበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ክስተት የብዙዎች ሸማቾች ዕለታዊ ገጠመኝ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በሀቅ እንዲያገለግሉ የተፈበረኩ መለኪያዎችን በተንኮል የሚያዛቡ ነጋዴዎች በርካታ ናቸው፡፡

ሐሰተኛ ሚዛን ያማረራቸው አንዲት ወይዘሮ፣ ሰሞኑን በቴሌቪዥን የተናገሩት ይጠቀሳል፡፡ ወይዘሮዋ አትክልትና ፍራፍሬ ሲገዙ የከፈሉበትን ያህል ኪሎ የሚመዝን መጠን እንደማይሸጡላቸው ባወቁ ጊዜ፣ ሸቃቦቹን በመተው በትክክለኛው ሚዛን እንደሚሸጥ ወዳመኑበት ነጋዴ ለመሄድ መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡

ችግሩ ግን በትክክለኛ ሚዛን ይሠራሉ የሚባሉትም ቢሆኑ ሙሉ ለሙሉ ከስህተት መንገድ የተላቀቁ አለመሆናቸው ነው፡፡ የሚዛን ቅጥፈትን ይበልጥ ለማስረዳት በልኳንዳ ቤቶችና በሱፐር ማርኬቶች የሚሸጠውን የሥጋ መጠን ማመዛዘኑ በቂ ነው፡፡

ሁሉም ሱፐር ማርኬቶች ሀቀኛ ሚዛን አላቸው ብሎ መደምደም ባይቻልም፣ በርካቶቹ ዲጂታል ሚዛን ስለሚጠቀሙ ሽቀባ ብዙም አይዳዳቸውም፡፡ ከትልልቅ ኪሎ እስከ አነስተኛ ባለው መጠን በግራም ልክ መሸጣቸውም ይህንን አባባል ያጠናክረዋል፡፡ ከብዙዎቹ ልኳንዳ ቤቶች ሁለት ወይም ሦስት ኪሎ ተብሎ የሚሸጠው ሥጋ በትክክለኛ ሚዛን ቢለካ ጉድለት አያጣያውም፡፡ እንደውም የሥጋ ልኬት ሚዛን ሳይነካው በእጅ፣ በግምት እየሆነ እንደመጣ እየታዘብን ነው፡፡

ጥሬ ወይም ጥብስ ሥጋ ለመብላት ጎምዥተው አንድ ኪሎ አዘዋል እንበል፡፡ ያዘዙት መጠን ነው ተብሎ የቀረበልዎትን ሥጋ በትክክለኛ ሚዛን ቢሰፍሩት ግን የተባለውን መጠን ላያሳይዎ ይችላል፡፡ ጥቂት የማይባሉት ሥጋ ሻጮች እንዲህ ባለው ድርጊት ውስጥ መሳተፋቸው የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ ወጣ ሲሉ፣ አንድ ኪሎ ተብሎ የሚቀርብልዎ የሥጋ መጠን በአዲስ አበባና በአጎራባች ከተሞች ከሚቀርበው ጋር ሲነፃፀር ጉድለቱ ምን ያህል እንደሆነ ያሳየናል፡፡

የሥጋ ነገር ከተነሳ አይቀር አንድ ቀልድ አዘል ወግ ልጥቀስ፡፡ ልኳንዳ ቤቱ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ ምርጥ ሥጋ እንደሚያቀርብ ይነገርለታል፡፡ ስለዚህ የመሸጫ ዋጋውም ከአብዛኛዎቹ ልኳንዳዎች ይልቅ ከፍ ያለ ነው፡፡ አንድ ኪሎ ሥጋ በ350 ብር ይሸጣል፡፡ ዋጋው ውድ ስለሆነ ብቻ ግን በላተኛ አላጣም፡፡ አቅም ያላቸው ገንዘባቸውን እየመዠረጡ የሚቆርጡበት ቤት ነው፡፡ ይሁንና በአንዱ ቀን ከተማውን ሲያካልሉ ከሚውሉ ሎተሪ አዟሪዎች መካከል ሁለቱ በሰው የተሞላውን ይህን ልኳንዳ ቤት ይመለከታሉ፡፡ የሚገዛን ብናገኝ በማለት ለመግባት ሲሞክሩ   ጥበቃዎች ይከለክሏቸዋል፡፡ ሎተሪ ሻጮችና ጥበቃዎች በእንግባ አትገቡም አንድ ሁለት ይባባላሉ፡፡ ከጥበቃዎቹ አንዱ ግን ‹‹እባካችሁ ልጆች ብትሄዱ ያሻላል፡፡ ብትገቡ እንኳ አንዳችሁም አትሸጡም፡፡ ምክንያቱም እዚህ ቤት የሚገባ ሁሉ ሎተሪ የደረሰው ነው፤›› በማለት ቁርጣቸውን እንደነገራቸው ሲወራ ቆይቷል፡፡

የጥበቃው አነጋገር ግልጽ ነው፡፡ ለአንድ ኪሎ ሥጋ የወር ቀለብ የሚሸምት ገንዘብ በላተኛው ሲያወጣ እየታዘበ ስለሚውል ሎተሪ ለመግዛት ግድ የሚለው የለም ለማለት የፈለገ ይመስላል፡፡ ነገር ግን እዚህ ቤት ያለው ሚዛንም ቢሆን ከሌሎቹ ቀበኛ ሚዛኖች ይለያል ብዬ አላምንም፡፡ ልኳንዳ ቤቶች ሆይ የሚከፈላችሁ የተጋነነ ዋጋ ሳያንስ ስለምን በሚዛን ትጎዱላናችሁ? በነገራችን ላይ አንድ ኪሎ ሥጋ በ80 ብር የሚሸጥ እንዳለ ሁሉ፣ 350 ብር የሚጠየቅ ልኳንዳ ቤትም በብዛት አለ፡፡ በኪሎ ከ150 እስከ 200 ብር የሚሸጡትም በርካቶች ናቸው፡፡

ሸቃቢ ሚዛኖች ከልክ በላይ በሚከፈልባቸው ቤቶች ውስጥም አልታጡም፡፡ ሸማቾች ለከፈሉት ገንዘብ በትክክለኛው መለኪያ ተሰፍሮ እንደቀረበላቸው ማረጋገጥ ካልተነሱ ለተጠመዘዙ ሚዛኖች መንሰፋራት ምክንያት ስለሚሆኑ ለችግሩ ተጠያቂ እንደሆኑ መናገር ይችላል፡፡ ዛሬ በቸልታ፣ ምን ይደረግ ብለን የምናልፈው ነገር ገበያው ለመበረዝ ሰበብ እንደሚሆን የታወቀ ነው፡፡

 ሥጋን አነሳን እንጂ በሌሎች ምርቶች ዘንድም መስክ በልኬት የሚፈጸመውን ጸያፍ ተግባር ለመግታት አልቻለም፡፡ ሸቃቢ ሚዛኖችን ለመቆጣጠር ዘመቻ ይወጣል፡፡ ብዙም ሳይቆይ ግርግር አስነስቶ ወዲያው የውኃ ሽታ ሆኖ ይቀራል፡፡ የሸማቾች አንገብጋቢ ችግር፣ ለነጋዴዎችም የሥነ ምግባር ዝቅጠት የሆነውን ጉዳይ ለመፍታት የተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቶች ተነሳሽነት ዝቅተኛ በመሆኑ፣ የሚያደርጉትም ቁጥጥር ወለም ዘለም የበዛበት ስለሆነ፣ የአጭበርባሪ ሚዛን ሲሳይ መሆናችን፣ እንደ ደባል አብረን የምንኖረው ለማዳን ችግራችን ከቆየ ሰንብቷል፡፡   

በዚህ ዓመት መጀመርያ ሰሞን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ይህን ችግር ለመቅረፍ ዲጂታል ሚዛኖች ጥቅም ላይ እንዲውሉ እሠራለሁ ሲል ጊዜ ጥሩ፣ እሰየው ተብሎ ነበር፡፡ ችግሩን እንደሚቀንስ ቢታመንበትም ዘመናዊው ዲጂታል ሚዛን በመላው የግብይት ሥርዓት ውስጥ ሊታይ አልቻለም፡፡ ማጭበርበር የለመደ፣ ዲጂታል ሚዛኑን ነካክቶ ሐሰተኛ የሚያደርግበት መንገድ ይጠፋዋል ማለት ዘበት ቢሆንም፣ እንደ የሽቦ ሚዛኖች በቀላሉ አይጠመዘዙ ይሆናል፡፡

ስለዚህ ሸማቹ በሽቀባ እንዳይበዘበዝ ለማድረግ የተሻሉ መለኪያዎች፣ መተማመንን የሚያሰፍኑ የተመሰከረላቸውን ሚዛኖች ማስለመድ ተገቢ ነው፡፡ ትክክለኛ መለኪያ መጠቀም አስገዳጅ የሚሆንበት አሠራርም ቢጠናከር ይመረጣል፡፡

ከቸርቻሪው ባሻገር አምራቾች የሚያመርቱት ምርትም የልኬት ጉድለት እንደሚታይበት መታዘብ ከባድ አይደለም፡፡ 500 ግራም እንደሚመዝን የተጻፈበት፣ የታሸገ ፓስታ ትክክለኛ ልኬቱ ሲታይ ግን 500 ግራም ላያሳይ ይችላል፡፡ አስገራሚው ነገር የታሸገ ፓስታ እንደ ትክክለኛ መለኪያ በየኪዮስኩ ሌላ ዕቃ ሲመዘንበት መታየቱ ነው፡፡ ግማሽ ሊትር ተብሎ ማሸጊያው ላይ የተጻፈበት ወተት በትክክል የተባለውን ሳይሆን፣ ጎዶሎ ሆኖ የሚገኝበት አጋጣሚ እየታየ ነው፡፡

ስለዚህ በየጊዜው የሚንጠን የዋጋ ጭማሪ ራሳችንን ማዞሩ ሳያንሰን፣ በልኬት መሣሪያዎችም የሚደርስብንን በደል ለመቀነስ የሚመለከተው መሥሪያ ቤት መነሳትና ማስተካከል ይጠበቅበታል፡፡

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት