Wednesday, March 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የ2010/11 የነዳጅ ግዥ ጨረታ ሊያወጣ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ከ2010/11 በጀት ዓመት ለአገሪቱ የነዳጅ ፍጆታ የሚውሉ የተለያዩ የነዳጅ ውጤቶች ግዥ ጨረታ፣ በመጪው ሳምንት እንደሚያወጣ ታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የአገሪቱ ዓመታዊ የነዳጅ ፍላጎት 3.8 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የደረሰ ሲሆን፣ ይኼም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ13 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ የጨረታ ሰነድ ዝግጅቱ እንደተጠናቀቀ የገለጹት አቶ ታደሰ፣ ዓለም አቀፍ ግልጽ የሆነ ጨረታ በመጪው ሳምንት ይወጣል ብለዋል፡፡  

ጨረታው ለ45 ቀናት ክፍት ሆኖ የሚቆይ ሲሆን፣ በጥቅምት ወር አጋማሽ ውጤቱ ታውቆ ከአሸናፊው ኩባንያ ጋር ስምምነት ይፈረማል፡፡ አሸናፊ የሚሆነው ኩባንያ የተለያዩ የነዳጅ ውጤቶችን ከጥር 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ዓመት ያቀርባል፡፡

ያለፈውን ዓመት ጨረታ ፔትሮ ቻይና የተሰኘ ግዙፍ የቻይና የነዳጅ ኩባንያ አሸንፎ የተለያዩ የነዳጅ ውጤቶችን በማቅረብ ላይ ሲሆን፣ ኮንትራቱ በታኅሳስ 2010 ዓ.ም. እንደሚጠናቀቅ ታውቋል፡፡

ከ2010 /2011 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት 408,378 ሜትሪክ ቶን ቤንዚን፣ 2,546,786 ሜትሪክ ቶን ነጭ ናፍጣ፣ 661,790 ሜትሪክ ቶን የአውሮፕላን ነዳጅ፣ 124,914 ሜትሪክ ቶን ላምባ፣ 38,805 ሜትሪክ ቶን ቀላል ጥቁር ናፍጣ፣ 39,470 ሜትሪክ ቶን ከባድ ጥቁር ናፍጣ፣ በአጠቃላይ 3,820,142 ሜትሪክ ቶን ነዳጅ ለመግዛት አቅዷል፡፡

አብዛኛውን ነዳጅ የሚያቀርቡት ሱዳንና ኩዌት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በተፈራረሙት የሁለትዮሽ ትብብር ስምምነት ያለ ጨረታ ነው፡፡ መንግሥት አስተማማኝ የነዳጅ አቅርቦት በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት ሲል ከኩዌትና ከሱዳን መንግሥታት ጋር በገባው የረዥም ጊዜ ውል፣ የኩዌት መንግሥት ንብረት የሆነው ኩዌት ፔትሮሊየም ኮርፖሬሽንና የሱዳን መንግሥት ኩባንያ የሆነው ሱዳን ፔትሮሊየም ኮርፖሬሽን ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ ያቀርባሉ፡፡

በዚህ መሠረት ሱዳን ፔትሮሊየም ኮርፖሬሽን 40 በመቶ ቤንዚን ፍጆታ ሲያቀርብ፣ 60 በመቶው ከዓለም አቀፍ ነዳጅ አቅራቢዎች በግልጽ ጨረታ የሚሸመት ነው፡፡ የኩዌት ፔትሮሊየም ኮርፖሬሽን 50 በመቶ ነጭ ናፍጣ የሚያቀርብ ሲሆን፣ የተቀረው 50 በመቶ በጨረታ ይገዛል፡፡

ላምባና የአውሮፕላን ነዳጅ ሙሉ በሙሉ የሚያቀርበው ኩዌት ፔትሮሊየም ኮርፖሬሽን እንደሆነ ታውቋል፡፡ የጥቁር ናፍጣ አቅርቦት ውል የሚያበቃው በየካቲት 2010 ዓ.ም. በመሆኑ፣ የተለየ ጨረታ በታኅሳስ ወር ውስጥ እንደሚወጣ አቶ ታደሰ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች