Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትቻይና በስፖርቱ ከኢትዮጵያ ጋር ለመሥራት ፍላጎት ማሳየቷ ተገለጸ

ቻይና በስፖርቱ ከኢትዮጵያ ጋር ለመሥራት ፍላጎት ማሳየቷ ተገለጸ

ቀን:

  • በሚኒስትሩ የተመራው ልዑክ የቻይና ቆይታውን አጠናቆ ተመልሷል

ከዓለም ኃያል አገሮች አንዷ የሆነችው ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር የጀመረችውን ኢኮኖሚያዊ ትብብር በስፖርቱም ለመቀጠል ፍላጎት ማሳየቷ ተገለጸ፡፡ በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ርስቱ ይርዳው የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ በቻይና ይፋዊ ጉብኝት አድርጎ ተመልሷል፡፡ ሁለቱ አገሮች በስፖርቱ በትብብር መሥራት የሚችሉበት መግባቢያ ሰነድ በቅርቡ ይፈራረማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተገልጿል፡፡

በአቶ ርስቱ ይርዳው የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ ከነሐሴ 21 ቀን 2009 ዓ.ም. እስከ መስከረም 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ በቻይና ባደረገው የልምድ ልውውጥና ይፋዊ ጉብኝት፣ ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ እንዲሁም ከክልሎች የትግራይና የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የስፖርቱ ዘርፍ ኃላፊዎችን ያካተተ እንደነበር የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ትብብር እንዳላት የገለጹት ዶ/ር አሸብር ጉብኝታቸው ቻይናውያን ዘንድሮ ለ13ኛ ጊዜ ያዘጋጁት የመላ ቻይና ጨዋታዎችን መነሻ በማድረግ ኢትዮጵያ በረዥምና መካከለኛ ርቀት ቻይና ደግሞ በብዙ ስፖርቶች ያላቸውን ውጤታማነት በትብብር ለማሳደግና ለማበልፀግ ያለመ ነው፡፡

በቻይና ቲያንጅ ከተማ የተዘጋጀው የመላ ቻይናውያን ጨዋታ ከአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ጀምሮ የታላላቅ ዓለም አቀፍ የስፖርት ተቋማት መሪዎች በተገኙበት ስፖርታዊ ውድድሩ መጀመሩን ያስረዱት ዶ/ር አሸብር፣ ቻይና በቅኝ ግዛት በነበረችበት ወቅት የተከፋፈሉ ግዛቶቿን ማለትም የሆንግ ኮንግና የማክዋ ግዛቶች ምንም እንኳ በራስ ገዝ የሚተዳደሩ ቢሆኑም በስፖርታዊ ውድድሩ ላይ ግን የሚያለያያቸው ምንም ዓይነት ችግር ሳይገጥማቸው ማጠናቀቃቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ዝግጅት ለማከናወን ተሞክሮው እጅግ ጠቃሚ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡

ሁለቱ አገሮች በትብብር ለመሥራት ዕቅድ ከያዙባቸው ነጥቦች መካከልም በአትሌቲክሱና በሌሎችም ስፖርቶች በኢትዮጵያ የተለያዩ የስፖርት አካዴሚዎችን ከመገንባት አንስቶ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ከስታዲየሞች ጀምሮ አያያዝና አጠቃቀምን እንዲሁም የስፖርት መሠረተ ልማቶች ከሚሰጡት ስፖርታዊ አገልግሎት በተጨማሪ ተጨማሪ ጥቅም እንዴት መስጠት ይችላሉ? የሚለው በልምድ ልውውጡ መካተቱን ገልጸዋል፡፡ በቻይናም ሆነ በኢትዮጵያ በተለይ ታዳጊ ወጣቶች ላይ ለሚሠሩ ማናቸውም ወጪዎች በቻይና መንግሥት የሚሸፈን ስለመሆኑ ስምምነት ላይ መደረሱን ጭምር ዶ/ር አሸብር ተናግረዋል፡፡

በጉብኝቱ ወቅት ቻይና እ.ኤ.አ. በ2008 ላስተናገደችው የቤጂንግ ኦሊምፒክ በወፍ ጎጆ ያሰናዳችው ስታዲየም በአሁኑ ወቅት ለአገሪቱ እየሰጠ ያለውን አገልግሎት በልምድ ልውውጡ ላይ መገንዘባቸውንም ተናግረዋል፡፡

በሁለቱ አገሮች ትብብርና ስምምነት በኢትዮጵያ የሚገነቡ አካዴሚዎችን በተመለከተ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ዓለም ላይ ከ450 በላይ ተቋማትን እንደገነባና በመገንባት ላይ እንደሚገኝ የሚነገርለት የቻይናው ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኩባንያ፣ ትልቅ ድርሻ የሚኖረው በመሆኑ የስምምነቱ አካል መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በቅርቡም የዚህ ተመሳሳይ የልምድ ልውውጥ በእንግሊዝ ለማድረግ ዕቅድ መያዙን ያከሉት ዶ/ር አሸብር፣ በፕሮግራሙ ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ልዑካናት በተጨማሪ የኦሮሚያና የደቡብ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች እንደሚካተቱ ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አዲሱ አመራር መደበኛ ሥራውን የጀመረው ከክልሎች በተጨማሪ የብሔራዊ ፌዴሬሽኖችን አደረጃጀትና ወቅታዊ ቁመና ግምገማዊ ጉብኝት ለማድረግ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው፣ ፌዴሬሽኖቹ ለመጪው 2020 ኦሊምፒክና ለሌሎችም የኦሊምፒክ ስፖርቶች በታዳጊ ወጣቶች ላይ መሥራት እንዲችሉ ለእያንዳንዳቸው 100 ሺሕ ብር ድጎማ እንደሚያደርግ ቃል መግባቱም ይታወሳል፡፡ ይህንኑ አስመልክቶ ፕሬዚዳንቱ፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖቹ በሚያቀርቡት ዕቅድ መሠረት ከሙያተኛ አቅም ግንባታ ጀምሮ ድጋፍና ክትትሉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡ ከዚህም በላይ በ2020 ኦሊምፒክ ከአትሌቲክሱ በተጨማሪ በሌሎችም ስፖርቶች ተሳትፎ ለማድረግ ዕቅድ ሲያዝ መነሻው ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ስለመሆናቸው ጭምር የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ፕሬዚዳንት አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...