Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ለተማሪዎች የሚቀርበው ትራንስፖርት ይሻሻል!

አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር የዕረፍቱ ወራት ተገባደው አዲስ የትምህርት ዘመን ይጀመራል፡፡ ከሕፃናት መዋያ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ባሉት ዕርከኖች ትምርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ያቀናሉ፡፡ በዚህ ሳምንት መደበኛ ትምህርት የጀመሩ ትምህርት ቤቶች ቢኖሩም አብዛኞቹ ግን ገና ናቸው፡፡ ትምህርት ሲጀመር እንደ አዲስ አበበ ባሉ ከተሞች ውስጥ የሚፈጠረው የትራንስፖርት ውጥረት ሳይነሳ አይታለፍም፡፡ የትራፊክ ፍሰቱን የበለጠ ሲያጨናንቀው ተመልክተናል፡፡

የተማሪዎችና የትራንስፖርት አገልግሎቱ ቁርኝት እየሰፋ በመምጣቱም በርካታ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን በራሳቸው ተሽከርካሪዎች እንዲገለገሉ እያደረጉ ነው፡፡ አንዳንድ ወላጆችም በጋራ በመሆን መደበኛ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ሚኒባሶችን ተኮናትረው ልጆቻቸውን ከቤት ወደ ትምህርት ቤት የማመላለሱን ልማድ አዳብረዋል፡፡ እንደየአቅማቸው በታክሲና በከተማ አውቶቡስ ተጓጉዘው ትምህርታቸውን የሚከታተሉም በርካታ ናቸው፡፡ በእግር የሚጓዙም ይካተታሉ፡፡

የትራንስፖርት አገልግሎት የሚፈልጉ ተማሪዎች ቁጥር እያደገ መምጣት ሌሎች ተገልጋዮች ላይ ጫና እያሳደረ ነው፡፡ ተማሪዎችን ለማመላለስ ኮንትራት የወሰደ ታክሲ፣ ለተማሪዎች የሚሰጠው አገልግሎት እንደተጠበቀ ሆኖ ተማሪዎችን በሚያጓጉዝበት ወቅት መደበኛ አገልግሎቱን ማቋረጡ፣ ሌሎች ትራንስፖርት ፈላጊዎችን ያጉላላል፡፡ ይህም የትራንስፖርት እጥረቱን አባባሽ ምክንያት እየሆነ ነው፡፡

በርካታ ተማሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚዎች እየሆኑ የመምጣታቸውን ያህል፣ በርካታ ክፍተቶችም ይስተዋላሉ፡፡ የተማሪዎችና የትራንስፖርት አገልግሎት ራሱን በቻለ መንገድ መስተናገድ እንዳለበት ግልጽ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከመኖሪያ አካባቢያቸው ከሚማሩ ተማሪዎች ይልቅ፣ በትራንስፖርት ተጓጉዘው የሚማሩ ተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ ከመምጣቱ አንፃር በቂ የትራንስፖርት አቅርቦት እየታየ አይደለም፡፡

በመደበኛ ትራንስፖርት የሚጓጓዙ ተማሪዎች በሚያጋጥማቸው የትራንስፖርት እጥረት ሳቢያ፣ የክፍል መግቢያ ሰዓታቸው ሲስተጓጎል እንታዘባለን፡፡ አውቶቡስም ሆነ ታክሲ ለመሳፈር ረዣዥም ሠልፎችን መጠበቅ ግድ የሚላቸው ተማሪዎች፣ በለስ ካልቀናቸው በሰዓቱ ትምህርት ገበታቸው ላይ መገኘት እያቃታቸው ነው፡፡ ችግሩ እየሰፋ በመምጣቱ አሳሳቢ ነው፡፡ ህኗልትን

ተማሪዎች በወቅቱ ትምህርት ገበታቸው ላይ እንዳይገኙ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን፣ በትራንስፖርት ዕጦት ሰበብ የሚረፍድባቸው ተማሪዎች፣ አልባሌ ቦታ እንዲውሉ የሚጋብዝ መሆኑም ልብ ሊባል ይገባል፡፡

በእርግጥ ተማሪዎች ትምህርት ገበታቸው ላይ ለመገኘት አስፈላጊውን ዝግጅት በወቅቱ ማድረግ ቢጠበቅባቸውም፣ የተመቻቸ የትራንስፖርት አገልግሎት ከሌለ ወይም እነሱን በተለየ መንገድ የሚያስተናግድ አሠራር ካልተዘረጋ ግን የቱንም ያህል ዝግጁ ቢሆኑ ከአቅማቸው በላይ በሆነው የትራንስፖርት ችግር መቸገራቸው እየታየ ነው፡፡

ሌላው ሊነሳ የሚገባው ጉዳይ ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎቻቸው የሚያቀርቧቸው ተሽከርካሪዎች የቴክኒክ ብቃት ነው፡፡ ሕፃናት ከሚገባው በላይ ታጭቀው የሚጓዙባቸው የትምህርት ቤት አውቶቡሶች (ሰርቪስ) በእርጅና የተጎሳቆሉ፣ የተማሪዎቹን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ በመሆናቸው፣ የአደጋ ሥጋት የሚያንዣብባቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ ልጆቻችን የሚማሩባቸውን ትምህርት ቤቶች ጥራትና ብቃት በጥንቃቄ እንደምንመርጠው ሁሉ፣ ስለሚጓጓዙበት ተሽከርካሪ ደኅንነትም ማሰብ ይገባናል፡፡

 ትምህርት ቤቶች በሚያቀርቧቸው የተማሪዎች ማመላለሻ አውቶቡሶች የሚታየው አጫጫንም ቢሆን ሥርዓት አልባ ሆኖ ይታያል፡፡ በልክ የሚጭኑበት ሥርዓት እስካልተከተሉ ድረስ ለአደጋ ተጋላጭነታቸው የጎላ ነው፡፡ ስለዚህ የተሽከርካሪዎቹን ደኅንነት የሚያረጋግጥ አሠራር ሊኖር ይገባል፡፡ አሽከርካሪዎቹም ማንነት እንዲሁ በሚገባ መረጋገጥና ሥነ ሥርዓታቸው፣ የትራፊክ ሕግ አክባሪነታቸው ሊፈተሽ ይገባል፡፡ ታክሲ ተኮናትረው የሚጠቀሙም ቢሆኑ፣ የተሽከርካሪውን ይዘትና የአሽከርካሪውን ማንነት በቅጡ አውቀው፣ ሊፈጠር ከሚችል አደጋ መታቀብ ይኖርባቸዋል፡፡

ለተማሪዎች ብቻ ተለይተው አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችን መመደብ ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ ሸገር የብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ለትምህርት ቤቶች ትራንስፖርት መስጠት እንደሚጀምር የተገለጸ ቢሆንም፣ እያደገ ካለው ፍላጎት አንፃር እንዲህ ያሉ አማራጮች ሊስፋፉ ይገባቸዋል፡፡

የትራንስፖርት አገልግሎቶችን በየጊዜው እያደገ ከሚመጣው ፍላጎት አኳያ በማጣጣም አዳዲስ አሠራሮችን ማስተዋወቅና ማስለመድ ፈርጀ ብዙ ጥቅም ሊያስገኝ ይችላል፡፡ የትምህርት ቤቶች የትራንስፖርት አቅርቦትም ቢሆን አንድ ወጥ አሠራር እንዲኖረው ማድረግ ይገባል፡፡ ለትራፊክ አደጋ መባባስ ምክንያት እንዳይሆንም እንዲህ ያለውን አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችን ብቃትና የቴክኒክ አቅም በመፈተሽ በየወቅቱ ማረጋገጫ የሚሰጥበት አሠራር መዘርጋትም ጥቅሙ ለሰፊው ሕዝብ ነው፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት