Tuesday, April 16, 2024

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መካከል በድጋሚ ያገረሸው ግጭት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ሥርዓት፣ ለብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር እስከ መገንጠል  መብት ይሰጣቸዋል፡፡ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ያቀፉት ዘጠኙ ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የራሳቸው አስተዳደራዊ ወሰን ኖሯቸው ክልላቸውን ወይም የከተማ አስተዳደራቸውን የማልማት፣ የማሳደግና ድንበራቸውን የመቆጣጠር ሥልጣንም ተሰጥቷቸዋል፡፡

እነዚህ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች እርስ በርሳቸው በሚያገናኙዋቸው አካባቢዎች ወሰኖች አሏቸው፡፡ ይሁንና ክልሎች ይህ መሬት ለእኔ ይገባኛል፣ በሚል ሰበብ ሲጋጩና ሲጣሉ ብዙ ጊዜ ይታያል፡፡ ለምሳሌ አፋርና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች በጋራ ወሰን አካባቢ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲጋጩ ታይቷል፡፡ በግጦሽ መሬት አማካይነት ደም ያፋሰሰ ግጭት ውስጥ ገብተው ያለፉበት ጊዜም ነበር፡፡ በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል ተመሳሳይ ችግሮች ነበሩ፡፡ በተለይ ሁለቱ ክልሎች በሚዋሰኑባቸው በጎንደርና በሌሎች አካባቢዎች ባለው የጋራ ወሰን ግጭቶች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ለዓመታት ሲያወዛግብ የነበረው በጠገዴና በፀገዴ መካከል የወሰን ይገባኛል ጥያቄ ብዙ ክርክሮችና ውዝግቦች አስነስቶ ቆይቷል፡፡ በአማራ ክልሉ የጠገዴ ወረዳና በትግራይ ክልል የፀገዴ ወረዳ መካከል ባለው የጋራ ወሰን ይገባኛል ጥያቄ ለዓመታት የዘለቀ ችግር ነበር፡፡ ይህን ችግር በቅርቡ፣ የሁለቱ ክልሎች አመራሮችና ሕዝቦች በመነጋገርና በመወያየት እንደፈቱት ቢነገርም፣ በሌሎች አካባቢዎች ተመሳሳይ ችግሮች ይታያሉ፡፡

በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች መካከል ያለው ውዝግብ ሌላው ማሳያ ነው፡፡ በኦሮሚያና በጋምቤላ መካከል ያለውም እንዲሁ፡፡ በኦሮሚያና በአማራ በተለይም በሰሜን ሸዋና በሌሎች አካባቢዎች ተመሳሳይ ችግሮች አሉ፡፡ በኦሮሚያና በደቡብ፣ በኦሮሚያና በአፋር ክልሎች መካከል ባለው አስተዳደራዊ ወሰን ምክንያት ግጭቶች ሲነሱና ከዚያም ታልፎ የሰው ሕይወት ሲጠፋና ደም ሲፈስ ይታያል፡፡ በተለይ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ መጠናቸው እየሰፋና እየገዘፈ መምጣቱን የተለያዩ ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡  

በኢትዮጵያ ሰፊ የቆዳ ስፋትና ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያለው ክልል ኦሮሚያ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ኦሮሚያ ክልል ሰባቱን ክልሎችና ሁለቱን የከተማ አስተዳደሮች የሚያዋስን ነው፡፡ ይህ ክልል ሰፊ ከመሆኑና ከትግራይ ክልል በስተቀር ሁሉንም የኢትዮጵያ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የሚያዋስን በመሆኑ ምክንያት፣ ከሚያዋስናቸው ክልሎች ጋር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአስተዳደራዊ ወሰን የማካለል ሥራ ሲያከናውን ነበር፡፡ ኦሮሚያ ክልል ከአማራ፣ ከቤንሻንጉል፣ ከጋምቤላ፣ ከአፋር፣ ከድሬዳዋ፣ ከአዲስ አበባና ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ጋር ውዝግቦች ነበሩበት፡፡ እነዚህ የወሰን ውዝግቦች ለዓመታት ሲንከባለሉና ደም አፋሳሽ ግጭቶች ውስጥ ሲያስገቡ ነበር፡፡

በአገሪቱ በ2008 ዓ.ም. ተከስቶ ለነበረው ቀውስ አንዱ ምክንያት በክልሎች መካከል ያለው አስተዳደራዊ ወሰን በቅጡ ባለመካለሉ ሳቢያ የሚነሱ ከማንነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ወቅታዊ ምላሽ አለመሰጠቱ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በዚህ መሠረት መንግሥት በ2009 ዓ.ም. አዲስ አወጣሁት ባለው የጥልቅ ተሃድሶ እንቅስቃሴ፣ ከፌዴራል እስከ ክልል እንዲሁም ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ባሉ የመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ ለመልካም አስተዳደር ቁርጠኛ ሆነው ሥራቸውን በተገቢው ሁኔታ አልሠሩም ያላቸውን አመራሮች አንስቷል፡፡ በዚህ ጥልቅ ተሃድሶ የአመራር ለውጥ ከተደረገባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ የኦሮሚያ ክልል ነው፡፡

የኦሮሚያ ክልል የክልሉን ርዕሰ መስተዳደር ጨምሮ ሌሎች ቁልፍ፣ ቁልፍ ቦታ ላይ የነበሩትን አመራሮችን በአዲስ ተክቷል፡፡ አቶ ለማ መገርሳ የሚመሩት የክልሉ አዲሱ አመራር ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ ከዚህ በፊት አይነኬ የሚመስሉ ጉዳዮችን ሲያከናውንና የክልሉን ችግር ዘላቂ በሆነ መንገድ ለመፍታት ደፋ ቀና ሲል ተስተውሏል፡፡ አዲሱ አመራር ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ የክልሉ ሕዝብና ወጣቶች በተደጋጋሚ ሲያነሱዋቸው የነበሩ ጥያቄዎችን ለመፍታት እየሞከረ ነው፡፡ ኦሮሚያ ከሚያዋስኑት ክልሎች ጋር ያለውን የአስተዳደራዊ ወሰን ችግር ለመፍታት ከቀድሞው በተለየ ሁኔታ ሲንቀሳቀስ ነበር፡፡ በክልሉ ውስጥ ለረዥም ዓመታት በባለሀብቶች ታጥረውና አይነኬ ሆነው የነበሩ መሬቶችን በመንጠቅ ለወጣቶች መስጠቱም ይታወሳል፡፡ በዚህም የተነሳ በብዙ የክልሉ ተወላጆች ዘንድ ሲሞካሽ ተደምጧል፡፡ እርግጥ ነው ከመጀመርያውም ጀምሮ እነዚህን አዳዲስ ጥረቶች በጥርጣሬ ያዩ አልጠፉም፡፡

የክልሉ አመራር በተለይ ከሚያዋስኑት ክልሎች አመራሮች ጋር በመነጋገር የአስተዳደራዊ ወሰን ችግሮችን ለመፍታት ትልቅ የቤት ሥራ አድርጎ መንቀሳቀሱም ይታወቃል፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ከቤንሻንጉልና ከጋምቤላ ብሔራዊ ክልሎች አመራሮች ጋር በመነጋገር ችግሮችን ለመፍታት ያደረገው ጥረት ነው፡፡ ከእነዚህ ክልሎች ጋር ያለው ሥራም ከሞላ ጎደል መጠናቀቁን የክልሉ መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አዲሱ አረጋ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መካከል ያለው አስተዳደራዊ ወሰን ከ85 በመቶ በላይ መጠናቀቁ ቢነገርም፣ እስከ ዛሬ ድረስ በሁለቱ አዋሳኝ አካባቢዎች ደም አፋሳሽ ግጭቶች ቀጥለዋል፡፡ በሁለቱ ክልሎች መካከል ያለው አስተዳደራዊ ወሰን በ1997 ዓ.ም. በሕዝብ ውሳኔ እንዲለይ መደረጉን የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር የሁለቱ ክልሎች አመራሮች ሚያዝያ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ባካሄዱት የዕርቅ ሥነ ሥርዓት ቢገልጽም ችግሩ እስከ ዛሬ ድረስ እንደቀጠለ ነው፡፡  

በሁለቱ ክልሎች መካከል ያለው የአስተዳደራዊ ወሰን ችግር የበርካታ ሰዎች ሕይወት የጠፋበት ግጭት አስከትሏል፡፡ በ2009 ዓ.ም. ከጥቅምት ወር ጀምሮ ለብዙ ወራት የዘለቁ ግጭቶች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ የሁለቱ ክልሎች አመራሮች ይህንን ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚፈቱት በሚያዝያ ወር 2009 ዓ.ም. አካሂደውት በነበረው የዕርቅ ሥነ ሥርዓት ላይ ተናግረው ነበር፡፡

የሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ሚያዝያ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. በፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር አዳራሽ ባካሄዱት የዕርቅ ሥነ ሥርዓት ላይ ‹አልፋና ኦሜጋ ዕርቅ› ማካሄዳቸውን ተናግረው ነበር፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹ይህን ስምምነት ከአሁን በኋላ የሚያፈርስ ካለ እንደ ጠላት ነው የምናየው፤›› ብለው ነበር፡፡ ‹‹ኦሮሚያ በቂ መሬት አለው፡፡ ሶማሌም በቂ ብቻ ሳይሆን ከበቂ በላይ አለው፡፡ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ግን በሆነ ትንሽ ቀበሌ ምክንያት የሰውን ደም ማፍሰስ ከዚህ በፊት ሆኗል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን መቼም እንደማይደገም እናረጋግጥላችኋለን፤›› በማለት ተናግረው ነበር፡፡ ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታትም በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚኖሩ ሕዝቦችን በልማት ማስተሳሰር ተገቢ እንደሆነ አስታውቀውም ነበር፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው፣ ‹‹ይህ የፀረ ሰላም ኃይሎች አጀንዳ ሆኖ የቆየው የወሰን ጉዳይና ከዚህ ጋር ተያይዞ የነበረው ነገር ለአንዴና ለመጨረሻ ተፈትቷል፤›› በማለት ተናግረው ነበር፡፡ ይህን ተመሳሳይ ባህል፣ ቋንቋና አኗኗር ያለው ሕዝብ በደም የተሳሰረና የተዋሃደ በመሆኑ ማንም ቢሆን ሊለያየው እንደማይችል ገልጸው ነበር፡፡ ‹‹በደረስንበት ደረጃ ሆኜ ሳስበው ድልም ነው፣ ውድቀትም ነው፡፡ ድሉ ምንድነው ካላችሁ የዘገየ ቢሆንም ከብዙ ጥፋት በኋላ ቢሆንም እዚህ ደረጃ ላይ መድረሳችን ሲሆን፣ ሌላው ትምህርት ልናገኝበት የሚገባ ትልቅ የአመራር ውድቀት ደግሞ ዛሬ የደረስንበት የስምምነት ፊርማ ላይ ቀደም ብሎ ደርሰን ቢሆን ኖሮ፣ ያላግባብ የጠፋውን ብዙ ሕይወት መታደግ እንችል ነበር፤›› ብለዋል፡፡ ይህንን የጋራ ኅብረተሰብም በልማት በማስተሳሰር የቆየ አብሮ የመኖር ልማዱንና ወጉን ማጠናከር ተገቢ እንደሆነ ጠቁመው ነበር፡፡

በወቅቱ የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር የነበሩት አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን በበኩላቸው፣ የአካባቢው አስተዳደርና ማኅበረሰብ በንቃት እንዲሳተፍበት በማድረግ በተከናወነው ሰፊ የማግባባት ሥራ ሕዝበ ውሳኔ ከተካሄደባቸው ቀበሌዎች ውስጥ የአብዛኞችን ስኬታማና ውጤታማ በሆነ  መንገድ መከለላቸውን ገልጸው ነበር፡፡ የሁለቱ ክልሎች አመራሮች ቁርጠኛ በመሆንና ሕዝቡን ማዕከል በማድረግና ውይይት በማካሄድ ቀሪ ሥራዎች መሥራት እንደሚገባ ማሳሰቢያም ሰጥተው ነበር፡፡

በዚህ ማሳሰቢያ መሠረትም የሁለቱ ክልሎች አመራሮች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት የሁለቱ ክልል ነዋሪዎች በድሬዳዋ ከተማ የውይይትና የዕርቅ ሥነ ሥርዓት ማካሄዳቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ ዕርቅ መሠረትም በ1997 ዓ.ም. በሁለቱ ክልሎች መካከል ያልተዋሰኑ አካባቢዎችን ሕዝቡን መሠረት ባደረገ መንገድ ሲከልሱና ሲወስኑ ቆይተዋል፡፡ በዚህ መሠረት ሁለቱ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ ሲያነሱባቸው ከነበሩ የአስተዳደራዊ ወሰን ጉዳዮች መካከል ከ85 በመቶ በላይ ማካለል እንደተቻለ መረጃዎች ይመለክታሉ፡፡ 

ከሁለቱ ወገኖች በኩል ሲሰማ የነበረው ጉዳይ ይህ ቢሆንም ድንገት ሳይታሰብ ከአሥር ቀናት በፊት በሁለቱ ክልሎች መካከል ባሉ አዋሳኝ አካባቢዎች፣ በተለይም የኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ውስጥ ባሉ ወረዳዎችና የኢትየጵያ ሱማሌ ክልል የሚያዋስኑ አካባቢዎች ግጭቱ እንደገና አገርሽቷል፡፡ በዚህ ግጭትም የበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱንና ከሃያ ሺሕ በላይ ዜጎች ከቀያቸው እንደተፈናቀሉ ተነግሯል፡፡

የዚህ ግጭት መንስዔው ምን እንደሆነ መንግሥት ቁርጥ ያለ ነገር ባይናገርም፣ ክልሎች እርስ በርሳቸው መወነጃጀልና አንዱ ክልል ሌላውን ጥፋተኛ ወደ ማድረግ ደርሰዋል፡፡ ግጭቱ የተከሰተባቸው አካባቢዎች ከጉርሱም እስከ ሞያሌ ከ1,200 ኪሎ ሜትር በላይ ወሰን የሚጋሩ አካባቢዎች ናቸው፡፡ በአካባቢው የሚኖሩ ሕዝቦች በጋብቻ የተሳሰሩ ጭምር በመሆናቸው፣ ለግጭት የማያበቃ ጉዳይ እንደሌላቸው አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ አንድ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊ ጉዳዩን ሲገልጹት፣ ‹‹በሁለቱ ክልል አመራሮች መካከል እየተቆሰቀሰ ያለ እሳት እንጂ በሕዝቦች መካከል አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ነጋሶ ጊዳዳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹ይህ ችግር የሚፈታበት ዘዴ በሕገ መንግሥቱ ላይ ሠፍሮ እያለ ከሁለቱ ወገኖች ይህን ያህል ሰው ማለቅ የለበትም ነበር፤›› ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው እየተንቀሳቀሱ ያሉ ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሪፖርተር በላኩት መግለጫ ላይ በግጭቱ ምክንያት ከመኖሪያ ቤታቸው የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን ወደ መኖሪያ ሠፈራቸው በመመለስ፣ ከተቋቋሙና ከተረጋጉ በኋላ በሕዝቡ ነፃ ፍላጎት፣ እንዲሁም በሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ወገኖች ጋር በመሆን ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ጠይቀዋል፡፡ የኦሮሞና የሶማሌ ሕዝቦችን የጋራ ትስስርንና አብሮነት በምንም መልኩ አሳጥሮ መግለጽ እንደማይቻልም ገልጸዋል፡፡  የአሁኑ ችግር የሕዝብ ለሕዝብ ሳይሆን የፀረ ሰላም ኃይሎች ችግር መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሶማሌና የኦሮሚያ ክልል በሞያሌ በኩል በመንገድ ብቻ እንደተከለሉ አስታውሰዋል፡፡ ከዚህ መለስ የኦሮሞ፣ ከዚህ መለስ የሶማሌ ተብሎ መንገድ የሚከለልለት ከተማ ነው ያላቸው፡፡ ነገር ግን ኅብረተሰቡ አንድ ነው፡፡ አብሮ የሚኖር ሕዝብ ነው፡፡ ልትነጣጥለው የምትችለው ሕዝብ አይደለም፤››  በማለት አስረድተዋል፡፡

‹‹ድሬዳዋ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ሶማሌና ኦሮሞ ነው በጋራ እያስተዳደሯት ያሉት፡፡ ድሬዳዋን የመሰለ ከተማ ዕጣ ፈንታዋ ምንድነው የሚሆነው የሚለው ነገር በጣም ያሳስበናል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ዶ/ር ጫኔ ይህን ችግር በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው እንደዚህ ዓይነት ግጭት የሚነሳባቸውን አካባቢዎች በአግባቡ መምራት የማይችሉ ክልሎች ካሉ፣ በፌዴራል መተዳደር እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ ድሬዳዋ ለምሳሌ በፌዴራል መንግሥት መተዳደር እንደሚገባት፣ አዲስ አበባ ደግሞ ወደፊት ሌላ የግጭት ማዕከል ትሆናለች ተብሎ እንደሚያሠጋ ገልጸዋል፡፡

በሚያዝያ ወር 2009 ዓ.ም. ተካሂዶ የነበረው የዕርቅ ሥነ ሥርዓት ተሽሮ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች አሁን ይህን ያህል ደም አፋሳሽ ግጭት ይከሰታል ብሎ ያሰበ ሰው እንዳልነበረ አስተያየት ሰጪዎች ሲናገሩ እየተደመጠ ነው፡፡ የሁለቱ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮችና ሕዝቦች በድሬዳዋና በሌሎች አካባቢዎች የቀሩ የወሰን ጉዳዮችን ለመፍታት ሲመክሩ ሰንብተው፣ አሁን ግን ወደ ሌላ ደም አፋሳሸ ግጭት ውስጥ ገብተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ይባስ ብሎ ጉዳዩ በሰከነ መንገድ እንዲበርድ ከመሥራት ይልቅ፣ ክልሎቹ እርስ በራሳቸው በመወነጃጀልና ጥፋተኛ በመባባል ላይ የተጠመዱ ነው መሆናቸው ብዙዎችን አሳስቧል፡፡ ይህ መወነጃጀል ማቆሚያውስ የት ነው እየተባለ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሐሙስ መስከረም 4 ቀን 2010 ዓ.ም. መግለጫ አውጥቶ ነበር፡፡ የመግለጫው መግቢያ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሕዝብና መንግሥት የአገሪቱን የፌዴራል ሥርዓት በመጠበቅና ዘብ በመቆም ቆይቷል ይላል፡፡ ‹‹የክልላችን ሕዝብና መንግሥት በብዝኃነት ላይ የተመሠረተውን ልዩነት በማክበር በመቻቻልና በመፈቃቀር ለዘመናት ከብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በጋራና በጥሩ ጉርብትና አምኖና ተባብሮ የሚኖር ጨዋ ሕዝብ ነው፤›› ካለ በኋላ፣ ክልሉ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች በኦሮሚያ ክልል መንግሥት የሚደገፍና በክልሉ በታጠቁ ኃይሎች፣ በክልሉ ፖሊስ፣ ማሊሻና አሸባሪው የኦነግ ቄሮ አባላት በተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈጽሙና ወረራ ሲያካሂዱ መቆየታቸውን አብራርቷል፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በበኩሉ፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያወጣውን መግለጫ እጅግ በጣም አሳፋሪና ኃላፊነት በጎደለው መንገድ የቀረበ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ ‹‹መግለጫው አሁን ያለውን ችግር ከማርገብ ይልቅ ወደ ሌላ አቅጣጫ ሊወሰድ የሚችልና አገርን ከሚያስተዳድር ትልቅ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ይሰጣል ተብሎ የማይጠበቅ አሳፋሪ መግለጫ ነው፤›› ሲል አጣጥሎታል፡፡ መግለጫው የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የተጣለበትን ሕዝባዊና መንግሥታዊ ኃላፊነት ከመሸከም አንፃር ያለበትን ደካማ ቁመናና ዝቅተኛ ደረጃ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ከመግለጫው ስህተቶች አንዱ ራሱን የፌዴራል ሥርዓቱ ብቸኛ ዘብና ጠባቂ አድርጎ የማቅረቡ ጉዳይ እንደሆነ ጠቅሷል፡፡ ሁለተኛው የመግለጫው ስህተት አድርጎ የወሰደው ደግሞ ኦሮሚያ ክልልን ‹‹የኦሮሞ ክልል›› ብሎ ከሕገ መንግሥቱ ውጪ መሰየሙን አስታውሷል፡፡ ‹‹መግለጫው ይህን አጻጻፍ የተከተለው የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልልን ‹የኦሮሞዎች ብቻ› እንደሆነችና ሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችን የማታቅፍና አግላይ አስመስሎ የማቅረብ አደገኛ ተልዕኮ ያለው አጻጻፍ ነው፤›› ሲልም ኮንኗል፡፡

የመግለጫው ሦስተኛ ስህተት አድርጎ የወሰደው ደግሞ የክልሉን መንግሥት በአሸባሪነትና በኦነግነት መፈረጁ እንደሆነ ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የወጣው መግለጫ ያመለክታል፡፡ መግለጫው ኦሮሚያና የኦሮሞ ሕዝብ የኢትዮጵያ አንድነት ምሰሶዎች መሆናቸውን ጠቅሶ የክልሉ አመራሮችም ለፌዴራላዊ ሥርዓቱ ማበብና መጎልበት፣ የሕዝቦች ወንድማዊ ግንኙነትና እኩል ተጠቃሚነት እንዲሰፍን ለማድረግ እየታገለና መስዋዕት እየከፈለ ያለ የሕዝብ ልጅ እንጂ፣ በአሸባሪነትና በኦነግነት የሚፈረጅ እንዳልሆነ አስገንዝቧል፡፡

የኢትዮጵያ ሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በመግለጫው ላይ በኦሮሚያ ክልል ነዋሪ በሆኑ የሶማሌ ተወላጆች ላይ የዘረኝነት ጭፍጨፋ የተጀመረው፣ በተለይ በአወዳይ ከተማ ረቡዕ መስከረም 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ከ50 በላይ ንፁኃን ዜጎች ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ አካላቸውን በመቆራረጥና በእሳት በማቃጠል ሕይወት መቀጠፉን አስታውቋል፡፡ ከሦስት መቶ በላይ የሚሆኑ ደግሞ በመከላከያ ሠራዊት ኃይል ሕይወታቸው እንዲተርፍና ወደ ሐረር እንዲገቡ መደረጉን ገልጿል፡፡ ሐሙስ መስከረም 4 ቀን 2009 ዓ.ም. የ30 ዜጎች የተቆራረጠና የተቃጠለ ሬሳ ወደ ክልሉ መሄዱን ጠቁሟል፡፡ ክልሉ ዓርብ መስከረም 5 ቀን 2010 ዓ.ም. በይፋ የቀብር ሥነ ሥርዓት ማከናወኑ ተገልጿል፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ከላይ ያለውን መግለጫ የማይቀበለው መሆኑን ገልጾ፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ግጭትን በሚያባብሱ አደገኛ ቃላትንና በተጋነኑ ውሸቶች መሞላቱን አመልክቷል፡፡ በተፈጠረው ግጭት የሰው ሕይወት መጥፋቱን አስታውሶ፣ በዚህ ረገድ ግን ኦሮሞም ይሁን ማንም ሰው መሞት የሌለበት መሆኑን አብራርቷል፡፡ ለዜጎች የሕይወት መጥፋት እጃቸው ያለባቸው ሰዎች ለሕግ መቅረብ አለባቸው ብሎ የሚያምን መሆኑን ጠቅሷል፡፡ ‹‹መስከረም 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ከጉርሱም ወደ ሐረር እየተጓዙ ያሉ ሰላማዊ የኦሮሞ ተወላጆችን የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የፀጥታ አካላት ቦምባስ ከተማ ኬላ ላይ ይዘው ያስራሉ፡፡ እነዚህ ታሳሪዎች አቶ ሰለማ መሐመድ (የጉርሱም ወረዳ አስተዳዳሪ የነበሩ)፣ አቶ ታጁዲን ጀማልና ሌሎች ሁለት ሰዎች በነጋታው በደረሰባቸው ድብደባ መሞታቸው ተሰማ፡፡ የሰላማዊ ሰዎች ያልተጠበቀ ሞት የምሥራቅ ሐረርጌ ነዋሪዎችን በማስቆጣቱ በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን አወዳይ፣ ደደር፣ ቆቦና መልካ ራፉ ከተሞች ያልተጠበቀ የሕዝብ ቁጣና ሠልፍ አስከተለ፡፡ በተለይ አወዳይ የነበረው ሠልፍ ወደ ግርግር ተሸጋገረ፡፡ በተፈጠረው ግርግርም የ18 ሰዎች ሕይወት ሊያልፍ ችሏል፡፡ በዚህ ግርግር ሕይወታቸውን ካጡት 18 ሰዎች 12 የሶማሌ ተወላጅ ወንድሞቻችን ሲሆኑ፣ ስድስቱ ደግሞ የጃርሶ ጎሳ ተወላጅ ኦሮሞዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ድንበር ላይ እየተፈጸመ ካለው ጥቃት ጋር ምንም ተያያዥነት የሌላቸው፣ በላባቸው ሠርተው የሚያድሩ ሰላማዊ ዜጎች ናቸው፤›› ሲል መግለጫው አስታውቋል፡፡ የሶማሌ ክልል ገለጻም ፍፁም ተቃራኒ የሆነን ምክንያት ለግጭቱ መነሻ ማድረጉን ይገልጻል፡፡ በዚህ ድርጊት ተሳትፈዋል ተብሎ የተጠረጠሩ 200 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑንም የኦሮሚያ ክልል መግለጫ ጠቅሷል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ዓርብ መስከረም 5 ቀን 2010 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፣ በሁለቱ ክልሎች መካከል የተቀሰቀሰውን ግጭት ለማስቆም የመከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ አባላት በአካባቢው እንዲሠፍሩ ተደርጓል፡፡ በዚህ ግጭት ቁጥራቸው እስካሁን በውል ያልታወቀ ዜጎች መሞታቸውን ጠቅሰው፣ ከሃያ ሺሕ በላይ ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን አረጋግጠዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግጭቱ ሙሉ በሙሉ ቆሟል ብሎ መናገር እንደማይቻል፣ ከአሁን በኋላም ግጭት እንዳይከሰት የፌዴራል መንግሥት እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የዚህ ችግር መሠረታዊ ምክንያት የወሰን ማካለል ብቻ እንደማይሆን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ ጉዳዩ ተጣርቶ ወደፊት የሚገለጽ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሸን ቢሮ ኃላፊን ለማናገር የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር የተከሰተውን ግጭት በተመለከተ እያከናወነ ያለውን ለማወቅ የተደረገው ጥረትም አልተሳካም፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -