አገርን ከቀውስ ወደ ቀውስ በማሸጋገር ትርምስ መፍጠር አልበቃ ብሎ አሁን ደግሞ በዜጎች ውድ ሕይወት ላይ መቆመር ያሳዝናል፡፡ የኢትዮጵያዊነት የጋራ መገለጫ የሆኑት ጨዋነት፣ አስተዋይነትና አርቆ አሳቢነት ወደ ጎን እየተገፉ ግንፍልተኝነትና ግትርነት እየገነኑ ነው፡፡ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች መካከል የተፈጠረው ደም አፋሳሽ ግጭት በተቻለ መጠን በፍጥነት ካልቆመ፣ ሕዝብን ለዕልቂት አገርን ደግሞ ለማያባራ ጦርነት ይዳርጋል፡፡ ከዚህ ቀደም የበርካታ ወገኖችን ሕይወት የቀጠፈ፣ ለአካል ጉዳት የዳረገና ለመፈናቀል ያበቃ የሁለቱ ክልሎች የወሰን ግጭት በፌዴራል መንግሥት ማግባባት በሰላማዊ ስምምነት መቋጨቱ ይታወሳል፡፡ ውይይትና መደማመጥ ሲኖር ከግጭት ይልቅ ሰላምና መረጋጋት ይፈጠራል፡፡ በሚያዝያ ወር 2009 ዓ.ም. የተደረገው ስምምነት የሁለቱን ክልሎች አመራሮች ቁጭት ውስጥ በመክተት ዳግም ወደ ግጭት ላለመግባት ቃል አስገብቶ ነበር፡፡ ይህ በፀፀት የተሞላ ስምምነት ከጥቂት ወራት በኋላ ተጥሶ እንደገና ሌላ ዙር ግጭት ተቀስቅሶ በርካታ ንፁኃን ዜጎቻችን ተገድለዋል፡፡ እጅግ በጣም ያሳዝናል፣ ያሳምማል፡፡ ይህ ኩሩና ጨዋ ሕዝብ መቼም ቢሆን የመረረ ጥላቻ ውስጥ ገብቶ አይጋጭም፡፡ የሕዝብ ችግር ነው ብሎም ማሳበብም አይቻልም፡፡ ችግሩ ያለው ፖለቲከኞች ዘንድ ነው፡፡
ከአዲሱ ዓመት ዋዜማ ጀምሮ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ሥፍራዎች ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ኃላፊነት የጎደላቸው ድርጊቶች ተፈጽመዋል፡፡ ክልሎቹን የመምራት ሕዝባዊ ኃላፊነት ያለባቸው ወገኖች እጅግ በመረሩ ቃላት ሲወጋገዙ ተሰምተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ሰላም አስፍነው የተፈጠረውን ችግር በሕጋዊ መንገድ ለመፍታት የተስማሙ ወገኖች፣ ልዩ ኃይሎቻቸውን አሠልፈው ተዋጉ ሲባል ምን ማለት ነው? በሰከነ መንገድ ተወያይቶ መፈታት ያለበትን ችግር ከመጠን በላይ እያጦዙ በቃላት መወራረፍና ሌላ ዙር ግጭት ለማስነሳት መጣደፍ ምን የሚሉት ነው? የግጭት አፈታት ሥርዓቶችን ተጠቅሞ መፍትሔ መፈለግ ሲገባ የአገር ሰላምን ማተራመስ ለማን ይጠቅማል? ከሕጋዊው መንገድ ይልቅ ይኼኛው ለምን ተመረጠ? ለዘመናት ተጋብቶና ተዋልዶ አብሮ የሚኖር ሕዝብን መበጥበጥ ምን የሚሉት በሽታ ነው? በሕገ መንግሥቱ መሠረት ከክልሎች በውክልና የመላ አገሪቱን ሥልጣን የያዘው የፌዴራል መንግሥትስ ምን እያደረገ ነው? የአገሪቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሲቪክና የሙያ ማኅበራት፣ ምሁራን፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና የመሳሰሉት የኅብረተሰብ ክፍሎች ምን እያደረጉ ነው? የሕዝብ ሕይወት እየተቀጠፈና የአገር ሰላም እየደፈረሰ እንዴት ዝም ይባላል? በፍጥነት መልስ የሚያስፈልገው ጊዜ ላይ ነን፡፡ በታሪክ ያስጠይቀናል፡፡
አሁን ትልቁና አንገብጋቢው ጉዳይ የተፈጠረውን ቀውስ ከፖለቲካ የገመድ ጉተታ ማላቀቅ ነው፡፡ ይህ ኩሩና ጨዋ ሕዝብ ችግር ሲፈጠር ወይም ቀውስ ሲያጋጥም የሚፈታበትን የሽምግልና ሥርዓት በሚገባ ያውቃል፡፡ ሕዝባችን የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የባህልና የአመለካከት ልዩነቶችን እንዴት አስተናግዶ መኖር እንደሚችል ለዘመናት በተግባር ያሳየ ከመሆኑም በላይ፣ የግጭት አፈታት ሥርዓቱም አስደናቂ ነው፡፡ ይህንን ተምሳሌታዊ አገር በቀል ዕውቀት ገሸሽ እያደረጉ ሕዝቡን ለዕልቂት መዳረግና አገርን ማተራመስ ግን ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው፡፡ በትውልድም በታሪክም ያስጠይቃል፡፡ ትናንት በተፈጸሙ አስከፊ ድርጊቶች ተፀፅተናል እንዳልተባለ፣ ዛሬ ያ ሁሉ ተረስቶ ይህ አስተዋይና አርቆ አሳቢ ሕዝብ ለጉዳት ሲዳረግ ማየት ያንገበግባል፡፡ ለመሆኑ የአሁኑ ግጭት መነሻ ምን እንደሆነ ይታወቃል? ታጣቂዎች በየቦታው ተሰማርተው አሰቃቂ ድርጊት ሲፈጽሙስ ከልካይ አልነበረም? የትናንቱ በፀፀት የታጀበ ስምምነት የማያዳግም መፍትሔ አስገኘ ከተባለ በኋላ እንደገና አገርሽቶ የንፁኃን ወገኖቻችንን ሕይወት ሲቀጥፍ ምላሹ ምን ይሆን? ይኼ እንቆቅልሽ በአስቸኳይ መፈታት አለበት፡፡ አሁን ባለው አሳፋሪና አስደንጋጭ ሁኔታ መቀጠል አይቻልም፡፡
በአሁኑ ጊዜ በጣም አሳሳቢ የሆነው የሁለቱ ክልሎች አመራሮችና የፌዴራል መንግሥት ኃላፊዎች እንዴት ተቀምጠው መነጋገር አዳገታቸው የሚለው ነው፡፡ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ውስጥ ከሚኖሩ ዜጎቻችን በተጨማሪ፣ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሚኖሩ ዜጎችም ጭንቀት ውስጥ ናቸው፡፡ በሁለቱ ክልሎች ሹማምንት መካከል የተደረጉት አላስፈላጊ የቃላት ልውውጥ ግጭትን የሚያባብሱና የሌሎች ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት የሚጋብዙ ናቸው፡፡ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያ (ፌስቡክ) ላይ ሥራዬ ብለው የተሰማሩ ኃይሎች አጋጣሚውን በመቀጠም ግጭቱን ሌላ ገጽታ እያላበሱት ነው፡፡ ከሁለቱ ክልሎችና ከፌዴራል መንግሥት ቁጥጥር ውጪ እየሆኑ ያሉት እሰጥ አገባና ተደጋጋሚ ግጭቶች፣ ሕዝብን ለዕልቂት አገርን ለትርምስ ብሎም ለውድመት እንደሚያጋልጡ ማሰብ እንዴት ያዳግታል? አሁን ባለው ሁኔታ ማንም ብቻውን አሸናፊ እንደማይሆን ማመን ተገቢ ነው፡፡ ይልቁንም ሕይወታቸውን ባጡ ወገኖቻችን ቁጥር ወይም ብዛትና አሰቃቂነት ላይ የቃላት ጨዋታ ከመደርደር፣ አጥፊዎችን ለሕግ ማቅረብና የተጎዱትን በአስቸኳይ መልሶ ማቋቋም ይቅደም፡፡ የአንድ ሰው ሕይወት መጥፋት ሊያንገበግበን ይገባል እንጂ ‹ይኼን ያህል ነው፣ ይኼን ያህል አይደለም› እየተባለ መቋሰል ለማንም አይጠቅምም፡፡ ኃላፊነትን ለማኅበራዊ ሚዲያ አሳልፎ በመስጠት እሳት ላይ ነዳጅ ማርከፍከፍ የሕዝብን ሰቆቃ ያባብሳል፡፡ የአገርን ሰላም ያናጋል፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡ ከምንም በላይ መደመጥ ያለበት የሕዝብ የልብ ትርታ ብቻ ነው፡፡ ሕዝብ ደግሞ ከምንም ነገር በላይ የሚፈልገው ሰላም ነው፡፡ ሰላም ለሁሉም መባል አለበት፡፡
በአገሪቱ አዛውንቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ምሁራን፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖችና የመሳሰሉት ዝምታቸውን መስበር አለባቸው፡፡ የአገርን ጉዳይ ችላ በማለት በዝምታ መሸበብ ማብቃት አለበት፡፡ ፖለቲከኞች ለያዥ ለገናዥ አስቸግረው የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ሲደርሱ መገሰጽና ማስማማት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ፖለቲከኞችም ከእልህና ከግትርነት በመላቀቅ ለውይይትና ለድርድር ራሳቸውን ማስገዛት አለባቸው፡፡ በስህተት ላይ ሌላ ስህተት መጨመር ትርፉ ውድቀት ነው፡፡ በተለይ የሁለቱ ክልሎች አመራሮች በማኅበራዊ ሚዲያ ጭምር የሚሰነዘሩ አላስፈላጊ መወጋገዞችንና የስም ማጥፋት ዘመቻዎችን ማስቆም አለባቸው፡፡ የሁለቱም ክልሎች የሕዝብ ተወካዮችና የምክር ቤት አባላት ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ኅብረ ብሔራዊው የፌዴራል ሥርዓት እየተገነባ ነው እየተባለ የእንቧይ ካብ ማድረግ ለማንም እንደማይጠቅም መግባባት ያስፈልጋል፡፡ ውጥረቱ ይርገብ፡፡ ራስን በራስ ማስተዳደር፣ በራስ ቋንቋ መማርና መዳኘት፣ የገዛ ባህልን መጠቀምና ማሳደግ የመሳሰሉትን ፀጋዎች ማበላሸት አይጠቅምም፡፡ የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ሕዝቦች ተዋሳኝ ከመሆን ባለፈ ወንድማማቾች ናቸው፡፡ ከዚያም አልፈው ተርፈው ተጋብተው የተዋለዱ ናቸው፡፡ በአኗኗራቸውም ሆነ በሥነ ልቦና በጣም ተቀራራቢ ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖቻችን እንዲጋጩ ማድረግ ኃጢያት ነው፡፡ ችግር ቢፈጠር እንኳ በቀላሉ መፍታት ይቻላል፡፡ አሁን እያስቸገረ ያለው የፖለቲከኞች ግትርነት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በታሪክና በትውልድ የሚያስጠይቅ ነው፡፡ የገዛ ወገኑን ገድሎ የሚፎክር ሕዝብ የለንም፡፡ ይህ ሕዝብ ጨዋና ኩሩ ከመሆኑም በላይ በሰብዓዊነት የተሞላ ነው፡፡ ይህንን የመሰለ ታላቅ ሕዝብ በሥርዓት ለመምራት አለመቻል ሊያስቆጭ ይገባል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱን ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት ጌጥ ማድረግ ሲገባ አፍራሽ ድርጊት መፈጸም ያሳምማል፡፡ የአፍሪካውያን መሰባሰቢያ የሆነችውን ይህችን ታላቅ አገር በአንድነት ማሳደግ ሲገባ፣ ያልተገባ ድርጊት መፈጸም ይቅር የማይባል ነው፡፡
መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አገርን ለትርምስ ብሎም ለበለጠ ጥፋት የሚያጋልጠውን ይህንን ግጭት ለማስቆም ድምፁን ማሰማት አለበት፡፡ ‹የመሪ እንጂ የተመሪ መጥፎ የለውም› እንዲሉ ከእዚህ ግጭት ጀርባ እጃቸው ያለበት በሕግ እንዲጠየቁ፣ ግጭቱን የሚያባብሱ መግለጫዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ወይም ፈር እንዲይዙ፣ በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ላይ ቁጣ የፈጠሩ ድርጊቶች በፍጥነት እንዲወገዱ፣ የሁለቱ ክልሎች መሪዎች በፍጥነት ለድርድር እንዲቀመጡና ዘላቂ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈጠር ጫና ማሳደር ተገቢ ነው፡፡ ለሒደቱ መፋጠን አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግም የግድ ነው፡፡ የአሁኑን አሳዛኝና አስከፊ አጋጣሚ በመጥለፍ የፖለቲካ መጫወቻ ለማድረግ የሚፈልጉ ኃይሎችን ወደ ጎን በማለት ለሕግ የበላይነት መስፈን አስተዋጽኦ ማድረግ ይገባል፡፡ የፌዴራል መንግሥትና የሚመለከታቸው ተቋማትም ከምንም ነገር በላይ ለዚህ ችግር እልባት ለመስጠት ሙሉ ጊዜያቸውን መጠቀም አለባቸው፡፡ የአገር ጉዳይ የሚመለከታቸው ዜጎች በሙሉ ለዚህ ጥረት ሙሉ ድጋፋቸውን ይስጡ፡፡ በእሳት ላይ ነዳጅ በማርከፍከፍ የንፁኃን ሕይወትን የመቅጠፍና አገር የማተራመስ አጀንዳ ያላቸው ኃይሎች ደግሞ ቀዳዳው ይደፈንባቸው፡፡ በመልካም ምኞት ልውውጥ የተጀመረው አዲሱ ዓመት ሲንከባለሉ በመጡ ችግሮች ምክንያት የግጭት መናኸሪያ አይሁን፡፡ በዚህ አሳዛኝ ግጭት ሕይወታቸው ያለፈ ንፁኃን ነፍሳቸው በሰላም እንዲያርፍ፣ ጉዳት የደረሰባቸው ከጉዳታቸው በፍጥነት እንዲያገግሙ፣ በኃይልና በሥጋት የተፈናቀሉ በአስቸኳይ ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ፣ አጥፊዎች በሕግ እንዲዳኙ፣ የደፈረሰው ሰላም በመረጋጋት ተተክቶ በእኩልነትና በመከባበር ላይ የተመሠረተች ዴሞክራሲያዊት አገር እንድትኖረን በጋራ ለጋራ ዓላማ መቆም አለብን፡፡ ይህንን ቸል ብሎ ሕዝብን ለግጭት አገርን ለትርምስ መዳረግ በታሪክም በትውልድም ያስጠይየ()
Editorial
ቃል!