Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሃያ ሁለት መግቢያ በሮች የሚገቡ የኤርትራ ስደተኞች ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱ ተገለጸ

በሃያ ሁለት መግቢያ በሮች የሚገቡ የኤርትራ ስደተኞች ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱ ተገለጸ

ቀን:

በባድመ የድንበር ይገባኛል ጥያቄ አማካይነት በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ደም አፋሳሽ ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ከ1990 ዓ.ም. ወዲህ፣ በሃያ ሁለት መግቢያ በሮች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ኤርትራውያን ስደተኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣቱ ተጠቆመ፡፡

የስደተኞችና ከስደት ተመላሽ ጉዳዮች አስተዳደር የሕግና ፕሮቴክሽን መምርያ ኃላፊ አቶ እስጢፋኖስ ገብረ መድኅን ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በሚያዚያ ወር ብቻ በቀን ከ350 በላይ ኤርትራውያን ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ኤርትራውያን ስደተኞች ቁጥር ከሚያዝያ ወር ጀምሮ እየጨመረ መምጣቱንም ጠቁመዋል፡፡

አቶ እስጢፋኖስ እንደገለጹት፣ ኤርትራውያን ስደተኞች በአሁኑ ወቅት ሃያ ሁለት መግቢያ በሮችን በመጠቀም ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ነው፡፡ የኤርትራ መንግሥት በድንበር አካባቢ ጥብቅ ቁጥጥር እያደረገ ቢሆንም፣ ስደተኞቹ ወደ ኢትዮጵያ ከመግባት እንዳልተቆጠቡ አስረድተዋል፡፡  

እንደ አቶ እስጢፋኖስ ገለጻ፣ ለጥበቃ ተብለው ድንበር ላይ የተመደቡ ወታደሮች ሳይቀሩ ሸሽተው ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ነው፡፡ ሃያ ሁለቱን የመግቢያ በሮች በመጠቀም ሕፃናት፣ እናቶች፣ ዶክተሮች፣ መምህራን፣ ኢንጂነሮች፣ ወጣቶችና ሌሎት የኅብረተሰብ ክፍሎች ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ እንደሆነ አክለዋል፡፡  

በሥርዓቱ ውስጥ አሁን ያለው አስገዳጅ ውትድርና የኢኮኖሚ ነፃነት ባለመኖር፣ የሕዝቡ በነፃነት የመሥራትና የመንቀሳቀስ ዕድሎች ባለመኖርና በሌሎች ተያያዥ ችግሮች ኤርትራውያኑ ወደ ኢትዮጵያ ለመሰደድ ምክንያት እንደሆኑዋቸው አቶ እስጢፋኖስ ተናግረዋል፡፡ 

ወደ ኢትዮጵያ ከሚገቡ ኤርትራውያን ስደተኞች መካከልም 40 በመቶ ያህሉ ወታደሮች እንደሆኑ አቶ እስጢፋኖስ ገልጸው፣ ኤርትራውያን ስደተኞችን ለመቀበልም በኢትዮጵያ ስድስት የመጠለያ ጣቢያዎች እንዳሉና ከእነዚህ መካከልም አራቱ በትግራይ፣ ሁለቱ ደግሞ በአፋር ክልሎች እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜም በዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት የተመዘገቡ 194,443 ኤርትራውያን ስደተኞች በኢትዮጵያ እንደተጠለሉ አቶ እስጢፋኖስ ገልጸዋል፡፡ በኤርትራ ውስጥ ካሉ ዘጠኝ ብሔረሰቦች መካከልም ስምንቱ በኢትዮጵያ ተመዝግበው እንደሚገኙ አክለዋል፡፡  

ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ኤርትራውያን ስደተኞችን አያያዝ በተመለከተ  ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት እዚያ ያለውን ሥርዓትና ሕዝብ ይለያል፡፡ የፖሊሲያችን ማዕቀፍም ሕዝቡንና ሥርዓቱን ለይቶ የሚያይ ነው፤›› በማለት ለስደተኞቹ ጥሩ አቀባበል ይደረግላቸዋል ብለዋል፡፡

‹‹እንግዳ ተቀባይ ሕዝባችን ስደተኞችን ከተቀበላቸው በኋላ መንግሥት ካምፕ በማስገባት አስፈላጊ የሆነ ምዝገባ አድርጎና አሻራ ወስዶ ተገቢውን እንክብካቤ ያደርግላቸዋል፤›› ሲሉም አቶ እስጢፋኖስ አስረድተዋል፡፡ ስደተኞቹ ካምፕ ከገቡ በኋላም በአገራቸው የማያገኙት የነበረውን የሃይማኖት ነፃነት እንዲያገኙ ከማድረግ በተጨማሪ፣ በተለያዩ የትምህርትና የሥልጠና መስኮች እንዲሳተፉ እንደሚደረግ አቶ እስጢፋኖስ ገልጸዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ