ጽንፈኝነት ከስያሜው ጀምሮ ምቾት አይሰጥም፡፡ የራስን ፍላጎት በሌሎች ላይ የመጫን ወይም የማስገደድ አባዜ የተጠናወተው የኋላቀርነት መገለጫ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ወይም በሃይማኖት ሽፋን ውስጥ ሆኖ ሥልጣን ወይም የኢኮኖሚ የበላይነት ለማግኘት እንደ መሣሪያ ያገለግላል፡፡ ይህ አስተሳሰብ በቀኝ ወይም በግራ፣ እንዲሁም አማካይ ሥፍራ ካሉ አስተሳሰቦች በማፈንገጥ የከረሩ አቋሞችን ይወክላል፡፡ በዚህም ሳቢያ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመዘዙ ሐሳቦችን ካለመቀበሉም በላይ፣ ራሱ በተቃኘበት መንገድ ብቻ በመንቀሳቀስ ሌሎችን መደፍጠጥ ይፈልጋል፡፡ የጽንፈኝነት አስተሳሰብ ‹ከእኔ ወይም ከዚያ ምረጥ› የሚል አጣብቂኝ መፍጠርና ተቃራኒን በማናቸውም ዘዴ ማፈን ወይም ማስወገድ ዋናው መገለጫው ነው፡፡ ዛሬ በዓለም ዙሪያ የሚታዩ ጽንፈኛ ኃይሎች ለዴሞክራሲያዊ እሴቶች ዋጋ ባለመስጠት ፍላጎታቸውን በኃይል ያስፈጽማሉ፡፡ ንፁኃንን በጅምላ ሰለባ የሚያደርጉ የሽብር ተግባራትን ይፈጽማሉ፡፡ በዚህ በሠለጠነ ዘመን ጽንፈኝነት ምን ያህል እንደማይበጅ እየደረሱ ካሉ አሳዛኝ ድርጊቶች መገንዘብ በጣም ቀላል ነው፡፡
ወደ አገራችን አጠቃላይ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች መለስ ስንል በርካታ ውጥንቅጦች ይታያሉ፡፡ በፖለቲካው መስክ ልዩነቱ ከመጦዙ የተነሳ በጠላትነት መፈራረጅ የበርካታ ዓመታት ልምድ ሆኗል፡፡ ‹‹በሐሳብ መለያየት ሞት አይደለም›› በሚባልበት በዚህ ሥልጡን ዘመን፣ የተለየ ሐሳብ የያዘ ሰውን ማስተናገድ ፈጽሞ የማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከእሱ በተቃራኒ የተሠለፉትን ‹የጥፋት ኃይሎች›፣ ‹ፀረ ሕዝቦች›፣ ‹አገር አፍራሾች›፣. . . እያለ በጅምላ ሲፈርጃቸው መስማት አዲስ አይደለም፡፡ በተቃራኒው የተሠለፉትም ከዚህ ያልተናነሱ አሉታዊ ስያሜዎችን በመስጠት ውግዘት ውስጥ ናቸው፡፡ ግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል ያስቆጠረው የአገሪቷ የፖለቲካ ዓውድ በደም የተጨማለቀ ታሪክ ነው ያለው፡፡ ከዚህ ቀደም አንዱ ሌላውን ለማጥፋት የጦር መሣሪያ በመተኮስ የተካሄደው ፍጅት አልበቃ ብሎ፣ በዚህ ዘመን ለተመሳሳይ ፍጅት የሚያዘጋጅ ሌላ ዙር ፍጥጫ ይታያል፡፡ በዴሞክራሲ ስም እየማሉና እየተገዘቱ ዛሬም በጥላቻ ውስጥ ሆነው ለመጠፋፋት የሚሞክሩት የፖለቲካ ኃይሎች ዋናው ችግራቸው ጽንፈኝነት ነው፡፡ በሠለጠነ መንገድ ለመነጋገርና ለመደራደር ጥረት ከማድረግና አንዱ ለሌላው ዕውቅና ሰጥቶ የተበላሸውን ታሪክ ከማደስ ይልቅ፣ በጽንፈኛ አቋም ውስጥ ሆኖ ደም በለበሰ ዓይን መተያየት ተመርጧል፡፡ ዴሞክራሲ ግን ይህንን አይቀበልም፡፡ የተገነባባቸው መርሆዎችም ቢሆኑ ጽንፈኝነትን ለማስተናገድ ፍጹም አይፈልጉም፡፡
ሕዝባችን ከሚታወቅባቸው አኩሪ ታሪኮቹ ውስጥ ዋነኛውና ተጠቃሽ የሚሆነው ከምንም ነገር በላይ አስተዋይ መሆኑ ነው፡፡ ይህ በመልካም ሥነ ምግባርና በጨዋነት የተኮተኮተ የኢትዮጵያ ሕዝብ አኩሪ የጋራ እሴት፣ የሚወዳትን አገሩን በጋራ ከመጠበቅ ጀምሮ ተስማምቶና ተባብሮ እንዲኖር ረድቶታል፡፡ ከዚያም ባለፈ በተለያዩ መንገዶች የሚገለጹ ልዩነቶችን አክብሮና አስተናግዶ፣ ተጋብቶና ተዋልዶ በመኖር ዘመናትን በሰላምና በፍቅር አሳልፏል፡፡ ይህ ኩሩና ጀግና ሕዝብ ችግሮች ሲያጋጥሙት እንኳን እጅግ በጣም በሚከበረው የሽምግልና ሥርዓት ይጠቀማል፡፡ በሕዝባችን ውስጥ አዛውንቶችን ማክበርና ምክራቸውን መስማት ትልቁ ፀጋ ነው፡፡ ዕድሜና ልምድ ትልቅ ግምት ይሰጠዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ያጠፋ ይቅርታ ጠይቆ፣ የተበደለ ደግሞ ይቅር ብሎ በሰላም መኖር የዚህች አገር ጨዋ ሕዝብ ወግና ልማድ ነው፡፡ ይህንን አኩሪና ዘመን ተሻጋሪ ቅርስ ወደ ጎን በማለት ጽንፈኝነት ውስጥ እየተወሸቁ ሕዝብን ማሳዘንና አገርን ለችግር መዳረግ መቼ ነው የሚያበቃው?
ጽንፈኝነት ሁሌም ራስን ብቻ ልክ የማድረግ በሽታ ነው፡፡ ይህ በሽታ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገርና ቂምና ጥላቻ እንዲስፋፋ የሚፈልጉ የዚህች አገር ታሪካዊ ጠላቶች አሁንም እንዳሰፈሰፉ ነው፡፡ በዓለም ዙሪያ በየቀኑ የሚሰሙ ብዙዎቹ ዜናዎች ከግጭትና ከትርምስ ጋር የተያያዙ በመሆናቸው፣ በተለይ በአፍሪካ ቀንድ ለዓመታት መብረድ ያልቻለው ግጭት አሁንም በሶማሊያና በደቡብ ሱዳን ውስጥ አለሁ ይላል፡፡ በዚህ ላይ በመካከለኛው ምሥራቅ ከየመን ጀምሮ እስከ ሶሪያ ድረስ ያለው ውድመት ጽንፈኝነት የፈጠረው ነው፡፡ የዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮች ወደ አፍሪካ ቀንድ የሚያደርጉት መስፋፋትና በየመን ላይ ያወጁት የውድመት ጦርነት አለመቆም፣ ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን አሁንም ውስጣቸው መታመሱና ለመፍትሔ የሚደረጉ ጥረቶች አመርቂ ውጤት አለማስገኘታቸው ያሳስባል፡፡ እንደ አገር የእነዚህ ቀውሶች ሰለባ ላለመሆን ብሔራዊ መግባባት መፍጠርና ጠንከር ብሎ መገኘት አለመቻልም ሥጋት ይፈጥራል፡፡ ጽንፍ የያዙ አቋሞችን ይዞ በሚነድ እሳት ላይ ነዳጅ የማርከፍከፍ አባዜ ውጤቱ ተያይዞ መጥፋት ነው፡፡
በተለይ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ ደግመው ደጋግመው ማሰብ የሚገባቸው እስካሁን የመጡበት መንገድ ስህተት መሆኑን ብቻ ነው፡፡ ሥልጣን የያዘው ኃይል ተፎካካሪዎቹን ከጨዋታ ውጪ እያደረገ በዚህ መንገድ መቀጠል እንደማይችል በቅርቡ አገሪቱን ከገጠማት ፈተና ካልተገነዘበ ችግር አለ፡፡ በተቃራኒው ጎራ የተሠለፉ ኃይሎችም ቢሆኑ የእስካሁኑ ጉዞአቸውን መፈተሽ ካልቻሉ ይህም ራሱን የቻለ ችግር ነው፡፡ በሰላማዊው የፖለቲካ ትግል ውስጥ አለን የሚሉትም በሕዝብ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት ምን ያህል እንዳዘቀጠ ተረድተው፣ መሠረታዊ የሆነ ለውጥ አካሂደው በጥንካሬ መቅረብ ካልቻሉ መኖራቸው በራሱ ፋይዳ የለውም፡፡ ከሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ አፈንግጠው ሌላ አማራጭ ውስጥ ነን የሚሉም ቢሆኑ በራሳቸው ላይ መሠረታዊ ለውጥ ሊያካሂዱ ይገባል፡፡ አሁን ካሉበት ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ከፕሮፓጋንዳቸው ውጪ ምንም መሠረት እንደሌላቸው ሊያውቁት ይገባል፡፡ እነሱም ቢሆኑ በተለያዩ ክፍልፋዮች ውስጥ ሆነው የሚለቁት ውዥንብር ከጠቀሜታው ይልቅ አጥፊነቱ ይብሳል፡፡ እርስ በርሳቸው መነጋገር ከማይፈልጉ ጽንፈኛ ፓርቲዎች ምንም ጠብ የሚል የለምና፡፡ የዴሞክራሲ ፍንጭ የሌላቸው፣ ከእነሱ በተቃራኒ የቆሙ ወይም አማካይ ሥፍራ ላይ ያሉ ወገኖችን በጠላትነት የሚፈርጁ ኃይሎች ለዚህ ሥልጡን ዘመን አይመጥኑም፡፡
ኢትዮጵያ ታላቅ አገር ናት፡፡ ሕዝቧም እጅግ የተከበረ ነው፡፡ ይህንን እውነታ ወደድንም ጠላንም በዓለም አደባባይ ጀግኖቹ አባቶቻችን ያረጋገጡት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ኩራት የሆነው ታላቁ የዓደዋ ፀረ ኮሎኒያሊስት ተጋድሎና ድል ምስክር ነው፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ የአገሪቱ መልክዓ ምድር ውስጥ የሚኖረው ኩሩውና ጀግናው ሕዝባችን በከፈለው መስዕዋትነት የተገኘ ታላቅ ድል ነው፡፡ ይህ የሚያኮራ ሕዝብ ከሚጠቀሱለት ተምሳሌታዊ አኩሪ ተግባራቱ ውስጥ አንዱ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቱን አጠናክሮ ዘመናትን መሻገር መቻሉ ነው፡፡ አንዳንዶች እንደሚያስቡት ይህ አንድነት የተገኘው በግዳጅ ሳይሆን በፍፁም ፍላጎት ነው፡፡ በዚህም ኢትዮጵያዊነት የሚባል ትልቅ ምሥል ተፈጥሯል፡፡ ይህ ትልቅ ምሥል መከበር አለበት፡፡ በጽንፈኝነት ሊናድ አይገባም፡፡ የራስን አጀንዳ ከአገር በማስበለጥና ሕዝብን በመለያየት ለማበጣበጥ መሞከር፣ ባረጀና ባፈጀ ግትርነት ውስጥ ሆኖ ትልቁን የኢትዮጵያዊነት ምሥል ማደብዘዝና አገርን ለባዕዳን ጥፋት ማመቻቸት ተቀባይነት የለውም፡፡ ሥልጣንን ለማጠባበቅ ሲባልም ሆነ ወይም ሥልጣን ፍለጋ በሚል ሰበብ አገርን ማዋረድ አይፈቀድም፡፡ ይልቁንም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ፣ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ ፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል እንዲኖርና ዜጎች በገዛ አገራቸው በነፃነት አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲራመዱ የሚያስችል ጠንካራ መሠረት እንዲጣል በትጋት ይሠራ፡፡ አምባገነንትና ኢዴሞክራሲያዊነት እንዲያበቃ ጥረት ይደረግ፡፡ ለዚህም የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ዜጎች ድምፃቸውን ያስተጋቡ፡፡ በየትኛውም ማዕዘን የቆመ ጽንፈኝነት መቼም ቢሆን ለአገር አይበጅም!