Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዳግም ጥያቄ ያስነሳው የንብ ኢንሹራንስ ጨረታ በፀረ ሙስና ኮሚሽን ዕግድ ወጣበት

ተዛማጅ ፅሁፎች

ንብ ኢንሹራንስ ከ16ቱ የግል መድን ድርጅቶች ኢንዱትሪውን በመቀላቀል ቀደምት ከሚባሉት ውስጥ የሚመደብ ነው፡፡ ኩባንያው የራሱን የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ለመገንባት ዕቅዱን ይፋ ካደረገ ከ12 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ለመገንባት ያቀደውም እህት ኩባንያው ከሆነው ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ጋር በመሆን ነበር፡፡

እህትማማቾቹ ኩባንያዎች የጋራ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አዋቀረው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ዋና መሥሪያ ቤታቸውን በጋራ ለመገንባት የሚያበቋቸውን በርካታ ሥራዎች ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡ በዚህ እንቅስቃሴያቸውም በርካታ ገንዘብ ወጪ እንዳደረጉም ይነገራል፡፡

ሆኖም ባልተጠበቀ ክስተት ኩባንያዎቹ በጋራ ለመገንባት ሲያደርጉ የነበረውን እንቅስቃሴያቸውንና ስምምነታቸውን በማፍረስ በጋራ በየፊናቸው መጓዝን መርጠዋል፡፡ አብሮ የመገንባት ውጥናቸውን እንዳፈረሱም ለአክሲዮን ባለድርሻዎቻቸው አስታውቀው፣ በተናጠል በየኩባንያዎቹ ስም በተመዘገበው መሬት ላይ የየራሳቸውን ሕንፃ ለማቆም ይወስናሉ፡፡ ይህ ውሳኔ እንኳ ይፋ ከተደረገ ከሁለት ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በዚህ መሠረት ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በስሙ በያዘው ቦታ የራሱን ሕንፃ ለብቻው ለማስገንባት የሚያስችለውን ስምምነት በመፈረም ወደ ግንባታ ሥራ ገብቷል፡፡

ኢንሹራንስ ኩባንያው በበኩሉ በቦሌ መንገድ፣ አፍሪካ ቻይና ጎዳና ሜጋ ሕንፃ አካባቢ በሚገኝና ከግለሰቦች በገዛው ከ1,400 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ 18 ወለሎች ያሉት ሕንፃ ለመገንባት ወስኖ ለግንባታው መንቀሳቀስ ጀምሯል፡፡

ለዋና መሥሪያ ቤቱ አገልግሎት ለሚለው ሕንፃ መገንቢያ ቦታ ከዘጠኝ ሚሊዮን ብር ያላነሰ ወጪ በሊዝ ገዝቷል፡፡ ቦታውን በእጁ ካስገባ ግን ከስምንት ዓመታት በላይ ቢያስቆጥርም በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ግንባታ ሳይገባ ቆይቷል፡፡ ይሁንና ከሦስት ወራት በፊት ሙሉ የሕንፃ ግንባታውን ማካሄድ ለሚችሉ ተቋራጮች መድን ድርጅቱ እንዲሳተፉ ጨረታ አውጥቶ ነበር፡፡ ኩባንያው አውጥቶት የነበረው የግንባታ ጨረታ መሥፈርት ግን ከአገር በቀል ተቋራጮች ተቃውሞ እንደተነሳበት መዘገቡ ይታወሳል፡፡  

ኩባንያው ለሕንፃ ግንባታ ያወጣው የጨረታ ሰነድ አገር በቀል ተቋራጮችን ከተሳትፎ ያርቃል፣ መሥፈርቱንም አግላይ በሚያስመስል መልኩ አክብዶ አቅርቧል የሚል ተቃውሞ ቀርቦበት ነበር፡፡ ከመሥፈርቶቹ መካከል በግንባታ ጨረታው ለመወዳደር የሚፈልግ ተቋራጭ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ከ20 ወለል በላይ የሆነ ሕንፃ የገነባ መሆን አለበት የሚለው ይጠቀሳል፡፡

 ‹‹በዚህ አግባብ ሕንፃ የገነባ የአገር ውስጥ ተቋራጭ እንደሌለ እየታወቀ፣ ይህ መሥፈርት መቅረቡ እንዳይሳተፉ በማሰብ ሆን ተብሎ የተደረገ ነው፤›› የሚል ቅሬታ ሲቀርብ ቆይቷል፡፡ ተቋራጮች ካቀረቡት ቅሬታ በኋላ ኩባንያው ማስተካከያ ለማድረግና ሁሉንም ተቋራጫቾች ለማሳተፍ የሚያስችል ጨረታ ዳግመኛ እንደሚያወጣ በማስታወቅ አጨቃጫቂውን ጨረታ ይሰረዛል፡፡

ይህን አዲስ የወጣውም አሠራር ቢሆን አከራካሪ ሁኔታ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ ይህም ለሕንፃ ግንባታው ያወጣው ዳግመኛ ጨረታ፣ እንደቀድሞው ሳይሆን የግንባታ ሥራውን ለሁለት ከፍሎ በመሥጠት የመሠረት የቁፋሮውንና ቀሪውን የግንባታ ሥራ ለየብቻ እንዲሠራ የሚያደርግ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ በውሳኔው መሠረትም በቁፋሮ ሥራው መሳተፍ የሚችሉት ተቋራጮች ከተቀረው ግንባታ ውጭ እንዲሆኑ በሚያደርግ አግባብ ጨረታው ዳግመኛ ይወጣል፡፡ የጨረታ መክፈቻ ጊዜውም ግንቦት 3 ቀን 2009 ዓ.ም. እንዲሆን ይወሰናል፡፡

የጨረታው ሒደት ላይ ትክክል እንዳልሆነ የሚገልጽ አቤቱታ ግን ዳግመኛ መቅረቡ አልቀረም፡፡ ዋነኛ ጥያቄም ሥራውን ከፋፍሎ መሥራት ለምን አስፈለገ? ከሚለው የሚነሳ ነው፡፡ የወጣው ጨረታ አግባብ አለመሆኑን የሚናገሩ ወገኖች፣ ከቁፋሮ ጀምሮ አጠቃላይ ሕንፃውን ለመገንባት በአንድ ኩባንያ ለማስገባት የሚረዳ ጨረታ ማውጣት ሲገባ፣ ከፋፍሎ ለማሠራት የተፈለገበት ምክንያት አሳማኝ አይደለም ይላሉ፡፡ እንደውም እንዲህ ባለው መንገድ ማሠራቱ ኩባንያውን ለከፍተኛ ወጪ ከመዳረጉም ባሻገር፣ ለሌላ ላልተገባ አሠራር በር ይከፍታል በማለት የጨረታ ሒደቱን ኮንነዋል፡፡

ችግሩ ይህ ብቻ አለመሆኑን የሚገልጹት ቅሬታ አቅራቢዎች፣ የቁፋሮ ሥራውን ለማሠራት በመጣው ጨረታ ማንኛውም ጠቅላላ ተቋራጭ እንዳይሳተፍ መደረጉም ለቅሬታቸው ተጨማሪ ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በቁፋሮ ሥራ ጠቅላላ የግንባታ ሥራ ፈቃድ ያላቸውና ለቁፋሮው የሚውል መሣሪያ ያላቸው ተቋራጮች የሚሠሩት ቢሆንም፣ በዚህ ጨረታ እንዳይሳተፉ በመደረጉ ሒደቱን ለመቃወም እንዳበቃቸው ገልጸዋል፡፡ ጨረታው ሁሉንም የሚያሳትፍ መሆን አለበት የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ሆኖም ኩባንያው በጨረታው መካፈል የሚችሉት ለመሠረት ቁፋሮ ሥራ ፈቃድ ያላቸው ብቻ ናቸው በሚለው አቋሙ ጸንቷል፡፡ ጉዳዩን እየተከታተሉ ያሉ ወገኖች ግን ደረጃ አንድ ሕንፃ ተቋራጮች በቢሊዮን ብሮች የሚገመቱ የሕንፃ ግንባታ ሥራዎችን የመሥራት አቅም ቢኖራቸውም፣ በጨረታው አትሳተፉም መባላቸው አግባብነት እንደሌለውና አካሄዱም ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው ማድረጉን ከመግለጽ አልታቀቡም፡፡

የሕንጻ ግንባታ ጨረታ ሲመጣ በተመለደው አሠራር፣ ከመሠረቱ ጀምሮ እስከ መጨረሻው የሕንፃው ማጠናቀቂያ ድረስ ያለውን አካትቶ ቢሆንም ለንብ ኢንሹራንስ ሕንፃ ግንባታ በወጣው ጨረታ ግን የመሠረት ቁፋሮ ሥራው ላይ የትኛውም ተቋራጭ እንዳይሳተፍ ክልከላ ያደርጋል ሲሉ ቅሬታ ያደረባቸው ተቋራጮች ኮንነውታል፡፡

የኩባንያው ተቀዳሚ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ዙፋን አበበ ግን ጨረታው የወጣው ለተቋራጮች እንዳልነበር አጽንኦት ሰጥተው ይከራከራሉ፡፡ የመሠረት ቁፋሮ ሥራ ለሚሠሩ ኩባንያዎች ብቻ የወጣ በመሆኑ ተቋራጮችን ያላሳተፈው ጨረታ ነው የሚለውንም ስሞታም አይቀበሉትም፡፡ ለመሠረት ቁፋሮ ሥራ ፈቃድ የተሰጣቸው ኩባንያዎች ስላሉ እነዚሁ ቢሠሩት ትክክል በመሆኑ የተወሰደ ዕርምጃ ነው በማለት አስረድተዋል፡፡ ኩባንያ ጨረታውን ከማውጣቱ በፊት ከኮንስትራክሽን ሚኒስቴር መረጃ ለማግኘት ሞክሮ፣ በዚህ ሥራ መስክ የተሠማሩ ሦስት ኩባንያዎች ብቻ እንደሆኑ መረዳቱን የገለጹት ወ/ሮ ዙፋን፣ ‹‹አሠራራችን ትክክል ነው፤›› ይላሉ፡፡ የሕንፃ ግንባታውን ለሁለት ከፍሎ ማሠራት በኩባንያው ላይ ወጪ ያበዛበታል የሚለውን ስሞታም ወ/ሮ ዙፋን አይቀበሉትም፡፡

ሕንፃውን ለሁለት ከፍሎ እንዲሠራ የተደረገውም ግንባታ ለማስጀመር ያለው ጊዜ አጭር በመሆኑ ነው የሚሉት ወ/ሮ ዙፋን፣ ለሁለት ተከፍሎ መሠራቱ ከጊዜ አኳያ ጥቅሙ ታይቶ ነው ይላሉ፡፡ ሥራው በአስቸኳይ እንዲሠራ የተፈለገው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በስድስት ወራት ውስጥ ግንባታ መጀመር አለባችሁ የሚል ማስጠንቀቂያ እንደሆነም ኩባንያው ይገልጻል፡፡ ‹‹የአስተዳደሩን ማስጠንቀቂያ መሠረት በማድረግ ከቦርድ አባላት ጋር ሆነን ጉዳዩ የሚመለከተው የከተማው አስተዳደር ቢሮ በግንባር ቀርበን ያረጋገጥን በመሆኑ ግምገማ አድርገን ልንጨርስ የምንችለው የመሠረት ቁፋሮ ሥራውን ለብቻ ጨረታ በማውጣት ሥራ ማስጀመር በመሆኑ ሥራውን ከፋፍለነዋል፤›› ይላሉ፡፡ በዚህ ጨረታ ሒደት ላይ ቅሬታ አለን የሚሉ ወገኖች ግን በዚህ ሐሳብ አይስማሙም፡፡ ይህን ያህል ጊዜ ሳይሠራበት የተቀመጠ ቦታ፣ እንዲህ በቶሎ የሚነጠቅበት ምክንያት እንደሌለ ያስረዳሉ፡፡ በጥድፊያ ጨረታው ቢከፈትም መጪው ክረምት በመሆኑ፣ ሥራው ሊጀመር እንደሚችል ግን ቀድሞው በመርሐ ግብሩ መሠረት ይታወቃል ይላሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ‹‹የጨረታ ሒደቱን የበለጠ እንድንጠራጠር ያደረገን ለአንድ ጨረታ የሚሰጠው የ45 ቀናት ቆይታ ቢሆንም ኩባንያው ግን ለዚህ ጨረታ የሰጠው የአየር ጊዜ 22 ቀን ብቻ መሆኑ ነው፤›› በማለት ተጫራጮቹ ተናግረዋል፡፡

በተመለደው አሠራር ዋናው ተቋራጭ የመሠረት ቁፋሮውን መሥራት ካልፈለገና ካልቻለ፣ በዋናው ተቋራጭ ሥራ ለመሥራት ከሚፈልጉ ጋር ተዋውሎ የሚሠራበት አግባብ ቢኖርም፣ አንዳንዴ ግን አሠሪው ተቋም የገንዘብ እጥረት ወይም ሌላ አስገዳጅ ሁኔታ ሲገጥመው የመሠረት ቁፋሮውን ለሚሠሩ ጨረታ አውጥቶ ማሽኑ ያለው ሕንፃ ተቋራጭ ወይም መሠረት ብቻ የሚሠራ ተቋራጭ ሁለቱም በጋራ የሚሳተፉበት ግልጽ ጨረታ መውጣት ይችል እንደነበርም ያስረዳሉ፡፡

ወ/ሮ ዙፋን እንደሚያብራሩት፣ በእርግጥ ለሹሪንግ ሥራው የሚሆን ማሽነሪ ያላቸው ኮንትራክተሮች እንዳሉ እናውቃለን ካሉ በኋላ ‹‹እኛ ጨረታውን ያወጣነው የመሠረት ቁፋሮ ሥራ ብቻ ለመሥራት ፈቃድ ላላቸው ነው፡፡ በመሠረት ቁፋሮ ሥራ የተሠማሩ ኩባንያዎች ይግለጹልን ስንል ለጠየቅነው ጥያቄ፣ ሚኒስቴሩ ሦስት መሆናቸውን ጽፎ ተሰጥቶናል፤›› በማለት ወ/ሮ ዙፋን ገልጸዋል፡፡ ጉዳዩ በዚህ ደረጃ ላይ ሳለ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለፀረ ሙስና ኮሚሽን አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡ ከጨረታ አሠራር ውጭ ለጨረታ 45 ቀን መፈቀድ ሲኖርበት፣ ኢንሹራንስ ኩባንያው ግን 22 ቀናት ብቻ በመስጠት ጨረታ ማውጣቱንና ተቋራጮች እንዲሳተፉ ማድረጉን ጨምሮ በአጠቃላይ የጨረታ ሒደቱ ትክክል አለመሆን የሚገልጽ አቤቱታ ለኮሚሽኑ አስገብተዋል፡፡

በመሆኑም ኩባንያው ለቁፋሮ ሥራ ያወጣውን ጨረታ ግንቦት 3 ቀን 2009 ዓ.ም ለመክፈት በተዘጋጀበት ወቅት፣ ከፀረ ሙስና ኮሚሽን በደረሰው ዕግድ እንዲሁም በዕለቱ ለጨረታው ሰነድ ያስገባው አንድ ተጫራች ብቻ በመሆኑ ሳይከፈት ቀርቷል፡፡

በተቀመጠው ሕግ መሠረት እየተሠራ ነው የሚሉት ወ/ሮ ዙፋን፣ የፀረ ሙስና ኮምሽንም ጨረታውን አትክፈቱ የሚል ዕግድ ቢያወጣም፣ አንድ ተጫራች ብቻ በመቅረቡ ጭምር አልተከፈተም በማለት ጨረታው መቋረጡን አረጋግጠዋል፡፡ ከዕግዱ በኋላ ፀረ ሙስና ኮሚሽን በጨረታው ሒደት ላይ የቀረበውን ቅሬታ መነሻ በማድረግ ምርመራ እያካሄደ ሲሆን፣ ውሳኔውንም በቅርቡ እንደሚያሳውቅ ይጠበቃል፡፡

በእንጥልጥል ላይ የሚገኘው የሕንጻ ግንባታ ሒደት የኮሚሽኑን ውሳኔ ለመጠበቅ እንደሚገደድ ወ/ሮ ዙፋን አስታውቀዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች