Friday, April 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በ400 ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ የሚንሠራፋ ባለአምስት ኮከብ ሪዞርት ሆቴል ሊገነባ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከ3.5 ቢሊዮን ብር በላይ (150 ሚሊዮን ዶላር ገደማ) የሚጠይቅና በኢትዮጵያ ትልቁ ሪዞርት እንደሚሆን የሚነገርለት ሆቴል በለገዳዲ ከተማ ለመገንባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ፡፡ በሆቴል ማስተዳደር ሥራ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣ የእስያ ኩባንያም አዲሱን ሪዞርት ለማስተዳደር በቅርቡ ስምምነት እንደሚፈርም ይጠበቃል፡፡

ከአዲስ አበባ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ለገዳዲ ከተማ ‹‹ደሲ ታኒ ኮንፈረንስ ኤንድ ዌልነስ ሪዞርት አዲስ አበባ ለገዳዲ›› በሚል መጠሪያ በ400,000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ እንደሚገነባ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ፍሬ ፀጋ በተባለ የአገር ውስጥ ኩባንያ ባለቤትነት የሚገነባውን የሪዞርት ሆቴል ፕሮጀክት በማማከር የተሳተፈውና በታይላንዱ ኩባንያና በኢትዮጵያው ባለሀብት መካከል የሚደረገውን ስምምነት ያደራደረው የኦዚ ቢዝነስና ሆስፒታሊቲ ግሩፕ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ቁምነገር ተከተል ሒደቱን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በባለአምስት ኮከብ ደረጃ ይገነባል ተብሎ የሚጠበቀው የሪዞርት ሆቴል፣ እንደ አቶ ቁምነገር ገለጻ ከሆነ፣ በምሥራቅ አፍሪካ በትልቅነታቸው ቀዳሚ ከሆኑ ሪዞርቶች አንዱ እንደሚሆን የሚገልጹበት ምክንያትን ጠቅሰዋል፡፡

ለሪዞርቱ የተዘጋጀው ቦታ በ400 ሺሕ ካሬ ሜትር መሆኑ አንዱ ሲሆን፣ ከፕሮጀክቱ ዲዛይን አኳያም በባለአምስት ኮከብ ደረጃ የተያዙ ሁለት ፕሬዚዳንሺያል፣ 38 ሌግዤሪ ቪላዎችን ጨምሮ በጠቅላላው 358 የመኝታ ክፍሎች የሚኖሩት መሆኑ የሪዞርቱን ትልቅነት እንደሚያሳይ ይናገራሉ፡፡ በዚህን ያህል ደረጃ የመኝታ ክፍሎች ያሉት ሪዞርት በምሥራቅ አፍሪካ አለመኖሩን የሚጠቅሱት አቶ ቁምነገር፣ አንድ ሺሕ ሸዎችን ለማስተናገድ የሚችል የስብሰባ ማዕከል፣ ሲኒማ ቤትና ሌሎችም የሚያካትታቸው ግንባታዎችና አገልግሎቶች ታክለውበት፣ በምሥራቅ አፍሪካ የመጀመሪያው የ‹‹ማይስ›› መዳረሻ እንዲሆን ታስቦ ዲዛይን መደረጉንም አቶ ቁምነገር ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ በማይስ ቱሪዝም መስክ እየሠራች ነው ያሉት አቶ ቁምነገር፣ የማይስ ቱሪዝም ከሚስፋፉባቸው መንገዶች አንዱም መሠረተ ልማቶች መሟላታቸው በመሆኑ፣ አዲሱ ሪዞርት ሆቴል ይህንን እንዲያሟላ ታስቦበት የሚገነባ ነው ብለዋል፡፡ ለማይስ ኢንዱስትሪ መስፋፋት እንደሚረዱ ከሚታሰቡ ግንባታዎች መካከል አንዱ የሆነው፣ አዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽን ማዕከል ሲሆን እንዲህ ያሉ ግንባታችም በጉጉት የሚጠበቁ ናቸው፡፡ ከዚህ ባሻገር ይህንን የሚያለሙ ስፔሻላይዝድ ያደረጉ ሆቴሎች የሚያስፈልጉ በመሆኑ፣ ዴስ ታኒ ዓለም አቀፍ ሆቴል ይህንን ሊያሟላ የሚችል እስከ አንድ ሺሕ ሰዎች መያዝ የሚችል አዳራሽና የተለያየ መጠንና አቅም ያላቸው ስምንት ተጨማሪ አዳራሾች እንደሚኖሩት ይጠበቃል፡፡

ይህን ፕሮጀክት የተለየ የሚያደርገውም አነስተኛ የሆኑ ኤግዚቢሽኖችን ለማዘጋጀት የሚያስችሉ አዳራሾችን እንዲያካትት የተደረገ ሲሆን፣ የሕፃናት መጫወቻ፣ የሕክምና ማዕከል፣ የፈጣን ምግቦች መሸጫ ማዕከልን አካቶ የሚገነባ ነው፡፡  

ሪዞርቱ ሆቴሉን የሚያስተዳድረው የታይላንዱ ኩባንያ፣ ይህንን ሪዞርት ሲያስተዋውቀው በአካባቢው የመጀመሪያው ኮንፈረንስና የማይስ መዳረሻ መሆኑን የሚገልጽ የማስተዋወቂያ ስልት እንደሚያራምድም ተነግሯል፡፡

የፕሮጀክቱ ጥናት እንደሚያመለክተውም፣ ይህንን ሁሉ አገልግሎቶች ይዞ የሚገነባው ሪዞርት ሆቴል 60 በመቶውን አቅሙን ቢጠቀም ተብሎ በተጠናው መሠረት፣ በዓመት ከ17 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያስገኛል ተብሎ ይገመታል፡፡

ፕሮጀክቱ እስከ ጥቅምት 2010 ዓ.ም. ድረስ ተጀምሮ በአራት ዓመታት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቅ ነው፡፡ ዲዛይኑን ጌሬታ አርክቴክትስ የተባለ አገር በቀል ኩባንያ ከደቡብ አፍሪካ አጋሮቹ ጋር በመሆን እንዳሰናዳው ከአቶ ቁምነገር ለመረዳት ተችሏል፡፡

ሪዞርቱን ለማስተዳደር ኮንትራቱን ይፈርማል የተባለው የታይላንድ ኩባንያ፣ የተለያዩ ብራንድ ያላቸው 29 ሆቴሎችና ሪዞርቶችን በተለያዩ አገሮች የሚያስተዳድር መሆኑም ታውቋል፡፡ በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ውስጥም 51 አዳዲስ ሪዞርቶችንና ሆቴሎችን ለማስተዳደር የሚያስችለውን ዝግጅት እያደረገም እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ፕሮጀክቱን በባለቤትነት የሚያስገነባው ፍሬ ፀጋ የተባለው ኩባንያ፣ በኮንስትራክሽን፣ በሪል ስቴትና በኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች አቅራቢነት የተሠማራ ኩባንያ እንደሆነ ታውቋል፡፡  

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች