በሳሙኤል ረጋሳ
ኦሮሚያ እንደ ክልል ከተቋቋመች ጊዜ ጀምሮ ይነስም ይብዛ ሕዝቡ ያለ ተቋውሞና ያለ ግርግ ያሳለፈው አንድም ዓመት የለም ለማለት ይቻላል፡፡ እንደ ክልሉ ስፋት፣ እንደ ሕዝቡ ብዛትና እንደ አገሪቱ የመዳረሻ ማዕከልነት የሚፈጠሩ ችግሮች ከሌሎች ክልሎች ጎላ ብለው ቢታዩ አይገርምም፡፡ ነገር ግን ችግሮቹ የሚከሰቱት ከክልሉ ተፈጥሮአዊና አስገዳጅ ባህሪ ሳይሆን እጅግ በወረዱ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ዝንፈቶች ነው፡፡ አመራሮቹ ለኃላፊነት የሚበቁት ብቃታቸው ታይቶ ሳይሆን ጥቅምን፣ ወገንን፣ ጎሳንና አካባቢን ማዕከል ባደረገ የእከከኝ ልከክልህ ስሜት በመሆኑ የክልሉ ሕዝብና ባለሥልጣናቱ ከዓመት ዓመት አንዴም ሳይስማሙ እዚህ ደርሰዋል፡፡
የክልሉ ሕዝብ ቁጥር ከግማሽ በላይ በወጣትነት ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ፣ የሚታየውን በደልና ሠርቶ በሰላም የመኖር ፍላጎቱን የሚፃረር ማንኛውንም አካል በሕጋዊም ሆነ በስሜታዊነት መብቱን ለማስከበር የሚያደርገው ትግል በቀላሉ የሚቆም አልሆነም፡፡ መብቶቻችን አልተከበሩልንም፣ በይዞታችንና በንብረታችን ላይ የባለቤትነት መብታችን በሕገ መንግሥቱ መሠረት አልተከበረልንም የሚሉ አያሌ ናቸው፡፡ በክልሉ ውስጥ እነዚህንና ሌሎች መሰል ችግሮችን በአግባቡ ሊያስወግድ የሚችል አቅም ያለው ቆራጥ አመራር ባለመኖሩና እንዲኖርም ባለመፈለጉ ችግሩ ሥር እንዲሰድ ሆነ፡፡
አሁን ኢሕአዴግና አባል ድርጅቶቹ የነብረንን ችግር በጥልቅ ተሃድሶ ገምግመንና አውቀን ለችግሮቹ ሁሉ መፍትሔ አስቀምጠናል እያሉ ነው፡፡ ከእነዚህ መፍትሔዎች ውስጥ የኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮት አንዱ እንደሆነ ነው የሚነገረው፡፡ ከስሙና ከአጀማመሩ እንደምንረዳው ከሆነ የክልሉን ኢኮኖሚ በአጭር ጊዜ ለማሳደግና ልማትን በአፋጣኝ ለማምጣት የታሰበ ይመስላል፡፡
የኢኮኖሚ ዕድገቱን ለማሳካት አንዱና ዋና ሆኖ ሊተገበር እየተሞከረ ካለው ሥራ ውስጥ ለክልሉ ሥራ አጥ ወጣቶች በቂ የሥራ ዕድል በመፍጠርና የወጣቱ አንገብጋቢ ጥያቄ ለሆነው በቂ መልስ ለመስጠት እየተሞከረ ነው፡፡ ይኼን ዕቅድ ለማሳካት በጣም ብዙ ተግዳሮቶች ከፊት ለፊት የሚታዩ ቢሆንም፣ ሐሳቡን ማመንጨትና ለተግባራዊነቱ የሚሆነው ጅማሬ በራሱ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ይኼን ለመተግበር እየተደረገ ካሉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ አንዱ ለግንባታ የሚውሉ የተፈጥሮ ሀብቶች አሸዋ፣ ጠጠርና ድንጋይ የመሳሰሉት ከግለሰቦች ተወስደው ወጣቱ ተደራጅቶ እንዲጠቀምባቸው የክልሉ መንግሥት ያሳለፈው ውሳኔ ነው፡፡ ቀደም ሲል በነበሩት አመራሮችና በክልሉ መንግሥት ላይ ሕዝቡ ተቃውሞውን ሲያሰማ የነበረው አንዱ በዚህ ጉዳይ ላይ ነው፡፡ ይኼ ጥያቄ ተገቢነት ያለው ጥያቄ በመሆኑ አሁን የተጠሰው ውሳኔ እጅግ የዘገየ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡
መንግሥት በምን ሕግና መሥፈርት የሕዝቡን ሀብት ነጥቆና ገበሬውን አፈናቅሎ ግለሰቦች እንዲወርሱት እንዳደረገ አይታወቅም፡፡ ስሙ ለኢንቨስተር የተሰጠ መሬት ነው ይባላል፡፡ አሸዋ አፍሰው፣ ድንጋይ ጭነው፣ ገረጋንቲ ዘግነውና ጠጠር ሰባብረው መሸጥን ከኢንቨስትመንት ጋር የሚያገናኘው ጉዳይ የለም፡፡ ልዩ ሙያና ዕውቀት ወይም በርካታ ገንዘብ የሚጠይቅ አይደለም፡፡ ኢንቨስተር ተብዬዎቹ በማምረት ሒደት ውስጥ የሚያሳልፉት ተግባር ወይም የሚጨምሩት እሴት የለም፡፡ አንድ ሰው የቀረበለትን እንጀራ ቆርሶ በወጥ አያይዞ ቢበላው ምን እሴት ጨመረ? ይኼንን ሥራ ማንኛውም ጉልበት ያለው ሰው ዕድሉን ካገኘ ሊሠራው የሚችለው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከሥራ አጡ ወጣት የተሻሉ ባለመብት ሊኖር አይችልም፡፡
ነገር ግን አልፎ አልፎ እንደሚስተዋለው አንዳንዶች ይኼ ተግባር የኢንቨስተሮችን መብት እንደሚነካና ከአንዱ ቀምቶ ለሌላ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በወጣቱም ላይ የጠባቂነትን መንፈስ እንደሚፈጥር ነው የሚነግሩን፡፡ በመጀመርያ ደረጃ በክልሉ መንግሥት ፈቃድና ድጋፍ አንድ ግለሰብ የበርካቶችን ይዞታ ነጥቆ አሸዋ እየሸጠ ሲከብር፣ ግለሰቡን ኢንቨስተር ነው ማለት ቃሉን ያለቦታው መጠቀም ይሆናል፡፡ በዚህ መንገድ ለመምጣት የሚፈልግ ኢንቨስተር ያለመምጣቱ ጠቃሚ እንጂ የሚጎዳ ነገር የለውም፡፡
ቀደም ሲል መንግሥት ከሕዝብ ቀምቶ ለግለሰቦች እነዚህን የተፈጥሮ ሀብቶች ሲያድል ጉዳዩ ያልቆረቆረንና ምንም ተቃውሞ ያላሰማን ሰዎች፣ አሁን ለሕጋዊ ባለቤቱ ለብዙኃን ጥቅም ተብሎ ሀብቱ ሲመለስለት ተቃውሞ ማሰማት የጤና አይመስልም፡፡ ወጣቱም ቢሆን የዚች አገር የኢኮኖሚና የሥራ ዕድል ማንቀሳቀሻ ሞተሩ መሬት መሆኑ እየታወቀ፣ እነዚህን በቀላሉ ሊሠራቸው ለሚችላቸው የሥራ ዕድል ካልተመቻቸለት ያለ ሥራ መቀመጡን የጠባቂነት መንፈስ አድርጎ ማሰብ ተገቢ አይደለም፡፡
መንግሥት ይኼን ጉዳይ ሲተገብር በዋናነት ማሰብ የሚገባውና ክፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግለት የሚያስፈልገው የአፈጻጸሙ ጉዳይ ነው፡፡ በጎ በመመኘትና በጎ በማሰብ ብቻ በጎ ውጤት አይገኝም፡፡ ምንም እንኳን ወጣቶቹ በቂ ጉልበት ቢኖራቸውና ሠርተው ለመለወጥ ያስባሉ ተብሎ ቢገመትም፣ የሚደራጁት ወጣቶች የተለያየ ፀባይ ያላቸው ከመሆኑም በላይ ሁሉም እኩል ብርታት ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ለጊዜው የማምረቱም፣ ገበያ የማፈላለጉም፣ ተደራጅቶ የመሥራቱም ሊከብዳቸው ይችላል፡፡ በተለይ ይኼ ሥራ ከሲሚንቶ ፋብሪካዎችና ከተለያዩ የግንባታ ሥራዎች ጋር ከፍተኛ ትስስር ስላለው በበቂ መጠን አምርተው በሚፈለገው ጊዜ ማቅረብ አለባቸው፡፡ እነዚህና ሌሎች ጉዳዮች በአግባቡ ኃላፊነተት በሚሰማው ክፍል ካልተመሩ ጉዳቱ በአገር ኢኮኖሚ ላይም ነው፡፡ ፕሮግራሞችን፣ የፋይናንስ አስተዳደሩንና ቴክኒካዊ ማኔጅመንትን ለመከወን ብቁ እስኪሆኑ ድረስ የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን የባለሙያ እገዛ ሊያደርግላቸው ይገባል፡፡ ወጣቶችን እየደገፉ ከሥራው ጋር ማዋሀድና ተገቢውን መዋቅር እንዲፈጥሩ ማድረግ ቀዳሚ ሥራ መሆን አለበት፡፡
ሌላው የኢኮኖሚ አብዮቱ ፍንጭ ከሰጠባቸው ጉዳዮች ጎልቶ የታየው የመንግሥት ሠራተኛንና የገጠሩን አርሶ አደር የከተማ ቤት ባለቤት የማድረጉ ዕቅድ ነው፡፡ ለጊዜው ዝርዝር ጉዳዩ የተገለጸ ባይሆንም፣ በዚህ ውሳኔ ላይ በርካታ ጥያቄዎች በአዕምሮአችን መመላለሱ አይቀርም፡፡ እንደሚታወቀው በኢሕአዴግ ዘመን ከተራ የመንደር ደላላ እስከ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ድረስ ተዝቆ የማያልቅ፣ ንብረትና የገንዘባቸው ምንጭ የከተማ ቦታ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ መንግሥትና እነዚህ በመሬት የከበሩ ሰዎች የከተማ ቦታን ጥቅም እኩል ስላወቁ በመካከላቸው የጥቅም ግጭት ተፈጥሯል፡፡ ዕድሉን ሊያገኙ ይልቻሉ ተራ ዜጎችም ቢሆን ሲሆን ሸጠው ለውጠው ጥሪት የሚያስቋጥራቸው ያለበለዚያም የሕዝቡን ኑሮ ካመሰቃቀለውና ኑሮን ትርጉም ከሰጠው የቤት ኪራይ የሚገላግላቸው ቦታ የማግኘት ዕድልን ከሰማይ እንደወረደ መና ሊቆጥሩት ይችላሉ፡፡ በዕድሉ ለመጠቀም የማይፈልግ ይኖራል ተብሎ አይገመትም፡፡
ለአምስት መቶ ሺሕ የመንግሥት ሠራተኞችና በብዙ ሚሊዮን ለሚቆጠሩ አርሶ አደሮች ይኼን ዕድል ለማዳረስ መሞከር ድፍረት ባይሆንብኝ ከምኞት የዘለለ ሊሆን አይችልም፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ይኼን ሁሉ ሰው የሚያስተናግድልን ቦታ ከየት ይመጣል? መቼም ሰላማዊ አብዮት የለም ከተባለና ከከተሞች አካባቢ ያሉትን አርሶ አደሮች ከይዞታቸው በብዛት በማባረር ከሩቅ ያሉ አርሶ አደሮችንና ከተሜ ሠራተኞችን በይዞታቸው ላይ ለመትከል መሆኑ አያጠራርም፡፡ የአርሶ አደርን ማሳ ቀምቶ ለተለያዩ አካላት መሬት መስጠትን ኢሕአዴግ ትንሽ እንኳ ቅር ሳይለው እንዲያውም የሚኩራራበት አቋሙ ነው፡፡ ነገር ግን አንድን ሰው እንኳ ቢሆን ግድ ካልሆነ በስተቀር ከትውልድ ቀየው ነቅሎና ሌላ ምንም ቋሚ መተዳደሪያ በውል ሳይኖረው ማባረር ምን ያህል ውስጥን እንደሚያሳምም መገመት ለባለ ህሊና ሁሉ ቀላል ነው፡፡
ለበርካታ ፕሮጀክቶች ጥያቄ መንግሥት መሬት አቀርባለሁ እያለ ሲናገር ይሰማል፡፡ ይኼ የሚገርምና በጣም ድፍረት የተሞላበት አባባል ነው፡፡ ምክንያቱም አቀርባለሁ የሚለው መሬት እንደ ጥሬ ገንዘብ በእጅ ያለ ሳይሆን በቀላሉ ከአርሶ አደሩ ቀምቼ እሰጣለሁ ለማለት ነው፡፡ አሁንም የኦሮሚያ መንግሥት አቋም ይኼ ኢሕአዴጋዊ አቋም ከሆነ ቆም ብሎ የማሰቢያ ጊዜ ሊኖረው ይገባል፡፡ ከገበሬ የማይነጥቅ ከሆነ ደግሞ መሬት እንደ ላስቲክ ተጎትቶ የሚለጠጥና የሚሰፋ ባለመሆኑ ሌላ የከተማ ቦታ ምንጭ ሊኖረው አይችልም፡፡ ይኼ ደግሞ ቀደም ሲል እንደታየው የአዲስ አበባ ዙርያ ችግርን በመድገም እንዲያውም በሁሉም ክልል ውስጥ ሌላ ቀውስ፣ ሌላ ሁከትና ግርግር ሊፈጥር ይችላል፡፡
አንድ ሰው በማኅበር ተደራጅቶ ወይም በግሉ የመኖሪያ ቤት መሥራት ቢፈልግ ራሱን በቻለ ተፈጥሮአዊና ተለምዶአዊ ሁኔታዎች ሊፈጽመው ይችላል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ መንግሥት የሚያበረታታውም የሚደግፈውም ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ በተረፈ ግን ሁሉንም የመንግሥት ሠራተኛና ሰፊውን አርሶ አደር የከተማ ቤት ባለቤት አደርገዋለሁ ማለት በራሱ ምን ማለት ነው፡፡ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በተለይ አርሶ አደሩ የግድ የከተማ ቤት ሊኖረው አይገባም፡፡ ሰው ቤት የሚሠራው ጥሮ ተጣጥሮ በራሱ መንገድ፣ በራሱ ፍላጎት፣ በራሱ ጊዜና በሚፈልገው ቦታ በራሱ ተነሳሽነት መሆን አለበት፡፡ በአንድ ክልል ውስጥ ያለን ሕዝብ ሙሉ በሙሉ የቤት ባለቤት አደርገዋለሁ ማለት ሐሳቡ መጥፎ ባይሆንም የተለመደና ለመተግበር የሚቻል አይደለም፡፡
ለመሆኑ አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ቤት መሥራት ቢፈልግስ አሁን በተያዘው ዕቅድ መሥራት አሁን በሚሠራበት ከተማ ነው፡፡ ወይስ ለወደፊት ዘላቂ መኖሪያዬ አደርገዋለሁ በሚለው ከተማ ውስጥ ነው የሚስተናገደው? ግለሰቡ አሁን የሚሠራበት ምድብ የሥራ ቦታው ለገጣፎ ቢሆንና ለወደፊት የዘለቄታ መኖሪያውን በግንደበረት ከተማ ለማድረግ ካሰበ የት እንዲሠራ ነው የሚጠበቀው? በግልባጩስ ቢሆን? ሌላው ጉዳይ አንድ ሰው የሠራውን ቤት ለሌላ ሦስተኛ ወገን አያስተላልፍም ተብሏል፡፡ በአገሪቱ ሕግ ያልተቀመጠ ክልከላን የክልሉ መንግሥት ከየት አመጣው? አንድ ያለትዳር የሚኖር ሰው ቤቱን ከሠራው በኋላ በዕድገት ወይም በዝውውር አካባቢውን ቢለቅ ወይም ለትምህርት ወይ ለሥራ ወደ ውጭ አገር ቢሄድ የሥራውን ቤት ለማን ጥሎ ሊሄድ ነው?
ደግሞስ ቤተ ሠሪዎቹ እንደ ማንኛውም የከተማ ነዋሪ መሬት ያገኙ እንደሆነ እንጂ፣ ቤቱን የሚሠሩት በራሳቸው ገንዘብ እስከሆነ ድረስ ለሚፈልጉት ሰው በሕጉ መሠረት ማስተላለፍ ካልቻሉ እንዴት ነው ቤት አላቸው ማለት የሚቻለው? በዚህ ዓይነት ጉዳዮችን በዝርዝር ብናየው መልስ የሚፈልጉ ጥያቄዎች የትየለሌ ናቸው፡፡ በምሁራን የተሞላው የክልሉ ካቢኔ ለሚነሱ ጥያቄዎች ሁሉ መልስ ይኖረዋል ተብሎ ይገመታል፡፡ ነገር ግን ወደ ሥራ ከተገባ በኋላ የሚፈጠረው አዳዲስ አስተሳሰቦች ከአሁኑ ሊስተናገዱ ስለሚገባቸው የክልሉ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ዝርዝር ማብራርያ በቅድሚያ መስጠት አለበት፡፡
መንግሥት ሁልጊዜ ጥንካሬውን ከሚያሳይባቸው ጉዳዮች አንዱ ይደርሳል ተብሎ ለሚጠበቅ ችግር ቅድሚያ መፍትሔ ማስቀመጥ ሲችል ነው፡፡ የማይሞከሩ ነገሮችንም ያለመሞከር ነው፡፡ ኢሕአዴግ የሕዝቡን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት በራሱ ገንዘብ ሙሉውን ወጪ ችሎ የኮንዶሚኒየም ቤቶችን ሠርቶ ለተጠቃሚዎች አከፋፍሏል፡፡ እያከፋፈለም ነው፡፡ በዚህ ቤት እደላ ውስጥ አንዱ ተጠቃሚው ሊያውቀውና ሊተገብረው የሚገባ ጉዳይ የቤቶቹን ካርታ ያላገኘና አምስት ዓመት በእጁ ያላቆየ የቤት ባለቤት ኃላፊነት እንዳለበት ነው፡፡ ነገር ግን በተጨባጭ ያየነው እንደሆነ ዕጣው የወጣለት ሰው በጋዜጣ ስሙን ካየ ሄዶ ቦታውንና ቤቱን ሳያይና ሳይረከብ አየር ባየር ይሸጠዋል፡፡ ትንሽ አሳምሮ እንኳን መሸጥ የአባት ነው፡፡ ታዲያ ኦሮሚያ ከዚህ ምን ተሞክሮ አግኝቷል? የሕገወጥ ደላሎችና የሙሰኛ ባለሥልጣናት ሥራ እኮ አንዱ ይኼ ነው፡፡
የኦሮሚያ ኢኮኖሚ አብዮት የተጀመረበት ጊዜ በጣሙን ጥንቃቄ የሚፈልግና ሌላ ቅሬታ በቀላሉ የሚፈጥር መሆን የለበትም፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሲያበቃ አገሪቱ ሙሉ በሙሉ በሰላም አንድትቀጥል የሚያግዝ መደላድል ነው መፈጠር ያለበት፡፡ ይኼን መደላድል ስንፈጥር ግን ብስል ከጥሬ የሆነ አሠራር እንዳይፈጠር መጠንቀቅ አለብን፡፡ ለበጎ ብለን የምናስባቸው ጉዳዮች የጎንዮሽ ጉዳት እንዳይኖራቸው፣ የኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮትን ከጊዜ ሁኔታ ጋር እንመዝን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡