ከተንቀሳቃሽ ነፍሳት ወገን የሚደመረው ጉንዳን በተናካሽነት፣ ተቆናጣጭነቱ ይታወቃል፡፡ ጥሬ እህል ለቀለቡ ባፉ እየያዘ ወደ ጉድጓድ የሚያገባ፣ የሚከት፣ የሚጐደጉዳ ጥቁሩ ጉንዳን ነው፡፡ ብልህነትም አላጣም፡፡ የያዘው ጥሬ እህል እንዳይነቅዝበት እየከካ በውጭ በፀሓይ ላይ የሚያሰጣ አግዝ ነው ይሉታል፡፡ እንደ ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት አገላለጽ፣ ሌላኛው የጉንዳን ዘር ቀይ መልክ ያለው ነው፡፡ ሥጋና ቅባት ወዳድነቱም አይጣል ነው፡፡ ውበት አያጣውም፡፡ ‹‹መልከ ቀይ፣ ማረ በላ፤ ፈጣን›› ይለዋል፡፡
በጉንዳን ተፈጥሮ የተደመሙ የሜካኒካል ምሕንድስና ባለሙያዎች፣ ጉንዳኖች ባላቸው ከአካላቸው ብዙ እጥፍ የሚበልጥ ክብደት የመሸከም ችሎታ በማድነቅ ብቻ አልተወሰኑም። በንቁ!—2016 እትም በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የኦሃዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያሉ መሐንዲሶች፣ ጉንዳኖች ያላቸውን ይህን ችሎታ ለመረዳት ሲሉ የኮምፒዩተር ሞዴሎችን አዘጋጅተዋል፤ ሞዴሎቹ የጉንዳኖቹን አካል አወቃቀርና ባሕርይ እንዲሁም እንቅስቃሴ የሚያሳዩ ናቸው። ሞዴሎቹ የተሠሩት የጉንዳኖቹን ውስጣዊ የአካል ክፍል የሚያሳይ የራጅ ምስል (ረቂቅ ሲቲ ስካን) እና ጉንዳኖች ከባድ ሸክም ሲሸከሙ ኃይላቸውን የሚጠቀሙበትን መንገድ የሚያሳዩ ምስሎችን በመጠቀም ነው።
የጉንዳኖች አንገት ትልቅ ሚና አለው፤ ምክንያቱም አንድ ጉንዳን በአፉ የሚይዘው ከባድ ሸክም ሙሉ ክብደት የሚያርፈው አንገቱ ላይ ነው። በጉንዳኑ አንገት ውስጥ የሚገኙ ለስላሳ ሕብረ ሕዋሳት በደረቱ አካባቢ (ሰውነቱ) እና በጭንቅላቱ ላይ ካሉት ጠንካራ ድጋፍ ሰጪ አጥንቶች ጋር የተቆላለፉ ናቸው፤ ይህም በታጠፉ እጆች ላይ ጣቶች ከሚቆላለፉበት ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ነው።
“ይህ መቆላለፍ ያለው ንድፍና አወቃቀር፣ የአንገቱ መገጣጠሚያ ለሚያከናውነው ተግባር ወሳኝ ነው” በማለት ከተመራማሪዎቹ አንዱ ይናገራል። “የአንገቱ መገጣጠሚያ ይበልጥ ጥንካሬ እንዲኖረው ያደረገው ነገር ጠንካራና ለስላሳ የአካል ክፍሎቹ የተያያዙበት መንገድ ሳይሆን አይቀርም፤ ምናልባትም መገጣጠሚያው ከባድ ሸክም እንዲሸከም የሚያስችለው ይህ ንድፍ ሊሆን ይችላል።”
የጉንዳን አንገት እንዴት እንደሚሠራ በግልጽ መታወቁ ለሰው ሠራሽ ሮቦቶች ንድፍ መሻሻል አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚችል ተመራማሪዎች ተስፋ ያደርጋሉ።