Friday, September 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የ180 ሺሕ ታብሌት ኮምፒዩተሮች ግዢ ጨረታ ማወዛገቡን ቀጥሏል

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዳዊት እንደሻው

በአወዛጋቢነቱ የቀጠለው 180 ሺሕ ታብሌት ኮምፒዩተሮችን ለመግዛት ሲከናወን የነበረውን ጨረታ በድጋሚ ቅሬታ ቀረበበት፡፡ ቅሬታው የቀረበው ከሳምንት በፊት የመንግሥት ግዢዎችና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የቅሬታ ሰሚ ቦርድ በሰጠው ውሳኔ ላይ ነው፡፡ ታብሌት ኮምፒዩተሮቹ እንዲገዙ የተፈለገው በመጪው ዓመት ለሚደረገው የሕዝብ ቆጠራ ነው፡፡

  ከሳምንት በፊት ቦርዱ ሌኖቮ የተባለውን የቻይና ኩባንያ ለዚሁ ቦርድ ባቀረበው ቅሬታ መሠረት ወደ ቀጣይ ዙር እንዲያልፍ መወሰኑ ይታወሳል፡፡ ከዚህ ቀደም ይኼ ኩባንያ ጨረታውን ባወጣው በመንግሥት ግዥዎችና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ወደ ቀጣዩ የፋይናንስ ግምገማ ማለፍ እንዳልቻለ ተነግሮት የነበረ ሲሆን፣ የቅሬታ ሰሚ ቦርዱ ግን ይኼንን ውሳኔ እንደቀለበሰው አይዘነጋም፡፡

ቦርዱ ይኼን ሲወስን ሌኖቮ አብሮ ባያያዘው ተመሳሳይ ቅሬታ ከአሁን ቀደም በአገልግሎቱ ወደ ፋይናንስ ግምገማ እንዲያልፍ ተደርጎ የነበረው ባክ ዩኤስኤ እንዲወድቅ ተደርጓል፡፡

ሌኖቮ ሦስት ሚሊዮን ታብሌቶችን በዓመት መሸጥ አለበት የሚለውን መሥፈርት አላሟላም ብሎ ለቦርዱ ባስገባው ቅሬታ፣ ባክ ዩኤስኤ ማለፍ እንደማይገባው ተከራክሮ እንደነበር የሪፖርተር ምንጮች ተናግረዋል፡፡

በዚህም መሠረት ባክ ዩኤስኤ እንዲወድቅ ተደርጓል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ወደ ፋይናንስ ግምገማ እንዲያልፉ የተደረጉትን የሁዋዌንና ሌኖቮን የፋይናንስ መዝገብ (ዶክሜንት) በአገልግሎቱ እንደተከፈተ ይታወሳል፡፡

ነገር ግን ከአሁን ቀደም አግልግሎቱ የካቲት 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ለባክ ዩኤስኤ በጸፈው ደብዳቤ፣ ሦስት ሚሊዮን ታብሌቶችን በዓመት መሸጥ አለበት የሚለውን መሥፈርት ማረጋገጫ የጨረታው ሒደት ካለቀ በኋላ መቅረብ እንደሚችል ገልጾ ነበር፡፡

በጭቅጭቅና በቅሬታ በተሞላው የጨረታ ሒደት ከአሁን ቀደም በጨረታው ላይ ተሳትፈው የነበሩ ስድስት ኩባንያዎች ለአገልግሎቱ ቅሬታ አቅርበው ነበር፡፡ አገልግሎቱ ግን ቅሬታቸውን ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ዜድቲኢ፣ አይላይፍ፣ ቴክኖ፣ ሲምቦ ሪሶርስ፣ ሌኖቮና መስቴክ አፍሪካ የተባሉት ድርጅቶች ውጤቱን እንደማይቀበሉትና ጉዳያቸው እንደገና በአገልግሎቱ እንዲታይ አመልክተው ነበር፡፡

በዚህም ምክንያት በአገልግሎቱ ውሳኔ ያልተደሰቱ ሦስት የጨረታው ተሳታፊ ኩባንያዎች ቅሬታቸውን ወደ ኤጀንሲው ወስደዋል፡፡

በዚህም መሠረት ከስድስቱ ተጫራቾች ቴክኖ፣ ሲምቦ ሪሶርስና ሌኖቮ የተባሉ ተጫራቾች ያቀረቡትን ቅሬታ ሲያይ ቆይቶ ባለፈው ሳምንት ውሳኔ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ አገልግሎቱ በቴክኖና ሲምቦ ሪሶርስ የቀረበውን ቅሬታ ውድቅ አድርጎ፣ እነዚህ ሁለት ኩባንያዎች ወደ ፋይናንስ ግምገማ ማለፍ የለባቸውም የሚለውን ውሳኔ አፅድቋል፡፡

ከአሁን ቀደም አገልግሎቱ የአሜሪካው ባክ ዩኤስና የቻይናው ሁዋዌ ኩባንያዎች ወደ ቀጣዩ የፋይናንስ ግምገማ ዙር እንዲያልፉ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

በዚህ ጨረታ ቴክኖ ሞባይል እንደ አገር ውስጥ ተጫራች ተወዳድሮ የነበረ ሲሆን፣ ቦርዱ በወሰነው ውሳኔ መሠረት ቴክኖ ከዓመታዊ ሽያጭ ጋር በተያያዘ በትንሹ ሦስት ሚሊዮን ታብሌቶችን በዓመት መሸጥ አለበት የሚለውን መሥፈርት ባለማሟላቱና ከሞባይል ሶፍትዌር አስተዳደር ጋር የተያያዙ መረጃዎችን በዝርዝር ባለማቅረቡ ቅሬታው ውድቅ ተደርጓል፡፡

ሌላው ሲምቦ የተባለው ኩባንያ ደግሞ ከታብሌቶቹ ውስጣዊ መሣሪያዎች መረጃ የመያዝ አቅም ጋር በተያያዘ የተፈለገውን መሥፈርት ባለማሟላቱ እንዲሁ ሊወድቅ ችሏል፡፡

ባክ ዩኤስኤ ካቀረበው ቅሬታ ጋር በተያያዘ በአሁኑ ጊዜ ኤጀንሲው ጉዳዩን እየተመለከተው እንደሆነ የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የባክ ዩኤስኤ ምንጮች ሌኖቮ በኩባንያው ላይ አቅርቦት የነበረውን ቅሬታ አሳሳችና በቂ እንዳልሆነ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አጨቃጫቂ ሆኖ የቀጠለው የጨረታው የቴክኒክ ግምገማ ከመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ እንዲሁም ከመረጃና ደኅንነት ኤጀንሲ በተወጣጡ ባለሙያዎች መደረጉ ይታወሳል፡፡

ታብሌት ኮምፒዩተሮቹ በግንቦት 2009 ዓ.ም. ግዢያቸው ተጠናቆ ይቀርባሉ ተብሎ ቢጠበቅም፣ በተፈጠረው የጨረታ መዘግየት አቅርቦቱ ለአንድ ወር ተራዝሟል፡፡

በሚቀጥለው ዓመት ለሚካሄደው የሕዝብ ቆጠራ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በአጠቃላይ ወደ ሦስት ቢሊዮን ብር መድቧል፡፡ ታብሌቶቹ ደግሞ እስከ አንድ ቢሊዮን ብር ያስወጣሉ ተብሏል፡፡

ግዥው ከተፈጸመ በኋላ ታብሌቶቹ በአውሮፕላን ተጓጉዘው ይገባሉ፡፡ የሕዝብ ቆጠራው ከተደረገ በኋላ ደግሞ ለሌሎች ተመሳሳይ ቆጠራዎች ይውላሉ፡፡

ለደኅንነትም ሲባል ባትሪያቸው እስከ 30 በመቶ ብቻ እንዲሞሉ ይደረጋል፡፡ ከአሁን ቀደም ኤጀንሲው ለዋናው የሕዝብ ቆጠራ ዝግጅት እንዲረዳው የሙከራ ቆጠራ ባለፈው ዓመት የጀመረ ሲሆን፣ በዚህም 220 የሚሆኑ የተመረጡ ቦታዎች በታብሌት ኮምፒዩተሮች የታገዘ ቆጠራ ተደርጎላቸዋል፡፡

በኅዳር 2010 ዓ.ም. ይደረጋል ተብሎ ለሚጠበቀው የሕዝብ ቆጠራ ብሔራዊ ቆጠራ ኮሚሽን መቋቋሙ ይታወሳል፡፡ አገሪቱ ከዚህ በፊት የመጨረሻውንና ሦስተኛውን ቆጠራ በ1999 ዓ.ም. አድርጋለች፡፡ በዚህም ቆጠራ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 73.8 ሚሊዮን መድረሱ ይታወሳል፡፡ አሁን ባለው መረጃ መሠረት ደግሞ 100 ሚሊዮን ይጠጋል እየተባለ ነው፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች