የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰሞኑን በተንቀሳቃሽ ስልኮች ላይ እየላካቸው ካሉ የጽሑፍ መልዕክቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት በቅርቡ ባወጣው ድንጋጌ መሠረት ሰነድ አልባ የውጭ ዜጎች በ90 ቀናት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በዚህ ትዕዛዝ መሠረት ቀነ ገደቡን ጠብቀው የሚወጡ ዜጎች ያፈሩትን ሀብትና ገንዘብ ይዘው እንደሚወጡ፣ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ቃል ገብቷል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ቤት ለቤት በሚደረግ አሰሳ የሚያዙ የውጭ ዜጎች ንብረታቸው ይወረሳል፡፡ እነሱም እስር ቤት ከገቡ በኋላ በግዳጅ ይባረራሉ ብሏል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በተባለው መሠረት ኮማንድ ፖስት አቋቁሞ ዜጎችን ለመመለስ ጥረት ቢያደርግም፣ ከ300 ሺሕ በላይ ሰነድ አልባዎች ውስጥ የተመዘገቡት 23 ሺሕ ብቻ ናቸው ተብሏል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዚህ በፊት እንደደረሰው ዓይነት እንግልትና ስቃይ እንዳይደርስ ነው ሳዑዲ ያሉ ዜጎችን ለማስመለስ ይኼንን ጥሪ ያቀረበው፡፡ በምሥሉ ላይ የሚታዩት ከዚህ ቀደም ከሳዑዲ ዓረቢያ በግዳጅ የተባረሩ ዜጎች ናቸው፡፡