Tuesday, February 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መንገዶች ባለሥልጣን በነካ እጅህ ለጎርፉም ተነሳ!

ከአንድ ወር ተኩል በኋላ መደበኛው የክረምት ወቅት እንደሚገባ ይጠበቃል፡፡ ክረምት በመጣ ቁጥር ግን እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ውስጥ የምንኖር ሰዎች በተደጋጋሚ አቤት የምንልበት ጉዳይ አለ፡፡

ይኸውም ከአዲስ አበባ ከተማ መንገዶችና የክረምቱ ወራት እሳትና ጭድ መሆናቸው ነው፡፡ ዝናብ ጠብ ባለ ቁጥር ጠብ አላቸው፡፡ የዝናብ ውኃ ያቆሩ መንገዶች፣ ሲቦረቦሩና ሲሸረሸሩ፣ አገልግሎት ሲያጓድሉ ኖረዋል፡፡ ነገሩ ተጋኗል ካልተባለ በቀር የከተማው መንገዶች የሚተኛባቸው ውኃ ጀልባ ሳያስቀዝፍም አይቀር፡፡

ውኃ የሚተኛባቸው የከተማው መንገዶች የትራፊክ እንቅስቃሴ ሲያውኩ እየታየ ብዙውን ጊዜም አፋጣኝ መፍትሔ ሳያገኙ የሚቆዩበት ምክንያት ግራ ያጋባል፡፡ ይህ በመሆኑም የመፍትሔ ያለ ማለቱ ግድ ነው፡፡

መንገዶች ውኃ በሚተኛባቸው ጊዜ የቤት አውቶሞቢልን የመሳሰሉ ቀላል ተሽከርካሪዎች በቀላሉ ማለፍ ሲሳናቸው ይታያል፡፡ ደፍረው ወደ ውኃው የሚገቡም አሰነካክለው ያርፉታል፡፡ ይህ ችግር ለዓመታት የዘለቀ እንደመሆኑ መጠን፣ ውኃ በሚያቁሩ መንገዶች በኩለወ ሰርክ አገልግሎት የሚሰጡ የትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች በሚንጣለለው ውኃ ምክንያት እንቅስቃሴያቸው ሲገታ ይታያል፡፡ ውኃው ወደሚሄበት ሄዶ መንገዱን እስኪለቅ ድረስ ባሉበት ለመቆም ሲገደዱ ታዝበናል፡፡ ተማሪ የሚያመላልሱ መኪኖች መላወስ አቅቷቸው ሲያዙ፣ በልጆቻቸው መዘግየት ወላጆች ሲረበሹ፣ ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤት ለማምጣት ሔደው ውኃው ከመንገድ ያስቀራቸው፣ ህመምተኛ ሆስፒታል ለማድረስ የሚከንፉ አምቡላንሶች መሻገሪያ አጥተው በቆሙበት እዬዬያቸውን ሲያቀልጡ አብረን አላቅሰናል፡፡ የዚህ ሁሉ ምክንያቱ ውኃ ያቆሩ ጎዳናዎች መፍትሔ ሳይበጅላቸው በመቆየታቸው ነው፡፡

 ፋብሪካዎቻቸው ከተዘጉ ዓመታትን ያስቆጠሩ፣ ያፈጁ ተሽከርካሪዎች የሚርመሰመሱበት ከተማ በመሆኑ፣ እነዚህን ተሽከርካሪዎች ከላይ ዝናብ ከሥር ጎርፍ ሲፈራረቅባቸው ተንተፋትፈው ለመቆም ይገደዳሉ፡፡ የሌሎች ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴም ይገታሉ፡፡ ጎዳናዎቹ ላይ የተኛው የዝናብ ውኃና ጎርፍ ከሄደ በኋላም የትራፊክ ችግሩ ማተራመሱን አያባራም፡፡

ስለዚህ የክረምቱ ውኃ በአግባቡ እንዲወገድ የሚያደርግ መፍትሔ ካልተሰጠው በቀር ጦሱ ከየአቅጣጫው ስለሚበራከት፣ ከዚህ አዙሪት እንድንወጣ የሚያስችን እውነተኛ መፍትሔ እንሻለን፡፡ 

ክረምት በገባ ቁጥር ለአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን አቤት ሲባልባቸው ከቆዩ የከተማው መንገዶች አንዱ የቀለበት መንገድ ነው፡፡ በቀለበት መንገዱ ቢያንስ ስድስት አካባቢዎች ዝናብ እንደሚተኛባቸው እማኝ ሳይጠሩ መናገር ይቻላል፡፡

በኢምፔሪያል፣ በአደይ አበባ፣ በሐኪም ማሞ መታጠፊያ አካባቢ፣ በ18 ማዞሪያ የሚያልፈው የቀለበት መንገድ ላይ ውኃ እየተኛበት ለእንቅስቃሴ ጋሬጣ መሆን ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ለቀለበት መንገድ ውኃ ማስተላለፊያ ተብለው የቀበሩ ቱቦዎች ጠባቦች፤ አንዳንዶቹም ከነጭራሹ በቆሻሻ በመደፈናቸው ምክንያት የሚፈጠር ችግር እንደሆነ እስኪታክተን ተናግሮናል፡፡ የተኛውን ውኃ ተቀብለው ወደ ሚሄድበት ቦታ ለመሸኘት ያላቸው አቅም ደካማ መሆኑ ታውቆ መፍትሔ ሊሰጥባቸው አለመቻሉ ግራ ያጋባል፡፡

በቀላሉ ማስተካከል እየተቻለ ችግሩን መቅረፍ አልተቻለም፡፡ ክረምቱ ሲገባ የሚፈጠረውን መተረማመስ ለመግታት፣ ዝናብ ከመጣሉ በፊት ለዓመታት እሮሮ ሲቀርብባቸው የነበሩ አቋሪ መንገዶችን ዘንድሮ እንኳ እረፉ ቢለን በማለት ክረምት  ለባለሥልጣኑ አቤት እንላለን፡፡ ነገሩን ለማንሳት የወደድኩት፣ በ2009 በጀት ዓመት ባለሥልጣኑ በከተማዋ ለመንገድ ጥገና ሥራዎችና ለትራፊክ ፍሰት እንቅፋት ናቸው የተባሉ አደባባዮችን አፍርሶ የመንገድ መጣበብን ለመቀነስ እየሠራ እንደሚገኝ በማየታችን፣ ለጎርፉም መለያ አያጣለትም ከሚል ዕምነት ነው፡፡ የባለሥልጣኑን የወቅቱ ሥራ እያደነቅን በዚሁ ትንፋሽና ወኔው የዓመታት ጥያቄያችንን እንዲመልስልን በመሻትም ነው፡፡

ሰሞኑን ከባለሥልጣኑ የተሰማው ዜና ክረምቱ ከመግባቱ በፊት የተጎዱ መንገዶችን የመጠገን ሥራ እንደሚያገዳድድ የሚያስታውቅ ነው፡፡ እንዳያያዙ ያለው ተግባሩም ይሠምራል ብለን እናምናለን፡፡

ላለፉት ተከታታይ ወራት ያሳየው ትጋት መንገዶች ላይ እየተኛ ያስቸገረውን ጎርፍ ለማስቀረት የሚያስችል አቅም እንዳለው የሚያሳይ በመሆኑ፣ በነካ እጅህ ከጎርፍ የሚጠብቃቸውንም ሥራ እባክህ ጨምርበት እንለዋለን፡፡

ክዳናቸው የተነሳ የፍሳሽ ማስተናገጃ ቱቦዎች ሲያገኙ ያለሐሳብ ቆሻሻ የሚጥሉ ነዋሪዎችም የመንገድ ጠንቆች ናቸው፡፡ ከየቤታቸው እንዳሻቸው በየመንዱ ዳር ቆሻሻ የሚነሰንሱትም እንዲህ ካለው ነውረኛ ድርጊት ቢታቀቡ የመንገዱ ጤና ትንሽ መለስ ማለቱ አይቀሬ ነው፡፡ ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ከየአካባቢያችን በዝናብ ሰበብ እየተጣሉ ፍሳሽ ማስወገጃዎችን የሚደፍኑ ደረቅ ቆሻሻዎችን በአግባቡ በማስወገድ ኃላፊነታችንን ብንወጣ ምሬታችንን ልንቀንስ እንችላለን፡፡ ይህ ካልሆነ የከተማችን ጎዳናዎች በመጪው ክረምትም በውኃ ተጥለቅልቀው ‹‹ዛሬ የጣለው ዝናብ የከተማዋን የትራፊክ እንቅስቃሴ አስተጓጎለ፤››፣ ‹‹የፍሰሽ ማስወገጃዎች በመደፈናቸው በተፈጠረ ጎርፍ የእከሌ ቀበሌ ነዋሪዎች በጎርፍ ተመቱ፤›› የሚሉ ዜናዎችን እየሰማን መዝለቃችን አይቀሬ ነው፡፡ ክረምቱን ለአደጋ ከሚጋልጡ መንገዶችና የውኃ መስመሮች የተጠበቀ በማድረግ ማሳለፍ የምንችልበት እንደሆን ሁሉም በየፊናው ይዘጋጅ፡፡ ባለሥልጣኑም ለዚህ የሚመጣጠን የመፍትሔ ዕርምጃ ይውሰድ፡፡

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት