Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትአትሌቲክስ ፌዴሬሽንና ሔይኒከን ኢትዮጵያ የ30 ሚሊዮን ብር የስፖንሰርሽፕ ስምምነት አደረጉ

አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና ሔይኒከን ኢትዮጵያ የ30 ሚሊዮን ብር የስፖንሰርሽፕ ስምምነት አደረጉ

ቀን:

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከትልልቅ የንግድ ኩባንያዎች ድጋፍና ማበረታቻ ብዙም ሳያገኝ የቆየ ዘርፍ ነው፡፡ አትሌቲክሱ ብቻም ሳይሆን የተቀረውም የስፖርት ዘርፍ እንዲህ ያሉ የኩባንያዎችን ድጋፍ አያገኝም ማለት ይቻላል፡፡

ከሰሞኑ ግን እንደ ሔይኒከን ያሉ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በስፖርቱ ዘርፍ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሠረተ የስፖንሰርሽፕ ስምምነት ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ኩባንያው ከዚህ ቀደም የበደሌ ምርት በሆነው ዋሊያ ቢራ አማካይነት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የማስታወቂያ ስፖንሰርሽፕ ስምምነት ማድረጉ ይታወሳል፡፡ በዚሁ አኳኋን ሔይኒከን ኩባንያዎች አንዱ የሆነውና ሶፊ ማልት የኢትዮጵያ አትሌቲክስን ለአምስት ዓመት በ30 ሚሊዮን ብር ስፖንሰር ለማድረግ ኮንትራት ፈርሟል፡፡ በፌዴሬሽኑና በሔይኒከን መካከል የተደረገው ስምምነት ለሁለቱም ወገኖች የጋራ ጥቅም እንደሚኖረውም ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኃይሌ ገብረሥላሴና የሔይኒከን ኢትዮጵያ ማኔጅንግ ዳይሬክተር ሔሪት ቫንሎ በተገኙበት፣ ግንቦት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሒልተን የተከናወነው የስፖንሰርሽፕ ስምምነት ለኩባንያውም ሆነ ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሰጠው ግልጋሎት ከፍተኛ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ዳይሬክተሩ ሔሪት ቫንሎ፣ ‹‹ሶፊ ማልት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዋና ስፖንሰር በመሆኑ ኩራት ይሰማዋል፡፡ ምክንያቱም ስምምነቱ ዓለም ላይ ትልቅ ስምና ዝና ያላቸው የኢትዮጵያን አትሌቶች ለመደገፍ ዕድል የፈጠረለት መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ አትሌቶች አቅም ያላቸው በመሆናቸው ከኩባንያውና ከምርቱ ጋር የተመሠረተው አጋርነት ትክክለኛ አቻነትን የፈጠረ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በቀጣይም በስፖንሰርሽፕ ዓላማዎች በመመሥረት ሶፊ ማልት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድንን ለመጪዎቹ ውድድሮች የሚያዘጋጃቸው የተለያዩ ኩነቶች እንደሚኖሩትም ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለይም በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቁ ትጥቅ አምራች ኩባንያዎች አዲዳስና ናይኪን ከመሳሰሉ ጋር ለዓመታት የሚዘልቅ የስፖንሰርሽፕ ስምምነት ያደረጉ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ራሱ ከአዲዳስ ጋር የቆየና ወደፊትም የሚቀጥል ስምምነት እንዳለው ይታመናል፡፡ ከዚህ በመነሳት በስምምነቱ ወቅት የተለያዩ ጥያቄዎች ማለትም ለአምስት ዓመት 30 ሚሊዮን ብር አያንስም ወይ? አትሌቶቹም ሆኑ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ቀደም ሲል ከገቡት ስምምነት አንፃር የአሁኑ የጥቅም ግጭት አይፈጥርም ወይ? የሚሉ በርካታ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡

ለተነሱት ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጠው ሻለቃ ኃይሌ፣ ‹‹የኢትዮጵያ አትሌቲክስም ሆነ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በስፖርቱ እንዳላቸው ስምና ዝና ተጠቃሚዎች እየሆኑ አይደለም፡፡ እንዲያውም በእኔ እምነት ገና ብዙ ይቀረናል፡፡ የሚፈጥረው የጥቅም ግጭት ግን አይኖርም፤›› ብሏል፡፡ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዓለም ላይ ካላቸው ስምና ዝና አኳያ ፌዴሬሽኑ በአምስት ዓመት ውስጥ የሚያገኘው 30 ሚሊዮን ብር አያንስም ወይ? ለተባለው ደግሞ፣ ከዚህ ቀደም ምንም በሌለበት የአሁኑ ‹‹ያንሳል? አያንስም?›› ብሎ መከራከር በዚህች ወቅት መነሳት እንደሌለበት፣ ይሁንና ለወደፊቱ ግን ዘርፉ ሊያስገኝ በሚችለው ጥቅም ላይ ከተሠራ ጥያቄውን በማንሳት መደራደር እንደሚቻል ጭምር በመግለጽ አስረድቷል፡፡

ፌዴሬሽኑ በዚህ ገንዘብ ሊጠቀምበት ያሰበውን ፕሮጀክት አስመልክቶ ኃይሌ ሲናገር፣ አትሌቲክስ የሜዳ ተግባራትን ጨምሮ በርካታ የስፖርት ዘርፎችን እንደሚያቅፍ፣ ይሁንና በኢትዮጵያ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ደግሞ አገሪቱ ‹‹ውጤታማ ነኝ›› የምትለው አምስትና አሥር ሺሕ እንዲሁም በማራቶን ካልሆነ በተቀረው የስፖርት ዘርፍ እንደሌለችበትም ተናግሯል፡፡

አሁን ፌዴሬሽኑን እያስተዳደረ የሚገኘው የሥራ አመራር ቦርድም ኃላፊነቱን በተረከበ ማግሥት ያደረገው ቢኖር፣ በአገሪቱ በሁሉም አቅጣጫ ባለሙያዎች በመላከ የዳሰሳ ጥናት እንዲደረግ በማድረግ ስትራቴጂክ ዕቅድ ማዘጋጀቱንም ገልጿል፡፡ ገንዘቡንም ለዚህ ዕቅድ እንደሚጠቀምበት ጭምር አስረድቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...