Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አቶ ልደቱ አያሌው ከሸሪኮቻቸው ጋር በላሊበላ ከተማ ሪዞርት መገንባት ጀመሩ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ፖለቲካና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ የሚያማክር ኩባንያ መሥርተዋል

በኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ ጉልህ ሥፍራ ያላቸው አቶ ልደቱ አያሌው፣ በታሪካዊቷ ላሊበላ ከተማ ሪዞርት መገንባት ጀመሩ፡፡ አቶ ልደቱ ከሪዞርት ግንባታው በተጨማሪ፣ በራሳቸው ስም ምኅፃረ ቃል የሚጠራ (L.A) አማካሪ ኩባንያ መሥርተዋል፡፡

አቶ ልደቱ ከ11 ሸሪኮቻቸው ጋር ማይኔስት ሪል ስቴት የተሰኘ ኩባንያ አቋቁመዋል፡፡ ይህ ኩባንያ በሪል ስቴት ሥራ ላይ የተሰማራ ነው፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት የአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የላሊባላ ከተማ አስተዳደር ያወጣውን የሊዝ ጨረታ በማሸነፍ ወደ ሪዞርት ግንባታ ገብቷል፡፡

የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ከከተማው ወጣ ብሎ በሚገኘው መካልድ ተራራ ላይ ለመዝናኛ የሚውል 6,500 ካሬ ሜትር ቦታ በሊዝ ለማስተላለፍ ያወጣውን ጨረታ አቶ ልደቱና ወዳጆቻቸው ያቋቋሙት ማይኔስት ሪል ስቴት፣ በአንድ ካሬ ሜትር 1,806 ብር በማቅረብ አሸናፊ ሆኗል፡፡

ኩባንያው ማይኔስት ጨረታውን ያሸነፈው ከሦስት ዓመት በፊት ቢሆንም፣ በወሰን ማስከበርና በመሠረት ልማት አለመሟላት ችግሮች ምክንያት ዘግይቶ ግንባታው ከጀመረ ገና ዘጠኝ ወሩ ነው፡፡

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) መሥራችና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ልደቱ አያሌው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በመሠረተ ልማት በኩል ባለፉት ስድስት ወራት መሻሻሎች ቢኖሩም፣ አሁንም የኤሌክትሪክ ኃይልና ውኃ የለም፡፡

አቶ ልደቱ ጨምረው እንደገለጹት፣ ለሪዞርቱ ግንባታ እስካሁን 38 ሚሊዮን ብር ወጥቶበታል፡፡ ኩባንያው ማይኔስት 40 በመቶው የሚሆነው ገንዘብ ኢንቨስት ካደረገ በኋላ፣ 60 በመቶው የሚሆነውን ከባንክ በብድር ለማግኘት ዕቅድ አለው፡፡

‹‹ሪዞርቱ አካባቢውን የሚመስል፣ የአካባቢውን ኅብረተሰብ አኗኗር የሚያሳይ፣ የአካባቢውን ምርት የሚጠቀም ይሆናል፤›› ሲሉ የገለጹት አቶ ልደቱ፣ ‹‹የአካባቢውን ባህል፣ ወግና ሥርዓት ተግባራዊ ያደርጋል፤›› በማለት ሪዞርቱ ከአካባቢው ማኅበረሰብና ሥነ ምኅዳር ጋር የሚወዳጅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አቶ ልደቱ ከፖለቲካ ተሳትፏቸው በተጨማሪ በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ይታወቃሉ፡፡ ለአብነትም የተለያዩ ተሽከርካሪዎች ከውጭ አስመጥቶ መሸጥና የእህል ወፍጮ ሥራዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በአሁኑ ወቅት እየገነቡ ካሉት ሪዞርት በተጨማሪም ኤልኤ አማካሪ ኩባንያ አቋቁመዋል፡፡ አቶ ልደቱ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አዲሱ የቋቋሙት አማካሪ ድርጅት በፖለቲካና በኢኮኖሚ ጉዳዮች የማማከር ሥራዎችን ያከናውናል፡፡

‹‹በፖለቲካና በኢኮኖሚ ዘርፎች ክፍተቶች አሉ፡፡ የእኔ ኩባንያ እነዚህን ክፍተቶች ለመሙላት ይሞክራል፤›› ሲሉ አቶ ልደቱ ገልጸዋል፡፡

በንግድ ሥራዎች ላይ መጠመዳቸው በፖለቲካ ተሳትፎአቸው ላይ ተፅዕኖ አይኖረውም ወይ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ልደቱ ሲመልሱ፣ ‹‹እንዲያውም በተሻለ ደረጃ የፖለቲካ ተሳትፎዬን ያጠናክራል፡፡ ራሱን ችሎ የሚጓዝ ቢዝነስ ሲኖር ፖለቲካ ላይ ትኩረት ማድረግ ይቻላል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

አቶ ልደቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ካገኟቸው የታሪክና የፖለቲካ ሳይንስ ዲግሪዎች በተጨማሪ፣ እንግሊዝ ለንደን ዩኒቨርሲቲ ስኩል ኦፍ አርየንታል ኤንድ አፍሪካን ስተዲስ በዴቨሎፕመንታል ስተዲስ የማስተርስ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡

አቶ ልደቱ የፖለቲካ ትንታኔዎች ላይ ያተኮሩ ሦስት መጻሕፍትን ያበረከቱ ሲሆን እነሱም ‹የአረም እርሻ፣ መድሎትና ቴአትረ ቦለቲካ› ይሰኛሉ፡፡      

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች