Thursday, May 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርት‹‹ናትና›› የጎዳና ሩጫ በመቐለ

‹‹ናትና›› የጎዳና ሩጫ በመቐለ

ቀን:

በማደግ ላይ ከሚገኙ ከተሞች አንዷ በሆነችው መቐለ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች የታደሙበት የጎዳና ላይ ሩጫ ባለፈው ሳምንት ተሰናድቶ ነበር፡፡ ‹‹ናትና›› [የእኛ] የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ የአሥር ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ ያሰናዱት አንጋፋዎቹ ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያምና ባለቤቱ ወርቅነሽ ኪዳኔ ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ሲሆን፣ ሚያዝያ 29 ቀን 2009 ዓ.ም. በተካሄደበት ወቅት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችና የከተማው ነዋሪዎች በነቂስ በመውጣት ስፖርታዊ ክንውኑን አድምቀውታል፡፡ ሰሜናዊቷ ኮከብ መቐለ፣ በ2010 ዓ.ም. ለሦስት ታላላቅ ውድድሮች ስድስተኛውን የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች፣ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችንና የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎችን ዓመታዊ ሻምፒዮናዎች የምታስተናግድ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ‹‹ናትና›› የአሥር ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድርን ከመስፍን ኢንጂነሪንግ በወንዶች ኃይለ ማርያም ኪሮስና በሴቶች ደግሞ ቅዱሳን አለማ ርቀቱን በ32፡32፡09 እና በ36፡12፡91 አጠናቀው አሸናፊዎች ሆነዋል፡፡ እያንዳንዳቸው 30 ሺሕ ብር ተሸልመዋል፡፡ የመሰቦ ሲሚንቶዎቹ በወንዶች አረዶም ጡዑማይ በ32፡32፡69 እና በሴቶች ፎቴን ተስፋዬ በ36፡26፡92 አጠናቀው እያንዳንዳቸው 20 ሺሕ ብር ሲሸለሙ፣ ሦስተኛ በመሆን ከመስፍን ኢንጂሪነግ አብርሃ ሐንሳ በ32፡34፡16 እና ከመሰቦ ሲሚንቶ ንግስቲ ሐፍቱ በ36፡34፡38 አጠናቀው እያንዳንዳቸው 10 ሺሕ ብር ተበርክቶላቸዋል፡፡ የ‹‹ናትና›› የጎዳና ላይ ሩጫ መሥራች ገብረ እግዚአብሔር ገብረማርያም የውድድሩን ዓላማ አስመልክቶ እንደተናገረው፣ አትሌቲክስን የክልሉ በኅብረተሰቡ ዘንድ ለማስረጽ ነው፡፡ በሚገኘው ገቢ የክልሉን ስፖርት ማስፋፋት ይቻል ዘንድ ለማዕከላት ግንባታ እንደሚውል ተናግሯል፡፡ ስያሜውን ‹‹ናትና›› ያለበት ምክንያት ደግሞ አትሌቲክሱ እንዲህ እንደ አሁኑ ባልዘመነበት ኢትዮጵያውያን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው የተመሠረተው በእግር ጉዞ በመሆኑ፣ የሩጫ ስፖርትም የኢትዮጵያውያን መሆኑን ለማሳየት እንደሆነ ተናግሯል፡፡ የኅብረተሰቡን ተሳትፎ በሚመለከት ውድድሩ የመጀመሪያ እንደመሆኑ መጠን ከተሳታፊው ቁጥር ሦስትና አራት እጥፍ የሚሆነው ተመልካች እንደነበረ የተናገረው ገብረእግዚአብሔር፣ እንደዚያም ሆኖ ከተጠበቀው በላይ የተሳታፊ ቁጥር መመዝገቡንና አሥር ሺሕ የመሮጫ ቲሸርት መሸጡንም ተናግሯል፡፡ በጎዳናው የሩጫ ውድድር በክብር እንግድነት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኃይሌ ገብረሥላሴን ጨምሮ ቀደምቶቹ ደራርቱ ቱሉ፣ ገዛኸኝ አበራና አምበሴ ቶሎሳ፣ ከአሁኖቹ ደግሞ ደጀን ገብረመስቀል ተገኝተው ነበር፡፡ አትሌቶቹ ከውድድሩ ቀን አስቀድሞ ከ31 ሺሕ በላይ ተማሪ በሚገኝበት መቐለ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ በመገኘት ለተማሪዎቹ ተሞክሮዎቻቸውን አካፍለዋል፡፡ በቅጥር ግቢው በነቂስ የተገኙት ተማሪዎችም ለቀድሞዎቹ አትሌቶች ያላቸውን ክብርና አድናቆት ገልጸውላቸዋል፡፡ የነበረውን ሁኔታ የታዘቡ አንድ የዩኒቨርሲቲው ምሁር፣ አገሪቱ ከእነዚህ አትሌቶች ልትጠቀም የምትችልባቸው በርካታ ነገሮች እንደሚኖሩ አጋጣሚውን በመመልከት መረዳት መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ የውድድሩ አዘጋጅ ገብረ እግዚአብሔር ገብረማርያም፣ ቀደምቱን የአገር ባለውለታዎች የናትና› የጎዳና የሩጫ ውድድር የክብር እንግዳ ለማድረግ ሲወሰን ዓላማና ፍላጎቱም ይኼው መሆኑን ነው ያስረዳው፡፡ ቀደምቱ ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ በተጨማሪ በከተማዋ በተዘዋወሩባቸው ሁሉ ከፍተኛ የሆነ ክብርና አድናቆት ሲቸራቸው ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...