Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየስፖርት ጋዜጠኞችን ያስተሳሰረው ማኅበር

የስፖርት ጋዜጠኞችን ያስተሳሰረው ማኅበር

ቀን:

በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ስፖርታዊ ክንውንን መዘገብ ከተጀመረ ስምንት አሠርታት ግድም እንዳስቆጠረ ይነገራል፡፡ እስከ 1928 ዓ.ም. የነበሩ ክንውኖች በተወሰነ መልኩ ቢዘገቡም፣ በፋሺስት ጣሊያን ወረራ ዘመን (1928-1933) ይወጡ በነበሩ የአማርኛ ጋዜጦች እግር ኳስን፣ ብስክሌትና ሌሎችን ስፖርቶች አንዳንድ ክንውን ሲዘገቡ ቆይተዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ድል በኋላ በሁለገብ የአገር ግንባታ ሒደት አንዱ አካል በነበረው ስፖርት፣ ወዘተ ክንውኑን በወቅቱ የነበሩት ጋዜጦች የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ አዲስ ዘመን፣ ስፖርቱን የተመለከቱ ዘገባዎች ያስተናግዱ እንደነበር ይወሳል፡፡ ከቀደምት ጋዜጠኞች መካከል እነ ፍቅሩ ኪዳኔ፣ ሰሎሞን ተሰማ፣ ነጋ ወልደሥላሴ፣ ይንበርበሩ ምትኬ ወዘተ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በኅትመት የተጀመረው ወደ ሬዲዮና ቴሌቪዥን እንዲሁም በቅርቡ ወደ ድረ ገጽ አድማሱን በማስፋት፣ ከሦስት አሠርታት ወዲህ በተለይ በግል ሚዲያዎች ጭምር በተፈጠረው መስክ በርካታ የስፖርት ጋዜጠኞች በአሁኑ ጊዜ በሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡ በየተቋማቸው እየሠሩ ካሉት ተግባር ጎን ለጎን በጋራ የሚያገናኛቸው፣ የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት ለአህጉራዊና ዓለም አቀፍ መድረኮች የሚያስበቃቸውን ማኅበር በማቋቋም እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ በ2004 ዓ.ም. እንደ አዲስ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበር (ኢስጋማ) ይባላል፡፡ የሚመራውም ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ የስፖርት ጋዜጠኛና በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን 94.4 ኤፍኤም ሬዲዮ ኃላፊ፣ በአፍሪካ ስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባሉ ዮናስ ተሾመ ነው፡፡ በማኅበሩ እንቅስቃሴ ዙሪያ ከፕሬዚዳንቱ ዮናስ ተሾመ ጋር ሔኖክ ያሬድ ለአፍታ ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- የማኅበሩ አመሠራረት እንዴት ይገለጻል?

አቶ ዮናስ፡- ማኅበሩን ለመጀመሪያ ጊዜ የመሠረተው አሁን ያለው አመራር አይደለም፡፡ ከዚህ በፊት በእነአቶ ጎርፍነህ ይመር፣ ደምሴ ዳምጤ፣ ከበደ በየነ፣ ገዛኸኝ ጽዮን መስቀል በመሳሰሉት አንጋፋ ጋዜጠኞች ተመሥርቶ ነበር፡፡ ይሁንና ማኅበሩ ምክንያቱን ለጊዜው እንዲህ ነው ብለን መናገር ባንችልም ብዙ መጓዝ አልቻለም ነበር፡፡ የማኅበሩን አባላት አንድ በማድረጉ ብዙ አልሄደም፡፡ ህልውና ለረዥም ዓመታት የማኅበሩ ህልውና ደብዝዞ እንዲቆይ ሆኖም ነበር፡፡ ይሁንና ከአምስት ዓመታት በፊት ማኅበሩን እንደገና ያቋቋምነው በ2004 ሲቋቋም በአጋጣሚ ነበር፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ የኢትዮጵያ እግር  ኳስ ፌደሬሽን እነ አቶ ሳህሉ ገብረወልድ በነበሩበት ጊዜ እግር ኳሱን በሚመለከት አንድ ጥናት ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ጥናቱ በቀረበበት መድረክ ለስፖርቱ እንደ አንድ ችግር ተደርጎ የተወሰደው የስፖርት ሚዲያው ነበር፡፡ በወቅቱ ለዘገባ በስፍራው የነበሩ ጋዜጠኞች የቀረበው ጥናት ላይ ከተነጋገሩበት በኋላ ለእግር ኳሱ መውደቅ ተጠያቂው የሚያስተዳድረው አካል መሆን ሲገባው የስፖርት ሚዲያው በምክንያትነት መነሳቱ ተገቢ እንዳልሆነ በመነጋገር ስብሰባው እንደተጠናቀቀ፣ የስፖርት ሚዲያው ቢያንስ የራሱን ሐሳብ የሚያነፀባርቅበት አንድ ነገር ሊኖረው እንደሚገባ በመስማማት ወዲያውኑ ከፌደሬሽን አመራሮች ጋርም በመገናኘት ሚዲያው በምክንያትነት መጠቀሱ ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረናል፡፡ በዚህ ብቻ ሳንወሰን እግር ኳስ ፌደሬሽን በስፖርት ሚዲያው ላይ ያቀረበው ውንጀላ አግባብ እንዳልሆነም ቁጥራቸው 50 የሚደርስ የስፖርት ጋዜጠኞች ፒቲሽን ተፈራርመን ለሚመለከተው አካል ደብዳቤ አስገብተናል፡፡ እዚህ ላይ የተደረሰውም የስፖርት ሚዲያው ያቋቋመው ማኅበር በመዳከሙ የመጣ ጫና ነው በማለት፣ አሁን ያለው ማኅበር እንደ አዲስ ተቋቋመ፡፡ በወቅቱም ታላላቅ የሚባሉት የስፖርት ጋዜጠኞች ጭምር ተሳትፈውበት ነው አሁን ያለው አመራር የተመሠረተው፡፡ በወቅቱ የነበረውና በአሁኑ ወቅት የፈረሰው ስፖርት ኮሚሽን ለገሀር አካባቢ ለማኅበሩ አንድ ቢሮ ሰጥቶት ሥራውን ቀጥሏል፡፡ በኢንተር ኮንትኔንታል አዲስ በ2004 ዓ.ም. የተመሠረተው ማኅበራችን ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ በኃይሌ ዓለም ሕንፃ ውስጥ ቢሮ ሰጥቶን እየተጠቀምንበት እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከዓላማው አንፃር ማኅበሩ እንዴት እየሄደ ነው?

አቶ ዮናስ፡- ይኼ ማኅበር በመሠረታዊነት የተቋቋመው አራት መሠረታዊ ነገሮችን ማለትም ማኅበሩ የሙያ አባላቱን  እንደ ማንኛውም የሙያ ማኅበር ዘገባዎችን በነፃነት የመዘገብና የጋዜጠኛው መብት እንዲከበር፣ ጋዜጠኞቹ ሙያቸውን የሚያጎለብቱበት መድረኮችንና ሥልጠናዎችን ማዘጋጀት፣ የስፖርት ጋዜጠኛው ዓለም አቀፍ ልምድ የሚያገኝበትን መድረክ ማመቻቸት በመጨረሻም ጥቅሞቹን ማመቻቸት የሚለው በዋናነት ተጠቃሽ ነው፡፡ በማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ ላይም እነዚህ አንኳር ነጥቦች እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ከአንድ ኦሊምፒያድ በላይ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ምን አከናውኗል?

አቶ ዮናስ፡- ቀደም ሲል የጠቀስናቸውን የማኅበሩን ዋና ዋና መርሆዎች ለማሳካት ጥረት አድርጓል፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች በማኅበሩ አባላት ላይ በሚነሱ ችግሮች ላይ እንደ ማኅበር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመገናኘት ችግሮቹ መፍትሔ እንዲያገኙ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ ሌላው ለጋዜጠኛው ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን አዘጋጅተናል፡፡ ይሁን እንጂ በተለይም የእግር ኳስና አትሌቲክስ ዘገባዎችን በተመለከተ መድረኮች ተፈጥረው ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር  በመነጋገር በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ በእርግጥ አሁንም ይህ በቂ ነው እያልን አይደለም፡፡  ገና ብዙ የሚቀረን እንዳለ እናምናለን፡፡ ከእነዚህ ሁለት ተቋማት በተጨማሪ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና ከዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር ጭምር በመነጋገር የተለያዩ መድረኮች ተፈጥረው ሥልጠናዎች ተሰጥተዋል፡፡ ከዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ጋር ባለን ግንኙነት ጋዜጠኞቻችን በየዓመቱ ወደ ውጭ ሄደው ዓለም አቀፍ ተሞክሮ የሚያገኙበትን መድረክ በመፍጠር ሥልጠናዎች እንዲሰጡ አድርገናል፡፡ ትራንስፖርትና ሆቴል እየተቻላቸው በርካታ በአጠቃላይ ከ20 በላይ የማኅበራችን አባላት የዚህ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርገናል፡፡ ሌላው ይኼ ማኅበር በአፍሪካ ስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበር ውስጥ የሥራ አስፈጻሚነት ቦታ አለው፡፡ ይኼ እውነቱን ለመናገር የማኅበሩን ጥንካሬ የሚያሳይ ነው፡፡ እርግጥ ነው ኢትዮጵያ የአፍሪካን እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ከመሠረቱ አራት አገሮች አንዷ ብቻ ሳትሆን ከመሥራቾቹም አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያውያን በአፍሪካ መድረክ ሊኖረን የሚገባው ቦታ ቢያንስብን እንጂ  አይበዛብንም፡፡ ሌላውና ትልቁ ነገር ደግሞ አገሪቱ ትልቅ ዓለም አቀፍ ዝናና ክብር ያተረፉ አትሌቶች ያሉባት አገር ነች፡፡ ከዚህ በመነሳት ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የስፖርት ጋዜጠኞቻችን ተሳትፎ ከአቶ ፍቅሩ ኪዳኔ ውጭ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ከዚህ ባለፈ ማኅበራችን የዓለም አቀፍ ስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበር (አይ ፒኤስ) አባል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የአቶ ፍቅሩ ኪዳኔ አስተዋጽኦ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ ከመጀመርያው ማኅበሩ ለአይፒኤስ የአባልነት ክፍያንም እየከፈሉልን ነው፡፡ ሲቀጥልም ማኅበራችን ተጠናክሮ እንዲቀጥል ትልቁን ሥራ ከሠሩ ግንባር ቀደሙ ናቸው፡፡ በዚህ አጋጣሚ በማኅበሩ ስም ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ የማኅበሩ አመራርም የማኅበሩ አባላት የዓለም አቀፉን መታወቂያ እንዲያገኙ ባደረገው ጥረት ለበርካታ አባላቱ የአይፒኤስ መታወቂያ ባለቤት እንዲሆን አድርጓል፡፡ ከዚህ አመራር በፊት በነበረው ይህን መታወቂያ የያዙ አባላቱ ከአሥር አይበልጡም ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ቁጥሩ ከእ ብሏል፡፡ በዚህ ግንኙነታችን ሐቻምና የዓለም አቀፍ ስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበር ዓመታዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ተደርጓል፡፡ ይህ የማኅበራችን የግንኙነት ውጤት ነው፡፡ ለጉባኤው መሳካት ኃይሌ ገብረሥላሴና ቀነኒሳ በቀለም የነበራቸው ድርሻ ቀላል አልነበረም፡፡ ማኅበራችን ዓለማቀፍ ማኅበሩ በሚያደርገው ጉባኤ ሲገኝ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድጋፍ አልተለየውም፡፡

ማኅበራችን አሁንም ሙሉ በሙሉ ተሳክቶልናል ማለት እንዳልሆነ መወሰድ አለበት፡፡ በርካታ ተግዳሮቶች አሉት፡፡ ከተግዳሮቶቹ መካከል የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አማተር እንደመሆኑ ሙሉ ጊዜ ስለማይሰጥ የሥራ መጓተቶች ይገጥሙናል፡፡ በዚህም የማኅበሩ ሥራዎች በተገቢው ጊዜ አይከናወኑም፡፡ በአጋጣሚ ሥራ አመራሩ የሚግባባና የሚደማመጥ ስብስብ በመሆኑ ያን ያህል የሥራ መዝረክረክ አልገጠመንም፡፡ እንደዛም ሆኖ ሥራ አመራሩ በሥራና በተለያዩ ምክንያቶች ቁጥሩ መመናመኑ ጉዳት ነበረው፡፡

ሪፖርተር፡- ክፍተቱን ለመድፈን ምን እያደረጋችሁ ነው?

አቶ ዮናስ፡- ይኼ ማኅበር ትልቅ ሆነ ማለት ለጋዜጠኛው ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱ ስፖርት የሚኖረው ሚና ትልቅ ይሆናል፡፡ በተለይም ለወደፊቱ መደረግ አለበት ብለን የምናምነው፡፡ ለዚያ ደግሞ አጋሮቻችን በቋሚነት ከማኅበሩ ጋር አብረው የሚዘልቁበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት ብለን እናምናለን፡፡ ለዚህም ሲባል ብዙ ተጉዘናል፡፡ ሙሉ በሙሉም ባይሆን አሁን አሁን ምልክቶችን እያስተዋልን ነው እናሳካዋለንም፡፡ ምክንያቱም ያንን ማሳካት ከቻልን የስፖርት ጋዜጠኞቻችን አቅማቸው ይዳብራል፡፡ ብቃታቸው የተሻለ ከመሆኑም ባሻገር በነፃነት የሚዘግቡ ይሆናሉ የሚል እምነት ስላለን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስብጥራችሁስ?

አቶ ዮናስ፡- ከዚህ በፊት ስብጥሩን በሚመለከት ቅሬታዎች ነበሩ፡፡ አሁንም ችግሩ ሙሉ በሙሉ ተወግዷል ብለን አናምንም፡፡ ከዚህም አልፎ ሚዲያው ኅትመትና ብሮድካስት እንደመሆኑ ይህን አጣጥሞ ማስኬድ ከባድ ነበር፡፡ በዚህም የተወሰኑ ልዩነቶች ነበሩ፡፡ ሆኖም በኛ እነዚህን ልዩነቶች ለማጥበብ እየጣርን ነው፡፡ ምሳሌ አድርግን የሥራ አስፈጻሚውን ስብጥር ብንመለከት ከሁሉም የሚዲያ ዘርፍ አድርገን ነው ለማዋቀር የሞክርነው፡፡ አሁን አሁን ከኦን ላይን (ድረ ገጽ) ሚዲያ ጭምር እያካተትን ነው፡፡ ይኼ ቀደም ሲል የነበረውን ክፍተት በተወሰነም ቢሆን እያቃለለልን  ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡ ማኅበሩ የሚለው ከአዲስ አበባ ውጭ አባላት አሏችሁ?

አቶ ዮናስ፡- ከአዲስ አበባ ውጭ የሚገኙ የስፖርት ጋዜጠኞችም የማኅበሩ አባል ናቸው፡፡ እርግጥ ነው ሁሉም አይደሉም፡፡ በቅርቡ ባካሄድነው ዓመታዊ ጉባኤ ይኼው እንደ ክፍተት ተነስቶ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ከሚገኙት ዕድሎችም ተጠቃሚ የሚሆኑበት አግባብ እንዲኖር መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ እንደ አጠቃላይ ግን ክፍተት ተደርጎ ታይቷል፡፡ አመራሩም በዚህ ረገድ መሻሻል ያለባቸው አሠራሮች እንዳሉ ያምናል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የኦሮሚያ፣ የአማራ፣ የትግራይ፣ የደቡብና የድሬዳዋ አስተዳደር የስፖርት ጋዜጠኞች የማኅበሩ አባል ለመሆን ጥያቄ እያቀረቡ ነው፡፡ ማኅበሩም ራሱን የቻለ ለዚህ ብቻ አገልግሎት የሚውል አካል አዘጋጅቷል፡፡ ችግሩም በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ይቀረፋል ብለን እናምናለን፡፡ ይህ ማለት ከክለብ አፈ ቀላጤዎች (ሕዝብ ግንኙነት) በስተቀር ከስፖርት ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው የፎቶ ጋዜጠኞች ጭምር የማኅበሩ አባል የመሆን መብት አላቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የስፖርት ጋዜጠኝነት በዕውቀት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ምን እያደረጋችሁ ነው?

አቶ ዮናስ፡- ማኅበሩ የሙያ ማኅበር እንደመሆኑ ጋዜጠኞች የሙያውን ሥነ ምግባር የጠበቁ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ያምናል፡፡ ከዚህ ውጭ ደረጃ የማውጣት ሥራ ውስጥ ሊገባ አይችልም፡፡ ነገር ግን ማኅበሩ በየዓመቱ በምንፈጥራቸው የተለያዩ መድረኮች በተለይም ስፖርት ሚዲያው ላይ ያተኮሩ ሥልጠናዎች እንዲሰጡ እናመቻቻለን፡፡ ከመረጃና ዘገባ ጋር የተያያዙ ክፍተቶችን ለመቅረፍ ጥረት እናደርጋለን፡፡ ከዚህም በላይ አንድ የስፖርት ጋዜጠኛ በአመዘጋገብ ዙሪያ ሊኖረው የሚገባው ሥነ ምግባር ምን ሊሆን እንደሚገባ በመመሪያ መልክ ለማዘጋጀት ዕቅድ አለን፡፡ ሥልጠናም እንሰጣለን፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለይም የኅትመት ሚዲያው አደጋ ውስጥ በመሆኑ ያንንም ታሳቢ ያደረገ ሥልጠና ጭምር ለመስጠት ዕቅድ አለን፡፡ በአጠቃላይ የስፖርት ጋዜጠኛው ሁሉን አቀፍ የሆነ ዕውቀት ይኖረው ዘንድ ማኅበሩ አቅም በፈቀደ መጠን መድረኮችን ማመቻቸት እንዳለበት ያምናል ይሠራልም፡፡ በአጠቃላይ ግን ከመረጃና ዶክሜንቴሽን (ስነዳ) ጋር በተያያዘ ማኅበሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር  አብሮ መሥራት ይጠይቃል፡፡ ማኅበሩ እንደ አንድ ባለድርሻ ጥረት ማድረጉን ይቀጥላል፡፡ ሌላው ይህ ማኅበር ከሌሎች አቻ ማኅበራት አንፃር ሲታይ በጣም እንጭጭ ነው፡፡ የጎረቤት አገር ኬንያን ብንመለከት ልዩነታችን የሰማይና የመሬት ያህል ነው፡፡ እኛ በጣም ኋላ ነን፡፡ አባሎቻችን የአባልነት  ክፍያ በአግባቡ ለመክፈል እንኳ ፈቃደኞች አይደለንም፡፡ ማኅበሩ የቀን ተቀን ሥራውን እያንቀሳቀሰ ያለው ከስፖንሰሮች በሚያገኛት አነስተኛ የፋይናንስ ምንጭ ነው፡፡ ወደፊት በጣም ብዙ ሥራዎች ይጠብቁናል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ ለአንጋፋ የስፖርት ጋዜጠኛ እውቅናና ሽልማት ሰጥታችኋል፤ ቀጣይ ነው?

አቶ ዮናስ፡- ጋዜጠኞቻችን ባገለገሉት መጠን ተገቢው ዕውቅና እንዲያገኙ ማኅበሩ ያልተቆጠበ ጥረት ያደርጋል፡፡ በቅርቡም በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ለረዥም ዓመታት ላገለገለው ሰለሞን ገብረእግዚአብሔር ዕውቅና የሰጠው አገልግሎቱን ብቻ ተመልክቶ አይደለም፡፡ ለሙያው ያለው ዲሲፕሊን ጭምር ታይቷል፡፡ ከዚያም ባለፈ ጋዜጠኛው ለሁሉም ስፖርቶች የሚሰጠው ትኩረት እኩል ነው፡፡ አርአያም ጭምር እንደሚሆን ስለታመነበት ነው የሸለምነው፡፡ ጅምር ስለሆነ ቀጣይነት እንዲኖረው እንፈልጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኝነት ታሪክ በመሰነድ በኩል የሚታሰብ ነገር አለ?

አቶ ዮናስ፡- ማኅበሩ በቀጣይ አጠናክሮ ከሚሠራባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ለዚህ የሚጠቅሙ አንጋፋ የስፖርት ጋዜጠኞች ስላሉን ሙያው ከየት ተነስቶ የት ላይ ይገኛል? የሚለውን በትክክል ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ይቻል ዘንድ ለማዘጋጀት  ዕቅድ አለን፡፡ በሕይወት የሌሉት ሰለሞን ተሰማ፣ ደምሴ ዳምጤ፣ ጎርፍነህ ይመር፣  ሌሎችንም በሕይወት ካሉት ደግሞ እንደነ ፍቅሩ ኪዳኔ፣ ይንበርበሩ ምትኬ የመሳሰሉት የስፖርት ጋዜጠኝነት ታሪክ ማዘጋጀት የማኅበሩ ኃላፊነት ነው ብለን እናምናለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...