Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህል‹‹በየድንኳኑ ከበሮ ጠራኝ እባል ነበር››

‹‹በየድንኳኑ ከበሮ ጠራኝ እባል ነበር››

ቀን:

ተወዛዋዥ እንዬ ታከለ

‹‹የሕዝብ ለሕዝቧ ፈርጥ›› እየተባለች የምትጠራው ተወዛዋዧ እንዬ ታከለ ተወልዳ ያደገችው ደንቢያ ወረዳ ቆላ ድባ ከተማ ነው፡፡ ከልጅነቷ ጀምሮ ለእስክስታ ልዩ ፍቅር ያላት እንዬ በ1975 ዓ.ም. ፋሲለደስ ኪነትን ተቀላቅላ መሥራት ከመጀመሯ በፊት በትውልድ ቀዬዋ የቀበሌ ኪነት ትሠራ ነበር፡፡ ወደ ጎንደር አቅንታ በፋሲለደስ ኪነት  በየአውራጃው ተዘዋውራ ውዝዋዜ ታሳይም ነበር፡፡ ከብዙዎች ህሊና የማይጠፋው ግን በ1979 ዓ.ም. ሕዝብ ለሕዝብን ተቀላቅላ ያሳየችው የውዝዋዜ ብቃት ነው፡፡ መድረክ ላይ ስትወጣ በውዝዋዜ ተመልካችን የምታስደምመው እንዬ፣ የቡድኑ ፈርጥ ነበረች፡፡ በተለይ እንደ አደይ አበባ ሆና ስትጫወት የበርካቶችን ቀልብ ትስብ ነበር፡፡ በሕዝብ ለሕዝብ ብዙ አገሮችን ከተዘዋወረች በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመልሳ ለጥቂት ጊዜ ሠርታለች፡፡ ሆኖም ቡድኑ በመበታተኑ ቀድሞ አብረዋት ይሠሩ ከነበሩ የሙያ አጋሮቿ ጋር ሌላ ቡድን ለማቋቋም ተገደዱ፡፡ ትርዒት ለማሳየት ከአገር ከወጡ በኋላ አብዛኞቹ ስለተበታተኑ ወደ 20 ዓመታት ገደማ ከአገሯ ወጥታ ኖራለች፡፡ በአሜሪካ ዴንቨር ቆይታዋ የኢትዮጵያ ባህላዊ ሬስቶራንት ከፍታ ነበር፡፡ ለጥቂት ጊዜ በሬስቶራንቱ ውዝዋዜ ስታቀርብም ነበር፡፡ ሆኖም ረዘም ላለ ጊዜ ከሙያውና ከሕዝብ ዕይታም ርቃ ነበር፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመጣች ሲሆን፣ በቅርቡ ለከተሞች ፎረም ጎንደር ከተማ ተገኝታ ነበር፡፡ ስለ ሙያዊ ተሞክሮዋና ሕይወቷን በተመለከተ እንዬ ታከለን ምሕረተሥላሴ መኰንን አነጋግራታለች፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙዎች አንቺን ሲያስቡ መጀመሪያ ሕዝብ ለሕዝብን በግንባር ቀደምነት ያስታውሳሉ፡፡ ሕዝብ ለሕዝብን ከመቀላቀልሽ አስቀድሞ የነበረውን ወቅትና በቡድኑ ውዝዋዜ ከጀመርሽ በኋላ የነበረውን እንዴት ትገልጭዋለሽ?

- Advertisement -

እንዬ፡- ሕዝብ ለሕዝብን የተቀላቀልኩት ከጎንደር የባህል ቡድን ተመርጠን ወደ አዲስ አበባ በሄድንበት ወቅት ነበር፡፡ ከጎንደር ፋሲለደስ የባህል ቡድን ወደ 15 የምንሆን ልጆች ኮሪያ ለጉብኝት ትሄዳላችሁ ተብለን ተመረጥንና አዲስ አበባ ከብዙ አርቲስቶች ጋር ቴአትር ቤት ተቀላቀልን፡፡ እኛ የአማራ ክልል ውዝዋዜ እንጂ የሌላ ክልል አናውቅም ነበርና የልምድ ልውውጥ አደረግን፡፡ ከኛ ቱባውን የአማራ ክልል እስክታ ልምድ ሲቀስሙ እኛ የሌሎች ብሔረሰቦችን ተማርን፡፡ በዚህ መሀል የኮሪያው ጉዞ ተሰረዘ፡፡ ሲሰረዝ ለሞራላችን ተብሎ በየቴአትር ቤቱ እንድናሳይ ባህል ሚኒስቴር ፈቀደልን፡፡ ብሔራዊ ቴአትር፣ አገር ፍቅር፣ ራስ ቴአትርና ማዘጋጃ ቤት እየዞርን ማሳየት ጀመርን፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ እስክስታ ብዙም አይታም ነበር፡፡ የጎንደር የአንገት እስክስታ፣ የወሎ ጭፈራ፣ የጎጃም እንቅጥቅጥ በብዛት መታየት የጀመረው እኛ ከገባን በኋላ ነው፡፡ በየቴአትር ቤቱ ይህን ስናሳይ ሕዝቡ ወደደው፡፡ ተቀባይነትም አገኘን፡፡ ከዚያ የሕዝብ ለሕዝብ ቡድንን የማቋቋም ዕድል ተፈጠረ፡፡ በየቴአትር ቤቱ እንዞር ስለነበርና ሕዝቡም ስላወቀን ሦስት ሰዎች ታጨን፡፡ በዚያን ወቅት ከምንም በላይ ትልቅ ፍቅር ነበረን፡፡ ገንዘቡም ሌላውም ተትቶ ለሙያው ፍቅርና ክብር ነበረን፡፡ አንድ ዓመት ጉባዔ አዳራሽ ውስጥ ሠልጥነን ትልቅ ሥራ ሠራን፡፡ ያ ወቅት ልዩ ትዝታ አለው፡፡

ሪፖርተር፡- ልዩ ትዝታ ጥሎብሽ ያለፈ የጉዞው አካል የቱ ነው?

እንዬ፡- የአትላንታን ትዝታ አልረሳውም፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያኖች አትላንታ ነበሩ፡፡ ልዩ አቀባበል ነበር ያደረጉልን፡፡ የተለየ ደስታና ፍቅር ያየሁበት ነበር፡፡ ሁሉም ቦታ ስንሄድ ብዙ ኢትዮጵያውያን ስላገኘን ጥሩ ጊዜ አሳልፈናል፡፡ ድሮ የሠራነውን እየተመለከቱ እሳት የሆኑ ልጆች ተፈጥረው ማየት ያስደስታል፡፡ እኛ እንኳን ብናረጅም ወጣት ተክተናል፡፡ በኛ ዘመን ቴሌቪዥን ብዙም ባልነበረበት ወቅት አንድ ሰው ቤት ተሰባስቦ ነበር የሚታየው፡፡ እስካሁን የማይረሳ ትዝታ የሰጠኝ ያም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በሕዝብ ለሕዝብ ወቅት አደይ አበባን ስትጫወቺ ይታወሳል፡፡ በዓመት አንዴ የምትመጣ አደይ አበባን ወክሎና የትርዒቱ ማዕከል ሆኖ መጫወት ምን ይመስል ነበር?

እንዬ፡- አደይ አበባ የማይረሳ ትዝታ ጥሎብኝ አልፏል፡፡ የምሠራው የኢትዮጵያ ልጅ ሆኜ ነበር፡፡ ከሁለት ወንዶች አንዱ ጉልበተኛ አንዱ ፀባይኛ ሆነው አደይ አበባን ለመውሰድ ይፎካከራሉ፡፡ ትርዒቱ በምንጃር ወንዶቹ ሲፎካከሩ በቆቱ አደይ አበባዋ ጠፍታ ስትፈለግ የሚያሳይ ውዝዋዜና ድራማ ነው፡፡ እናቴ ኢትዮጵያ ከሁለቱ ምረጪ ስትል ፀባይኛዋን እመርጣለሁ፡፡ ሳራ ተክሌ ኢትዮጵያ ሆና ትጫወት ነበር፡፡ አልማዝ ጥላሁንና አበበ በለውም ይጠቀሳሉ፡፡ አበበ ብርሃኔና ኃይልዬ ታደሰ ከተወዛዋዦቹ መሀል ነበሩ፡፡ በወቅቱ ከነበሩት እነ የሻነው የሺዋስ፣ ንዋይ ደበበ፣ አረጋኸኝ ወራሽን እዚህ ስመጣ አግኝቻቸዋለሁ፡፡ ጋሽ መሐሙድ ዶክትሬቱን ሊወስድ ጎንደር መጥቶ ተገናኝተናል፡፡ ያን ዘመን አልፎ ደግሞ መገናኘት ልዩ ደስታ ይሰጣል፡፡

ሪፖርተር፡- ጥላሁን ገሠሠን ጨምሮ ከበርካታ አንጋፋ ባለሙያዎች ጋር መድረክ መጋራት ምን ዓይነት ስሜት ይሰጥሽ ነበር?

እንዬ፡- ጎንደር እያለሁ እንኳን ከታላላቅ አርቲስቶች ጋር አብሬ ልሠራ በዓይኔ አያቸዋለሁ ብዬም አላስብም ነበር፡፡ እግዚአብሔር ብሎ በቴሌቪዥን ከማያቸው ከነ ጋሽ ጥላሁንና ጋሽ መሐሙድ ጋር መድረክ አግኝቼ መሥራቴ ትልቅ ማዕረግ ነው፡፡ አብረን ስንሠራ ፍቅራችን ሌላ ነበር፡፡ ስንገናኝ ሳቅና ጨዋታ ነው፡፡ ጋሽ ጥላሁን ከኛ ጋር ዝቅ ብሎ ይጫወት ነበር፡፡ ከነሱ ጋር አብሮ መሥራት እውነት እውነት አይመስለኝም ነበር፡፡ የምናከብራቸውና የምንወዳቸው ንጉሦቻችን ናቸውና መታደል ነው፡፡ ከጊዜ ብዛት ስሞቹን ረሳኋቸው እንጂ ብዙ ቅጽል ስሞች ስንሰጥ ትዝ ይለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ሕዝብ ለሕዝብ በአገሪቱ ኪነ ጥበብና አገሪቱን ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ የነበረውን ሚና እንዴት ትገልጽዋለሽ?

እንዬ፡- ሕዝብ ለሕዝብ ትልቅ ታሪክ ሠርቷል፡፡ የኢትዮጵያ ስም ሲጠራ የት ነው?  ለሚሉ አገሮች አስተዋውቋል፡፡ ባህሉን፣ አጨፋፈሩንና አለባበሱን ዓለምን ዞሮ አስተዋውቋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ቡድን አሁንም ቢፈጠር ደስ ይለኛል፡፡ ታላላቅ ድምፃውያንና ተወዛዋዦች በማውጣት የሠራው ሥራ ቀላል አይደለም፡፡ እንደተሠራው ሥራ ለሕዝብ ለሕዝብ ቡድን የሚገባው አልተደረገለትም፡፡ ይሆናል ተብሎ ከተጠበቀው በታች ነው፡፡ ሆኖም ሕዝቡ በአዕምሮ ውስጥ ቀርቶ እስካሁን ባለመረሳታችን እንጽናናለን፡፡ ያንን ከመሰለ ቡድን ብዙ ነገር መቅሰም ሲቻል በቀላሉ ተበታትኖ ቀርቷል፡፡

ሪፖርተር፡- የፋሲለደስ ኪነት የጎንደር መለያ መሆን የቻለና በርካታ ባለሙያዎችን በማፍራት ዕውቅናን ያተረፈ ቡድን ነው፡፡ ፋሲለደስ ገናና በነበረበት ወቅት ቡድኑን የመቀላቀል ዕድል እንዴት አገኘሽ? በወጣትነትሽ ከታዋቂ ባለሙያዎች ጋር መሥራትስ ምን ይመስል ነበር?

እንዬ፡- ጎንደር የራሱ የኪነት ቡድን ነበረው፡፡ አስተዳደሩ አዲስ ቡድን እንዲቋቋም ሲያዝ በየወረዳውና በየአውራጃው የሚመለምሉ ነበሩ፡፡ ነፍሱን ይማረውና እንደ አባታችን የምናየው ይርጋ ዱባለና ወርቁ ይማም እየዞሩ መመልመል ጀመሩ፡፡ ከጎንደር ወጣ ብሎ ቆላ ድባ ከሚባለው ቦታ ሁለት ሰዎች ተመረጥንና በምንፈልጋችሁ ጊዜ ትመጣላችሁ አሉን፡፡ ጎንደር ቀበሌ 17 ካምፕ ውስጥ እንድንቀላቀል ሲነገረን ግን እናቴ አዝማሪ ልታሰኚኝ ነው ብላ አትሄጂም አለችኝ፡፡ ቃሏን ለመጠበቅ አልሄድኩም፡፡ በየአውራጃው የተሰባሰበው ቡድን ግን ወደ ሁለት ወር ሠርቶ ነበር፡፡ በአጋጣሚ ወርቁ ይማም ወደ ተመረጥኩበት ቆላ ድባ መጣ፡፡ እናቴ በድጋሚ እንቢ ብትልም ወረዳ አስተዳደር የምትሠራ ሴት ዕድሏን አያበላሹ ብላ ተቆጣቻትና እግዚአብሔርም ብሎልኝ ወደ ጎንደር እንድሄድ ፈቀደች፡፡ በወቅቱ በአሥራዎቹ መጨረሻ ዕድሜ ክልል ነበርኩ፡፡ ፋሲለደስን ስቀላቀል ልጅነትና ዓይን አፋርነትም ነበር፡፡ በጎንደር ፋሲለደስ እንደ እህትና ወንድም አብረን ነው ያደግነው፡፡ እንደ ቀለመወርቅ ደበበና ገዛኸኝ ወርቁ ያሉ ጥሩ አሠልጣኞች ነበሩን፡፡

ሪፖርተር፡- ጎንደር ፋሲለደስ፣ ወሎ ላሊበላና ሌሎችም የኪነት ቡድኖች ከፍተኛ ጥበባዊ ንቅናቄ መፍጠር የቻሉ ናቸው፡፡ ከነበራቸው አስተዋጽኦ አንፃር መፈራረሳቸው በኪነ ጥበቡና በባለሙያዎቹ ምን ተፅዕኖ አሳደረ?

እንዬ፡- እኔ አዲስ አበባ የመጣሁት ቡድኑ ሳይፈርስ በፊት ነበር፡፡ የተበታተነው ለውጡ ሲመጣ ነበር፡፡ የተወሰንን ሰዎች ወጥተን አዲስ አበባ እየሠራን ነበርን፡፡ የተደነቀ ቡድን ስለነበር ብዙ ሰው የት ደረሰ? ብሎ ይጠይቅ ነበር፡፡ የምሽት ክበብ ተሰባስብን በምንሠራበት ወቅት የባህል ቡድን ሁኔታ ያሳሰበው ባለቤቴ አሰባሰብን፡፡ ብዙዎች የኪነቱ አባላት ወደ ውጪ አገር ሄደውም ነበር፡፡ ያ ቡድን ተንገላቷል፡፡ የት አላችሁ? የት ወደቃችሁ? ያለን አልነበረም፡፡ የተወሰነው አሁን ጥሩ ኑሮ እየኖረ ነው፡፡ ፋሲለደስ ቱር ማድረግ ጀምሮ ነበር፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ችግሮች ስለነበሩ ለመቀጠል አልቻልንም፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ልጅነት ዘመንሽ ተመልሼ ወደ ውዝዋዜ ስለገባሽበት ሁኔታ ብትነግሪን?

እንዬ፡- ውዝዋዜ ተሰጥኦ ነው፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ ጭፈራ እወዳለሁ፡፡ የተወለድኩባት ትንሽ ከተማ ላይ ክርስትናና ሠርግ ሲኖር ከበሮ ሲመታ ሙዚቃውን መከተል እንጂ የማን ክርስትና? የማን ሠርግ ነው? ብዬ አልጠይቅም፡፡ በፍላጎቴና በልምድ እስክስታ ስለምችል እንዬ መጥታለች ልቀቁላት እባል ነበር፡፡ ጨፍሬ ከጨረስኩ በኋላ የማን ሠርግ ነው? ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ በየድንኳኑ ከበሮ ጠራኝ እባል ነበር፡፡ በዚህ መንገድ መጀመሪያ ወደ ቀበሌ ኪነት ከዚያም ወደ ፋሲለደስ ኪነት ገባሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ተወዛዋዥ መሆን መፈለግሽን ቤተሰቦችሽ አልደገፉትም ነበር፡፡ በወቅቱ ለኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የሚሰጠውን አነስተኛ ግምት እንዴት ተቋቋምሽው?

እንዬ፡- እንደጀመርኩ አዝማሪ አስብለሽ ልታሰድቢን ነው ተብዬ ተከልክዬ ነበር፡፡ ኪነት ውስጥ የገባሁት ካልገባችሁ ትታሠራላችሁ ተብለናል ብዬ ዋሽቼ ነው፡፡ ከቆላ ድባ ኪነቱን ለመቀላቀል ስመረጥ ቤተሰብ ስለማይፈቅድልኝ ጓደኞቼንና የሚመርጡትን ሰዎች ትታሰራለች በሉልኝ አልኩ፡፡ የደርግ ጊዜ ከባድ ስለነበረ ትታሰራለች ከተባለ ይፈራል፡፡ ግዳጇ ስለሆነ ልጅቷ ወደ ሙያው መግባት አለባት ብለው ጠይቀውልኝ ተቀላቀልኩ፡፡ ያኔ ዶክተር መሆን ወይም ሌላ ሙያ እንጂ ኪነ ጥበብ አይደገፍም ነበር፡፡ እኔ ከጎንደር እስክስታ በበለጠ አገውኛ ጥሩ እጫወት ነበር፡፡ የጎንደር ውዝዋዜን ስክስክ ወይም የአንገት እስክስታው የተለየ ያደርገዋል፡፡ ሰውም ይወደዋል፡፡ የሚጫወተውም ሰው በደስታ ይጨፍራል፡፡

ሪፖርተር፡- መድረክ ላይ ስትወጪ ከውዝዋዜው በተጨማሪ የፊት አገላለጽሽ በተለይም የከንፈርሽ እንቅስቃሴ የተለየ ነው፡፡ ከስሜት የመነጨ ነው?

እንዬ፡- መድረክ ላይ ስወጣ ሳላውቀው እቀየራለሁ፡፡ ከመውጣቴ በፊት እረበሻለሁ እፈራለሁ ስገባ ግን ስሜት ውስጥ እገባለሁ፡፡ ብዙዎች አፍሽን ትከፍቻለሽ ይሉኛል፡፡ እኔ ግን አይታወቀኝም፡፡ ከልቤ ስለሆነ መቆጣጠር አልችልም፡፡ መድረክ ላይ ሌላ እንዬ እሆናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- መድረክ ላይ ስትወዛወዥ ተመልካቾች አድናቆታቸውን የሚገልጹባቸው መንዶች ምን ዓይነት ስሜት ይሰጡሻል?

እንዬ፡- ሰው ስለሚወደኝ አድናቆቱን ለመግለጽ ሲመጣ እንደአመጣጡ እመልሳለሁ፡፡ ብር የሚሸልም አለ፡፡ ማቀፍና መሳምን ለምጄዋለሁ፡፡ ከፍቅራቸው ብዛት ሲያቅፉኝ አንዳንዴ አቋርጨም አቅፋቸዋለሁ፡፡ ከመድረክ ውጭ የተለያየ ስጦታ የሚሰጡኝም አሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ውጪ ስጨፍር የሚያዩ ፈረንጆች ትከሻሽን ምን እያደረግሽው ነው? ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ቢራቢሮ የሚል ቅጽል ስም የተሰጠኝም ጊዜ ነበር፡፡ ትልቁ ሀብቴ የሰው ፍቅር ነው፡፡ ከማንም በልጬ ሳይሆን የፈጣሪ ስጦታ ነው፡፡ በድሮ ጊዜ ክፍያችን 120 ቢበዛ 180 ብር ነው፡፡ ለኛ ግን በወቅቱ ብዙ ነው፡፡ በዚያች ብር ጥሩ ለብሰንና አጊጠን እንታያለን፡፡ የክፍያ ነገር የድሮውና የአሁኑ አይመጣጠንም፡፡

ሪፖርተር፡- የጎንደር ፋሲለደስ የባልህ ቡድን ዳግም በወጣቶች ተቋቁሟል፡፡ ሌሎችም አዳዲስ የባህል ቡድኖች እየተመሠረቱ ይገኛሉ፡፡ በባህላዊ ውዝዋዜ ረገድ የወጣቶችን እንቅስቃሴ እንዴት ታይዋለሽ?

እንዬ፡- እኛን ዓይተው የተፈጠሩ ብዙ ልጆች አሉ፡፡ አንዳንድ ቦታ የማያቸው ልጆች ያስደስቱኛል፡፡ ያኮሩኛል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ለሙያው ደንታ የላቸውም፡፡ እኛ መድረክን እንደ ቤተክርስቲያን ነው የምናየው፡፡ እናከብረዋለን፡፡ የድሮ አርቲስት ለገንዘብ ሳይሆን ለሙያው ነበር የሚሠራው፡፡ አሁን ውዝዋዜውን ሲሠሩ ከዘመናዊ ጋር ይቀላቅሉታል፡፡ የሙዚቃ ምቱ ይፈጥናል፡፡ የጎጃም፣ የወሎና ሌሎችም ውዝዋዜዎች ይቀላቀላሉ፡፡ ባይደባለቅ ደስ ይላል፡፡ በአለባበሱና በፀጉር አሠራሩ የሚያኮራውን ቱባ ባህል ይዞ መሄድ ይገባል፡፡ ባህላዊና ዘመናዊ፣ የየብሔረሰቡም ጨዋታ መለያየት አለበት፡፡ ልጆች ስለሆኑም ሊሆን ይችላል መድረክ ላይ ሌላ ጨዋታ ይጀምራሉ፡፡ እኛ ጋ መድረክ ላይ ከወጡ በኋላ መሳቅና ማሾፍ ፈጽሞ አይታሰብም፡፡ ውዝዋዜውን ትተው የሚያወሩም ገጥመውኛል፡፡ ሙያውን የሚያውቅና ክብር የሚሰጥ ሰው ከጎናቸው ያስፈልጋቸዋል፡፡ አለንላችሁ ማለት ራሱ ለአርቲስት ሞራል ይሰጣል፡፡ ድጋፍ የሚሰጣቸው ቢኖር ለሙያው ዕድገት ይረዳል፡፡ ልጆቹን መጠቀሚያ አድርጎ ትቶ መጥፋት ሳይሆን እስከመጨረሻው የማይለይ ሰው ያስፈልጋቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ወጣቶች ራሳቸውን በተቀረው የዓለም ክፍል ለማስተዋወቅ ባህላዊውን ከዘመናዊ ጋር የመደባለቅ አካሄድ እየተከተሉ ነው፡፡ ስለዚህ ምን አስተያየት አለሽ?

እንዬ፡- ይህ አካሄድ ትክልል አይደለም፡፡ የኛው ባህል ክራር፣ ማሲንቆና ዋሽንት ልዩ ቅርሶቻችን ናቸው፡፡ በራሳችን የባህል መሣሪያና በራሳችን አለባበስ መሠራት አለበት፡፡ ባህላዊና ዘመናዊ ሲቀላቀል ሁሉም እንደ ዳንስ ይሆናል፡፡ አዲስ የመጣው ትውልድ ባህሉን እየረሳ ይሄዳል፡፡ ባህላዊውን የሚሠራ እዳልሠለጠነ የሚታይበትም ጊዜ አለ፡፡  ቱባ ባህል እየወደቀ እንዳይሄድ ሰው ያስፈልጋል፡፡ ከልጆቹ ጎን አስቲስቶችና ባህልና ቱሪዝም መለየት የለባቸውም፡፡ ለምሳሌ ባላገሩ አይዶል ላይ ያየናቸው ልጆች ጎበዝ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የሚባሉ ቡድኖችም ጎበዝ ናቸው፡፡ በውድድሩ ለዳኝነት ጋብዘውኝ ስከታተል የተወዛዋዦቹ ፀጉር ፍሪዝ ነበር፡፡ ጥሩ እየሠራችሁ ቢሆንም አለባበሳችሁና ፀጉር አበጣጠራችሁን አስተካክሉ አልኳቸው፡፡ በሁለተኛው ግምገማ ሲመጡ ፀጉራቸውን አስተካክለው ነበር፡፡ እንደዚህ የሚነገራቸውን የሚሰሙ አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ከኢትዮጵያ ከወጣሽ ረዥም ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በአሜሪካ የነበረሽ ሕይወት ምን ይመስል ነበር?

እንዬ፡- ከኢትዮጵያ ውጭ መኖር ይከብዳል፡፡ ሙያችንን ለማሳየት ቡድኑን ይዘን ወጥተን መጥፎ ጊዜ ስለነበረ መመለስ አልተቻለም፡፡ ሌላው ሰው የሚሠራውን እየሠራን ኑሯችንን ጀመርን፡፡ እኔ ሕዝቤን ስለምወድና ባለቤቴም ባህልን ስለሚያከብር በምኖርበት አገር የባህል ምግብ ቤት ከፈትኩ፡፡ ውጪ ሆኜ ከሕዝቤ ጋር እንዳልርቅ በማሰብ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ምግብ፣ አለባበስና ጭፈራ በማስተዋወቅ ብዙ ሠርተናል፡፡ በአንዳንድ ምክንያቶች ሬስቶራንቱን ከአሥር ዓመት በፊት ተውኩት፡፡ እዛ የሚለፋውና የሚደከመው በአገር ላይ ቢሆን የበለጠ ጥሩ ይሆናል፡፡ አሁን ሙያውን ትቼ ልጆቼን እያሳደኩ ነው፡፡ ብዙ ቆይቼ ስመጣ የሕዝቡ ፍቅር ልዩ ነበር፡፡ በቴሌቪዥን የሚያየኝ ሕዝብ ለኔ ያለው አክብሮትና ፍቅር ደስ ይላል፡፡ ተሰድጄ ከኖርኩበት አገር ወደ አገሬ መጥቼ ከናፈቅኩት ሕዝብ ጋር መገናኘት ያስደስታል፡፡ እዚህ አንዳንድ ነገሮች ለመሥራት ብፈልግም እንዳሰብኩት አልሆነም፡፡ ጤና ካለ ለወደፊትም ያሰብኳቸው ነገሮች አሉ፡፡ ከ20 ዓመታት ቆይታ በኋላ አሁን ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት ለሦስተኛ ጊዜ ነው፡፡ መጀመርያ ስመጣ ያልጠበኩትና ለኔ የማይገባ አቀባበል ነበር፡፡ ጌታነህ ፀሐዬና ሌሎችም አርቲስቶች አየር መንገድ ድረስ መጥተው በልዩ ሁኔታ ተቀብለውኛል፡፡ ልቤን አሸፍቶ ወደ አገሬ እንድመለስ ያደረገኝም ይህ ፍቅር ነው፡፡ አሁን ወደ አገሬ እየተመላለስኩ ነው፡፡ ሐሳቤ ወደ አገሬ መምጣት ነው፡፡ ነገር ግን አሜሪካ ልጄ አለች፡፡ ከተስተካከለ እሷን አምጥቼ እዚህ መኖር እፈልጋለሁ፡፡  

ሪፖርተር፡- ከአገር ወጥተሽ በኖርሽባቸው ዓመታት ከአገሬ ጋር የሚያስተሳስረኝ የምትይው ምን ነበር?

እንዬ፡- ከባለቤቴ ጋር ተነጋግሬ ሬስቶራንት የከፈትኩት ከሕዝብ ጋር እንድገናኝ ነበር፡፡ ቢያንስ የአገሬን ሰዎች አያለሁ፡፡ የሕይወት ጉዳይ ነው እንጂ እዚያ ያለው አርቲስት አገሩን ይወዳል፤ ይናፍቃልም፡፡  እንደኔ ከናፈቀው ሕዝብ ጋር ቢገናኝና ፍቅሩን ቢገልጽ ምኞቴ ነው፡፡ ብዙ አርቲስቶች የሚኖሩት ዋሽንግተን ዲሲ ነው፡፡ እኔ የምኖረው ዴንቨር ኮሎራዶ ነው፡፡ ከአያሌው መስፍን ውጪ ማንም አልነበረም፡፡ ሬስቶራንቱ በነበረበት ወቅት አልፎ አልፎ እጫወት ነበር፡፡ ኢትዮጵያን የማያውቁ ሁሉ ይመጡ ነበር፡፡ እንጀራ እንዴት እንደሚበላና ስለ ጠጅና ጠላው ስንነግራቸው ይደሰታሉ፡፡ እኔ ከሙያው ስለራቅኩና ሌላ ስቴት ስለምኖር ከብዙ አርቲስቶች ጋር አልገናኝም፡፡ ሌሎቹ ግን ሾው ወይም ፌስቲቫል ሲኖር ይገናኛሉ፡፡ ሥራቸውን እየሠሩም ባህላቸውን ያስተዋውቃሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በሕይወትሽ ትልቅ ቦታ የምትሰጪው ወቅት የቱ ነው?

እንዬ፡- ሕዝብ ለሕዝብ መቼም የማልረሳው ብዙ ነገር ያሳለፍኩበት ወቅት ነው፡፡ ለዚህ ብዬ ልጄን አደይ አበባ ብያታለሁ፡፡ ልጄ የሙዚቃ ፍላጎት አላት፡፡ በድምፅና እስክስታም ጎበዝ ናት፡፡

ሪፖርተር፡- በባላገሩ አይዶል አማካይነት ከዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ስለመጣሽበት አጋጣሚ ብትነግሪን?

እንዬ፡- ዛሬ ነገ አገሬ እሄዳለሁ እያልኩ ለረዥም ጊዜ አልመጣሁም ነበር፡፡ ልጆች ማሳደግም ከባድ ስለሆነ በዚያው አጥፍቶ ያስቀራል፡፡ የዛሬ ሦስት ዓመት ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት በጌታነህ ፀሐዬ አማካይነት ነበር፡፡ ውጪ አገር የሚኖሩ በሕይወት ያሉ አርቲስቶች በአንዳንድ ሥራ መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ውጪ የሄድነው ባህላችንን ለማስተዋወቅ ቢሆንም፣ ያልሆነ ስም ሰጥተውናል፡፡ የፖለቲካ ነገር አንዳንዴ ሞራል ስለሚነካ ከሙያው ጠፍቼ ነበር፡፡ ጌታነህ የሞትኩኝ ነበር የመሰለው፡፡ በኔ ስም እየዞሩ ትዕይንት ማሳየት ፈልገው ነበር፡፡ ነፃነትን አዲስ አበባ አግኝተው ሐሳቡን ሲያማክሯት በሕይወት እንዳለሁ ነገረቻቸው፡፡ ጌትሽ አላመነም ነበር፡፡ እዛ ሆኜ በተከታታይ በቫይበር የተደወለልኝን ዓይቼ ስደውል ድምፄን ሲሰማ በደስታ ብዛት ማናገር አልቻለም፡፡ በስምሽ ልንዞር ነውና ፍቀጂልን አለኝ፡፡ ብዙ አርቲስቶች ቢኖሩም በሕዝብ ለሕዝብ የማትረሳዋ የታለች? ብላችሁ በመፈለጋችሁ ፈቅጃለሁ አልኩት፡፡ እሱ እኔን እያየ ተወዛዋዥ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ከዚያም በስምሽ ብቻ ከምንዞር አብረን እንሥራ አለኝ፡፡ በአጋጣሚ የዓባይ ግድብ መሠረት ድንጋይ የተጣለበት ጊዜ ይከበር ስለነበርም መጣሁ፡፡ ትልቁም ትንሹም እያጎነበሰ ፍቅሩን ሲገልጽ ተገረምኩ፡፡ እዛ አገር ያለ የሚያውቀኝና የሚያከብረኝ ሰው አልነበረም፡፡ እዛ ያለው የማያውቀኝ ነጭ ሰው ነው፡፡ ወደ አገሬ መምጣትን ማሰብ የጀመርኩትም ከዛ በኋላ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ውዝዋዜን የምትገልጭው በምን መንገድ ነው? ራስሽንስ በውዝዋዜ እንዴት ትገልጽዋለሽ?

እንዬ፡- ማሲንቆ፣ ዋሽንት፣ ክራርና ከበሮን አንድ ላይ ሲጫወቱት ከቁጥጥር ውጭ እሆናለሁ፡፡ እስክስታ በደንብ የምመታው ሙዚቃው ሲዋሃደኝ ነው፡፡ ሙዚቃውን በደንብ ካልተጫወቱ ውዝዋዜው ስለማይመጣልኝ ሰውነቴ ይደርቃል፡፡ የባህል ሙዚቃ መሣሪያዎች ደማችን ውስጥ ስላሉ ውዝዋዜው ተዋህዶናል፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ጎንደር ከተማ አርቲስት እንዬ ታከለ የባህል ምሽት ቤት የተሰኘ ባህላዊ ቤት አለሽ፡፡ ወጣት ተወዛዋዦችና ድምፃውያን ይሠሩበታል? በቀጣይስ ምን የመሥራት ዕቅድ ይዘሻል?

እንዬ፡- ዕቅዴ ባህሉን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተዋወቅ ነው፡፡ ባህላቸውን ይዘው ሳይጠፋ እንዲዘልቁ የማስቀጠል ሐሳብ አለኝ፡፡ ቱባው ባህል የሚታይበት የባህል ጭፈራ የሚያሳዩ ልጆች የሚፈሩበት፣ ባህልን የሚወክሉ ቅርሶች የሚቀርቡበት የባህል አዳራሽ መሥራት እፈልጋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በተወዛዋዥነት ዛሬ ያለሽበት ደረጃ እንደምትደርሽ አስበሽ ታውቂያለሽ?

እንዬ፡- ከበሮ በጮኸበት ሄዶ ከመጨፈር ባለፈ ለዚህ እበቃለሁ ብዬ ገምቼ አላውቅም፡፡ ከትንሽ ከተማ ወጥቼ ይህን ዓለም እዞራለሁ የሚል ህልምም አልነበረኝም፡፡ የትም ቢኖር የትም ቢኬድ ጌታ ከጻፈው ውጪ መውጣት አይቻልም፡፡ ሁሉም ልጅ ዶክተር መሆን ይመኝ ስለነበር እኔም ዶክተር መሆን እፈልጋለሁ እል ነበር፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...