Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ይድረስ ለሪፖርተርበለንደን ስለተገደለው ወንድማችን የእንግሊዝ መንግሥት እንዲያጣራ እንጠይቃለን!

በለንደን ስለተገደለው ወንድማችን የእንግሊዝ መንግሥት እንዲያጣራ እንጠይቃለን!

ቀን:

ከየ26 ዓመት በፊት በለንደን ከሚገኘው መኖርያ ቤቱ ደጃፍ ለተገለደው ወንድማችን ሞገስ ደመ ከልብ ሆኖ እንዳይቀር የአሟሟቱን ምክንያት የእንግሊዝ መንግሥት እንዲያጣራ ለመጠየቅ አቤቱታችንን ለማሰማት በማለት ይህንን ደብዳቤ ጽፈናል፡፡

ሞገስ ዓባይ የተባለው የ27 ዓመት ኢትዮጵያዊ በለንደን ከሚገኘው የወንድሙ፣ የዓለም ዓባይ መኖርያ ቤት ደጃፍ ላይ እ.ኤ.አ. ጁን 30 ቀን 1990 ሞቶ ተገኘ፡፡ ዓለም የወንድሙን ሞት ሲሰማ በሐዘን ተዋጠ። አሟሟቱን ግን እጅጉን እንዲጠራጠር ያደረገው አጋጣሚ ነበር፡፡ ሞገስ የሞተው ቼኒስ ጎዳና፣ ለንደን WC1 ከሚገኘው 4ኛ ፎቅ ላይ በመዝለል ሊሆን ይችላል ተብሎ ቢገመትም፣ ከምስክሮች የተገኘው ማስረጃ ግን በሟቹ ሰውነት ላያም ሆነ በአካባቢው አንዳችም የፈሰሰ ደም እንዳልተገኘ የሚያረጋግጥ ሲሆን፣ ስናገኘውም ሕይወቱ አልፋ ነበር ብለዋል፡፡ ስለዚህም የሞተው ቀደም ብሎ ሊሆን ይችላል የሚል መላ ምትም ሰፍሮ ነበር። ፖሊሶቹ ግን በተቃራኒው፣ እኛ ስንደርስ ሟች እስትንፋስ ነበረው፡፡ በሟቹ ሰውነት ላይም ደም ነበረ ብለዋል፡፡

ይህም ሆኖ ሞገስ ከሞተ ከ45 ደቂቃዎች በኃላ የደረሱት ዕርዳታ ሰጭ አምቡላነሶች፣ ሞገስን ለማንቃት ወይም ወደ ሕይወት ለመመለስ ሞክረው ነበር፡፡ ነፍሱ ከተለየችው 45 ደቂቃ በኋላ፣ ሬሳውን ለማንቃት መሞከር ለምን አስፈለገ? የሚለውን ጥያቄ ማንሳት የግድ ይላል፡፡ የሞተበት ምክንያት ከፎቅ ወድቆ በመከስከሱ ከመባል ፈንታየልብ ሕመም ሊሆን ይችላል ተብሎ በፓቶሎጂስት ሪፖርት መቅረቡም አንዱ መታየት ያለበት ነገር ነው። ሌላው ሞገስ ዘለለ የተባለበት መስኮት ክፍት ሆኖ ቢገኝም፣ ሁኔታውን ለማረጋገጥ የወንጀል ምርመራ ባለሙያዎች በቦታው ላይ የአሻራ ምርመራ አለማድረጋቸው ሌላኛው አጠራጣሪ ነገር ነው፡፡

- Advertisement -

ፖሊሶች የሞገስን ልብሶች አቃጥለነዋለል በማለት ልብሶቹን ለመመለስ እምቢተኛ በመሆናቸውም እንዲሁ የጥርጣሬ ምንጭ ነው፡፡ የሞገስ ጉዳይ እ.ኤ.አ በኦገስት 1990 በሴንት ፓንክራስ ኮሮነር ፍርድ ቤት በታየበት ጊዜ፣ ዳኛው ዶ/ር ዳግላስ ቻምበርስ፣ ‹‹ክፍት›› ውሳኔ (open verdict) ሰጥተዋል፡፡ ይህም ወሳኔያቸው የሞገስ አሟሟት አጠራጣሪ መሆኑን ይገልጻል። ነገር ግን 12 የፖሊስ መኮንኖች በተገኙበት ፍርድ ቤቱ አንድም ዋና ምስክር፣ ማለትም ጎረቤቶቹ፣ አስከሬኑን የዕለቱ ተረኛ በመሆን ያዩት የዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ዶክተርና ነርስ እንዲሁም የአምቡላንስ ቡድን አባላት እንዲመሰክሩ ባልተደረገበት ሁኔታ ከፍርድ ቤቱ ምን የተለየ ውጤት ይጠበቃል? ይህ ተደርጎ ቢሆን ኑሮ ግን ውሳኔው ተቀይሮ ምናልባትም ‹‹ሕገ ወጥ ግድያ›› ሊባል እንደሚችል እናምናለን። ስለዚህም ከአሟሟቱ ጋር የተያያዙ ማስረጃዎች ተሟልተው እንዲቀርቡ ባለመደረጉ ወይም ትኩረት እንዲያገኙ ባለመደረጋቸው ሞገስ ደመ ከልብ ሆኖ ቀረ በማለት ስናዝን ኖረናል፡፡ ወንድሜ ራሱን የሚገድልበት አንዳችም ምክንያት የለውም በማለት ዓለም የተባለው ወንድሙ ከመግለጹም በተጨማሪ፣ ዛቻዎች ይደርሱት እንደነበር ቢናገርም ይህን ለማጣራት የሜትሮፖሊታን ፖሊስ ፈቃደኝነቱን አላሳየም፡፡

 በኮሮነሩ ችሎት ላይ ቀርበው ቃላቸውን የሰጡት ፖሊሶች፣ ደም በሰውነቱ ዙሪያ ነበረበት ከማለት በስተቀር ሲደርሱ አስከሬኑ በብርድ ልብስ ተሸፍኖ ማግኘታቸውን በፍጹም አለማስታወሳቸው ሌላው አስገራሚ ጉዳይ ነው፡፡ በመጨረሻም ከጎረቤት ምስክሮች አንዷ እንደ ሌሎቹ ምስክሮች ምንም ደም አላየሁም ከማለት አልፋ፣ ከፎቅ የዘለለ አይመስለኝም ያለችውንና በቦታው የተገኘችውን ምስክር በፍትህ አሰጣጡ ሒደት አለማካተት የበለጠ እንድንጠራጠር ያደርገናል።

የመረጃ ሕግ 2000 (Information Act 2000) በመጠቀም K.Gallagher 15 January 2017 UNISON የተባለ (የሠራተኞች ማኅበር) የሞገስ አሟሟት ሁኔታ በስም ስህተት እንደሆነ የሚገለጽ አዲስ መረጃ በማካተት የሞገስ አሟሟት ሁኔታ እንዲመረመር ለማድረግ የሟች ወንድሙ ዓለም ከባለሙያዎች ጋር ምክክር አደርጓል፡፡

ጉዳዩ ከመሠረቱ በጥልቀት አልተመረመረም፡፡ አልተጣራም፡፡ በችሎቱ የተያዘው ማስታወሻም የተሟላ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ከፓቶሎጅስት የተሰጠው ማስረጃ ውድቅ መደረጉ ያስከተለውን የአካል ጉዳትም ሆነ ለሞት ምክንያት መሆን አለመሆኑን አይጠቁምም፡፡ ኮነስታብል ፖሊሷ ብዙ ጎረቤቶች አነጋግሬያለሁ ትበል እንጂ፣ ምስክርነታቸው እንዲሰማ አልተደረገም፡፡ የሟቹን ጤና እስከ መጨረሻው ይከታተሉ ከነበሩት አማካሪ ሳይኪያትሪሰትም ቢሆን የተወሰደ ማስረጃ አልነበረም፡፡ ባለሙያዎቹ  ከአምቡላንስ ቡድኑ የሚወሰደው ቃልም ለማስረጃነት ይጠቅም ነበር ብለዋል፡፡ የሞተበት ሰዓት የትም ቦታ ላይ አለመገለጹና ማስረጃም አለምኖሩ ምረመራውን በድጋሚ ለማንቀሳቀስ በቂ መግቢያ በር ይከፍታል ብለዋል፡፡

ሆኖም ግን ጉዳዩን ለማንቀሳቀስ ቢያንስ የ10,000 ሰው ፊርማ ስለሚያስፈልግ፣ ይህን አቤቱታ (ፔቲሽን) በመፈረም እውነትም ሞገስ ደመ ከልብ ሆኖ እንዳይቀር አንባብያን የበኩላችሁን ታደርጉልን ዘንድ በትህትና እንጠይቃለን። በተጨማሪም ለመርዳት ፈቃደኛ ከሆናችሁ ይህን መልዕክት በኢሜል፣ በፌስቡክና በአካልም በየሃይማኖትና በየኮሙኒቲያችን ማዕከሎች፣ በማኅበራትና ዕድሮች በማሰራጨት የበለጠ ሕዝብ እንዲፈርምበት ብትተባበሩን ስንል ከፍተኛ ምስጋናችንን አስቀድመን እናቀርባለን።

ፍትህ ተጓድሏል ብለን የምናምን በሙሉ በፊርማችን ድጋፋችንን እናሳያለን! ፍትህ ለሞገስ!

ለመበለጠ መረጃ በኢሜል አድራሻችን [email protected] ወይም በእነዚህ ስልክ ቁጥሮች ያግኙን 07376713828 or 07949770818

(የሞገስ ወዳጆች)

 

***

‹‹ብልህ ሲሳሳት ከገልቱ ይብሳል››

በአዲስ አበባ ቀድሞ ‹‹ሶማሌ ተራ›› ተብሎ ይጠራ ከነበረው አካባቢ ጀምሮ ሃይካን ሆቴል፣ ከሊፋ ሕንፃ ዙሪያውን እስከ ሀብተጊዮርጊስ ድልድይ ድረስ ብዛት ያላቸው ‹‹ሰማይ ጠቀስ›› ፎቆች እንዲሁም ከአሥር በላይ የተለያዩ የመንግሥትና የግል ንግድ ባንኮች የሚገኙበት አካባቢ የመብራት መቆራረጥ ችግር ተደጋግሞ እየተከሰተ ነው፡፡

 የሚገርመው በየቀኑ ያለማጋነን ከ12 ጊዜ በላይ መብራት ይጠፋል፡፡ የጠፋው መብራት ቆይቶ ይመጣል፡፡ ይህን ድርጊት ማንም ሊያረጋግጠው የሚችለው ሐቅ ነው፡፡ ‹‹ቅድመ ማስጠንቀቂያ›› የሚባል ነገር የለም፡፡ ችግሩ ትራንስፎርመር ይሁን የፊውዝ መቃጠል አለያም ደረጃቸውን ያልጠበቁ የኤሌክትሪክ ገመዶች ያስከተሉት ብቻ በትክክል መንስዔው የትኛው እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ብቻ ምን አለፋችሁ እዚህ አካባቢ ያለነው ድርጅቶች በጣም ተቸግረናል፡፡ እየተናደድን መሳቅ ጀምረናል፡፡

መዲናችን አዲስ አበባ ያለችበትን ሁኔታ እንገነዘባለን፡፡ በልማት የሚጓዝ አገር ብዙ ችግሮች ያግጥሙታል፡፡ ቀንና ማታ የሚገነቡት ሕንፃዎች፣ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ፊላጊዎች ናቸው፡፡ እንኳን እኛ ጎረቤቶቻችን ሳይቀሩ አሰፍስፈው የሚጠብቁት ግዙፍ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት እየተገነባ ነው፡፡

ይሁን እንጂ አሁን በጠቀስንላችሁ አካባቢ በተለየ ሁኔታ የሚፈጸመው በደል ግን ከይቅርታ በላይ ነው፡፡ አልፎ አልፎ የምንጠቀምባቸውን የኤሌክትሪክ ቁሳቁሶች ድንገት በሚለቀቀው ኃይል ሊቃጠሉብን ይችላሉ፡፡ ሥራችንን የምናካሂድበት የኢንተርኔት ኔትቀርክ አይኖርም፡፡ እንግዲህ መብራቱ ከሌለ ሥራም ገቢም ስለማይኖረን ይህ ችግር ትኩረት ይሰጠው፡፡

‹‹ሌባና ፖሊስ›› እየሆነ ያስቸገረን መብራቱ ሲጠፋ ጄኔሬተር እያበራን፣  እያጠፋን ቀኑ ሙሉ ስንደክም መዋላችን ነው፡፡ ሁኔታው መብራት ኃይሎች ጨምታ ጀምረዋል ያሰኛል፡፡ ለመሆኑ ወዴት እየሄድን ነው ያለነው?

እንግዲህ ከአፍሪካ ከፍተኛውን የኃይል ማመንጫ ለመገንባት እየተጓዘች ያለች አገር፣ አንዲት ትንሽ ሰፈር ውስጥ ለሰሚ ግራ የሚያጋባ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ በደል የሚደርስባት ከሆነ በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ አባቶች ‹‹ብልህ ሲሳሳት ከገልቱ ይብሳል፤›› ይላሉና እስቲ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የበላይ ኃላፊዎች መፍትሔ ይፈልጉልን፡፡ በቸር እንሰንብት፡፡

(ባጫ፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...