‹‹ኃይልና ፍጥነት ቁጥጥር ካልተደረገባቸው አደጋ ያስከትላሉ›› የሚባል አባባል አውቃለሁ፡፡ ስንፈጥን ራሳችንን መቆጣጠር አለብን፡፡ ፍጥነት በአካላዊ እንቅስቃሴ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ስንናገር ፍጥነታችንን ካልቀነስን የሚያዳምጥን አይኖርም፡፡ አንድ ሰው ቶሎ ቶሎ ሲናገር ወይም በቁጣ ውስጥ ሆኖ መልዕክት ሲያስተላልፍ የመደመጥ ዕድሉ አናሳ ነው፡፡ በፍጥነት የሚያሽከረክሩ ሰዎች ተሽከርካሪውን መቆጣጠር የማይችሉበት ደረጃ ከደረሱ ውጤቱ መጋጨት ወይም መገልበጥ ነው፡፡ የሚነገረውን ከቀልቡ የማይሰማ ሰው የተዛባ መረጃ ይደርሰውና ሌሎችንም ያሳስታል፡፡ ብዙ ጊዜ ለፍጥነት ከሚዳርጉን ምክንያቶች መካከል አንደኛው ስሜታዊነት ነው፡፡ ስሜታዊነት ግንፍልተኛ ያደርጋል፡፡ ግንፍልተኛ ሰው ደግሞ በቅጽበት በሚወስደው ዕርምጃ ምክንያት ለስህተት ይዳረጋል፡፡ አንዳንዴም የሰው ሕይወት በእጁ ሊያልፍ ይችላል፡፡ ይህ ከላይ የተንደረደርኩበት ሐሳብ ለዚህ ገጠመኜ መነሻ ይሆናል፡፡
በቅርቡ ከአራት ኪሎ ፒያሳ በእግሬ እየተጓዝኩ ነበር፡፡ ጊዜው ከቀትር በኋላ አሥር ሰዓት አካባቢ ነው፡፡ ቀስ እያልኩ ሳዘግም ራስ መኮንን ድልድይ ደረስኩ፡፡ በመንገዱ ግራና ቀኝ ባሉ ረድፎች በተቃራኒ አቅጣጫ ተሽከርካሪዎች ይተላለፋሉ፡፡ እኔም በመንገዱ የቀኝ ጠርዝ የእግረኛ መሄጃ ላይ ብንሆንም ዘና አላልኩም፡፡ ድንገት መስመሩን የሳተ መኪና እንዳይገጨኝ እየተጠነቀቅኩ ነበር፡፡ ጊዜው ያስፈራላ፡፡ በዚህ መሀል ድንገት ከኋላዬ ‹‹ጓ!›› የሚል ድምፅ ሰምቼ ዞር ስል ከፊትና ከኋላ የነበሩ ተሽከርካሪዎች መጋጨታቸውን አወቅሁ፡፡ በዚያ ብዙም ተሽከርካሪ በሌለበት መንገድ ላይ የሁለቱ መጋጨት ገርሞኝ ለማየት ቆም ስል ሁለቱም አሽከርካሪዎች ወረዱ፡፡ ከኋላ ያለው ረጋ ያለ ሲሆን፣ የፊተኛው ግን እጆቹን ለቡጢ አዘጋጅቶ ነበር የተንደረደረው፡፡ ይኼኔ ከእኔ በተሻለ ርቀት ላይ ያሉ ሰዎች መሀላቸው ገቡ፡፡ ለቡጢ የተዘጋጀው ፀያፍ ስድቦችን ማዥጎድጎድ ቀጠለ፡፡
ሰዎቹ ወደ መኪናው ገፋ አድርገውት ስድቡን እንዲያቆም ቢወተውቱትም አልሰማም ብሏል፡፡ ያኛው ደግሞ በመገረም ዝም ብሎ ይመለከተዋል፡፡ ይኼን ጊዜ ነው አንድ ትልቅ ሰው፣ ‹‹መጀመሪያ ትራፊክ ፖሊስ ይምጣና ይዳኛችሁ፡፡ ስለዚህ አንተ ይህንን ፀያፍ ስድብህን አቁምና በትግዕሥት ውጤቱን ተጠባበቅ. . .›› ከማለታቸው፣ ‹‹አንተ ሼባ ምንም የሚያገባህ ነገር የለም. . . ይኼ ጠጅ ቤት መሰለህ እንዴ. . .›› እያለ አዛውንቱን ሕዝብ ፊት ሲዘረጥጥ፣ ከየት መጣ የተባለ በአካል ብቃቱ የፈረጠመ ታዳጊ ወጣት ዘሎ እግሩን መንጋጋው ላይ ሲያሳርፍበት ያለማጋነን አምስት ሜትሮች ያህል ተፈናጥሮ ተዘረረ፡፡ ወጣቱም እየተጀነነ፣ ‹‹ሕግ የማይገዛውን ኃይል ይገዛዋል›› ብሎ ከአካባቢው በፍጥነት ተሰወረ፡፡ አዛውንቱ በተፈጠረው ድንገተኛ ነገር እንደ መደንገጥም እንደ መገረምም ብለው፣ ‹‹በአፍ ይጠፉ በለፈለፉ. . .›› ካሉ በኋላ እሳቸውም መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡ ሁለት ሴቶች መንገዱን ተሻግሮ ካለ ግሮሰሪ ቢጤ የታሸገ ውኃ አምጥተው የወደቀው ላይ ካፈሰሱበት በኋላ ቆይቶ ነቃ፡፡
ከወሰደው ሰመመን የነቃው ሰውዬ ከመሬት ላይ እንደምንም ተነስቶ ቢቆምም ራሱን መቻል አቃተው፡፡ ሁለት ጎረምሶች ደገፍገፍ አድርገውት መኪናውን ቢያስደግፉትም ምን እንደተፈጠረ የሚያውቅ አይመስልም፡፡ ለጥቂት ደቂቃዎች አንገቱን ደፍቶ ከቆየ በኋላ ቀስ እያለ ቀና ብሎ፣ ‹‹ምንድነው የተፈጠረው? የት ነው ያለሁት?›› ሲል አይ ሰው መሆን ከንቱ ያሰኝ ነበር፡፡ አንዱ ጠጋ ብሎ የሆነውን ሁሉ ሲነግረው፣ ‹‹አሁን ገባኝ፡፡ ጥፋቱ የራሴ ነበር፡፡ ለማንኛውም እግዚአብሔር ይስጥልኝ. . .›› ብሎ መኪና ውስጥ ገብቶ ሞተሩን አስነስቶ ከአካባቢው ተፈተለከ፡፡ ይኼ ሁሉ ሲሆን ከኋላ የገጨው ሰውዬ አንዲትም ቃል አልተነፈሰም ነበር፡፡ እሱም አሁን የሚጠይቀው ስለሌለ የመኪናውን በር ከፍቶ ሞተሩን ሲያስነሳ ጠጋ ብዬ፣ ‹‹ወንድም ምነው ዝም አልክ?›› አልኩት፡፡ እሱም፣ ‹‹ምን ልበል ታዲያ?›› ሲለኝ፣ ‹‹ይኼ ሁሉ ግርግር የተፈጠረው በአንተ ምክንያት ነው እኮ?›› ከማለቴ ከት ብሎ ስቆ፣ ‹‹እኔማ በአጋጣሚው አዝኜ ነበር፡፡ ግን ሰውየው ያልተረጋጋ ባለጌ ስለነበር የደረሰውን አየህ አይደል? ወንድሜ በል ክፉ አታናግረኝ. . .›› ብሎ ቆሰቆሰው፡፡
ማታ ቤት ስገባ ለባለቤቴ የገጠመኝን ሳጫውታት፣ እሷም የዚያን ቀን የሰማችውን አንድ ገጠመኝ ነገረችኝ፡፡ የሥራ ባልደረባዋ እንግዳ ለመቀበል ቦሌ ኤርፖርት ትሄዳለች፡፡ ከውጭ አገር የመጣው እንግዳ ኢትዮጵያዊ ሲሆን፣ በአሜሪካ ሠራዊት ውስጥ ያገለገለ ኮማንዶ ነው፡፡ ይህንን በ30ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኝ ኢራቅና አፍጋኒስታን የዘመተ ወታደር ዘመዷን ይዛ በቦሌ መድኃኔዓለም አቅጣጫ ስታሽከረክር፣ ከእሷ ፊት የሚያሽከረክር አንድ ጎረምሳ መንገድ እየዘጋ ያስቸግራታል፡፡ ቅዳሜ ማለዳ ላይ ስለሆነ መንገዱ ብዙም ተሽከርካሪ አልነበረውም፡፡ በኋላ መመልከቻና በግራና በቀኝ ስፖኬዎች እያያት እየሳቀና እያላገጠ መንገዱን ሲዘጋባት እንግዳው ‹‹አይዞሽ ታገሽ›› እያላት ነበር፡፡ እሷም ቢቸግራት ፍጥነት ቀንሳ ለመራቅ ስትሞክር ጎረምሳው በእጆቹ የብልግና ምልክት እያሳየ ይሰድባት ጀመር፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ወታደሩ ዝም ብሏል፡፡
የወታደሩ ዝምታ ያሳሰባት የባለቤቴ ጓደኛ መኪናዋን ዳር አስይዛ ትቆማለች፡፡ ከፊቷ ኮሮላ የሚያሽከረክረው ጎረምሳ ለምን ቆመች ይሁን ወይም በሌላ ምክንያት ይሁን አይታወቅም፣ እሱም ኮሮላውን አቁሞ በሩን ከፍቶ ወደሷ ይመጣል፡፡ ወታደሩ አሁንም ‹‹ዝም በይው›› ይላታል፡፡ ያ ደረቱ በቀሰም እንደተነፋፋች ዶሮ የተወጣጠረ ጎረምሳ፣ ‹‹ምነው ፈራሽ እንዴ?›› ብሎ በሯን ሊበረግደው ሲሞክር ተቆልፏል፡፡ ይኼኔ ወታደሩ ከኋላ በርግዶ ወጥቶ በማይታመን ፍጥነት በጠረባ ጥሎት አንገቱ ላይ ሲቆምበት የላባ ያህል እንኳን የከበደው አይመስልም ነበር፡፡ በዚያ ፍጥነትና መጠነኛ ምት አስፓልቱ ላይ የተዘረረው ፈርጣማ መሳይ ገለባ ከመውደቁ በላይ ራሱን ስቶ ነበር፡፡ ራሱን መሳት ብቻ ሳይሆን ጂንስ ሱሪው በሽንት ርሶ ነበር፡፡ ‹‹የቀበጡ ዕለት. . .›› እንዲሉ በኃይሉ የተመካው ዋተኔ እንዲያ ሆኖ ሲያዩት እንዴት ያሳፍር እንደነበር ባለቤቴ የሰማችውን ስትነግረኝ፣ ለእንዲህ ዓይነቶቹ ስሜታዊያን አዘንኩላቸው፡፡ የሌላውን ኃይልና ብርታት ከምንም ሳይቆጥሩ በራሳቸው ጉልበት ብቻ የሚመኩ ስሜታዊያን በየቦታው አሉና ልብ ቢሉስ?
(ዮናስ አሸብር፣ ከሃያ ሁለት ማዞሪያ)