በውብሸት ሙላት
የአዲስ አበባ ሕዝባዊ የፖለቲካ አጀንዳነት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጨመረ መጥቷል፡፡ በጥቅሉ ሲታይ ለፖለቲካዊ አጀንዳው መነሻ የሆነው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49 ላይ የተገለጹት ድንጋጌዎች ናቸው፡፡
በዚህ አንቀጽ መሠረት አዲስ አበባ የፌደራሉ መንግሥት ርዕሰ ከተማ ናት፡፡ የከተማ አስተዳደሩም ተጠሪነቱ ለፌደራሉ መንግሥት ነው፡፡ ይሁን እንጂ የከተማው ነዋሪ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን አለው፡፡ በተጨማሪም በፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ይወከላሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የኦሮሚያ ክልል በከተማው ላይ ያለው ልዩ ጥቅም እንደሚከበርለትም ተገልጿል፡፡
እነዚህን ጉዳዮች ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ቢያንስ ሁለት አዋጆች ማውጣት ግድ ነው፡፡ የመጀመሪያው የከተማዋ አስተዳደርን ሁኔታ የሚገዛ ቻርተር ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የኦሮሚያ ክልል በከተማ ላይ የሚኖረውን ልዩ ጥቅም የሚመለከት ነው፡፡ ሁለቱንም አዋጆች የማውጣት ሥልጣን የፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮች ነው፡፡
የመጀመሪያውን ጉዳይ በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት ማሻሻያ የተደረገባቸው አዋጆች ወጥተዋል፡፡ ከተማዋም በዚያ መሠረት እየተመራች ነው፡፡ ሁለተኛውን ጉዳይ የሚመለከተው ሕግ ግን ሳይወጣ ሃያ ሁለት ዓመታት እየሞላው ነው፡፡ በዚህ ዓመት ይወጣል ተብሎ ይጠበቃልም፡፡ ይህ ጽሑፍ የሚያጠነጥነው የአዲስ አበባ ከተማ ኗሪ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሥልጣንን የሚመለከት ነው፡፡
ከተማዋ የፌደራሉ መንግሥት ርዕሰ ከተማ ናት፡፡ በርካታ ዓለም አቀፋዊ ተቋማትም መቀመጫ ናት፡፡ ይኼንን የሚፈቅደው የፌዴራሉ መንግሥት ነው፡፡ በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል ሕገ መንግሥት መሠረት ደግሞ የክልሉ ዋና ከተማ ሆናለች፡፡
የከተማው ሕዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ቢልም ምን ምን ሥልጣን አለው? ወይም የሌሉት ሥልጣኖች ምን ምን ናቸው? የሚሉትን በተመለከተ ተጨማሪ ሕግ እንደሚያስፈልግ ግልጽ ነው፡፡ ይህን በቅጡ ለመረዳትና ጉድለቶችም ካሉበት ለመንቀስ እንዲረዳ፣ ስለ ራስን በራስ ማስተዳደር የተወሰኑ ነጥቦችን እንዲሁም ክልሎችም ያሏቸውን ሥልጣኖች በማንሳት የከተማዋ በምን ሊያንስ እንዳነሰ እንመለከታለን፡፡
ራስን በራስ ማስተዳደር፣ የውስጣዊ የራስን ዕድል በራስ መወሰን ዋናው መገለጫ ነው፡፡ አንድ ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ፣ በሕግ በታወቀና በተለየ ሁኔታ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የባህላዊ ጉዳዮቹን በራስ ማስተዳደር ነው፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ የተለያዩ ውሳኔዎች ማን ራሱን የማስተደዳር ወይም ራስ ገዝነት መብት አለው ለሚለው ቢያንስ በቋንቋ፣ በሃይማኖትና በብሔር ምክንያት አናሳ የሆኑ ቡድኖች ምንም እንኳን የመገንጠልና ማናቸውንም ዓይነት ውጫዊ የራስን ዕድል በራስ መወሰን መብት ባይኖራቸውም የራስ ገዝነት (ውስጣዊ የራስን ዕድል በራስ መወሰን) መብት እንዳላቸው ግን በግልጽ ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ማናቸውም በብሔር፣ በቋንቋና በሃይማኖት ምክንያት አናሳ የሆኑ ቡድኖች ምሉዕ የሆነ የራስ ገዝነት መብት ያላቸው መሆኑን ነው፡፡
ይህ ማለት ግን፣ በብሔር መሥፈሪያነት ያልተደራጁም ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ሊያስተዳድሩ አይችሉም ማለት ግን አይደለም፡፡ መብትም ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ማንኛውንም ጉዳይ ያለገደብ መወሰን ማለት አይደለም፡፡ ለማዕከላዊ መንግሥት ተቆርሶ የሚቀር ወይም የሚሰጥ ሥልጣን ይኖራል፡፡ ለብሔሩ ወይም ለብሔረሰቡ ወይም ለሕዝቡ የሚቀር በሕግ የሚለይ ሥልጣን አለ ማለት ነው፡፡
ራስን ማስተዳደር የመገንጠል መብትን አያካትትም፡፡ ራስን ለማስተዳደር በድንበር የተቀነበበ ቦታ አስፈላጊ ነው፡፡ ክልል፣ ዞን፣ ወረዳ፣ ቀበሌ ወይም ሌላ መስተዳድሩ የሚያካልለው ቦታ መታወቅ አለበት፡፡ ስለሆነም አንዱ ጉዳይ ድንበር መለየት ነው፡፡ ድንበሩ ብዙ ጊዜ ለአስተዳደር አመቺነት ሲባል የሚዘጋጅ ሲሆን በፌደራላዊ ሥርዓት ግን ፖለቲካዊም ሊሆን ይችላል፡፡
ሌላው በምን በምን ጉዳዮች ሥልጣን እንዳለው የሚያሳይ ድንጋጌ እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ የፌደራሉን ከክልሎች፣ የክልሎችን ከዞኖች ወዘተ ለይቶ የሚያሳይ ማለት ነው፡፡ ይህ የሥልጣን ክፍፍልን የሚመለከት ነው፡፡
ከላይ ከተገለጹት በተጨማሪ፣ ራሳቸውን ሲያስተዳደሩ ወይም በተወሰነ መልኩ ራሳቸውን ሲችሉ ወጪያቸውን የሚሸፍኑበት የፋይናንስ ጉዳይም መካተት አለበትና የዚሁ አካል መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡
የዓለም አቀፉ ሕግ፣ የውስጣዊ የራስን ዕድል በራስ መወሰን የሚችሉትን አካላት ሲዘረዝር እንዴት መወሰን እንደሚችሉ ሥነ ሥርዓቱን ግን አይገልጽም፡፡ በግልጽ የታወቀና በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው የአወሳሰን ሥርዓት የለም፡፡ አገሮች በራሳቸው ሕግ የሚወስኑት ጉዳይ ይመስላል፡፡
ስለሥነ ሥርዓቱ ብዙ በዓለም አቀፋዊ ሕግ ልምድ ባይኖርም፣ ይዘቱን በተመለከተ ግን የሰፋ ልዩነት የለም፡፡ ቢያንስ የራስ ገዝ መብት ያላቸው ራሳቸውን ማስተዳደርና በወሳኝ ፖለቲካዊ ጉዳዮች በማዕከላዊው መንግሥት በፍትሐዊነት መሳተፍን ይስማሙበታል፡፡
በኢትዮጵያም፣ ቢያንስ ከሽግግር ዘመኑ በኋላ ያለውን ስንመለከት በመጀመሪያ የምናገኘው አዋጅ ቁጥር 7/1984ን ነው፡፡ አዋጁ ራስን በራስ ማስተዳደርን በተመለከተ ትርጓሜ ሲሰጥ፣ ‘self-government’ የሚለውን የእንግሊዝኛ ሐረግ ተጠቅሟል፡፡ በአማርኛው ‹‹መስተዳድር›› የሚል አቻ ቃል ይጠቀምና ዐውዳዊ ትርጓሜውን ያስቀምጣል፡፡ እንዲህ በማለት ‹‹በብሔር ወይም በክልል ደረጃ የራሱን የሕግ አውጭ፣ የሕግ አስፈጻሚና የዳኝነት ሥልጣን አጠቃሎ የያዘ አካል ነው፡፡›› ይህ ዓይነቱ አሠራር የፌደራላዊ አስተዳደር ለሚከተሉ አገሮች ዋና መለያ ነው፡፡
የፌደሬሽኑ አባላት በሕገ መንግሥቱ ተለይቶና ድንበር ተለክቶ በተቀመጠው ሥልጣናቸው ተመሥርተው ሕግ የማውጣት፣ ያንን የማስፈጽምና ለሚያወጧቸው ሕጎች ትርጉም በመስጠት ግጭትን የሚፈታ የዳኝነት አካላት ማቋቋም ሥልጣን አላቸው፡፡ ይህ አሠራር ከክልል ባለፈም በሌሎች ዝቅተኛ እርከኖችም ላይ ሊደገም ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ ልዩ ዞን፣ ልዩ ወረዳ፣ ወረዳና ቀበሌዎች ይህ ዓይነት አወቃቀር አላቸው፡፡ የክልል ሕገ መንግሥት በተራቸው የክልሉንና የነዚህን የአስተዳደር እርከኖች ሥልጣን ለይተው ማስቀመጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ከራስ ገዛዊ አስተዳደሮች አንዱና ዋናው ክልል ነው፡፡ ክልል፣ ራስን በራስ ዘዬ የሚያስተዳድሩበት፣ የዴሞክራሲ ቤተ ሙከራ ነው፡፡ ቢያንስ በመርሕ ደረጃ የዴሞክራሲ ቤተ ሙከራ ለመሆን ደግሞ በቂ ሕገ መንግሥታዊ የመሞከሪያ ሥልጣንን ለክልሎች መተውን ይጠይቃል፡፡
ሕገ መንግሥቱ የፌደራሉንና የክልሎችን ሥልጣን ለይቶ አስቀምጧል፡፡ የፌደራሉን ዘርዝሮ ካስቀመጠ በኋላ ቀሪዎቹ የክልል እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ ምንም እንኳን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 51(2) ላይ እንደተገለጸው የፌዴራል መንግሥቱ ‹‹የአገሪቱን አጠቃላይ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የልማት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ዕቅድ ያወጣል፣ ያስፈጽማል፡፡›› ቢልም ክልሎቹም ይህንኑ መሠረት ያደረገ የራሳቸውን ‹‹የክልሉን አጠቃላይ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የልማት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ዕቅድ ያወጣል፣ ያስፈጽማል፡፡›› ይላል፡፡ በመሆኑም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 52(2)(ሐ) መሠረት ብዙ ሥልጣን አላቸው፤ የፌዴራሉ እንደ ቢጋር ወይም ጥቅል አቅጣጫ እንጂ ለክልል የሚሆን፣ የእያንዳንዱን ክልል ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ያስገባ ፖሊሲና ሕግ፣ የፌዴራል መንግሥቱ ስለማያወጣ፣ ከተጠቀሙበት የማውጣት ነጻነት አላቸው፡፡
ይህ ለክልሎች የተሠጠው ሥልጣን አዲስ አበባን አይመለከትም፡፡ ጥያቄው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ልክ እንደክልል እኩል ሥልጣን ካልተሰጠው ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን እንዳለው ከተቀመጠ፤ ከክልሎች በምንስ ያንሳል? እንዲሁም ለምን ያንሳል? የሚሉትን ጥያቄዎች ማየት ይገባል፡፡ ይህን ጉዳይ በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት ደግሞ የሌሎች ፌዴራላዊ ሥርዓትን የሚከተሉ አገሮች ዋና ከተሞቻቸው ያሏቸውን ሥልጣን መቃኘት ይጠቅማል፡፡
የፌዴራል መቀመጫ ሲወሰን ግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ በርካታ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ ለውጥም ሲደረግ እንዲሁ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የመጀመሪያው ከውጭም ከውስጥም የሚነሳን ሥጋት መከላከል የሚያስችል ቦታ መሆኑ ነው፡፡ በአሜሪካ፣ ዋሽንግተን ዲሲን ስትመረጥ በተቻለ መጠን ከአውሮፓ ሊነሱ ለሚችሉ ጥቃቶች በቀላሉ ያልተጋለጠ መሆን እንዲሆንም ጭምር አስባ ነው፡፡ በካናዳና በአውስትራሊያም ተመሳሳይ ነው፡፡
ሕዝባዊ አመጽ ቢነሳ ወይም የተወሰነ የሕዝብ ክፍል፣ ለምሳሌ ወታደሮች፣ፖሊሶች ወዘተ፣ በቀላሉ እንዳይቆጣጠረውም ግምት ውስጥ ይገባል፡፡ በተለይ በሥርዓቱ ላይ ቅያሜ ያለው ሕዝብ በሚኖርበት ቦታ ላይ ዋና ከተማ አይመሠረትም፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ዋና ከተማ ሲመሠረት አንድን ክልል የሚጠቅም ወይንም የሚጎዳ መሆንም የለበትም፡፡
ከተማው ለሚገነባበት ቦታ ቅርብ የሚሆነው ክልል ወይም ሌላ ከተማ፣ የበለጠ ተጠቃሚ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ለምሳሌ አውስትራሊያ ዋና ከተማዋ ሲዲኒ (የኒውሳውዝ ዌልዝ ክልል ዋና ከተማ) ወይንም ሜልቦርን (የቪክቶሪያ ክልል ዋና ከተማ) እንዳይሆን ያደረገችውና ከሲዲኒ ቢያንስ 100 ማይልስ እንድርቅ የተደረገበት በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ ዋና ከተማ የሚሆንበት ክልል ወይም ቅርብ የሆነ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች በርካታ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድሎች ይኖሯቸዋል፡፡ በሌላ ክልል ሊፈጠር የማይችል ዕድልና ተጠቃሚነት ማለት ነው፡፡ አዲስ አበባ ዋና ከተማ በመሆኗ በአቅራቢያዋ ለሚገኙ ከተሞች ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረገችው ማለት ነው፡፡
ሌላው ከተማው ቀድሞ የነበረና ትልቅ ሆኖ የነዋሪውም ብዛት ከፍተኛ ከሆነ የነዋሪውን መብቶች በሚገድብ መልኩ ርዕሰ ከተማ መቆርቆር የለበትም፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑት ሞስኮና በርሊን ናቸው፡፡ ዋና ከተማ ቢሆኑም ከክልል ጋር እኩል ሥልጣን አላቸው፡፡ በመሆኑም ትልቅ ከተማ ሲሆኑ የክልልነት ደረጃ መስጠት የተለመደ ነው፡፡ ትንሽ ሲሆን ደግሞ ለማዕከላዊው መንግሥት ተጠሪ እንዲሆን ይደረጋል፡፡
ርዕሰ ከተማን በሚመለከት የሚነሳ ሌላም ውጥረት አለ፡፡ ይህም፣ የፌዴራል መንግሥቱ እንደ ብሔራዊ ከተማ፣ መገለጫ መውሰድ፣ ብሔራዊ ውክልናና የባህል መለያ እንዲሆን ሲፈልግ፤ የአካባቢው ሕዝብ ደግሞ ቅድሚያ ለራሱ በማሰብ በራስ መንገድ ማስተዳደርና የራሱ መገለጫ እንድትሆን የመፈለጉ ጉዳይ ሁልጌዜም የማይጠፋው ውጥረት ነው፡፡
የፌደራሊዝም ምሁራን፣ የፌዴራል መንግሥት መቀመጫ እንጂ ዋና ከተማ የለውም ይላሉ፡፡ አባል ክልሎች በአንድነት አንድ አገር ይሆናሉ፡፡ ለማዕከላዊው መንግሥት የተሰጡትን ሥልጣን እና ሓላፊነት ለመወጣት ሲባል ማዕከላዊው መንግሥት በእርግጥ መሥሪያ ቤት ያስፈልገዋል፡፡ ይህ መሥሪያ ቤት የሚቀመጥበት ቦታ እንጂ የራሱ ከተማ ሊኖረው አይገባም ይላሉ፡፡ አንዳንድ አገሮች ይኼንኑ ተከትለዋል፡፡
የፌዴራል ሥርዓት የሚከተሉ አገሮች ዋና ከተሞቻቸውን ከሦስቱ በአንዱ መንገድ ማዋቀራቸው የተለመደ ነው፡፡ አንደኛው፣ ዋና ከተማው ከክልል ጋር በዕሪናነት እንዲቋቋም በማድረግ እኩል ሥልጣን እንዲኖረው በማድረግ ነው፡፡ ሞስኮ፣ በርሊን፣ ቪየና እና ብራሰልስ በዚህ መልኩ የተቋቋሙ በመሆናቸው ለፌዴራሉ መንግሥት ተጠሪነት የለባቸውም፡፡ በሽግግር ወቅቱ ጊዜ፣ አዲስ አበባም፣ ክልል አሥራ አራት ተብላ የክልልነት ደረጃ ነበራት፡፡
ሁለተኛው መንገድ ደግሞ፣ የፌዴራሉ መንግሥት መቀመጫ በአንድ ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ክልሎች ውስጥ ሆኖ የሚቋቋምበት ሥርዓት ነው፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት የሚያስተዳድረው መሬት ወይም ግዛት የለም፡፡ ደቡብ አፍሪካ፣ ሲውዘርላንድና ካናዳ ይኼንን ዓይነት አካሄድ መርጠዋል፡፡
ሦስተኛው በፌዴራሉ መንግሥት ሥር የሚገኝ ከተማና ለዚህም የሚሆን የተለየ ግዛት በመከለል የሚቋቋሙ ከተሞች ናቸው፡፡ የከተሞቹም ተጠሪነት ለፌዴራሉ መንግሥት ይሆናል፡፡ በርካታ አገሮች ዋና ከተሞቻቸውን በዚህ መንገድ ነው ያቋቋሙት፡፡ አዲስ አበባም ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ ክልልነቷ ቀርቶ የፌዴራል ከተማ (Federal District) ሆናለች፡፡
የፌዴራል ከተሞች ከሌሎች ክልሎች (የፌደሬሽኑ አባላት) የሚለዩባቸው የአስተዳደር ጠባይ አሏቸው፡፡ በጥቅል ሲታዩ በፌዴራል መንግሥቱ ውስጥ የሚኖራቸው ውክልናም ሆነ በአስተዳደሩ ውስጥ ተሳትፎ የተቀነሰ ነው፡፡ ይህ መሆኑ የሚያስነሳቸው ጥይቄዎች ይኖራል፡፡ የመጀመሪያ ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አንጻር ሲታይ እኩል መብትና ሥልጣን አለመኖር፣ አገሪቱን ከመምራትና ከማስተዳደር አኳያም አግላይ በመሆኑ ለእኩልነት መብት ተቃራኒ ነው የሚሉ አሉ፡፡
በዜጎችም መካከል የሚከሰት ልዩነት አለ፡፡ በእንዲህ ዓይነት ከተማ የሚኖሩና የክልል ኗሪዎች የተለያየ መብት ይኖራቸዋል ማለት ነው፡፡ ከፌዴራላዊ ሥርዓት መርሖች ጋርም አብሮ አይሔድም፡፡ ምክንያቱም በማዕከላዊው መንግሥት የሚኖራቸው ተሳትፎና ውክልና የተገደበ ነውና፡፡
ይሁን እንጂ፣ በከተማው ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ደግሞ በአገሪቱ በሌላው ክፍል ከሚኖሩት የበለጠ በብዙ ጉዳዮች ላይ የበለጠ ተጠቃሚ ስለሚሆኑ እንደማካካሻም ሊቆጠር ይገባዋል የሚልም መከራከሪያ አለ፡፡
እነዚህ ከተሞች እንደሌሎች ክልሎች ሉዓላዊነት የላቸውም፡፡ የከተማው አስተዳደር ተጠሪነቱ ለፌደራሉ መንግሥት ነው፡፡ የከተማው ባልተቤትነትም፣ በተለይ ደግሞ መሬት የግል በሆነባቸው አገሮች፣ የፌደራሉ መንግሥት ነው፡፡ ሕዝቡም የተገደበ ራሱን በራስ የማስተዳደር ሥልጣን አላው፤ አስተዳደሪው የፌዴራሉ መንግሥት ስለሚሆን፡፡ በዝርዝር ሲታዩ እነዚህ ጉዳዮች በራሳቸው እንደ የአገሮቹ ሁኔታ ይለያያሉ፡፡ የሚያመሳስላቸው ቢኖሩም የሚያለያያቸው ብዙ ነው ለማለት ነው፡፡
በሕገ መንግሥቱ ማብራሪያ ላይ ስለአንቀጽ 49 ወይም ስለ አዲስ አበባ ርዕሰ ከተማነት የሚከተለውን ይላል፡፡ ‹‹አዲስ አበባ የውጭ አገር መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች መናኸሪያ ከተማ የአገሪቱ ማዕከል በመሆኗ እንደ አንድ ክልል መታየቷ ቀርቶ የተለየ ቦታ እንዲኖራት ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት በሌላ ሕግ በዝርዝር የሚወሰን ራስን በራስ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ተሰጥቷታል፡፡ አዲስ አበባ ካላት የተለየ ይዘትና ባሕርይ የተነሳ ተጠሪነቷ ለፌደራሉ መንግሥት ነው፤›› ይላል፡፡
ለአዲስ አበባ የተመረጠው፣ የክልል ደረጃም ሳይኖራት በሌላ ክልል ውስጥም እንዳትሆን በማድረግ፣ እንዲሁም የነዋሪዎቹን መብት ከጠቅላላው ብሔራዊ ጥቅም ጋር ለማስታረቅ በማሰብ የተመረጠ ይመስላል፡፡ ስለሆነም፣ በትልቅነቱና ክልል መሆን ይገባት ስለነበር ሕዝቡ ራሱን እንዲያስተዳድር፤ ነገር ግን የከተማው መስተዳደር የመጨረሻው ተጠሪነቱ ለማዕከላዊ መንግሥት እንዲሆን ተደርጓል፡፡
የፌደራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተለያዩ ጊዜያት የተሻሻሉ ‘ቻርተሮች’ አውጥቷል፡፡ የከተማው ነዋሪዎች በምን መንገድ ራሳቸውን እንደሚያስተዳድሩም አስቀምጧል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ አዋጅ ቁጥር 87/1989 ነው፡፡ በዚህ አዋጅ መሠረት የከተማ መስተዳድሩ ያወጣቸው ደንቦች፣ መመሪያዎችና ውሳኔዎች አገራዊ የሚጎዱ ከሆነ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊታገዱና ሊሻሩ ይችላሉ፡፡ የከተማው ምክር ቤት ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለመረጠው ሕዝብ ነው፡፡ ምክር ቤቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ሊበትነው ይችላል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ ለከተማው ምክር ቤትና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪነት አለበት፡፡
ከዚህ ቀጥሎ የወጣው አዋጅ ቁጥር 311/1995 ነው፡፡ በዚህ ቻርተር መሠረት የከተማዋን ሁኔታና አስፈላጊነት ከቀድሞው አዋጅ ላይ ባልነበረ መልኩ፣ የፌዴራሉ መንግሥት ርዕሰ ከተማና አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት መቀመጫ በመሆኗ፣ የከተማው ነዋሪ ራስን በራስ ማስተዳደር መብት ለማስጠበቅ፣ የአገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጥንቅር መገለጫ ለማድረግ፣ የሚሉት ግቦች ተጨመሩ፡፡ ከዚህ አዋጅ በኋላም በወጡት አዋጆች ላይ አልተቀየረም፡፡
አዋጁም እነዚህን ግቦች ለማሳካት የከተማ መስተዳድሩ ላይ በርካታ ግዴታዎችን ያስቀምጣል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ከተማዋ የፌደራሉ መንግሥት ርዕሰ ከተማነቷንና የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀማጫ ሚናነቷን ማሳደግ እንዳለባት ይደነግጋል፡፡ የከተማው መስተዳድር አዲስ አበባ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በእኩልነት የሚኖሩባትና ባህላቸውም የሚንጸባረቅበት ማድረግ እንዳለበት ጭምር ይገልጻል፡፡ አስተዳደሩ፣ ከተማውን አገሪቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ማዕከል የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡
እነዚህ በዋናነት ከተማዋ ለአገሪቱ በጥቅሉ እንድትሠጥ የሚጠበቅባት ግዴታዎች ናቸው፡፡ ምናልባትም ዋና ከተማ በመሆኗ ኗሪዎቹ ከሚያገኙት የተለያዩ ዕድሎችና ጥቅሞች አንጻር በማካካሻነት እንዲያገለግል የተጣለባቸው ግዴታ ይመስላል፡፡
ራስን ከማስተዳደር አንጻር ደግሞ ነዋሪው በየደረጃው የሚገኙ የከተማውን ምክር ቤቶች ይመርጣል፡፡ የከተማው የምክር ቤቱ አባላትም ተጠያቂነታቸው ለሕገ መንግሥቱ፣ ለቻርተሩ፣ ለሕሊናቸውና ለመረጣቸው ሕዝብ ነው፡፡ ከንቲባውና ምክትሉ ከምክር ቤቱ ይመረጣሉ፡፡ ምክር ቤቱ ይሾማቸዋል፡፡ ምክር ቤቱ እንደተቋም ለፌዴራሉ መንግሥትና ለመረጠው ሕዝብ ሆነ፡፡ የሚበተነውም በተወካዮች ምክር ቤት ወይም በራሱ ሆነ፡፡ ከንቲባው ሪፖርት ለፌዴራል ጉዳይ ያደርጋል፡፡ የገንዘብ ድጋፍ ከፌዴራል መንግሥት መጠየቅ ይችላል፡፡ በፌዴራሉ መንግሥት በኩል በራሱ አፈላልጎ ይበደርለታል፡፡
የተወሰኑ ጉዳዮችን በተመለከተ የአዲስ አበባን ሁኔታ ከሌሎች የፌዴራል ከተሞች አንጻር በንጽጽር እንመልከተው፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት፣ ፓርላማ፣ ከከተማው ምክር ቤት የበላይ ነው፡፡ የከተማው ምክር ቤት የሚያወጣቸውን ሕጎችም ሊሽራቸው ይችላል፡፡ እንደሌሎች በርካታ የፌዴራል ከተሞች ሁሉ አዲስ አበባም በጀቷን በራሷ ታጸድቃለች፤ የሜክሲኮ ሲቲ ግን በፌዴራሉ ፓርላማ መጽደቅ አለበት፡፡ ብዙዎቹ የራሳቸውን መንግሥታቸውን ለመምረጥ ዜጎች ድምጽ ይሰጣሉ፤ የዋሽንግተን ዲሲን ግን አይመለከትም፡፡ የተወሰኑ ከተሞች (ለምሳሌ ካንቤራ እና ብራዚሊያ) በቅርብ ቢጀመሩም በፌዴራሉ ምክር ቤቶች የከተማው ነዋሪዎች ወኪሎች አሏቸው፡፡ አዲስ አበባ ግን ለፌደሬሽን ምክር ቤት ወኪል መርጣ አትልክም፡፡
አንዳንድ የፌዴራል ከተሞች ፍርድ ቤት፣ ፖሊስና ሌሎች የፍትሕ ተቋማት በራሳቸው የላቸውም፡፡ አዲስ አበባ ውስን በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሥልጣን ያላቸው የከተማ ነክና ማኅበራዊ ፍርድ ቤቶች እንዲሁም ዓቃቤ ሕግና ፖሊስ አላት፡፡
ይሁን እንጂ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተጠሪነቱ ለፌዴራል ፖሊስ ነው፡፡ አደረጃጀቱን፣ አሠራሩን፣ ሥልጣናን፣ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን የስታንዳርዳይዜሽኖችን አቅጣጫዎችን የሚወሰነው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ነው፡፡ የከተማው መስተዳድር በጀትና ዕቅድ ማጽደቅ፣ የዕለት ተግባር ስምሪትን ይከታተላል፡፡ የከተማ መስተዳድሩን ተቋማትና ባለሥልጣን ይጠብቃል፡፡ የከተማውን ጥቅም ያስጠብቃል፡፡ ኮሚሽነሩን ከንቲባው አይሾምም፡፡ ከኮሚሽኑ በታች የሚሾሙት ላይ ከኮሚሽነሩ ጋር ይመካከራል፡፡ በጀቱ በከተማ መስተዳድሩ ይሸፈናል፡፡ ሕግ የሚያወጣለትም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው፡፡ ኮሚሽነሩና ምክትሉም በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር በኩል ይሾማል፡፡ የፌዴራልና ዓለም አቀፍ ተቋማትን የመጠበቅ ኃላፊነት ግን የፌዴራል ፖሊስ ነው፡፡
እነዚህ ከላይ የተገለጹት ራስን በራስ ከማስተዳደር አንጻር የከተማው ነዋሪ ያሉትን መብቶች ለማስረዳት የቀረቡ ምሳሌዎች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ቀድማ የነበረችና የአስተዳደር ለውጥ ያደረገች እንጂ እንደ እነአሜሪካ፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ ቀድመው በቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ አገሮች ተሰባስበው የተመሠረተች አይደለችም፡፡ አስቀድሞ ለመቶ ዓመታት ገደማ አዲስ አበባ የማዕከላዊ መንግሥቱ መቀመጫ ነበረች፡፡ ከደርግ መንግሥት መውደቅ በኋላም በርዕሰ ከተማነት ቀጥላለች፡፡ የአሁኑ ሕገ መንግሥት ሲጸድቅም ዋና ከተማ መሆን የለባትም በሚል የተነሳ ክርክርም አልነበረም፡፡ የተነሳው ክርክር አንድ ብቻ ነበር፡፡ ይኸውም የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በከተማዋ ላይ ልዩ ጥቅም እንዲኖረው የቀረበው ሐሳብ ላይ ነው፡፡
እንደ ካንቤራ፣ ብራዚሊያ በርሊንና ብራሰልስ (በተለይ የአውሮፓ ሕብረት መቀመጫነቷ) የፌዴራሉ መንግሥት መቀመጫ በመሆኗ ብቻ ከፌዴራሉ መንግሥት ተለይቶ የታወቀ የገንዘብ ድጋፍ/ክፍያ አታገኝም፡፡ ነገር ግን ከላይ እንደተገለጸው ለማዕከላዊ መንግሥት ማድረግ ያለባት ግዴታዎች አሉ፡፡ ካናዳና ቤልጂየም ዋና ከተሞቻቸው በንብረት ላይ ለሚጣለው የከተማ የንብረት ግብር ካሳ ይከፍላሉ፡፡ አዲስ አበባ ግን አታስከፍለም፡፡
አዲስ አበባ ለከተማው መሥተዳድር ተቋማት መገንቢያና ለባለሥልጣናቷ የመኖሪያ ቤት መገንቢያ በተጨማሪ ለፌዴራል መንግሥቱ፣ ለኦሮሚያ ክልል እንዲሁም ለዓለም አቀፍ ተቋማትም መሬቷን ታቀርባለች፡፡ መሬት የመንግሥት ቢሆንም ሌሎች ክልሎች ግን ይኼ ሁሉ ግዴታ የለባቸውም፡፡ ራስን ማስተዳደር ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችንም መጨመሩ ግን ግልጽ ነው፡፡
አዲስ አበባ በዋናነት የምትተዳረው ነዋሪዎቿ በራሳቸው ባቋቋሙት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሳይሆን አራቱ የክልል ፓርቲዎች በፈጠሩት ግንባር (ኢሕአዴግ) በመሆኑ ከክልል የሚመጡ ከተማዋም የማታውቃቸው እነሱም የማያውቋት ሹመኞች መመራቷን እንደቀጠለች ነው፡፡ ክልሎች ግን በዚህ መንገድ አይመሩም፡፡ ከ1995 ዓ.ም. በኋላ ከተማውን እንደከተማ መምራት እንደነበረበት ፓርቲው አምኖ፣ መተግበር መጀመሩን ፓርቲው በራሱ ልሳን እንዲሁም አቶ በረከት ስምዖንም በመጽሐፋቸው ገልጸው ነበር፡፡ ራስን በራስ ማስተዳደር ግን በከተማው ነዋሪዎች መተዳደርንም ይጨምራል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ያልተሟሉ ነገሮችን መዘርዘር ይቻላል፡፡
ለማጠቃለል ያህል፣ አዲስ አበባ ርዕሰ ከተማ ስትሆን ወይም እንደሆነች ወዲያኑ ሥርዓት መያዝ የነበረባቸው በርካታ ጉዳዮች ነበሩ፡፡ ይሁን አንጂ በፓርቲ ውሳኔ፣ መደበኛ ባልሆነ ግንኙነት የተፈጸሙ በርካታ ጉዳዮች ግን አሉ፡፡ በዚሁ አካሄድ እየቀጠሉም ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን እንዳለው በሕገ መንግሥቱ ቢገለጽም በርካታ ጎዶሎዎቹ ገና አልተሟሉም፡፡
አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡