መላኩ ደምሴ ብሩህ ይሁንበላይ
ዶ/ር አረጋ ይርዳው፣ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰርና የሚድሮክ ጎልድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ
ዶ/ር አረጋ ይርዳው ላለፉት 18 ዓመታት የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰርና የሚድሮክ ጎልድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው እየሠሩ ነው፡፡ ጎንደር ተወልደው ወልዲያ አድገው እዚያው የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ፣ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኢንጂነሪንግ የትምህርት መስክ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአሥር ዓመታት እንደሠሩ ይናገራሉ፡፡ በስኮላርሽፕ ወደ አሜሪካ ከሄዱ በኋላ እዚያ ለሃያ ዓመታት ቆይተዋል፡፡ በአሜሪካ ቆይታቸውም ሁለት ፒኤችዲ ዲግሪዎች ማግኘታቸውን ይናገራሉ፡፡ ሆኖሉሉ ሃዋይ ከሚገኘው ፓስፊክ ዌስተርን ዩኒቨርሲቲና ከፊልዲንግ ግራጁዌት ዩኒቨርሲቲ ማለት ነው፡፡ በሙያቸው መሐንዲስ የሆኑት ዶ/ር አረጋ በአንድ በኩል እየተማሩ በሌላ በኩል እየሠሩ ነው ሁለተኛ ፒኤችዲ ዲግሪያቸውን ማግኘታቸውን የሚያስረዱት፡፡ ዘጠኝ ልጆችና አሥራ ሁለት የልጅ ልጆች አሏቸው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደወጡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በሜካኒካል ኢንጂነርነት ሠርተዋል፡፡ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ደግሞ እንግሊዝ አገር አግኝተዋል፡፡ ሰሞኑን የሚድሮክ ኢትዮጵያ ባለቤት ሼክ መሐመድ አል አሙዲና ቤተሰቦቻቸው በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች በተከሰተው ድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ዕርዳታ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሥር የሚገኘው ኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪም በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የእንስሳት መኖ በዕርዳታ እያቀረበ ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳይና የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕን አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ በተመለከተ መላኩ ደምሴና ብሩህ ይሁንበላይ ከዶ/ር አረጋ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ ሌላ መሥሪያ ቤት ተቀጥረው ነበር? ወይስ እዚህ ነው ሥራ የጀመሩት?
ዶ/ር አረጋ፡- አልሠራሁም፡፡ አሜሪካ አገር እሠራ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ነበርኩ፡፡ ከአየር መንገድ አሜሪካ ሄድኩኝ፡፡ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ገባሁ፡፡ ከዚያ የኤሮ ስፔስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ገባሁ፡፡ እዚያ እያለሁ ሼክ መሐመድ ዕርዳኝ ሲሉኝ ያንን አቋርጬ ነው የመጣሁት፡፡
ሪፖርተር፡- መቼ ነው ወደዚህ የመጡት?
ዶ/ር አረጋ፡- እዚህ የመጣሁት እ.ኤ.አ. በ1999 ይመስለኛል፡፡ ከዚያ በፊት ለሁለት ዓመት ያህል ሳጠና ነው የቆየሁት፡፡ ሚድሮክንና አገሩን አጥንቼ ነው የተመለስኩት፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ወደዚህ የመጣሁት፡፡ እ.ኤ.አ. በ2000 እዚህ ሥራ ጀምሬያለሁ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን እዚህ ነው እየሠራሁ ያለሁት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሌላ ሥራ አልሠራሁም፡፡
ሪፖርተር፡- ከአሜሪካ ከተመለሱ በኋላ ሼክ አል አሙዲ ድርጅት ውስጥ የነበረዎ ኃላፊነትስ?
ዶ/ር አረጋ፡- ከተመለስኩ በኋላ የአምስት ኩባንያዎች ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆኜ ነው ሥራ የጀመርኩት ኩባንያዎቹ እያደጉ፣ እያደጉ አሁን 25 ሆነዋል፡፡ እንደመጣሁ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነው የሆንኩት፡፡ ይኼ ነው ሥራዬ፡፡
ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ ሼክ አል አሙዲ በኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ውስጥ በተፈጠረው ድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ዕርዳታ ማድረጋቸው ተሰምቷል፡፡ ዕርዳታው ምንድነው? ስለዚህ ጉዳይ ትንሽ ያብራሩልን?
ዶ/ር አረጋ፡- ሼክ መሐመድ ሰሞኑን ከድርቁ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ዕርዳታ እያደረጉ ነው፡፡ በዚህም የደርባ ትራንስፖርትን በመጠቀም የኤልፎራና የአግሪሴፍት ምርቶችን አንድ ላይ በማጣመር በኦሮሚያ በደረሰው ድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ዕርዳታ አድርገዋል፡፡ ሦስት መቶ ሚሊዮን ብር አውጥተን አልፋ አልፋ የሚባል ምርት ለከብቶች እያቀረብን ነው፡፡ መቂና ሻሎ አካባቢ የሚመረት የከብቶች መኖ ነው፡፡ ይህ ዕርዳታ በኦሮሚያ ብቻ ሳይወሰን በሶማሌ ክልልም እየቀረበ ነው፡፡ ዕርዳታው አሁንም ቀጥሏል፡፡
ሪፖርተር፡- የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ከአምስት ኩባንያዎች ተነስቶ በአሁኑ ወቅት 25 ኩባንያዎችን የሚመራ ድርጅት ነው፡፡ እንዴት ነው የተቋቋመው? ኩባንያ ሁኖ ሲሠራ በሕግ የተቋቋመ ነው? ወይስ አስተባባሪ ነው? ምንድነው?
ዶ/ር አረጋ፡- በአሁኑ ጊዜ ካልተሳሳትኩ ሼክ መሐመድ ወደ 74 ድርጅቶች ያሏቸው ይመስለኛል፡፡ እዚህ እንደመጣሁ ጥናት በማድረግ ሚድሮክን አንድ ላይ ለማድረግ ሠርቻለሁ፡፡ እዚህ መጥቼ 70 ቀናት ስቆይ ይህንን ነበር የሠራሁት፡፡ ከዚያ ስመለስ የነበረው ዓላማም በማንኛውም ጉዳይ በሆልዲንግ ኩባንያ አንድ ላይ አድርገን እናቋቁም የሚል ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ እንደሚታወቀው የሆልዲንግ ኩባንያ ሕግ አልወጣም፡፡ አሁንም ወጥቶ ወደ ትግበራ የገባ አይመስለኝም፡፡ እኛ ያደረግነው ነገር ቢኖር እንደመጣሁ ሚድሮክ ጎልድ፣ የኮምቦልቻ ኮስፒና ሁዳን ጨምሮ አምስት ያህል ኩባንያዎችን አንድ ላይ ማድረግ ነበር፡፡ ይህ የፕሮጀክት ለውጥ ነበር፡፡ ከዚያ አንድ ላይ አድርጌ ማስተባበርና መምራት ጀመርኩ፡፡ አንድ እንብርት የሆነ ኩባንያ እውነቱን ለመናገር የለም፡፡ ስለዚህ ለሁሉም ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንደመሆን አድርገህ ብትወስደው እያንዳንዱ አርቲክል ላይ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሚል አለ፡፡ እዚያ የእኔ ስም አለ፡፡ የራሱ የሆነ ዋና ሥራ አስኪያጅ አለው፡፡ ስለዚህ በዚያ መልክ ነው የተቋቋመው፡፡ ሕጉ ስላልፈቀደልን፡፡ ከዚያ እያልን፣ እያልን መጣንና ኩባንያዎቹ እያደጉ ሲሄዱ ከ25 ኩባንያዎች ውስጥ ሚድሮክ ሲኢኦ የሚል ስም ሰጥተን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አደረግነው፡፡ የሚድሮክ ሲኢኦ ፒኤልሲ የሚባለው የማኔጅመንት ሰርቪስ ይሰጣል፡፡ ለ24ቱ ኩባንያዎች ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አሁን 24ቱ ኩባንያዎች ከሚድሮክ ሲኢኦ ጋር የማኔጅመንት ስምምነት አላቸው፡፡ ስለዚህ የማኔጅመንት ሰርቪስ እየሰጠን 24ቱን በዚያ መልክ ነው የያዝነው፡፡ ሆልዲንግ ካምፓኒ በሚሆኑበት ጊዜ እንግዲህ ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንዲጓዙ በዚህ መልኩ ነው ያደረግነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከስያሜው እንደምናየው ‹‹ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ›› ይላል፡፡ ቴክኖሎጂ ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች ይታያሉ፡፡ እንደገና ደግሞ የአገልግሎት ዘርፍ የሆኑ አሉ፡፡ እነዚህን እንዴት ነው አንድ አድርጋችሁ ኅብረት የምትፈጥሩት?
ዶ/ር አረጋ፡- ኅብረቱን እኔና አለቃዬ ቁጭ አልንና እስኪ ቴክኖሎጂና ቴክኖሎጂ ነክ የሆኑ ኩባንያዎች አንድ ላይ ሰብሰብ እናድርጋቸውና እንምራቸው የሚል ነገር ወሰንን፡፡ ስለዚህ ኮስፒን ወሰድን፣ ሚድሮክ ጎልድን ወሰድን፣ ሁዳን ወሰድን፡፡ እነዚህ እነዚህን አድርገን መጀመሪያ አምስቱን ወሰድን፡፡ ከዚያ በኋላ ቀስ እያልን ስንሄድ ቴክኖሎጂ የሚለው ተለመደና ቃሉ ቀጠለ፡፡ ሥራችን ግን እየሰፋ ሄደ፡፡ ለምሳሌ ሆም ዴፖ የሚባል የሰርቪስ ኩባንያ አለን፡፡ ሆም ዴፖን የፈጠርነው የቀለም ፋብሪካው ኤምቢአይ የሚባለው፣ የቆርቆሮ ፋብሪካው ኮስፒ የሚባለው እነዚህ የሚያመርቱዋቸውን ምርቶች የኮንስትራክሽን ምርቶች መሸጫ እንዲሆን ነው የከፈትነው፡፡ ኤልፎራን ብትወስደው ያመርታል ግን ችርቻሮ ውስጥ የለበትም፡፡ ስለዚህ የእሱን ምርት ለመቸርቸር ካስፈለገ ብለን ደግሞ ኩዊንስ የሚባል ሱፐር ማርኬት ከፈትን፡፡ ስለዚህ እንደዚህ እያለ ነገሮች እየሰፉ መጡና ቴክኖሎጂ የሚለው ቃል ተለምዶ ልንርቀው አልቻልንም፡፡ ለምሳሌ አየር መንገድ አለን ቴክኒካል ነው፡፡ እና በዚያ መልኩ ነው ታሪኩ የመጣው፡፡ ስለዚህ ሰርቪስ የሚሰጡ አንድ ሁለት አሉ፡፡ ለምሳሌ ኩዊንስ ሱፐር ማርኬት፣ ሆም ዴፖ እነዚህ ሰርቪስ የሚሰጡ ናቸው፡፡ ሒደቱ ግን አሁን ባልኩት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በአምስት ኩባንያዎች ተጀምሮ ወደ 25 ሲደረስ በካፒታልስ ምን ያህል ነው ያደገው? ሲጀምር በዚህን ያህል ካፒታል ነው የተጀመው፣ አሁን ደግሞ እዚህ ደረጃ ደርሷል ማለት ይቻላል?
ዶ/ር አረጋ፡- እንደሱ ብናደርግ ስህተት ውስጥ እንገባለን፡፡ 25 ኩባንያዎችን አንድ ላይ አድርገህ ካፒታል የምታደርግበት መንገድም የለም፡፡ እያንዳንዳቸው የራሳቸው ፒኤልሲ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ በጠቅላላው እነዚህ በዓመት ምን ያህል ይሸጣሉ ብትለኝ ልነግርህ እንችላለሁ፡፡ አምስት ሚሊዮንና አምስት ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ዓመታዊ ሽያጭ አለን፡፡ ስለዚህ እያንዳንዳቸው ኩባንያዎች የራሳቸው አቅም አላቸው፡፡ የራሳቸው ካፒታል አላቸው፡፡ እያንዳንዳቸው ኃላፊ አላቸው፡፡ አንዳንዶቹ ትርፋማ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ያላተረፉ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ አልፎ አልፎ ኪሳራ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው ሚድሮክ ጎልድ ነው፡፡ እንደመጣሁ የመጀመርያዎቹ አራት ዓመታት አካባቢ ኪሳራ ውስጥ ነው የነበረው፡፡ ከዚያ በኋላ ነው እሱም ትርፋማ እየሆነ የመጣው፡፡ እስካሁን ድረስ አትራፊ ኩባንያ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- እዚህ አገር ውስጥ ያለው የግል ሴክተር ብዙ እንቅፋቶች ያጋጥሙታል፡፡ የግሉ ሴክተር እያንሰራራ ከመጣበት ጀምሮ እርስዎ ከሕዝቡና ከመንግሥት ጋር ሆነው ብዙ እንቅፋቶችን ያዩ ይመስላሉ፡፡ ስለዚህ በዚህ ሒደት ውስጥ ያሉ መሰናክሎች ምንድናቸው ይላሉ? በእነዚህ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ያጋጠሙ ችግሮች ምንድን ነበሩ?
ዶ/ር አረጋ፡- እንደ ኩባንያ ኃላፊነቴና እዚህ አገር እንደ መሥራቴ ዴሞክራሲውም፣ አሠራሩም የሚያጋጥመው ችግር ይኖራል፡፡ መልኩን ይለውጣል በየዓመቱ፡፡ ስለዚህ ቀደም ብሎ መምጣትም ጥሩ ነገርም አለው፡፡ መጥፎ ነገርም አለው፡፡ ጥሩዎቹ ነገሮች በዚያን ጊዜ ብዙ ውድድር የለብህም፡፡ አሁን ያለው ፈተና ለየት ያለ ነው፡፡ ሁለተኛና ትልቁ ፈተና ለእኔ የነበረው ድርጅቶቹ የነበራቸው ባህል ነው፡፡ 25ቱ ኩባንያዎች አንዳንዶቹ ፍላጎት የፈጠራቸው ናቸው፡፡ ሆም ዴፖን ፍላጎት ነው የፈጠረው፡፡ ትራንስ ናሽናል ኤርዌይስ (ቲኤንኤ) የሚባለው አየር መንገዳችን አውሮፕላኖቹ እዚህ ዝም ብለው ቁጭ ብለው ስለነበር፣ ለምን ቁጭ ይላሉ ተብሎ ሥራ ይሻላል በሚል የተፈጠረ ነው፡፡ እንደነ ዋንዛ የመሳሰሉት ደግሞ ከስረው ተዘግተው ችግር በገቡበት ጊዜ ሼክ መሐመድ መዘጋት የለባቸውም ስለሚሉ፣ እነሱን ደግሞ አምጥተን ጠጋግነን ችግሮች ሲገጥሙ ወደ ማኔጅመንት የማስገባት ሒደት ነው የነበረው፡፡ ትልቁ ችግር አሠራሩ የተለያየ በመሆኑ፣ ጉራማይሌ በመሆኑ፣ አንደኛው ኩባንያ የራሱ ጠባይ ነው ያለው፡፡ ሌላኛውም እንዲሁ፡፡ ስለዚህ ወጥና መሠረታዊ የሆኑ ፖሊሲዎችን ያለማውጣት፣ ፖሊሲዎችን ካወጣን በኋላ ደግሞ ፖሊሲዎቹ እንደ ወንዝ ሆነው፣ ሥርዓት ሆነው ሰዎች እንዲዋኙባቸው የማድረግ ባህል ችግር ነበር፡፡ ይህ አሁንም ችግር ነው፡፡ ወደ መጀመርያው ላይ የነበረው ድርጅት በተቻለ መጠን ድርጅት እንዲመስል የምናደርገው ጥረት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ቀስ እያልክ ስትሄድ ውድድር አለ፡፡ ምርት አለ፡፡ ደንበኛ አለ፡፡ እነዚህ ደግሞ እየከበዱ፣ እየከበዱ መጡና አሁን ደግሞ ፈተናው በዛ ያለ ነው፡፡ ምክንያቱም አገር እያደገ ነው፡፡ የቀለም ፋብሪካ ድል ቀለም የተለመደ ነው፡፡ ዋንዛ የተለመደ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሌሎች ድርጅቶች እየመጡ ነው፡፡ እነዚህ ሲመጡ ውድድር ውስጥ ትገባለህ፡፡ ይህ ፈተና ነው፡፡ አዲስ የመጣው ትኩስ ነው፡፡ የቆየው ትንሽ እንደ ጭነት መኪና ገፋ ገፋ ማድረግ ይሻል፡፡ የእኛው ትንሽ ሮጥ ይላል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ለየት ያሉ ፈተናዎች ናቸው፡፡ ችግሮችን እንኳን ደህና መጣችሁ ማለት የሚገባን ነውና ብዙ ሰዎችን ማስተማርና ማሠልጠን ነበረብን፡፡
ከምታዩዋቸው ማኔጀሮች በብዛት እኛ ያስተማርናቸው ናቸው፡፡ እኛው ጋ የማኔጅመንት ዕውቀት አለን፡፡ በእዚህ አገር ማኔጄር መሆን ትችላለህ፡፡ መሪ መሆን ነው ችግሩ፡፡ የአመራር ነገሮች ከበድ ይላሉ፡፡ ዝም ብለህ ቁንጮ ላይ ቁጭ ብለህ ልሥራ ብትል እዚህ አገር አያሠራህም፡፡ ፒራሚዱን ወደ ላይና ወደ ታች መውጣትና መውረድ አለብህ፡፡ ትልቁ ነገር አንተ ማስተካከል መቻል አለብህ፡፡ ሌላው እሱ ላይ ያለን ትኩረት ነው፡፡ ድርጅቶች ሰው ላይ ያላቸው ዕይታና ተፅዕኖ ደካማ ነው፡፡ በእኔ ድርጅት ሀብቶች አሉ፡፡ ከሀብቶች ትልቁ ደግሞ ሰው ነው፡፡ ለሰው ሐርድዌሩ ቁሳቁስ ነውና ልትገዛው ትችላለህ፡፡ ሶፍትዌሩ ግን ሰው ነው፡፡ እዚህ ላይ ያለን ሞኝነት ግን ብዙ ጊዜ ጎድቶናል፡፡ እኛ ሰው ተኮር ነን ብለን እናምናለን፡፡ የምታሳይበት መንገድ ደግሞ ለሰዎች ያወጣኋቸው ፖሊሲዎች በምን ዓይነት መንገድ ነው? ሠራተኛው የራሴ ቤት እንዲል አድርገኸዋል ወይ? እኛ የሠራተኛ ማኅበር ያቋቋምን ሰዎች ነን፡፡ የሠራተኛው ማኅበር ብቻ አይደለም፣ ሠራተኛው እርስ በራሱ የሚገናኝበት መንገድ አለን፡፡ የቤተሰብ ቀን የምንለው አለን፡፡ በየዓመቱ ቤተሰቡ መጥቶ የምንገናኝበት ሁኔታ አለ፡፡ ስለዚህ ደስተኛ የሆነ ሠራተኛ ውጤታማ ነው የሚል እምነት አለን፡፡ እዚህ ላይ ኃይለኛ የሆነ ትኩረት አለኝ፡፡ በአሁኑ ወቅት 7,000 የሚጠጉ ሠራተኞች አሉን፡፡ ያለኔ ፊርማ የሚባረር አንድም ሰው የለም፡፡ ምክንያቱም ዓላማው ሰው መለዋወጥ ሳይሆን ሰውዬውን ማብቃት ነውና፡፡ በተቻለ መጠን ፖሊሲው አስገድዶን ማድረግ ካልተገደድን በስተቀር፣ ሰው ዝም ብሎ በቀላሉ የምታባርረው መሆን የለበትም የሚል እምነት አለን፡፡ ሰዎች ላይ ያለን ትኩረት ከበድ ያለ ነው፡፡ ሌላው ጉዳይ ሠራተኛው አንድ የሚሆንበትን መንገድ እንፈልጋለን፡፡ በወር አንድ ጊዜ ሁሉም ሠራተኛ ለአንድ ሰዓት ተኩል የፈለገውን ከሃይማኖትና ከፖለቲካ በስተቀር አንስቶ የሚወያይበት ስብሰባ አለን፡፡ ይኼ ጉዳይ ሠራተኛውን ቤተሰብ አድርጎታል ብዬ አስባለሁ፡፡ በተቻለ መጠን ማኔጅመንቱ ታች ያለው ሠራተኛ መልኩንም፣ ፊቱንም፣ ድምፁንም እንዲያውቅ ማድረግ አለበት፡፡ ሠራተኞቼ በሙሉ ያውቁኛል ብዬ አምናለሁ፡፡ እናም እንደዚህ ዓይነት ሰው ተኮር የሆነ ፖሊሲ አለን፡፡ በሌላ በኩል አንጫንም፡፡ የተወሰነ ትርፍ ቢመጣ ቶሎ ብለን ካፒታል ለማሳደግ እንዞራለን፡፡
ሪፖርተር፡- መጀመርያ ሲጠቅሱልን የሚያተርፉ ድርጅቶች አሉ፣ የማያተርፉ አሉ፣ እንዲሁም ኪሳራ የሚያስመዘግቡ አሉ፡፡ እንዴት ነው ታዲያ የሚቀጥሉት?
ዶ/ር አረጋ፡- ለአምስት ዓመታት ኪሳራ ያስመዘገበ ድርጅትን ትዘጋዋለህ፡፡ የአገሪቷ ሕግ ነው፡፡ ስለዚህ ኪሳራ እንዳያስመዘግብ መጣር ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እንደማንኛውም ኩባንያ እኛ ከሌሎች የተለየን አይደለንም፡፡ ምርትን በመለወጥ፣ ጥበብ በመፍጠር፣ የሥራ ዓይነትን በማስፋት ልታቻችለው ትሞክራለህ፡፡ ለምሳሌ እኛ ትረስት የሚባል ኩባንያ አለን፡፡ ትረስት የተቋቋመው ከፍላጎት ነው፡፡ እኔ ኤልፎራ የሚባለውን ትልቅ ኩባንያ ስመለከት በውስጡ ብዙ ጥበቃዎች አሉት፡፡ እነዚህ ጥበቃዎች ከኩባንያው ጋር አብረው በመኖራቸው ጠባቂውና ተጠባቂው አንድ ናቸው፡፡ ስለዚህ እኔ የትረስት ኩባንያን አቋቋምኩ፡፡ መጀመርያ ለእኛ እንዲሆነን፡፡ ቀጥሎ ሙያው እየመጣ ሲሄድ ደግሞ ለሌሎች እንዲሆን በማሰብ፡፡ ይኼንን ኩባንያ ስንጀምረው አንዳንዶች ሚድሮክ ጥበቃ ውስጥ ገባ እያሉ እያወሩ ነበር፡፡ ይህንን የወለደው ችግሩ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ይህንን ኩባንያ ዝም ብዬ ስመለከተው ለማደግ ተቸገረ፡፡ ከዚያም ምናልባት ትረስት ከዚህ ባሻገር ሌላ ሥራስ ቢሠራ ወደሚል ገባን፡፡ ለምሳሌ የጉምሩክ ሥራ እንሠራለን፡፡ ከጂቡቲ የሚገቡና የሚወጡ ዕቃዎችን ለማቀላጠፍ፡፡ ስለዚህ ይኼ ኩባንያ ይህንንም እንዲሠራ ተደረገ፡፡ ሰዎቹ እዚያው ናቸው፡፡ ሰው ስትጨምርላቸው የተሻለ ይሆናሉ፡፡ እንደዚህ እያደረግን አዳዲስ ነገሮችን እየጨመርን ነው የሄድነው፡፡
ኮስፒ ይታወቃል ብዬ አስባለሁ፡፡ ኮምቦልቻ ነው ያለው፡፡ ያመርት የነበረው ቆርቆሮ ነው፡፡ ያመረተውን ቆርጦ መሸጥ ብቻ ነበር ሥራው፡፡ ግን በዚያ ቢቀጥል ኖሮ አሁን ላይኖር ይችል ነበር፡፡ ስለዚህ ያደረግነው ምንድነው? ቆርቆሮ የሚሸጥ ከሆነ ለምንድነው ሚስማር የማያመርተው? ስለዚህ ሽቦ ወደ ማምረት ውስጥ ገባን፡፡ ሽቦ እያቀለጥን ሚስማር ሠራን፡፡ ከዚያ ቀጠለና እኛ’ኮ ወደ ኢንጂነሪነግ መሄድ አለብን በማለት ኮስፒ ደግሞ ጥሩ ነገሮችን እንዲሠራ ፈለግን፡፡ እንደ ነዳጅ ታንከርና የመሳሰሉትን፡፡ ከዚያ ስታዲዮም የሚሠራበት ደረጃ ደረስን፡፡ ትልልቆቹን መጋዘኖች እየሠራቸው ያለው ኮስፒ ነው፡፡ ስለዚህ ኩባንያዎቹ እንዳይወድቁብህ ስትፈልግ ሌላ አዳዲስ ፕሮጀክት ታመጣላቸዋለህ፡፡ በዚህ ሁኔታ እንዲቀጥሉ ታደርጋቸዋለህ፡፡ እውነታው ግን እንኳን 25 ኩባንያ ይዘህ ሦስትም ቢኖርህ አንድ ዓመት ይቀናሃል፣ አንድ ዓመት አይቀናህም፡፡ እናም እንደ ማንኛውም ኩባንያ እንጂ ሁሉም ጥሩ ናቸው ልልህ አልችልም፡፡ ለምሳሌ ቲኤንኤ አየር መንገድ ነው፡፡ ሁለት አውሮፕላኖች አሉት፡፡ ለፓይለቶች በጣም ብዙ ገንዘብ ትከፍላለህ፡፡ የውጭ ፓይለቶች አሉ፡፡ በዶላር ነው የምትከፍላቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ልናበራቸው አልቻልንም፡፡ ምክንያቱም 47 አካባቢ መንገደኞች ነው የሚይዙት፡፡ ያንን ሞልተህ ከአየር መንገድ ጋር ተወዳድረህ ድጎማ ከሚያደርግ ጋር በረህ አትችልም፡፡ ስለዚህ ወደ ሱዳን ወይም ወደ ሌላ አገር ትልካቸዋለህ፡፡ አንዳንድ ጊዜ የቻርተር በረራ ስለሆነ ገንዘብ ልታገኝ ትችላለህ፡፡ አውሮፕላን ግን የጥገና ወጪው በጣም ከፍተኛ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ቲኤንኤ መደበኛ የአገር ውስጥ በረራ ጀምሮ ነበር፡፡ ያኔ ትልቅ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ‘ስኬጁልድ ፍላይት’ ጀመረ ተባለ፡፡ የሆነ ጊዜ አቆማችሁት፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ፖሊሲው ነው? የግል አቪዬሽን ባለሀብቶች ብዙ አይደገፉም ይባላልና እስኪ ስለዚህ ይንገሩን?
ዶ/ር አረጋ፡- መጨረሻ የተባለው ትክክል አይመስለኝም፡፡ እኛን የሚጨቁን ወይም የማይጨቁን ፖሊሲ ያለ አይመስለኝም…
ሪፖርተር፡- ይቅርታ እዚህ ላይ ላቋርጥዎትና ሁልጊዜ ሲቪል አቪዬሽን በሚያዘጋጃቸው ስብሰባዎች ላይ የግል ባለሀብቶች ቅሬታ እያቀረቡ ነው፡፡ ቲኤንኤ አንዱ የችግሩ ሰለባ ነው ወይ ለማለት ነው ጥያቄው፡፡
ዶ/ር አረጋ፡- በጣም ጠንቃቃ መሆን አለባችሁ፡፡ እኛ የምንናገራቸውና የምንሠራቸው ነገሮች ሁሉ አገር መጉዳት የለባቸውም፡፡ ሰው በፈለገው ዓይነት ይጎዳዳ ግን አገር መጎዳት የለባትም፡፡ አየር መንገዳችን ለእኛ ትልቁ ምልክታችን ነው፡፡ ሠርቼበታለሁ፡፡ ቤቴ ነው፡፡ ለብዙ ዓመታት አገልግያለሁ፡፡ ወደ ጄት ዓለም ከቀየሩት ውስጥ አንዱ ነኝ፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ካደጉ ሰዎች ውስጥ አንዱ እኔ ነኝ ብዬ አምናለሁ፡፡ እስካሁን ድረስም ቤቴ ነው፡፡ በንጉሡ ጊዜ የነበረው የአገሪቱ ሕግ ለግል አየር መንገዶች ሃያ መንገደኞችን ብቻ ነበር የሚፈቅደው፡፡ ከዚያ ነው ጉዞው የሚጀምረው፡፡ ስለዚህ የመጀመርያው ያደረግነው ጉዳይ ፖሊሲ ማስለወጥ ነበር፡፡ ያንን ፖሊሲ ለማስለወጥ በትንሹ አሥር ዓመት ፈጅቷል፡፡ ፖሊሲ ማስለወጥ ማለት ከሃያ መንገደኛ ሃምሳ የሆነው የዛሬ ዓመት ገደማ ነው፡፡ 30 እና 40 ዓመታት ፈጅቷል፡፡ ቁጥሩን እንኳን ከፍ ለማድረግ ትግል ነበር፡፡ ከሃያ በላይ መንገደኛ አታደርግም ሲሉን ወንበሮችን አውልቀን ሃያ ብቻ አደረግንና ሥራ ጀመርን፡፡ ምክንያቱም ሃያ ከተባለ ሃያ አደርጋለሁ፡፡ እንደዚያም አድርገን ውጤታማ አልሆንም፡፡ ያውም አውሮፕላኑ ግዙፍ ነው፡፡ ብዙ ነዳጅ ይፈልጋል፡፡ የምትጭነው ሰው ትንሽ ነው፡፡ የእልህ ጉዳይ ሆኖ እንጂ እንደማይሠራ አውቃለሁ፡፡ አልተሳካልንም፡፡ ወደ ቻርተር ወሰድናቸው፡፡ ሕጉ ቀጠለ፡፡ ጭቅጭቁ ቀጠለ፡፡ እያለ እያለ ባለፈው ዓመት 50 ሰው ተፈቀደ፡፡ በዚህ ልክ ደግሞ ካርጎውን ወደ ማሰብ ሄድን፡፡ ቢያንስ ካርጎውን ልቀቁ አልን፡፡ ስለዚህ ነፃ አደረጉት፡፡ በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ቻርተር ነው እንጂ የምትሠሩት ስኬጁልድ የሆነ በረራ የለም ተባለ፡፡ አሁን ደግሞ ይኼንን መጋተር ፈለግን፡፡ ምክንያቱም ይህ ካልሆነ ለሚቀጥለው ማን ይሠራዋል? ስለዚህ እሱ ይፈቀድ ብዬ ደግሞ መበጥበጥ ጀመርኩ፡፡ መጨረሻ ላይ ብዙ ወዲያ ወዲህ ከተባለ በኋላ ተፈቀደ፡፡ የአየር መንገዱ ተፅዕኖ ነው የሚሉን አሉ፡፡ አየር መንገዱ ትልቅ ነው፡፡ እኛ በጣም ትንሽ ነን፡፡ አሁን አስፈቅጃለሁ፡፡ በኪሳራ ቢሆንም መንቀሳቀስ አለብኝ፡፡ ለሦስት ወይም ለአራት ወራት በኪሳራም ቢሆን በእልህ ሞከርን፡፡ ሠራንበት፡፡ ከዚያ አቆምነው፡፡ በወቅቱ ሁሉም ሰው ተገረመ፡፡ እኛ ግን ምን እያደረግን እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ስለዚህ መደበኛ የሆነ በረራ ለሌላ አየር መንገድ እንዲፈቀድ አደረግን፡፡ ይኼ አንድ ለውጥ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚያም ኢትዮጵያ ውስጥ ሔሊኮፕተር መብረር አለበት አልኩ፡፡ ምክንያቱም ሔሊኮፕተር ለአደጋ ጊዜ፣ ለእርሻና ለምንም ነገር አስፈላጊ ነው፡፡ በሠለጠነው ዓለም ፎቅ ሁሉ በሔሊኮፕተር ይገባል፡፡ እሷም አዲስ ሆነችና ችግር ፈጠረች፡፡ እንደምንም እሷንም አስፈቀድን፡፡ አንድ ነው የገዛሁት፣ በረራውን አስፈቀድኩ፡፡ ችግር የገጠማት በቅርብ ጊዜ ነው፡፡ ያለው ችግር እኔ እንደሚገባኝ ይኼ ነው፡፡ አሁን ዩናይትድ ኤር ዌይስን ብትወስዱ ዩናይትድ ኤክስፕረስ የሚባል አለው፡፡ ዩናይትድ ኤክስፕረስ በአገር ውስጥ በረራው ለትልቁ አውሮፕላን መንገደኞችን የሚያቀርብ ነው፡፡ እኔ ተስፋ የማደርገው አንድ ቀን አየር መንገዱ የአገር ውስጥ በረራው ይጠናከርና ለውጦች ይመጣሉ ብዬ ነው፡፡ አሁን እየደጎመው ነው፡፡ የግል ድርጅት ቢገባ ገንዘብ አያገኝም፡፡ ምክንያቱም በድጎማ መሥራት ስለማይቻል፡፡ ወደፊት ኢኮኖሚው እየጠነከረና አገር ቤት ያሉ ሰዎችም ጥሩ ገንዘብ መክፈል ሲጀምሩ፣ አየር መንገዱ የተወሰነ አክሲዮን ውስጥ ገብቶ እንደነዚህ ዓይነት ድርጅቶችን መደጎም አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡
አንዳንድ ጊዜ ትንሽ ዝሆን አለ፣ አንዳንዴ ደግሞ ትልቅ፡፡ ጥያቄያችንም አንድ ዓይነት አይመስለኝም፡፡ እኛ የምንለው ለአገር ውስጥ የሚሆነውን የሔሊኮፕተር አገልግሎት አየር ኃይሉ ይሠራል፡፡ እናም ይኼ ለምንድነው የማይበረታታው? ከኬንያ አንዳንድ ጊዜ ይመጣሉ፡፡ ከቱሪዝሙ ጋር ተያይዞ አንዳንዱ ብር ብሎ ሂዶ ላሊበላ ደርሶ መምጣት ይፈልጋል፡፡ ይኼ ጥሩ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ስለዚህ እነዚህ ስብሰባዎች ሲደረጉ መበረታታት አለብን ነው የሚባለው፡፡ አየር መንገዱን ብትወስደው ብዙ ዕቃዎች ሊያስመጣ ቢፈልግ ማለትም የመለዋወጫ ዕቃዎችና የመሳሰሉትን በራሱ አውሮፕላን ቶሎ ከተፍ ያደርገዋል፡፡ አውሮፕላኑ ቶሎ ተጠግኖ ይሄዳል፡፡ ሌላው የግል አየር መንገድ ይህንን ማድረግ ይቸገራል፡፡ ዶላር የሚያስፈልግህ ከሆነ ግን አውሮፕላኑ ቁጭ ሊል ነው፡፡ ስለዚህ እንደዚህ ዓይነቶቹ መብቶች ለምንድነው ለእኛስ የማይሆኑልን? የአገልግሎቱ ባህሪ አንድ ዓይነት ከሆነ ፈጣን ሊያደርጉት የሚችሉት ለምን አይበረታቱም? የሚለው አንዱ ነው፡፡ ሁለተኛው መደበኛ በረራ አቅም ካለ መፈቀድ አለበት ነው፡፡ ማኅበር አቋቋምን፡፡ አንድ ላይ ድምፃችንን ለማሰማት፡፡ እዚህ ላይ አውሮፕላኖቹ የጥገና መደብ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሲቪል አቪዬሽን የጥገና መደብ ከሌለህ ፈቃድ አይሰጥህም፡፡ ወይም የጥገና ኮንትራት ከአንድ ቦታ ከሌለህ ዝም ብሎ ሊፈቅድልህ አይችልም፡፡ ስለዚህ አየር መንገዱ የጥገና ማዕከሉን ቢያሰፋውና የግሎቹን ማስተናገድ ቢችል የተሻለ አቅም ስላለው ያሳድጋቸዋል፡፡ አሁን እኔ የሔሊኮፕተር በረራ ለመጀመር አንድ ከአፍሪካ አገር ያመጣሁት ፓይለት አለኝ፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊን ደቡብ አፍሪካ ልከን፣ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ አውጥተን አሠልጥነን፣ ላይሰንስ አስደርገን ነው ያመጣነው፡፡ አየር መንገዱ የፓይለት ትምህርት ቤት አለው፡፡ ትምህርት ቤቱ ቢያግዘን በተዘዋዋሪ መንግሥት ቢያግዝ ማለታችን ነው፡፡ ያድጋሉ ከሚለው አኳያ ምናልባት ጫጫታ የምናሰማ ቢሆን ከዚች ቦታ ላይ ለምንድነው ብድግ እንድንል የማይደረገው? የሚለው ይመስለኛል፡፡ አየር መንገዱም ዓለም አቀፍ በረራው እየበዛና እየከበደው ሲሄድ፣ የአገር ውስጥ በረራዎችን ተወት እያደረጋቸው ይሄዳል፣ ወይም ደግሞ አነስተኛ ግምት ይሰጣል የሚል እምነት አለን፡፡ እየበዛ ሲሄድ አንዳንዶቹ አውሮፕላን ማረፊያዎች ደግሞ አውሮፕላኑ ራሱ የሚያርፍባቸው አይደሉም፡፡ ስለዚህ ነገሩ እየተለወጠ ይሄዳል ብዬ አስባለሁ፡፡ ብዙ ስለአቪዬሽን የምናውቅ ሰዎች ይኼ ሒደት በሌላ ዓለም ላይም የተለመደ ነው እንላለን፡፡ አንድ ቀን ግን መንግሥት የአገር ውስጥ በረራው መብዛት አለበት፣ ሔሊኮፕተሮች መብዛት አለባቸው፣ ፈጣን የሆኑ ሔሊኮፕተሮች ለእርሻውና ለሌላው ሥራ ሮጠው ደርሰው መምጣት አለባቸው በሚልበት ጊዜ ዕድሉ ይሰፋል፡፡ አንዳንድ ጊዜም ልናቆም የማንችለውን ሒደት ነው ለማቆም የምንታገለው፡፡ እዚህ ስመጣ አስታውሳለሁ፡፡ ኢንተርኔት ካፌ የሚባለው ተጀመረ ተብሎ መሬት መያዝ ነው ምናምን ሲባል አሁን ያለበት ደረጃ ደርሷል፡፡ ይህ የማይቋረጥ ሒደት ነው፡፡ እዚህ ዓለም እኖራለሁ ካልክ የማያቋርጡ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ አንዳንዱ ሕግ እኮ ከተቻለ ፀሐይን መጋረድ ይፈልጋል፡፡ አየር ማቆም ይፈልጋል፡፡ ይኼም እንደዚያ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ አቪዬሽኑ ያድጋል፡፡ ትናንሽ አየር መንገዶች ሲኖሩ ቴክኒሻኖች ይሠለጥናሉ፡፡ ልክ የመጀመሪያ ደረጃና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አድርግና አስበው፡፡ ታች ያሉት በብዛት ካልመጡ ቀውስ ውስጥ ትገባለህ፡፡ ግን ሌሎችም ቢያሠለጥኑና ወደ ሌላ ቦታ መሄድ ቢጀመር ጥቅም አለው ብዬ አምናለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- እንግዲህ ከኩባንያዎቹ መካከል በግንባር ቀደምትነት ስሙ የሚጠቀሰው ሚድሮክ ጎልድ ነው፡፡ ሚድሮክ ጎልድ አሁን ያለበትን አጠቃላይ ሁኔታ ቢነግሩን?
ዶ/ር አረጋ፡- ጥሩ፡፡ ሚድሮክ ጎልድ አሁን ባለበት ሁኔታ ሁለት በጣም የተጠመደባቸው ሥራዎች አሉ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ለገደንቢ የሚባለው የማዕድን ፈቃድ አለው፡፡ እዚያ ወርቅ ይመረታል፡፡ ሁለተኛው ሳካሮ ብለን የጀመርነው ሁለተኛው ነው፡፡ ፈቃድ አለው ማለት ነው፡፡ ሦስተኛው መተከል የሚባለው ቦታ ላይ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሥር ዓመት ያህል የፍለጋ ሥራ በማከናወንና ወደ ሦስት መቶ ሚሊዮን ብር አውጥተን፣ መጨረሻ ላይ አሁን ሁለተኛ ወራችንን ያዝን መሰለኝ ፈቃድ ካገኘን፡፡ እነዚህ ዋናዎቹ ሥራዎች ናቸው፡፡ በተጨማሪ ሚድሮክ ጎልድ የፍለጋ ሥራውን አላቆመም፡፡ ለገደንቢ አካባቢ የፍለጋ ሥራ እናከናውናለን፡፡ መተከል አካባቢ እንሠራለን፡፡ መንታ ውኃ የሚባል በአማራ ክልል ውስጥ የፍለጋ ሥራ እንሠራለን፡፡ ስለዚህ የፍለጋ ሥራችንን ባናከናውን ኖሮ ለገንደንቢ የምንለው ሲያልቅ ይዘጋ ነበር፡፡ ስለዚህ የፍለጋ ሥራ ለስድስት ለሰባት ዓመታት ስለሠራን ሳካሮ የሚባለውን አገኘን፡፡ ስለዚህ ሚድሮክ ጎልድን አሁን ካለበት ሁኔታ የማስፋፋት ሥራ ላይ ለማዋል ደፍ፣ ደፍ እያልን ነው፡፡ በሌላ በኩል የማዕድን ሥራችንን እያከናወንን ነው፡፡ በተጨማሪም መተከል አካባቢም ሆነ እዚህኛው ተጨማሪ ፈቃድ ወስደን የፍለጋ ሥራ ለማከናወን እየተዘጋጀን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ኢንቨስትመንቱና ማስፋፊያውስ ምን ይመስላል?
ዶ/ር አረጋ፡- አሁን ያልኩህ ነው፡፡ ፍለጋ ባናደርግ ኖሮ ይህን ማድረግ አንችልም፡፡ ፍለጋ በጣም ውድ ነው፡፡ ለፍለጋ የሚያስፈልግህ ነገር ሁሉ ካፒታልና ወጪ ያስፈልገዋል፡፡ የመሣሪያዎቻችን ዕቃዎች ይበላሻሉ፣ ይለወጣሉ፣ ማስፋፊያ የምንለው ቅድም ያልኩትን ነው፡፡ ማስፋፊያ አላቆምንም፡፡ ብናቆም ኑሮ ሳካሮ አይኖርም ነበር፡፡ የማምረት አቅማችንን መቶ በመቶ አቅም ነው የምንጠቀመው፡፡ የፕሮሰሲንግ ፕላንቱ አንድ ጊዜም ተቋርጦ አያውቅም፡፡ አንድ ወር ወይም ሁለት ወር ዘግተን አናውቅም፡፡ 24 ሰዓት፣ ሰባት ቀን ነው የምሠራው፡፡ መጀመርያ የነበረው ‘ኦፕን ፒት’ ነው፡፡ ሳካሮ የምንሠራው ከመሬት በታች ነው፡፡ አሁን ደግሞ እዚህ የምነሠራው ‘ኦፕን ፒት’ ነው፡፡ ስለዚህ ሁለተኛ ወይም ሦስተኛ የወርቅ ማዕድን ይሆናል ብለን እንጠብቃለን፡፡ ሌላም መቐለ አካባቢ አንድ ያለ ይመስለኛል፡፡
ሪፖርተር፡- በዓመት ምርቱ ምን ያህል ነው?
ዶ/ር አረጋ፡- ሚድሮክ ጎልድ ምርቱ ግልጽ ነው፡፡ በዓመት ከ3,000 እስከ 4,000 ኪሎ ግራም ወርቅ ነው የሚያመርተው፡፡
ሪፖርተር፡- የኤክስፖርት ገቢውስ?
ዶ/ር አረጋ፡- እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ግን በአማካይ ወደ አንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር የተጠጋ ነው፡፡ መረጃዎች አሉ፡፡ ልሰጣችሁ እችላለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- መቼም ስትሠሩ ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ቀጥታ ግንኙነት እንደሚኖራችሁ ነው፡፡ ዘወትር እነሱ ፍተሻ ያደርጋሉ፡፡ እናንተም ሪፖርት ታደርጋለችሁ፡፡ ከማዕድን ሚኒስቴር አካባቢ ከኢንስፔክሽን ጋር በተያያዘ ችግር አለ የሚባል ወቀሳ ይሰማል፡፡
ዶ/ር አረጋ፡- የለም፡፡ እንደኛ ግልጽና በተገቢው መንገድ የተዋቀረ ኩባንያ የለም፡፡ ለምሳሌ እዚህ ቁጭ ብለን ወርቅ ልንሸጥ ብናስብ፣ አንደኛ እኛ ወርቅ ኢትዮጵያ ውስጥ አንሸጥም፡፡ ሸጠንም አናውቅም፡፡ የሚሸጠው ሁልጊዜ በገባነው ውል መሠረት አውሮፓ ውስጥ ነው፡፡ ወርቁ አንደኛ ነገር ከብር ጋር የተጣመረ ስለሆነ አንድ ላይ ሆኖ ነው የሚሄደው፡፡ ወደ ሃያ በመቶው ብር ነው፡፡ ወደ ሰማኒያ በመቶው ወርቅ ነው፡፡ አምርተን ከጨረስን በኋላ ከጉምሩክና ከብሔራዊ ባንክ ሰዎች አንድ ላይ አድርገን በአውሮፕላን እንወስዳቸዋለን፡፡ ‘ጎልድ ሩም’ የሚባል አለ፡፡ እዚህ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ይመዝናሉ፡፡ ሌቭል ይደረጋል፣ ይጫናል፣ በአውሮፕላን ይመጣል፣ ወደዚህ ቦሌ፡፡ እንደገና ይወርዳል ሰዎች አሉ፡፡ በሉፍታንዛ ወይም በሌላ እንጭናለን፡፡ ከዚያ በኋላ ጉምሩክም ሆነ ብሔራዊ ባንክ የራሳቸውን ወረቀት ይዘው ይሄዳሉ፡፡ እኛም የራሳችንን ይዘን እንሄዳለን፡፡ ይኼ አንዱ ነው፡፡ እኔ እውነቴን ነው የምነግራችሁ አንድም ቀን ተሳትፌ አላውቅም፡፡ ፖሊሲ አለ፡፡ በፖሊሲ ነው የምንሠራው፡፡ ሁለተኛው ተሸጠ ሲባል እዚያ ሄዶ ከደረሰ በኋላ ኒውዮርክ ባለው ገበያ ዋጋው ይነገራል፡፡ እኛ ቁጥጥር አናደርግም፡፡ ተሸጠ እንበል፡፡ ከተሸጠ በኋላ ገንዘቡ እንዲገባ የምናደርገው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፡፡ ንግድ ባንክ ይወስደዋል፡፡ በአገሪቱ ሕግ መሠረት ለ28 ቀናት ያቆዩታል፡፡ እስከዚያ ድረስ ልታወጣ የምትችለው ካለ የዕቃ መግዣ ከሆነ ይፈቀድልሃል፡፡ ካልሆነ ይመነዘራል፡፡ አገሪቷ ትጠቀምበታለች፡፡ ለማዕድን ሚኒስቴርም የምናደርግለት ይኼንን ነው፡፡ የመግባቢያ ደብዳቤ አለን፡፡ ስለዚህ ይህ ችግር የለም፡፡ ሁለተኛ ‘ኢንስፔክት’ ለማድረግ ‘ፕሮሰሳችንን’ ሪፖርት እናደርጋለን፡፡ የፍለጋ ሪፖርት ይደረጋል፡፡ የእኛም ሪፖርት ይደረግልናል፡፡ ሄደው ማየት ደግሞ መብት አላቸው፡፡ ሄደው ያዩታል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሳያሳውቁ ይመጣሉ መብታቸው ነው፡፡ በአጋጣሚ በሩ ላይ ሲደርሱ ለማንም ሳይነግሩ ልግባ ሲሉ እዚያ ያለው ጥበቃ ድርጅት ትረስት ነው፡፡ ምንድነህ አንተ? ወረቀት አለህ? ሊል ይችላል፡፡ ከዚያ ያስገባል፡፡ እኔ እስከማውቀው ሄዶ አትገባም ተብሎ የተመለሰ ሰው አላውቅም፡፡ ሁለተኛ እንድታውቁት ያህል ነው ሞባይል ይዞ መግባት ይከለከላል፡፡ እኛ ወርቅ ማዕድኑ ውስጥ ካሜራ አለን፡፡ ምክንያቱም በሞባይል አማካይነት ሥራዎቻችን ሊበላሹብን ይችላሉ፡፡ አንዳንዱ እኔ አለቃ ነኝ ከመንግሥት ቤት ነው የመጣሁት ሊልህ ይችላል፡፡ ስለዚህ እንደዚህ ዓይነቶች ካልሆኑ በስተቀር እኔ እስከማውቀው ድረስ አንድም ችግር የለም፡፡
ሪፖርተር፡- የኤክስትራክቲቭ ኢንዱስትሪስ ኢኒሼቲቭ ለሚባለው ተቋም ሪፖርት አታደርጉም ትባላላችሁ፡፡
ዶ/ር አረጋ፡- ውሸት ነው፡፡ ለኤክስትራክቲቭ ኢንዱስትሪስ ኢኒሼቲቭ ድጋፍ የምናደርግ እኛ ነን፡፡ እኔ እምልህ እዚህ አገር ሚድሮክ ጎልድ ከሌለ ኢንስትራክቲቭ ኢንዱስትሪስ እንዴት ሊኖር ይችላል? ኤክስትራክቲቭ ኢንዱስትሪስ ኢንተርናሽናል ኩባንያ ነው፡፡ እንዲያውም እኛ ገብተንበት ነው እዚህ የደረሰው፡፡ ለዚህ ቁርጠኛ የሆኑ ሰዎች አሉን፡፡ ለእዚያ ብቻ የተመረጡ፡፡ ሪፖርት ለሚባለው ምን ዓይነት ሪፖርት ነው መቅረብ ያለበት? ፋይናንሻል ስቴትመንት እናቀርባለን፡፡ በየጊዜው የምናመርተውን እናቀርባለን፡፡ ፕላናችንን እናቀርባለን፡፡ ሌላ ምን ሪፖርት ነው ማቅረብ ያለብን? ባንክ ያለውን ነገር መንግሥት ያውቀዋል የት እንደሚገባ፡፡ እመኑኝ እንደ ሚድሮክ ጎልድ ግልጽነት ያለው ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ብዬ አላምንም፡፡ ግን አለ አይደል ሰዎች ካለማወቅ ዝም ብለው ሊናገሩ ይችላሉ፡፡ ስንጠየቅም መረጃችንን እንሰጣለን፡፡ ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ብዙ ጊዜ እንከራከራለን፡፡ አዎ ብዙ ጊዜ ሕግ ሲወጣ፣ አዋጅ ሲወጣ እንከራከራለን፡፡ ኢንቨስት የሚያደርግ ከደቡብ አፍሪካም ሆነ ከሌላ አገር በሚመጣበት ጊዜ ኢትዮጵያ ለኢንቨስተር የሚመች ነገር ምን አላት? ይላል፡፡ ሰዎች እንደናንተ እዚህ ይመጣሉ፡፡ ልምዳችሁ ምንድነው ብለው ይጠይቁናል፡፡ ያንን ስለምናውቅ አዋጁ እንደ ሌሎች አገሮች አዋጅ እንዲሻሻል እንፈልጋለን፡፡ ይህንን በምንልበት ጊዜ ሁለት ግጭት ይኖራል፡፡ አንዱ እንደምንም ሸጬ ገንዘብ ነው የምፈልገው ይላል፡፡ አንዱ ደግሞ ኧረ ተው እንደምንም እንሳባቸውና ከብዛት እንጠቀማለን የሚል ይኖራል፡፡ ስለዚህ አዋጁ ብዙ ጊዜ ተለውጧል፡፡ እዚያ ላይ አንዳንድ ጊዜ መቆራቆስ አለ፡፡ አዋጁ የሚሰጥህ አንዳንድ ልዩ መብት አለ፡፡ ማይኒንግ የራሱ አዋጅ ነው ያለው፡፡ አሁን ያለው አዋጅ ለምሳሌ አይፈቅድልህም፡፡ አንድ ጊዜ ማዕድን ማውጣት ከጀመርክ በኋላ አይፈቅድልህም፡፡ እንደዚህ፣ እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ሲመጡ ትንሽ እንሞግታለን፡፡
አሁን ፍለጋውን አንተ እዚህ አገር ልሥራ ብለህ ብትመጣ ሥራ ብዙ መሣሪያ ይዘህ መምጣት አለብህ፡፡ አንድም ይሁን ሁለት በጣም ውድ መሣሪያ ይዘህ ትመጣለህ፡፡ ልትቆፍርና ልትፈልግ ነው የመጣኸው፡፡ ፈልገህ ላታገኝ ትችላለህ፡፡ ልታገኝም ትችላለህ፡፡ እንደኔ የመጣን መርዳቱ ነው የሚሻለው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ሁለት ነገሮች ይሠራል፡፡ አንዱ ፈልጎ ሲያጣ መረጃ ግዴታ ማቅረብ ስላለበት ያቀርባል፡፡ የመረጃ ባንካችን ጥሩ ይሆናል፡፡ የሚቀጥለው ከዚያ ጀምሮ እንዲጓዝ፡፡ ሁለተኛ ይኼ ሰውዬ የተወሰኑ ሰዎች ይቀጥራል፡፡ ስለዚህ ሰውዬው በሚመጣበት ጊዜ ጭንቅንቅ ማድረግ ሞኝነት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ከችግራችን አኳያ ነው፡፡ አገሩ ሀብታም ቢሆን ኖሮ ማን ያስታውሳል ይህንን፡፡ አሁን ግን ዶላሯም ስለምታጥር ትንሽ ችግር ያለ ይመስለኛል፡፡ እናም ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር አብረን ነው የምንሠራው፡፡ ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ያለው ሌላው ከዚህ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘንድም አንስቸዋለሁ፡፡ ማይኒንግ ማለት ምን ማለት ነው? በሚለው ትርጉም ነው፡፡ እናንተም በሙያችሁ ልታግዙ እንደምትችሉ አምናለሁ፡፡ ለእኔ ውኃ ማይኒንግ ነው፡፡ ከመሬት የሚገኝ ነገር ሁሉ ማይኒንግ ነው፡፡ ሲሚንቶ ማይኒንግ ነው፡፡ ጠጠር ማይኒንግ ነው፡፡ ድንጋይም እንዲሁ፡፡ ይኼ ማይኒንግ ከተባለ ማይኒንግ እዚህ አገር የለም ማለት አትችልም፡፡ ማይኒንግ በብዛት እየረዳ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ማይኒንግ ብለው የሚያስቧት ይችን ወርቅ ብቻ ከሆነ ግን ቁንጽል ነው እላለሁ፡፡ ሁለተኛ ደርባ ሲሚንቶን ብትወስደው፣ ሌላ ሲሚንቶ ፋብሪካን ብትወስድ ማይን ያደርጋል፡፡ ፋብሪካ ተከለ፡፡ ፕሮሰሲንግ ፕላንት ተከለ፡፡ ከመሬት አንድ ነገር ፕሮሰስ ያደርጋል፣ ያመርታል፣ ይሸጣል አይደል? ከሚድሮክ ጎልድ በምንድነው የሚለየው? ይቆፍራል፣ ፕሮስስ ያደርጋል፣ ከዚያ ያወጣል፡፡ ደርባ በአብዛኛው በንግድ ሚኒስቴር አካባቢ ነው የሚረዳው፡፡ እንደ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ተወስዶ፡፡ ወርቅ ደግሞ ማይኒንግ ነው የሚባለው፡፡ ይኼ አይገባኝም፡፡ ስለዚህ እኔ የምለው ግብዓቱ ላይ ያለው ሁሉ ማይኒንግ ነው፡፡
ፍለጋ ከሆነ ሌላ ነገር ነው፡፡ ፈቃድ መስጠት አለባቸው፡፡ ለምሳሌ ሳካሮ የሚባለው ወደ ሰባተኛ ዓመቱ ነው፡፡ በጄኔሬተር ነው የሚሠራው፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ከጠየቅኩ አራት፣ አምስት ዓመት ሆኖኛል፡፡ አሁን ገብቶኛል፡፡ ኢንዱስትሪ ሲሆን ግን አበባም ይሁን ሌላም ቶሎ ብለው ድጋፍ ያገኛሉ፡፡ ስለዚህ ትቀናለህ፡፡ ከዚህ አኳያ ብንመለከተው አንዳንዱ ዝም ብሎ ወርቅ ማዕድንማ ልዩ ነው ይላል፡፡ ያም የፕሮሰሲንግ ፕላንት ነው፡፡ ይኼኛውም እንዲሁ፡፡ ስለዚህ ሄዳችሁ ብታዩት ጥሩ ነው፡፡ የእናንተ ድምፅ የተሻለ ይሆናል፡፡ እኔ ይህንን በተደጋጋሚ ጊዜ አንስቼዋለሁ፡፡ አንዳንድ ጊዜም እንደ አየር መንገድና ሲቪል አቪዬሽን አድርጌም አንስቸዋለሁ፡፡ አየር መንገድ ይሠራል፡፡ ፈቃድ ተሰጥቶታል፡፡ ሰዎቹ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል፡፡ ባለሙያዎቹ ፈቃድ ያገኛሉ፡፡ አየር መንገድ ነጋዴ ነው፡፡ እንዲያደግ ማድረግ አለብህ እንጂ ይኼን ያህል ነው የምትሸጠው ብለህ እንቅ ብታደርገው ማደግ ያቅተዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በአንድ ወቅት አቧራ አስነስቶ ስለነበረው ጉዳይ ልመልስዎት፡፡ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሚድሮክ ጎልድ የሮያሊቲ ክፍያ አይፈጽምም ብሎ ሪፖርት አቅርቦ ነበር፡፡ እናንተ ደግሞ ያንን ሪፖርት አልተቀበላችሁም ነበር፡፡ ጭቅጭቅም ነበረበት፡፡ ስለሱ ጉዳይ ቢገልጹልን? አሁንም ችግሩ አለ? ችግሩ የማን ነው? የእናንተ ነው ወይስ የመንግሥት?
ዶ/ር አረጋ፡- እኔ መናገር የምችለው ስለራሴ ድርጅት ነው፡፡ ማንም ሰው መጥቶ ሊያየው ስለሚችል፡፡ እኛ አንድ ሳንቲም ቀሪ አናደርግም፡፡ እኛ ለመንግሥት ትንሽ ገንዘብ ባንሰጥ ኑሮ ሚድሮክ ጎልድ ምን እንደሚሆን አስበኸዋል? እንዲያው ኦዲተር ተናግሯል ብለው ዝም ይሉን ነበር? ኦዲተሩ ሲያቀርብ በወቅቱ ስህተት ነበር፡፡ መልሱን አይተኸው ከሆነ፡፡ በእናንተ ጋዜጣ መሰለኝ መረጃው የወጣው፡፡ መልሱን መልሻለሁ፡፡ መልሱም እዚያው አለ፡፡ ለኦዲተሩም ደብዳቤ ጽፈናል፡፡ ከዚያ በኋላ መቼስ እጁን ይዤ አስተባብል አልለው፣ ምን አልለው፣ ራሴን ተከላክዬ ቁጭ ማለት ነው፡፡ ነገ ለምርመራ ቢመጣ ማቅረብ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ የነበረው የአጻጻፍ ስህተት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከመጻፉ በፊት ማዕድን ሚኒስቴር ዘንድ ሄደው ቢጠይቁ ኖሮ እነሱ ይኖራቸው ነበር፡፡ በእኔ እምነት ሚድሮክ ጎልድ ያስቀረው ምንም ነገር የለም፡፡ ጉዳዩ ለምን መጣ ብትለኝ ሁለት አዋጆች ስለነበሩ ነው፡፡ የተሻሻለ አለ፣ የከበደ አለ፡፡ በዚያ መካከል ላይ እነሱ ተነጋግረው አንድ ዓይነት ሪፖርት ማቅረብ ሲገባቸው የመጣ ክፍተት ነው፡፡ እሱ እነሱን እንዴት ኦዲት እንደሚያደርጋቸው አላውቅም፡፡ እኛ ጋ መጥቶ ኦዲት አላደረገም፡፡ እሱ ኦዲት የሚያደርገው እኮ ማዕድን ሚኒስቴርን ነው፡፡ ማዕድን ሚኒስቴርን ኦዲት ሲያደርግ ያንን ነገር ነግሯቸው ቢሆን ኖሮ ይሻል ነበር፡፡ ስህተቱ የተፈጠረው እነሱን ኦዲት ሲያደርጋቸው የኩባንያ ስም በመጥራት ፈንታ፣ በእናንተ ሥር የሆነ ችግር አለ ብሎ ቢናገር ኖሮ ጥሩ ነው፡፡ ሚድሮክ ጎልድ ስለሆነ እናንተም ወሰዳችሁት፡፡ እኔም ሚድሮክ ጎልድ ስለሆነ መልስ ሰጠሁ፡፡ ያችን አቧራ ከዚያን ጊዜ ወዲህ አልሰማኋትም፡፡ የምትመጣም ከሆነ ዝግጁ ነኝ፡፡ እኔ የማውቀው የምሠራውን ነገር ብቻ ነው፡፡ ሕግ ማክበርንና ሕግ ማስከበርን በተመለከተ እንደኔ ዓይነት ሽማግሌ፣ ይህንን ያህል ፊደል የቆጠረ ሰው ለወጣቶች ስንል የማናደርግ ከሆነ ጥሩ አይደለም፡፡ እናም ይኼ ይለየናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሕግ አክባሪ ነው፡፡ መቶ በመቶ ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን እስከምናውቀው ድረስ እያደረግን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የሚድሮክ ጎልድ ኢንቨስትመንት ካለበት ለገንደቢ አካባቢ ከነዋሪዎች ጋር ጭቅጭቅ ነበር፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች በተለይ ለአካባቢ ጥበቃ የተሰጠው ግምት አነስተኛ በመሆኑ በሕይወታቸው ላይ ተፅዕኖ እንደፈጠረባቸውና ኑሮአቸውን እንዳመሰቃቀለባቸው በአደባባይ ሲናገሩ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ምን ተደረገ?
ዶ/ር አረጋ፡- መቼ ነው ይህ የሆነው?
ሪፖርተር፡- ከዓመታት በፊት፡፡ ከዚያ በኋላስ ምንድነው የተደረገው?
ዶ/ር አረጋ፡- ሚድሮክ ጎልድ ምንም ዓይነት የአካባቢ ተፅዕኖ በአካባቢው ላይ ፈጽሞ አያውቅም፡፡ እንደዚያ የተወራው በሙሉ ስህተት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በቴሌቪዥን ሳይቀር ቀርቦ ነበር፡፡
ዶ/ር አረጋ፡- ቆይ ልናገር፡፡ አንዳንድ የሌለ ታሪክ መልቀቅ ይኖርባችኋል፡፡ በዚያ ጊዜ እንዲያ ዓይነት ችግር አለ አሉ፡፡ አንዱ በሬ ገብቶ ችግር እንዳይፈጥር ትገድበዋለህ፡፡ የማጣሪያ ፕላንት አለን፡፡ ይኼ ዓለም አቀፍ አሠራር ነው፡፡ ውኃውን ቼክ ካደረግክ በኋላ ትለቃለህ፡፡ 500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው፡፡ እዚያ ሄዶ መመልከት ይቻላል፡፡ እዚህ ቁጭ ብሎ ወርቅ በሰፌድ የሚመረት የሚመስለው ስለዚያ ሲያወራ መስማት ስህተት ነው፡፡ የመጀመርያ ደረጃ መረጃ ከሁሉም የተሻለ ነው፡፡ አንዱ በሬ ገብቶ ሞቶብኛል ይላል፡፡ አንዱ መሬቱ ተበክሏል ይላል፡፡ ስለዚህ ይኼ ከሆነ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ እንዲያውም ታስታውስ ከሆነ ሼክ መሐመድ ወደታች ወረዱ፣ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ ወረዱ፣ እኔም ነበርኩ፡፡ ከዚያ ሕዝቡ ተሰበሰበ፡፡ ዋናው ጉዳይ ሼክ መሐመድን መውሰድ የተፈለገበት ምክንያት ዕርዳታ እንዲሰጥ ነው፡፡ በዚህም ለእያንዳንዱ ወረዳ አንዳንድ ሚሊዮን ብር ተሰጠ፡፡ ለቴክኒክ ትምህርት ቤቱ 15 ሚሊዮን ብር ተሰጠ፡፡ መንገድ ይሠራልን አሉ፡፡ ይኼንን መንግሥት መሥራት አለበት ተባለ፡፡ ከዚያ በኋላ ችግር አለ ተብሎ ሲነገር አቶ ዓለማየሁ የዚያን ጊዜ ሚኒስትር ነበሩ፡፡ ‘ይህ ኩባንያ ዓለም አቀፍ ሕግ ተከትሎ የሚሠራ አንድም ዓይነት የአካባቢ ተፅዕኖ ሪከርድ የለበትም’ ብለው መሰከሩ፡፡ እኛ የምንሠራው በአገሪቷ ሕግ ብቻ ነው፡፡ የተወሰኑ ግለሰቦች ለሚሰጡት አስተያየት አይደለም፡፡ አንደኛ መንደር የተወራውን ሁሉ ማስተባበል መሞከር ተገቢ አይደለም፡፡ እናንተም ዝም ማለት የለባችሁም፡፡ የምጠይቃችሁ ነገር ቢኖር እውነታውንና ኩባንያው የሚሠራውን ነገር ዓይቶና መዝኖ መናገር ጥሩ ብዬ ነው፡፡ ይህንን ማለት አገር መጉዳት ነው፡፡ ኩባንያውን አይደለም፡፡ አረጋንም ሆነ መሐመድን አይጎዳም፡፡ የሚጎዳው አገር ነው፡፡ ምክንያቱም ሌላ የማዕድን ኩባንያ እንዳይመጣ ማድረግ ነው፡፡ እኛ ምንም ምክንያት የለንም፡፡ መሐመድ ብር ሞልቶታል፡፡ አረጋ የብር ሰው አይደለም፡፡ ይህን ያስተማረኝን ሕዝብ ላገለግል ነው የመጣሁት፡፡ እና ቀጥፈን ገንዘብ የምንሰበስብበት ምንም ምክንያት የለንም፡፡ አንድ ነጠላ ምክንያት እንኳን የለንም፡፡ ምክንያቱም መሐመድ ነገ ሟች ነው፡፡ ቢሊዮን አይቶ የማያውቅ ሰው ሼክ መሐመድ ቢሊየነር የሆነው በሚድሮክ ጎልድ ነው ይላል፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ ባለፉት 18 ዓመታት ሼክ መሐመድ አንድ ዶላር ወስደው አያውቁም፡፡ ሪከርዱን ሄዶ መመልከት ነው፡፡ ስለዚህ ሚድሮክ ጎልድ ገንዘብ አግኝቶበታል? አዎ፡፡ ኢንቨስተር የሚመጣበት ዓላማውም እሱ መለሰኝ፡፡ ኢንቨስተር ነኝ ብሎ በእሱ የሚመጣውን ዲቪደንድ በዶላር ስጡኝ ብሎ መውሰድ መብቱ ነው፡፡ አንድም ቀን ያች ተደርጋ አታውቅም፡፡ ሀቅ ነው የምነግርህ፡፡ ብዙ ሀብታሞች እናያለን አይደል? እዚህ አገር የተወሰነውን ጂቡቲ ለመሸጥ፣ ዶላር ለማግኘት የሚያደርጉን አንተም ታውቃለህ አይደል? ይኼ ሰው በሕጋዊ መንገድ መውሰድ ሲችል አያደርግም፡፡ ስለዚህ እውነተኛ ለሆነ ሰው በትክክል መመስከር፣ ጥፋተኛ ከሆነ ደግሞ አጥፍተሃል ብለህ በትክክል መናገር ነው፡፡ ይኼ ሰዎችን ያበረታል፡፡ ስለዚህ የአካባቢ ተፅዕኖ የሚባለውን በተመለከተ እንደኛ ተጠንቅቆ የአካባቢውን ሁኔታ የሚያጠና፣ የሚሠራ የለም፡፡ እንዲያውም አጠርነው፡፡ አጥሩ ተወሰደ፡፡ የተወሰነ ጊዜ ድንበሩን ስላላወቅነው ነውና ድንበር አድርጉ ተባለ፡፡ ከብሔራዊ ማፒንግ ኤጀንሲ ባለሙያዎችን ቀጥረን ድንበር ማካለል እንዲሠሩ አደረግን፡፡ አስፈራርተው አስወጧቸው፡፡ ስለዚህ እንደዚያ ዓይነት ለግል ጥቅማቸው የሚሠሩ ሰዎችን ሐሳብ ወስዶ ማውራት ተገቢ አይደለም፡፡ ሄዳችሁ ዓይታችሁ ትክክለኛ የሆነ ሥራ ሥሩ፡፡ ስህተት ካለም ንገሩን፡፡ እናስተካክላለን፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ዳይሬክተር አለን፡፡ የአገሪቱን ፖሊሲ እንከተላለን፡፡ ዓለም አቀፉን ሕግ እንከተላለን፡፡ ዛፎችን በየዓመቱ እንተክላለን፡፡ የማዕድን ሕግ ገንዘብ አስቀምጥ ይላል፡፡ እሱን እናስቀምጣለን፡፡ ‘ሊንክ ፈንድ’ ይባላል፡፡ ዝም ብለን ፊደል አልቆጠርንም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ነገሮችን ልንሠራ ነውና በጥያቄው ደስተኛ ነኝ፡፡ ለእናንተ ግልጽ ከሆነ ለሌላውም ግልጽ ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- ጥያቄው መነሳቱ መልስ ስለሚያስፈልገው ነው፡፡
ዶ/ር አረጋ፡- በትክክል፡፡
ሪፖርተር፡- እርስዎ የ25ቱም ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነዎት፡፡ እንዲሁም የሚድሮክ ጎልድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነዎት፡፡ እዚህ አገር ውስጥ በማይኒንግ፣ በጂኦሎጂና በመሳሰሉት ተዛማጅ መስኮች የሠለጠኑ በርካታ ትልልቅ አቅም ያላቸው ሰዎች እያሉ እርስዎ ይህንን ኃላፊነት የያዙት ለምንድነው ይባላል፡፡ ምክንያቱን ይነግሩናል?
ዶ/ር አረጋ፡- በዚህ ዘርፍ የተማሩና የሙያ ልምድ ያካበቱ በደንብ ነው እንጂ ያሉት፡፡ ሲኒየር የሆኑ ሰዎች አሁንም አሉ፡፡ እኔ እንዲያውም ከማይኒንግ ኢንጂነሪግ ዓለም ውስጥ አይደለም የወጣሁት፡፡ ግን ማንኛውንም ቴክኒካል ኩባንያ ማስተዳደር እችላለሁ፡፡ በሄድኩበት ዓለም እንኳን የማይኒንግ ኢንዱስትሪ ይቅርና ሌላም ኢንዱስትሪ እንድመራ ያደርገኛል፡፡ ስለዚህ በአገራችን በርካታ የተከበሩና የታወቁ ባለሙያዎች አሉ፡፡ እኔም ጋ ያሉት ፈረንጆች አግልለዋቸው የነበሩትን፣ አሁን በአሥር ዓመት ‘ኢትዮጵያናይዝ’ አድርጌ ታች ያለውን የሚመሩት ኢትዮጵያዊን ናቸው፡፡ ቁልፍ ቦታ ላይ ያለውንም የሚመሩት ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ይኼን አድርገናል፡፡ በሌላ በኩል መነገርና መታወቅ ያለበት የሆስፒታል አስተዳዳሪ ወይም ጄኔራል ማኔጀር ዶክተር መሆን አለበት የሚለው ዘመን አልፏል፡፡ ሞቷል፡፡ ሆስፒታል ማስተዳደርና ሰርጂን መሆን የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ፕሮፌሽናል ሰዎች የሙያ ሥራ እንዲሠሩ ነው እንጂ ማኔጀር እንዲሆኑ አይደለም፡፡ ስለዚህ አሁን ባንኮክ ብትሄድ ሆስፒታሉን የሚመራው ዶክተር አይደለም፡፡ የሚመራው ቢዝነስ የተማረ ሰው ነው፡፡ ስለዚህ እኔ አሁን የሊደርሽፕና የማኔጅመንት ክህሎት ነው የምጠቀመው፡፡ አሁን ኤልፎራ እኔ ጋ ነው፡፡ አግሮኖሚ ተምረሃል ብትለኝ አልተማርኩም፡፡ ግን አግሮኖሚ የተማሩ ሰዎች እንዲሠሩ አድርጎ መምራት የሊደርሽፕ ሥራ ነው፡፡ ልዩነቱ ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ በዚህ በኩል ስትመለከተው አገራችን ውስጥ በብዛት የለም፡፡ ይኼ እውነት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ወደ ሁዳ ደግሞ እንምጣ፡፡ ሁዳ አዲስ አበባ ውስጥ ይታወቃል፡፡
ዶ/ር አረጋ፡- እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ መታወቁን አላውቅም፡፡ አዎ ብዙ ሥራዎች ሠርቷል፡፡ የወልድያውን ወርቅ የሆነ ዘመናዊ ስታዲዮም ገንብቷል፡፡ ደሴ ያለውን ዘመናዊ ሕንፃ የሠራው እሱ ነው፡፡ እነዚህ እኔ ከመጣሁ በኋላ ያሉት ናቸው፡፡ እኔ ከመምጣቴ በፊት የነበሩ ሎሊ፣ ናኒ ሕንፃዎች ነበሩ፡፡ የሁዳ ሀብቶች ናቸው፣ ጨርሰናል፡፡ ሎሊም እየተሠራ ነው፡፡ ሄዶ ማየት ይቻላል፡፡
ሪፖርረግ፡- ግንባታቸው የተጓተቱና ታጥረው የተቀመጡ መሬቶች ጉዳይስ?
ዶ/ር አረጋ፡- የተወሰነ መሬት በሁዳ ስም ተይዞ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ያ ነገር የታሰበው ለተወሰነ ሥራ ይሆናል፡፡ እሳቸው ባለሀብት እንደ መሆናቸው መጠን የሪል ስቴት ኩባንያ ካላቸው አንድ መሬት ሲፈልጉ በሪል ስቴት በኩል ያዙልኝ ቢሉ ነውር የለውም፡፡ ስለዚህ ከምትላቸው ነገሮች እኔ የማውቀውና ኃላፊ የሆንኩባቸው ሎሊ ሕንፃ፣ ናኒ ሕንፃ እውነት ነው የእኔ ናቸው፡፡ የወልድያ ስታዲየምና የደሴ ሕንፃ የእኔ ናቸው፡፡ እነዚህን ሠርቻለሁ፡፡ ስለሌላው ግን ትክክለኛው ሰው ዘንድ ሄዶ መጠየቅ ይቻላል፡፡ ስለተሠሩት ግን በሚገባ መነጋገር ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ የአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ወደ ማኑፋክቸሪንግ እየገቡ ነው፡፡ ከውጭም እየመጡ ነው፡፡ ብዙ መስፋፋቶችም እየታዩ ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮችም እየተገነቡ ነው፡፡ ወደፊት ከዚህ አኳያ በተለይ ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ምንድነው የሚያስበው?
ዶ/ር አረጋ፡- ጥሩ፡፡ የእኔ ኩባንያዎች የኢንዲስትሪ ፓርክ ውስጥ አይገቡም፡፡ የሚገቡበት ምክንያት የላቸውም፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርክ የተሠራው ሁሉንም ኩባንያ ሊከት አይደለም፡፡ በተወሰኑ ቦታዎች ላይ የተወሰኑ ሥራዎች እንዲሠሩ ነው፡፡ ኤክስፖርት ተኮር ሆኖ፣ ሰዎች ቀጥሮ የተወሰኑ ምርቶች እንዲያመርት ነው እኔ የሚገባኝ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ እስካሁን ድረስ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ሳይኖር የነበሩት ድርጅቶች ደግሞ በየቦታቸው ሥራቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ኮስፒ ማኑፋክቸር ያደርጋል ብዬ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የምገባበት ምክንያት የለኝም፡፡ ኮስፒ በተወሰነ ቦታ ላይ የተወሰነ ሥራ ፈጥሮ ለዓመታት የተረጋጉ ማኅበረሰቦች ይዟል፡፡ ስለዚህ የእኔ ድርጅቶች እዚያ ሲገቡ አላያቸውም፡፡ ሌሎቹ በየቦታው ያሉት የተቋቋሙት ማዕድንም ይሁኑ ምንም ይሁኑ ያሉት መቀጠል ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ አገራችን ሰፊ ነች፡፡ ሁለት፣ ሦስት፣ አራት ፓርኮች ቢኖሩህ እዚያ ጋ ብቻ ተከማችተው እናድርገው ብትል ሥራው ምን ሊሆን ነው? አስቡት እንጂ፡፡ ስለዚህ እኔ የኢንዱስትሪ ፓርኩን የማየው በዚህ መልክ አይደለም፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኩን የማየው በተወሰነ ቦታ ላይ ለተወሰነ ሥራ በብዛት ሰዎችን ሊቀበል በሚችል ሥራ ላይ ይገባል፡፡ ለእዚህም ዓለም አቀፍ ገበያ ያላቸው ነው የሚገቡት፡፡
ሪፖርተር፡- ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ወደፊት ሼድ በመውሰድ በራሱም ሆነ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ሆኖ ሊንቀሳቀስ ይችላል?
ዶ/ር አረጋ፡- እንደሱ ከሆነ ጥሩ፡፡ እንደ ሁኔታው የሚወሰን ይሆናል፡፡ ባለሀብቱ የኢንዱስትሪ ፓርክ እንዳለ ያውቃሉ፡፡ ከተስማማቸው አገሩን ያውቁታልና ይኼኛውን ብገባበት ይጠቅመኛል ቢሉ ተጠንቶ ቢገባበት መጥፎ ነው ብዬ አላስብም፡፡ ትረዳናለህ ወይ? ወደዚያ ቦታ አብረህ ትሠራለህ ወይ? ብባል ደስታውን አልችለውም፡፡ እያንዳንዱ ሰው የራሱ አቀራረብ አለው፡፡ ትልልቅ ኢንቨስትመንት ካላቸው ኩባንያዎች ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኩ እከሌ ገባ፣ እከሌ ገባ ሲባሉ አልሰማሁም፡፡ ሌሎችማ አዲስ እየመጡ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ የጫማና የጨርቃ ጨርቅ አምራቾች እየመጡ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ነገሯ ወርቅ ነች፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለአገራችን አስፈላጊ ነው፡፡ እንዲያውም ቢበዙ ነው የሚሻለው፡፡ አንዳንድ የቆርቆሮና ሌሎች ምርቶች እስካሁንም ተፈላጊ ናቸው፡፡ ለምን ወደ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገቡ የሚል አመለካከት ካለ ተሳስቷል፡፡ በእኔ እምነት ትክክል ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡
ሪፖርተር፡- እንደ ቢዝነስ መሪ ወደ ሁለት አሥርት ዓመታት ሲቆዩ የኢትዮጵያን ቢዝነስ ከባቢ እንዴት ነው የሚገልጹት? በተለይ ከግል ዘርፉ አኳያ?
ዶ/ር አረጋ፡- ከወደፊቱ ዕይታ ወይም ተስፋ ብጀምር በጣም፣ በጣም ግሩም ነው፡፡ አገራችን በአሁኑ ጊዜ ውጥረት አለባት ብዬ አምናለሁ፡፡ ግን ለእኔ የምንሄድበት አካሄድ ጥሩ ይሆናል፡፡ የነበረን የባህል ውህደት ከሚቀጥለው ቴክኖሎጂ ጋር ሲጣመር ከሌላው አገር የተሻለ ውጤት ይመጣል ብዬ አስባለሁ፡፡ በጣም ባህላዊ የሆንን ሰዎች ነን፡፡ ከመስረቅ ይልቅ የምንለምን ሰዎች ነን፡፡ ስጠኝ እባክህ የምንል ሰዎች ነን፡፡ የእኛ ፈተና የሆነው ዕድገት በምን ያህል ፍጥነት የሚለው ነው፡፡ በፍጥነት እንዳንሄድ የሕዝብ ብዛት፣ የካፒታልና የገበያ እጥረት አንቆ ይዞናል፡፡ የእውቀት ጉዳይ አይደለም፡፡ ትምህርት ቤቶቹ ጥሩ እየሠሩ ነው፡፡ ተስፋው ይታያል እውነቱን ለመናገር፡፡ እስከ ዛሬ የነበረውን የቢዝነስ ሒደት እንዴት ታየዋለህ ስትለኝ የነበርኩበትና አብሬ የተንከላወስኩ ስለሆነ፡፡ እናንተም አብራችሁ ነው ያደጋችሁት፡፡ ሳየው ልክ ሕፃን ልጅ ዳዴ ብሎ መራመድ ይጀምራል እንደሚባለው በዚያ ዓይነት በሁሉም መስክ በዴሞክራሲውም፣ በጋዜጣውም፣ በእኛም፣ በሁሉም በመልካም ሁኔታ የሄድን ይመስለኛል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ለአንዳንድ ሰዎች ፈተና ቢሆንም ይቋቋሙታል፡፡ ለአንዳንዶች ችኩል ለሆኑትና ትዕግሥት ለሌላቸው ያስቸግራቸዋል፡፡ አንድ ነገር ይታየኛል፡፡ ሁሉም ሰው ዕድገት የሚባለውን መዝሙር እየዘመረ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ ለውጥ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ያኛውም ማደግ ይፈልጋል፣ ይኼኛውም ማደግ ይፈልጋል፡፡ ኮብል ድንጋይ የሚቀጠቅጠው ጭምር ሁሉም ማደግ አለብኝ የሚል እምነት ያለው ይመስለኛል፡፡ ይህ አንድ ለውጥ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ሁለተኛው ስሠራ ብቻ ነው ላድግ የምችለው የሚለው ልምድ ቀስ እያለ እየመጣ ይመስለኛል፡፡ የሥራው ዓይነት ከፍ ወይም ዝቅ ያለ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ይህ የሥራ ባህል እየመጣ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከወደፊቱ አኳያ እነዚህን ስታያይዛቸው ጥሩ እየሆነ ይሄዳል ብዬ አምናለሁ፡፡ በግሉ ሴክተር ላይ ዕይታህ ምንድነው ስትለኝ የውጭ ኢንቨስተር ከሆነ ምንድነው የሚመለከተው ነው፡፡ ብዙ የተጀመሩ ነገሮች አሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ አንዳንድ ደግሞ ማሻሻል ያሉብን ነገሮች አሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ሕጎቻችን አንዳንዶቹ መሻሻል ይኖርባቸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ጋባዥ እንዲሆኑ፡፡ ቅድም ስለማይኒንግ አውርተናል፡፡ ይህ ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ኢንቨስተሮችን የምንስብባቸው ቴክኒኮች እየተሻሻሉ መሄድ አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ የሚባለው ቱሪዝም አሁን በቀላሉ ልትስበው የምትችለው ነገር ነው፡፡ ብዙ ኢንቨስትመንት አይጠይቅም፡፡ ነገር ግን ወደዚያ መውሰጃው ላይ ብዙ መልፋት ይኖርብን ይሆናል፡፡ የፖለቲካ መረጋጋት ራሱን የቻለ ለኢንቨስትመንት የሚያስፈልግ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚህ አኳያ የአፍሪካ አገር በመሆናችን ራሱን የቻለ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያደርጋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህም ፖዘቲቭ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ምናልባትም እስካሁንም የተሠራው ደህና ይመስለኛል፡፡ በፖለቲካ የተረጋጋን ነን፡፡
ሌላው ሄጄ ኢንቨስት በማድረግ ገንዘቤን ላወጣ እችላለሁ ወይ ለሚባለው ከሕግ አኳያ ደህና ነን ብዬ አምናለሁ፡፡ ወረቀት ላይ በሰፈሩ ሕጎች ላይ እስከዚህ ደካማ ነን ብዬ አላምንም፡፡ ሌላው ከጂኦግራፊ አኳያ አቀማመጣችን ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በተለይ ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ጋር ባለን ግንኙነት የእነሱ ምርታችንን የመፈለግ፣ በተለይ የእኛን ምግብ መፈለጋቸውና እኛ ደግሞ ለመስጠት ያለንን ተፈጥሮና አቅም ስመለከተው ያም ጥሩ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁን ከገባንበት ሁኔታ የምንወጣበት መንገድ ቀስ ያለ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ፈጣን ነው ብዬ አላምንም፡፡ ስለዚህ እኔ ኢንቨስተር ብሆን ብዙ ሊስቡኝ የሚችሉ ነገሮች እንዳሉ ይታየኛል፡፡ ፈተና አለ ወይ? አዎን ፈተና አለ ብዬ አምናለሁ፡፡ ጠንከር ያለ ፈተና የሥራ ጉዳይ ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ በተለይ በብዛት ወጣቶች አሉን፡፡ ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች አሉን፡፡ ብዙ ተመራቂዎች አሉን፡፡ ጥሩ አቅም አለ ብዬ አምናለሁ፡፡ ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የተረጋጋን ነን ብዬም አምናለሁ፡፡ አሁን ያለው ወጣት ዓለም ላይ የትም ሄጄ እሠራለሁ የሚል ነው፡፡ ወደኋላ ይህ ነበር፣ ያ ነበረ ብለህ ብትነግረው ብዙም ትኩረት የማይሰጥ ነው፡፡ ከእዚህ ትውልድ ጋር በጣም ተለያይተናል ብዬም አምናለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- እርስዎ ብዙ ኩባንያዎችን የሚመራ ተቋም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነዎት፡፡ ብዙ ውጣ ውረዶችና ጫናዎች አሉ፡፡ የሳምንቱን መጨረሻ እንዴት ነው የሚያሳልፉት? በትርፍ ጊዜዎስ ምን ይሠራሉ? ምንድነው የሚያስደስትዎት?
ዶ/ር አረጋ፡- አንደኛ እረፍት የሚባል ነገር አላውቅም፡፡ ጥሩ ነው ማለት አይደለም፡፡ እረፍት የተፈጠረው ራስን እንደገና ለሥራ ለማዘጋጀት ነው፡፡ ተፈጥሮ ሊሆን ይችላል፣ ልምድ ሊሆን ይችላል፣ አየር መንገድ ካለሁበት ጊዜ ጀምሮ እረፍት የሚባል ነገር የለኝም፡፡ እዚህ ሰባት ቀን ካልመጣሁ የሚያመኝ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ እሑድና ቅዳሜንም በብዛት እዚህ አሳልፋለሁ፡፡ በጣም የሚያስደስትህ ምንድነው ስትለኝ መኪና ቀየር አድርጌ ነድቼ ከከተማ ወጣ ብዬ ጫካ ውስጥ ከብቶችን አይቶ ነፃ ሆኖ መምጣት በጣም የምወደው ነው፡፡ የራሴ የሆኑ የሚያስደስቱኝ ነገሮች አሉ፡፡ ከመጣሁበት ከአገር ቤት ጋር የተያያዙ ነገሮች አሉ፡፡ ዕድለኛ ሆኜ የሚያለቅስ ልጅ የለኝም፡፡ ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆኜ ነው ሚስት ያገባሁት፡፡ ዩኒቨርሲቲ ስጀምር አንድ ልጅ ነው የወለድኩት፡፡ አምስት ዓመት ተምሬ አምስት ልጆች ነው ይዤ የወጣሁት፡፡ አሁን በእኔ ቋንቋ ‘ቦነስ ላይፍ’ የምላት አለችኝ፡፡ ቦነስ ላይፌን እየከፈለችኝ ላስተማረችኝ አገር እየከፈልኩ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህንን ዕዳ ለመወጣት እየተፍጨረጨርኩ ነው፡፡ እንዴ ሊመጣ አይደለም እንዴ ትልቁ እረፍት? ምን አስቸኮለን? አንዳንድ ጊዜ የቢዝነስ ሰው ስትሆን ወይን ትጠጣለህ፣ ከሰዎች ጋር ታወራለህ፡፡ እኔ ይህንን አላደርግም፡፡ ጄኔራል ማናጀሮቹ ባላቸው ኃላፊነት እንዲሳተፉ አደርጋለሁ፡፡ አሁን ከእዚህ ቃለ ምልልስ ስወጣ መስክ ነው የምሄደው፣ የኮንስትራክሽን ኩባንያ አለን፡፡ ማታ፣ ማታ ማየት አለብኝ፡፡ ቤቴ የምገባው ከምሽቱ አንድ ሰዓት ነው፡፡ ከዚህ ወጥቼ ማኪያቶ መጠጣት እችል ነበር፡፡ አንዳንድ ሰው ዝም ብሎ እኝኝ የሚል አለ አይደል ከሥራ ጋር? እንደዚያ አድርገህ ውሰደኝ እኔን፡፡ ውጤታማ ነኝ ብዬ አምናለሁ፡፡ እደሰትበታለሁ፡፡ እውነት ለመናገር ሥራ ባጣ ሳምንት የምቆይ አይመስለኝም፡፡ ስለጠየቃችሁኝ አመሠግናለሁ፡፡ ነገር ግን ጊዜውን በደንብ ከፋፍሎ ለሚሠራ ሰው ጥሩ ምሳሌ ነኝ ብዬ አላምንም፡፡ የእረፍት ሰዓት፣ የመዝናኛ ሰዓት፣ የመዋኛ ሰዓትና የመሳሰሉት ላይ የለሁበትም፡፡ ቢኖር ኖሮ ትሰሙ ነበር፡፡