Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመንግሥት በነዳጅ ማከፋፈል ዘርፍ የማሻሻያ ዕርምጃዎች ሊወስድ ነው

መንግሥት በነዳጅ ማከፋፈል ዘርፍ የማሻሻያ ዕርምጃዎች ሊወስድ ነው

ቀን:

‹‹ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንደ ትውልድ መንደሩ በነፃነትና በደስታ ኦሮሚያ መጥቶ ኢንቨስት እንዲያደርግ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ››

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት

በርካታ ችግሮች ለሚታዩበት የኢትዮጵያ የነዳጅ ማከፋፈል ኢንዱስትሪ ዕድገት ያግዛሉ የተባሉ ዕርምጃዎች ለመውሰድ በዝግጅት ላይ መሆኑን መንግሥት አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ የነዳጅ ማከፋፈል ዘርፍ ከተጋረጡበት በርካታ ችግሮች መካከል አንዱና ዋነኛው በቂ የነዳጅ ማደያዎች በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች አለመኖር ነው፡፡ ለዚህም እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚጠቀሱት አከፋፋይ ኩባንያዎችና ቤንዚን ማደያዎች፣ ከነዳጅ ሽያጭ የሚያገኙት የትርፍ ህዳግ አነስተኛ መሆንና የነዳጅ ማደያዎችን ለመገንባት የሚውል ቦታ የማግኘት ችግር ናቸው፡፡

ነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች የሚያገኙት የትርፍ ህዳግ አነስተኛ መሆን በዘርፉ ኢንቨስት ለማድረግ እንደማያበረታታ በመግለጽ፣ መንግሥት ተገቢውን ማሻሻያ እንዲያደርግ ሲወተውቱ ቆይተዋል፡፡ ነዳጅ ማደያ ለመገንባት በተለይ በአዲስ አበባ መሬት ማግኘት ፈታኝ እንደሆነባቸው ኩባንያዎች ምሬታቸውን ሲገልጹ ነበር፡፡

በአገሪቱ በአጠቃላይ 710,000 ያህል ተሽከርካሪዎች የሚገኙ ቢሆንም፣ የማደያዎች ብዛት ደግሞ 700 ብቻ ነው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ 400,000 ያህል ተሽከርካሪዎች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ያሉት ማደያዎች ቁጥር 100 ያህል ብቻ ነው፡፡ እያንዳንዱ ማደያ 4,000 ተሽከርካሪዎችን የሚያስተናግድ በመሆኑ፣ ከሌሎች ችግሮች ጋር ተደማምሮ በየማደያዎች የመኪኖች ሠልፍ መመልከት የተለመደ ነው፡፡ የዘርፉን ዋና ዋና ችግሮች ለመቅረፍ መንግሥት በዝግጅት ላይ መሆኑን ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የማዕድን ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር አቶ ሞቱማ መቃሳ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የነዳጅ ኩባንያዎች የሚያገኙት የትርፍ ህዳግ አነስተኛ መሆን ለዘርፉ ዕድገት ማነቆ ስለሆነ እንዲስተካከል የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ መንግሥት ችግሩን በመረዳት የማዕድን፣ ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር፣ የንግድ ሚኒስቴር ኃላፊዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የሚገኙበት ኮሚቴ በማቋቋም በትርፍ ህዳግ ጉዳይ ላይ ጥናት ሲካሄድ መቆየቱን የገለጹት አቶ ሞቱማ፣ ጥናቱ እንደተጠናቀቀ ማሻሻያ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ጥናቱ በመጠናቀቅ ላይ ነው፡፡ በቅርብ ቀን ይጠናቀቃል የሚል እምነት አለን፡፡ ጥናቱ እንደተጠናቀቀ በጥናቱ ላይ ተመርኩዞ ተገቢው ማሻሻያ ይደረጋል፤›› ብለዋል፡፡ የመሬት ችግርን አስመልክቶ ለሪፖርተር ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጀማል ረዲ፣ ከዚህ በፊት በነበሩት ዘጠኝ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላኖች ላይ የነዳጅ ማደያዎች ሥርጭት በተጠና መንገድ እንዳልነበር ገልጸው፣ በአሥረኛው ማስተር ፕላን በአራቱም ማዕዘናት የማደያዎች ግንባታ በጥናት የሚስተናገድበት ሁኔታ መመቻቸቱን ተናግረዋል፡፡

‹‹ችግሩ በተጨባጭ የነበረ ነው፡፡ አስተዳደሩ ችግሩን ተመልክቶ የማደያዎች ግንባታ በአዲሱ ማስተር ፕላን በተጠና መንገድ እንዲካሄድ አካቷል፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎትን ባገናዘበ ሁኔታ ኅብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ በነዳጅ ማከፋፈል ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ትርጉም ባለው መንገድ መሬት በቅንጅት ለማቅረብ ዝግጅት ተደርጓል፤›› ያሉት አቶ ጀማል፣ የነዳጅ ኩባንያዎችና ባለሀብቶች ለሚያቀርቡት የመሬት ጥያቄ ከከተማዋ ማስተር ፕላን ጋር ተገናዝቦ፣ የኩባንያዎችና ባለሀብቶች አቅም ተገምግሞ ጥያቄው ምላሽ እንደሚያገኝ ተናግረዋል፡፡

አዲስ አበባ ውስጥ 103 ያህል ማደያዎች ብቻ እንደሚገኙ የጠቆሙት አቶ ሞቱማ፣ 250 ያህል ተጨማሪ ማደያዎች እንደሚያስፈልጉ በጥናት መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይህን ችግር ለመቅረፍ ከአዲስ አበባ አስተዳደር ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ለማደያ ግንባታ የሚሆኑ ከ60 እስከ 65 ቦታዎች ለማቅረብ አስተዳደሩ በዝግጅት ላይ ነው፡፡ በቀጣይ ተጨማሪ ቦታዎች ከማስተር ፕላኑ ጋር እያገናዘበ ማቅረቡን ይቀጥላል፤›› ብለዋል አቶ ሞቱማ፡፡

በተያያዘ ዜና ጎመጁ ኦይል ኢትዮጵያ የተሰኘ አዲስ አገር በቀል የነዳጅ ኩባንያ ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል ባለሥልጣናት በተገኙበት፣ እሑድ ሚያዝያ 29 ቀን 2009 ዓ.ም. በይፋ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡

ጎመጁ ኦይል ኢትዮጵያ አቶ ቴዎድሮስ የሺዋስና ባለቤታቸው ወ/ሮ ገነት ገብረ እግዚአብሔር በተባሉ ባለሀብቶች በ53 ሚሊዮን ብር ካፒታል ከሁለት ዓመት በፊት የተቋቋመ ሲሆን፣ 24 ዘመናዊ ማደያዎችን በአዲስ አበባና በርካታ የክልል ከተሞች ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ኢንቨስትመንት ገንብቶ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ኩባንያው የተለያዩ የነዳጅ ውጤቶች፣ ቅባትና ዘይቶች እንዲሁም ሬንጅ በማከፋፈል ሥራ የተሰማራ መሆኑን፣ ከማደያዎቹ ጎን ለጎን የሱፐር ማርኬትና ሌሎች ተያያዥ አገልግሎቶች እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡

ጎመጁ ኦይል በአዲስ አበባ ቱሉ ዲምቱ አካባቢ የአዲስ አበባ አዳማ የፍጥነት መንገድ መግቢያና ቢሾፍቱ ከተማ ያስገነባቸውን ዘመናዊና ግዙፍ የነዳጅ ማደያዎች አቶ ሞቱማ መቃሳ፣ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ዓብይ አህመድና አቶ ጀማል ረዲ መርቀው ከፍተዋል፡፡

ጎመጁ ኦይል በቢሾፍቱ ከተማ የፍጥነት መንገድ መውጫ ላይ 257 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባው ግዙፍ የነዳጅ ማደያና ሕንፃ ምርቃት ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ዓብይ ነዳጅ በጣም ውድና አስፈላጊ ምርት መሆኑን ጠቁመው፣ መንግሥት በዓመት ለነዳጅ ግዢ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የውጪ ምንዛሪ እንደሚያወጣ ገልጸዋል፡፡ በነዳጅ አቅርቦት ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች፣ ዴፖዎችና አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች ቁጥር ከኅብረተሰቡ ፍላጎት ጋር የተጣጣመ ባለመሆኑ ጎመጁ ኦይል ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ የነዳጅ ማከፋፈልና ተያያዥ አገልግሎቶችን በሰፊው መጀመሩ የሚያስመሰግነው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ አቶ ዓብይ መንግሥት በነዳጅ ማከፋፈል ዘርፍ ያለውን ፍላጎት ለማሟላት አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ወደ ዘርፉ እንዲገቡ በእጅጉ እንደሚፈልግ ተናግረዋል፡፡ ኩባንያው የሥራ ዕድል መፍጠር ብቻ ሳይሆን ለክልሉ ወጣቶች ሥራ እንዴት ተሠርቶ ሀብት እንደሚገኝ እንዲያስተምር የጠየቁት አቶ ዓብይ፣ የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጎፍ እንደሚያደርግለት ገልጸዋል፡፡

‹‹ኦሮሚያ ሰፊ መሬትና በርካታ ሥራ ወዳድና ፈላጊ ወጣት ያለበት በመሆኑ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንደ ትውልድ መንደሩ በነፃነትና በደስታ ኦሮሚያ መጥቶ ኢንቨስት እንዲያደርግ፣ ሠርቶ ማሠራትና አድጎ ማሳደግ እንዲችል በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ዓብይ በክልሉ ሕግና ሥርዓት ተከትለው ማልማት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች የክልሉ መንግሥት እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹በንፁህ እጅ ለማልማት የሚመጡ ባለሀብቶች አብረን ለመሥራት ዝግጁ መሆናችንን አውቀው ያለምንም ሥጋት ኢንቨስት ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎችንም ባለሀብቶች ወደ ክልላችን እየጋበዙ እንዲሠሩ፣ በአገራችን የተጀመረውን ዕድገት ለማስቀጠል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪዬን አቀርባለሁ፤›› ብለዋል፡፡

የጎመጁ ኦይል ኢትዮጵያ መሥራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ የሺዋስ ኩባንያቸው የተመሠረተው በአገሪቱ የነዳጅ ማከፋፈል ዘርፍ ያለውን ችግር ለመቅረፍ በማሰብ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ዘመናዊና የተሟላ ማደያዎችን በመገንባት፣ ጥራት ያለው የነዳጅ ውጤቶችን በማቅረብና የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት በኢንዱስትሪው ውስጥ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሠሩ የተናገሩት አቶ ቴዎድሮስ፣ ኩባንያቸው በሁሉም ክልሎች ማደያዎች እንደሚከፍትና ትራፊክ ፍሰት በሚበዛባቸውና ደረቅ ወደብ በሚገኙባቸው ከተሞች ትኩረት እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ስኬታማ ሥራ መሥራት ጀምረናል፡፡ ወደፊት የተሻለ ነገር ለማድረግ ከሕዝብና ከመንግሥት ጋር ሆነን ጥረት እናደርጋለን፡፡ በምንወደው ሕዝብ ማዕከል ይህን ኢንቨስትመንት በመጀመራችን ታላቅ ደስታ ይሰማናል፤››  ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፣ ለሥራቸው መሳካት ዕገዛ ላደረጉላቸው ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ለኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅትና ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የቀድሞ የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩትና የጎመጁ ኦይል ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ይግዛው መኮንን፣ በኢትዮጵያ የነዳጅ ማደያ ግንባታና ነዳጅ የማከፋፈል ተግባር ከተጀመረ ከ60 ዓመታት በላይ ማስቆጠሩን፣ ከዚህ ውስጥ ለ50 ዓመታት ያህል ሥራው በአራት ድንበር ዘለል ኩባንያዎች ተይዞ መቆየቱን አውስተዋል፡፡ ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ በርካታ አገር በቀልና የውጭ ኩባንያዎች በነዳጅ ማከፋፈል የሥራ ዘርፍ መሰማራታቸውን፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ጎመጁ ኦይል ኢትዮጵያን ጨምሮ 13 ኩባንያዎች በነዳጅ ማከፋፈል ሥራ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ 100 ሚሊዮን ሕዝብ ባላት ኢትዮጵያ ውስጥ 700 ያህል ብቻ የነዳጅ ማደያዎች እንደሚገኙ፣ በአንፃሩ 50 ሚሊዮን ሕዝብ ብዛት ባላት ጎረቤት ኬንያ 65 የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎችና 2,000 ያህል የነዳጅ ማደያዎች እንደሚገኙ በመግለጽ ዘርፉ ወደኋላ መቅረቱን አስረድተዋል፡፡

የነዳጅ ምርት ፍላጎት ከአገር ልማትና ዕድገት እንቅስቃሴ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በቂ የነዳጅ ማደያዎች ባለመኖራቸው ሳቢያ ነዳጅ ተጠቃሚው ኅብረተሰብና ተቋማት ለበርካታ ችግሮች እንደሚዳረጉ ግልጽ ነው፡፡ ነዳጁን ለማግኘት የሚኬደው ርቀት፣ በሠልፍ የሚጠፋው ጊዜ፣ የልማት ፕሮጀክቶች ነዳጁን በወቅቱ ባለማግኘታቸው የሚያስከትለው ኪሳራ ዕድገታችንን እንደሚፈታተን ማስተዋል ከባድ አይደለም፤›› ያሉት አቶ ይግዛው፣ የትርፍ ህዳግ አነስተኛ መሆን፣ ለነዳጅ ማደያ የሚሆን መሬት ያለመገኘትና የፈሳሽ ጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች እጥረት የነዳጅ ማከፋፈል ዘርፍ ዕድገት ማነቆዎች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

‹‹ከአንድ ሊትር ነዳጅ ሽያጭ ማደያው የሚያገኘው የትርፍ ህዳግ ሰባት ሳንቲም ብቻ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ 100 ብር አውጥቶ  የሚያኘው የትርፍ ህዳግ 44 ሳንቲም ወይም 0.44 በመቶ ነው፡፡ በሌሎች አፍሪካ አገሮች ከሚገኘው ዝቅተኛው ህዳግ ብር 1.50 በሊትር ጋር ሲነፃፀር ያለው ልዩነት በጣም ሰፊ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የነዳጅ ተደራሽነት ለማሳደግ በከተሞችና በገጠር የነዳጅ ማደያዎች መገንባት አስፈላጊ ቢሆንም፣ ለማደያ ግንባታ የሚውል በቂ ስፋት ያለው አመቺ ቦታ ማግኘት ትልቅ ፈተና እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የትርፍ ህዳግ አነስተኛ መሆን በጊዜ ሒደት መንግሥት ያስተካክለዋል በሚል ተስፋና እምነት ባለሀብቱ አገሩን ከማገዙ አንፃር ደፍሮ ወደዚህ ኢንቨስትመንት ለመግባት ቢወስን እንኳ፣ መሬት የማግኘት ችግር ባለሀብቱ ኢንቨስት የማድረግ ውሳኔውን ለመለወጥ የሚያስገድደው ሊሆን ይችላል፤›› ብለዋል፡፡ አቶ ይግዛው ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ጎመጁ ኦይል በትርፍ ህዳግ ዙሪያ ያለውን ችግር መንግሥት ያስተካክለዋል ከሚል እምነት ያሉትን ችግሮች ሁሉ ተቋቁሞ በነዳጅ አቅርቦት ዘርፍ ያለውን ችግር ለመፍታት በማሰብ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ወደ ዘርፉ በድፍረት ገብቷል፡፡

‹‹የትርፍ ህዳጉ ጉዳይ በሰኔ ወር መፍትሔ ያገኛል የሚል መረጃ አለን፡፡ የመሬት አቅርቦትና የፈሳሽ ጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች እጥረት ችግሮችም መፍትሔ ሊበጅላቸው ይገባል፤›› ያሉት አቶ ይግዛው፣ ጎመጁ ኦይል ከፍተኛ ጥራት ያላቸው የነዳጅ ውጤቶች በማቅረብና የተቀላጠፉ አገልግሎቶች በመስጠት በነዳጅ ኢንዱስትሪው ውስጥ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

ጎመጁ ኦይል በአዲስ አበባ፣ ቢሾፍቱ፣ ሞጆ፣ ድሬዳዋ፣ ሐዋሳ፣ ቀብሪበያ፣ መቐለ፣ ባህር ዳር፣ ጎንደርና አሶሳ 24 ማደያዎች በመገንባት ለ400 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩ፣ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት 150 ያህል ማደያዎች የመገንባት ዕቅድ እንዳለው ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...