Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሐሰተኛ ሰነድ ሕንፃ የገዙት የቀድሞ የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ጳጳስ ኪሳራውን ራሳቸው ከፈሉ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት አስተዳደር የነበሩትና አሁን የኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት የቅዱስ ሲኖዶስ አባል አቡነ ዘካርያስ፣ በሐሰተኛ ሰነድ ተጭበርብረው ሕንፃ በመግዛታቸው የከሰረውን ገንዘብ ከራሳቸው ክፍያ ፈጸሙ፡፡

አቡነ ዘካርያስ ከስምንት ዓመታት በፊት ያስተዳድሩት በነበረው ሀገረ ስብከት ሥር ለሚገኙ ደቀ መዛሙርት ማሠልጠኛና ለአብነት ትምህርት ቤቶች ድጋፍ እንዲሆን በማሰብ፣ አንድ ሕንፃ ለመግዛት ተስማምተው ከ1.6 ሚሊዮን ብር በላይ ቀብድ ከፍለው ነበር፡፡ ነገር ግን ሕንፃውን ለመሸጥ የተስማማቸው ግለሰብ ውል እንዲፈጸም ያደረገው፣ በሐሰተኛ የሰነድ ማስረጃ በመሆኑ ገንዘቡን እንደተቀበለ መሰወሩን በወቅቱ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ሐሰተኛ የካርታና የቦታ ማስረጃ ሰነዶችን ያቀረበው ሻጭ መሰወሩ እንደታወቀ፣ የሰበካ ጉባዔው የሥራ አስፈጻሚ አባላት በሕግ የተጠየቁ ቢሆንም ‹‹መንፈሳዊ አባታችን ስላዘዙን ገንዘቡን ወጪ አድርገናል፤›› በማለት የሰጡትን ቃል አቡነ ዘካርያስ በመደገፍ ‹‹ኃላፊነቱን እኔ እወስዳለሁ፤›› በማለታቸው፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በነፃ ተሰናብተዋል፡፡

አቡነ ዘካርያስ ከምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ወደ አሜሪካ የሰሜን ምሥራቅ፣ ደቡብ ምሥራቅና መካከለኛ ኒውዮርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው የተመደቡ ቢሆንም፣ ሐሰተኛ ሰነድ መሆኑን ሳያውቁ ተጭበርብረው እንዲከፈል ትዕዛዝ የሰጡበትን ክፍያ ላለፉት ስምንት ዓመታት ሳይከፍሉ ቆይተው፣ በሁለት የዕለተ ሰንበት (እሑድ) የምዕመናን ተሳትፎ 1.6 ሚሊዮን ብር በማሰባሰብ ገቢ አድርገዋል፡፡

ገንዘቡ ለምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ተመላሽ ወይም ገቢ እንዲያደርጉ ተልከው አዲስ አበባ የመጡት ሊቀ ማዕምራን ሙሴ ሐረገ ወይን (ዶ/ር) እና የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ክፍል ኃላፊ አቶ ሰናይ ምንውየለት ናቸው፡፡ ሁለቱ መልዕክተኞች ገንዘቡን ያስረከቡት ሚያዝያ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ነው፡፡ ተወካዮቹ ገንዘቡን ያስረከቡት ፓትርያርኩ አቡነ ማቲያስ (ቀዳማዊ)፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማርቆስ በተገኙበት ነው፡፡

አቡነ ዘካርያስ በሥራ ብዛት በሐሰተኛ ሰነድ የተጭበረበሩትን ገንዘብ ሳይመልሱ መክረማቸውን በተወካዮቻቸው በኩል አስረድተዋል፡፡ አቡነ ዘካርያስ፣ ‹‹ሰው በፖለቲካ እንጂ በሃይማኖቱ መለያየት የለበትም፣ ወይም ልዩነት ሊኖረው አይገባም፤›› በማለት በውጭ የሚገኘውንና በአቡነ መርቆሬዎስ የሚመራውን ወደ አንድ ሲኖዶስ ለመመለስ ጠንክረው እየሠሩ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በሰጡት ቡራኬም ግለኝነትና እርስ በርስ መቀማማት በበዛበት ዓለም፣ አቡነ ዘካርያስ የፈጸሙትና እየፈጸሙት ያለው አባታዊ ተግባር ‹‹የክፍለ ዘመኑ ሐዋርያ›› ሊያሰኛቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ስላደረጉት አባታዊና ተቆርቋሪነት የበዛበት ተልዕኮ በቤተ ክርስቲያኗ ስም ምሥጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች