የአማራ ክልል የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የሥምሪት ተቆጣጣሪ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ግለሰብ ሕይወት በተሽከርካሪ አደጋ ማለፉን የሪፖርተር ምንጮች ገለጹ፡፡
ሐሙስ ሚያዝያ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ከባህር ዳር ወደ ዳንግላ በኮስተር መኪና ተሳፍረው ሲጓዙ የነበሩት የአማራ ክልል የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ሥምሪት ተቆጣጣሪ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስማቸው አማረ፣ በተሽከርካሪ አደጋ ሕይወታቸው ማለፉን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
አቶ ስማቸው የአማራ ክልል የመንገድና ትራንስፖርት ሥምሪትን በዋና ዳይሬክተርነት መምራት የጀመሩት በቅርብ ጊዜ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የክልሉ የመንገድና የትራንስፖርት ሥምሪት ያለበትን ችግር በማጥናትና አዲስ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት፣ በክልሉ የሚደርሰውን የተሽከርካሪ አደጋና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን ለዘለቄታው ለመፍታት ጥረት ሲያደርጉ እንደነበረ የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡
አቶ ስማቸው ሕይወታቸው ከማለፉ ሳምንት ቀደም ብሎ ከአማራ ክልል ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ በባህር ዳር ከተማ ስላለው አዲሱና አሮጌው የአውቶብስ መናኸሪያ ጉዳይ ሰፋ ያለ መረጃ ለክልሉ ሕዝብ ሲሰጡ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡
አቶ ስማቸው ቤተሰቦቻቸው ዳንግላ ከተማ ስለሚኖሩ ዘወትር ቅዳሜና እሑድ ወደ ዳንግላ ከተማ እንደሚመላለሱ የታወቀ ሲሆን፣ በዚህ የትራፊክ አደጋም ከአራት የሚበልጡ ሰዎች ሕይወት እንዳለፈ ተሰምቷል፡፡