Tuesday, May 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የጂፒኤስ ቴክኖሎጂ ጅምሮች

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከበርካታ የአገልግሎት ዘርፎች መካከል አንዱ የሆነው የትራንስፖርት ዘርፍ ሲሆን በዚህ ዘርፍ የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ በርካታ ችግሮች ይታያሉ፡፡ ከችግሮቹ አንዱ በዘመናዊ አሠራሮችን ያልታጠቀ ነው፡፡ አገልግሎት ላይ ያሉ ተሽከርካሪዎችን በአግባቡ የማስተዳደር ልምዱም ቢሆን ገና ከልማዳዊ አሠራር አልተላቀቀም፡፡ ዘርፉ ካሉበት በርካታ ተግዳሮቶች ውስጥ የተሽከርካሪዎችን ስምሪት በዘመናዊ መንገድ ማስተዳደርና መቆጣጠር አለመቻልም ይጠቀሳል፡፡ ዘርፉን ለማዘመን እንደሚያግዙ ከሚታመንባቸው የአሠራር ስልቶች መካከል ተሽከርካሪዎች ላይ አቅጣጫ ተቋሚና አመላካች መሣሪያ ወይም ጂፒኤስ በመግጠም ስምሪታቸውን ከማዕከል በማስተናበር እያንዳንዱን እንቅስቃሴያቸውን መቆጣጠር የሚያስችለው ቴክኖሎጂ ተጠቃሽ ነው፡፡ በተሽከርካሪዎች ላይ ተገጥሞ በሞባይል ስልኮችና በኮምፒውተር መቆጣጠር የሚያስችለውን ይህንን ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ ለማዋል እንቅስቃሴ ከተጀመረ ስምንት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በጂፒኤስ አማካይነት ተሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችለውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋሙ ኩባንያዎች ቁጥርም ተበራክተዋል፡፡ ስምንት ኩባንያዎች እንዳሉም ይታመናል፡፡ ሆኖም በቴክኖሎጂው የሚጠቀሙ ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰብ ባለንብረቶች ቁጥር አነስተኛ መሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡ ቴክኖሎጂው በመግጠምና በመከታተል አገልግሎት ከሚሰጡ ኩባንያዎች መካከል ካሳ ሶፍትዌር ትራኪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሲሆን፣ የኩባንያው ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ካሳ፣ ቴክኖሎጂው ከሚሰጠው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አንፃር ተጠቃሚው አነስተኛ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ አቶ ሰለሞን ቴክኖሎጂው ለባለንብረቶች ከሚሰጠው አገልግሎት በላይ በኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖረው አስተዋጽኦ እንደሚጎላም ይገልጻሉ፡፡ እየተጠቀሙበት የሚገኙ ግለሰቦችና ተቋማት ንብረታቸውን ከየትኛውም ሥፍራ ሆነው ያለገደብ ለመቆጣጠር ከመቻላቸውም በላይ፣ ከአሽከርካሪዎች ጋር የነበሩ አለመግባባቶችን ለማስቀረት እንዳገዛቸውም ይጠቅሳሉ፡፡ ከወራት በፊት በአገሪቱ በተከሰተው ፖለቲካዊ ግርግር ሳቢያ የጂፒኤስ አገልግሎት በመቋረጡ፣ በቴክኖሎጂው ሲጠቀሙ የነበሩ ተቋማትን ምን ያህል እንደተጎዱም አቶ ሰለሞን ያስታውሳሉ፡፡ ዳዊት ታዬ በቴክኖሎጂውና በአገልግሎቶቹ ዙሪያ አቶ ሰሎሞን ካሳን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከጂፒኤስ አገልግሎት ጋር የተሳሰረውን ቢዝነስ እንዴት መረጡ?

አቶ ሰለሞን፡- ይሄንን ቢዝነስ የመረጥንበት ዋነኛ ምክንያት ዜጎች ንብረት ካፈሩ በኋላ ንብረቶቻቸውን በአግባቡ ለመቆጣጠር የሚያስችል ዘመናዊ አሠራር ያልዳበረ መሆኑን በመረዳት፣ በዚህም ዜጎች እንደሚማረሩ በመገንዘባችን ነው፡፡ በተለይ ከተሽከርካሪዎች ስምሪትና አገልግሎት አሰጣጥ አንፃር የሚታዩ ችግሮችን በጥልቀት አስጠንተን፣ የአገራችን የትራንስፖርት ዘርፍ ከዚህ ችግር በመውጣት ወደ ዘመናዊ አሠራር እንዲገባ አንዱ መፍትሔ ተሽከርካሪዎችን በዘመናዊ መንገድ ለመቆጣጠርና ለማስተዳደር የጂፒኤስ አገልግሎትን ጠቀሜታ በመገንዘባችን ነው፡፡ ባደረግነው ጥናት መሠረት ቴክኖሎጂው በሌላው ዓለም እየተስፋፋና እያደገ የመጣ የቢዝነስ ዘርፍ ነው፡፡ የቴክኖሎጂው ተጠቃሚዎችን፣ እኛንና መንግሥትን በአጠቃላይ አገርን የሚጠቅም በመሆኑ፣ ወደፊት እየተስፋፋ የሚሄድ ቢዝነስ ይሆናል በሚል እምነት የገባንበት ነው፡፡ የዚህ ቴክኖሎጂ ጠቀሜታ በተለያየ መንገድ ሊገለጽ ይችላል፡፡ ጂፒኤስ የተገጠመለት ተሽከርካሪ በፕሮግራም እንዲሠራ ይረዳል፡፡ ሾፌሮችም በጂፒኤስ ቁጥጥር የሚደረግባቸው መሆኑን ስለሚያውቁ በተቀመጠላቸው ጊዜ ውስጥ የተባሉት ቦታ እንዲደርሱ በማገዝ የትራንስፖርት አገልግሎቱ የተቀላጠፈ አሠራር እንዲኖረው ማስቻሉም ሊጠቀስ ይችላል፡፡ የተሽከርካሪዎቹ ባለንብረቶችም በቀላሉ ንብረቶቻቸውን ለመቆጣጠር አቅም ይፈጥርላቸዋል፡፡ የቴክኖሎጂው አገልግሎት ተሽከርካሪዎች የት ቦታ ላይ ናቸው? የተባሉት ቦታ በትክክል ደርሰዋል ወይ? የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ ብቻም ሳይሆን፣ ሌሎች መረጃዎችንም የትራንስፖርት ድርጅቱ ባለቤት እንዲያገኝ የሚያስችለው ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ስለቴክኖሎጂው ጠቀሜታዎች ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ስለ ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ መረጃ ከመስጠት ባሻገር የሚሰጠው ሌላ ጠቀሜታ አለ? ለምሳሌ የነዳጅ ብክነት ይቀንሳል የሚባለው እንዴት ነው?

አቶ ሰለሞን፡- እንደሚታወቀው በትራንስፖርት ዘርፍ ነዳጅ ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል፡፡ የዚያኑ ያህል በትራንስፖርት ዘርፍ ውስጥ በተለያየ መንገድ ነዳጅ ይባክናል፡፡ ይሰረቃል፡፡ ስለዚህ ያልተገባ የነዳጅ ወጪ ለማውጣት የሚገደዱ በርካቶች ናቸው፡፡ አሸከርካሪዎችና ባለንብረቶች በዚህ ሳቢያ ይጋጫሉ፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ ለነዳጅ ብክነት መፍትሔ አለው፡፡ በተለመደው አሠራር አንድ ተሽከርካሪ ስምሪት ከወጣ በኋላ እንዲህ ያለውን ነገር ለመቆጣጠር የሚችሉበት ዕድል አልነበረም፡፡ ጂፒኤስ የተገጠመለት ተሽከርካሪ ግን ምን ያህል ነዳጅ እንደተጠቀመ መረጃ ይሰጣል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ጂፒኤስ የገጠመለት ተሽከርካሪ፣ ለአደጋ ተጋላጭነቱ ይቀንሳል፡፡ ምክንያቱም የሾፌሮችን አነዳድ በቀላሉ መቆጣጠር ስለሚያስችል ነው፡፡ ባለንብረቱ ተሽከርካሪዬ ከዚህ በላይ ፍጥነት እንዳይኖረው እፈልጋለሁ ካለ በሚፈልገው የፍጥነት ወሰን መሠረት ሶፍትዌሩ እንዲሠራ በማድረግ አሽከርካሪውን መቆጣጠር ይችላል፡፡

ለምሳሌ አንድ የማሽን አከራይ ዶዘር ሊሆን ይችላል በቀን ምን ያህል ሰዓት እንደሠራ ለማወቅ ይህ ቴክኖሎጂ እገዛ ያደርግለታል፡፡ አንድን መኪና ለማስተዳደር የሚቸገሩ ሰዎች፣ በዚህ ቴክኖሎጂ ከተጠቀሙ 30 መኪኖች ቢኖራቸው እንኳ 30ውንም ካሉበት ሆነው መቆጣጠር ያስችላቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ተጨማሪ ንብረት እንዲያፈሩ መንገድ ይከፍትላቸዋል፡፡ ስለዚህ ለኩባንያዎች ዕድገትም አስተዋጽኦ አለው ማለት ነው፡፡ የእያንዳንዱን አሽከርካሪዎቻቸውን የሥራ አፈጻጸም በመረጃ ማግኘት ይችላሉ፡፡ ተሸከርካሪዎቹ ምን ያህል ደንበኞች ጋር ደረሱ? ምን ያህል ሸጡ? የቱ ጋ ቆሙ? ምን ያህል ሰዓት ፈጁ? ስለሚሉት ጥያቄዎቻቸው ሁሉ መረጃ ስለሚሰጣቸው፣ ቴክኖሎጂው በደንበኞችና በአሠሪዎች መካከል የግንኙነት ድልድይ ይፈጥራል፡፡ በዚህ ድልድይ መሠረት ሁሉንም ነገር በቀላሉ ማከናወን ይቻላል፡፡ ቴክኖሎጂው የሚያበረክተው ሌላው ዕድል ደግሞ የተሽከርካሪዎችን ስምሪትና አጠቃላይ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ድንበር የማይገድበው መሆኑ ነው፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ሆነው እያንዳንዱን የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ያስችላል፡፡   

ሪፖርተር፡- ቴክኖሎጂው ይህንን ያህል ጥቅም ካለው ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል ተቀባይነት አግኝቷል? ከአገራችን የሥራ ባህል በተለይም በትራንስፖርቱ ዘርፍ ውስጥ ከሚታየው የዘልማድ አሠራር፣ አሽከርካሪዎችም ሆኑ ባለንብረቶች እንዴት እየተቀጠሙበት እንደሚገኙ እናንተስ ጥቅሙን አሳውቃችሁ ለውጥ እንደመጣ መናገር የምትችሉበት ደረጃ ላይ ደርሳችኋል?

አቶ ሰለሞን፡- ይህ ቴክኖሎጂ የሰውን የማሰብ ብቃት ጭምር የሚያሳትፍ ነው፡፡ ምክንያቱም ከዚህ ቀደም የምርት ኃይሎች የሚባሉት፣ የሰው ጉልበት፣ ገንዘብና መሬት ነበሩ፡፡ አሁን የምርት ኃይሎች ከሚባሉት ውስጥ የሰው የማሰብ ችሎታ ተካቷል፡፡ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መስክ አደጉ የምንላቸው አገሮች ከዚህ ቀደም ይጠቀሙበት የነበረው ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ በየጊዜው ተሻሽሎ የመጣው ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ግን ደግሞ አነስተኛ ወጪን የሚጠይቅ ነው፡፡ በዚህ ቴክኖሎጂ አንድ ሰው በኮምፒውተር ወይም በስማርት ስልክ አማካይነት የፈለጋቸውን ነገሮች ማከናወን እየቻለ በመምጣጡ፣ ለዚህ ቴክሎጂ የሚደረገው ኢንቨስትመንትም ብዙ ገንዘብ የሚፈልግ አይደለም፡፡ ስለዚህ ሰዎች እስካመኑበት ድረስ መጠቀም የሚያስችላቸውን ግንዛቤ ሊዳብሩ ይገባቸዋል፡፡ ይህ እንደየሰዎቹ ባህርይና አቅም ይወሰናል፡፡ ስለቴክኖሎጂው ጠቀሜታና አገልግሎት እኛ ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎች አካላትም ሊያስተዋውቁት ይገባል፡፡ እኛ የምንችለው እንደ አንድ የቢዝነስ ተቋም ለአገር ሊጠቅም እንደሚችል፣ ኩባንያዎችም ከዚህ ቴክኖሎጂ የሚያገኙት ጠቀሜታ ለዕድገታቸው መሠረት እንደሆነ እንደሚቻለን መጠን ማሳወቅ ነው፡፡ በዚህ አገልግሎት መስፋፋት ኩባንያዎች ብቻ ሳይሆኑ መንግሥትም ሆነ ኅብረተሰቡ እንደሚጠቀሙ ለመግለጽ እንሞክራለን፡፡ በተለይ ደግሞ ዘመናዊ አሠራርን ከማጎልበት አንፃር የሚሰጠውን ዕድል እየገለጽን ነው፡፡ ድጋፍ ግን ያስፈልጋል፡፡ በቴክኖሎጂው የሚጠቀሙ ድርጅቶች አሉ፡፡ ለመጠቀም ገና የሚመጡም አሉ፡፡ ስለቴክኖሎጂው ያልተገነዘቡም አሉ፡፡ ብዙ መሥራትን ይጠይቃል፡፡  

ሪፖርተር፡- ስለቴክኖሎጂው አተገባበር በርካቶች ተገቢው መረጃ እንደሌላቸው ይታመናል፡፡ ለግንዛቤ ያህል ጂፒኤስ ምንድነው? እንዴትስ ነው እናንተ አገልግሎቱን የምትሰጡበት?

አቶ ሰለሞን፡- ጠቅለል ባለ መልኩ ስለጂፒኤስ አመጣጥ ትንሽ ልንገርህ፡፡ ቴክኖሎጂው የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋማት ሲሠሩበት የቆየ ነው፡፡ በአንድ አጋጣሚ ግን ይህንን ቴክኖሎጂ ለወታደራዊ አገልግሎት ብቻ ለምን እንጠቀምበታለን የሚል ሐሳብ ተነስቶ፣ ከአሥር ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት ተደርጎበት ለምን ለሲቪል አገልግሎት አይውልም? በሚል መነሻ እ.ኤ.አ. በ1983 ጥቅም መስጠት ጀመረ፡፡ በቀደመው ጊዜ እነ ቫስኮ ደጋማ እነ ክርስቶፎር ኮሎምበስ ለአሰሳ ሲጓዙ፣ ትክክለኛውን ቦታ ለማግኘት ፀሐይን፣ ከዋክብትን ወይም ጨረቃን ምልክት እያደረጉ ነበር በኮምፓስ የሚጠቀሙት፡፡ አሁን ሁሉ ነገር ተለውጧል፡፡ ጂፒኤስ በየትኛውም ቦታ ከአራት ወይም ከዚያም በላይ ሳተላይቶች እያገዙት የሚሠራ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ 24 ሳተላይቶች ዓለምን ይዞራሉ፡፡ 2,200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሆነው 24ቱ ሳተላይቶች በዓለም ዙሪያ በሰዓት 14 ሺሕ ኪሎ ሜትር እየዞሩ፣ በ12 ሰዓት አንድ ጊዜ ዓለምን በመዞር ምድር ላይ የሚፈልጉትን አቅጣጫዎች በማሰስ መረጃ ያቀብላሉ፡፡ ቴክኖሎጂው ተቀባይ መሣሪያ ወይም ሪሲቨር አለው፡፡ ሳተላይቶቹ የሚረጩትን ጨረር ሪሲቨሩ ተቀብሎ ርቀቱ ስንት እንደሆነ ያሰላል፡፡ ሳተላይቶቹ ቦታውን ለይተው መረጃውን ወደ ሲም ካርድ በመላክ በሰርቨር አማካይነት ሰዎች የሚፈልጉትን ቦታ እንዲያገኙ፣ መኪናቸው ያለበትን ቦታ፣ የሚጓዝበትን የፍጥነት ወሰን፣ ወዴትና የት እንደሄደ የሚያመላክቱ መረጃዎችን እንዲያገኙ ይረዳቸዋል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የጂፒኤስ አልግሎትን ያነሳነው ተሽከርካሪዎች ላይ ተገጥሞ በመሥራት ላይ ካለው ቴክኖሎጂ አኳያ ነው፡፡ ከገለጻዎ መረዳት እንደቻልኩት የጂፒኤስ አገልግሎቶች በርካታ እንደሆኑ ነው፡፡ በአገራችን በዚህ ቴክኖሎጂ ልንጠቀምባቸው የምንችላቸው ሌሎች አገልግሎቶች ምንድን ናቸው?

አቶ ሰለሞን፡- ከሁሉም የቢዝነስ ዘርፎች ጋር የተያያዘ አገልግሎት ይሰጥበታል፡፡ ለብዙ ነገር ልትጠቀምበት ትችላለህ፡፡ አሁን የምናወራው ከተሽከርካሪዎት አንፃር ሆነና ሐሳባችንን መሰብሰብ አስፈለገን እንጂ፣ ከዚህ ቢዝነስ ውጪ ያሉ ዘርፎችንም ቴክኖሎጂው ይደግፋል፡፡ በተሽከርካሪዎችም ቢሆን አገልግሎቱ የተለያየ ነው፡፡ ለምሳሌ ከተሽከርካሪዎች ደኅንነት አንፃር ስንመለከተው፣ አጠቃላይ የትራንስፖርቱ ዘርፍ ጂፒኤስ መጠቀም ቢችል ኑሮ የአገሪቱን የተሽከርካሪ አደጋዎች ቁጥር መቀነስ የሚቻልበት ዕድል አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን በደንብ ቢያብራሩት፡፡

አቶ ሰለሞን፡- ለምሳሌ የጂፒኤስ አገልግሎትን ከመገኛ ብዙኃን ሥራ ጋር አገናኝተህ ልትተገብረው ትችላለህ፡፡ ሌሎች መንገዶችም አሉ፡፡ የት አካባቢ የትራፊክ መጨናነቅ እንዳለ በመመልከት መረጃውን ተሽከርካሪዎቹ ቀድመው እንዲያገኙት ማድረግ ትችላለህ፡፡ የቱ ጋር ዝናብ ሊዘንብ ይችላል? የሚለውንና የመሳሰሉትን መረጃዎች አሽከርካሪዎች እንዲያገኙ በማድረግ አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ ለማድረግ ያስችላል፡፡ አመቺ ያልሆኑ ወይም አደጋ የተከሰተባቸው ቦታዎች ሲኖሩም አሽከርካሪው በምን ያህል ፍጥነት መጓዝ እንዳለበትና ጥንቃቄ እንዲያደረግ የሚያሳስቡ መረጃዎችን ታስተላልፍበታለህ፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ፈተና የሆነው የትራፊክ ማኔጅመንት ነው፡፡ የትራፊክ ፍሰቱ የተጨናነቀ ነው፡፡ ይህንን ለማስተካከል ቴክኖሎጂው በምን መልኩ ሊጠቅም ይችላል?

አቶ ሰለሞን፡- ሌሎች አገሮች በዚህ ቴክኖሎጂ ይጠቀሙበታል፡፡ ተሽከርካሪው አደጋ ሲኖር መረጃ ቀድሞ እንዲያገኝ በማድረግ ከአደጋ እንዲጠበቅ ያደርጋሉ፡፡ የተጨናነቀ የትራፊክ ፍሰት ካለ፣ አሽከርካሪዎች በዚያ መስመር እንዳይገቡ ያደርጋል፡፡ አማራጮችን ይሰጣል፡፡ ጂፒኤሱን በመጠቀም ማሳወቅ ይቻላል፡፡ ትልቅ እገዛ ያደርጋል፡፡ እዚህ አገር በጂፒኤስ መጠቀም ካልተቻለ በቀር ለስንቱ መኪና የትራፊክ ፖሊስ አቁመህ ትችላለህ? ሕዝቡ ብዙ ነው፡፡ ተሽከርካሪውም እየበዛ ነው፡፡ የትራፊክ መጨናነቁን ስታየውም ይህንን ማኔጅ ለማድረግ በጂፒኤስ የተደገፈ ሥራ መሠራት እንደሚያስፈልግ ያሳይሃል፡፡

ሪፖርተር፡- የእኛ አገር ተሽከርካሪዎች በዚህ ቴክኖሎጂ መጠቀም የሚችሉበት አመቺ ሁኔታ ተፈጥሯል? መሠረተ ልማቱስ ተዘርግቷል?

አቶ ሰለሞን፡- መሠረተ ልማቱማ አለ፡፡ ይህንን መጠቀም የሚያስችሉ ዕድሎችም አሉ፡፡ ብዙ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅም አይደለም፡፡ ብዙ የሚፈልግ ነገር አይደለም፤ ቢሮ ውስጥ የምታደራጀው ነገር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጂፒኤስ ቴክኖሎጂውን እንዴት እየተጠቀማችሁበት ነው? ከኢትዮቴሌኮም ጋር ያላችሁ ግንኙነትስ እንዴት ነው?

አቶ ሰለሞን፡- የምናስመጣቸው የጂፒኤስ ቴክኖሎጂዎች በኢትዮቴሌኮም ፈቃድ አግኝተን ነው፡፡ የምንጠቀመውም የቴሌን ሲም ካርድ ነው፡፡ ሁሉም ደንበኞች መረጃዎችን የሚያገኙት የቴሌን ሲም ካርድ ተጠቅመው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከወራት በፊት አገሪቱ ውስጥ ተፈጥሮ በነበረ አለመረጋጋት ጂፒኤስ ያስገጠሙ ኩባንያዎች አገልግሎት ተቋርጦባቸው ስለነበር ተሽከርካሪዎቻቸውን መቆጣጠር አልቻሉም ነበር፡፡ እንዲህ ያለው መቆራረጥ አገልግሎቱን በምን መልኩ ይጎዳዋል? ከፀጥታ አኳያ ችግር ቢፈጠርና ኔትወርክ ቢቋረጥ አገልግሎቱን ለማስቀጠል አማራጩ ምንድን ነው?

አቶ ሰለሞን፡- በዚህ አገልግሎት ዙሪያ ሁሉም ባለድርሻ አካላት አጽንኦት ሊሰጡበት ይገባል፡፡ ባለፉት ሦስት ወራት አገልግሎቱ በመቋረጡ እኛን ጎድቶናል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ማግኘት የሚባውን ገንዘብ ማግኘት አልቻለም፡፡ ተገልጋዮችም ንብረታቸውን ለመቆጣጠር አልቻሉም፡፡ ደንበኞች ወጪ ያደረጉበትን አገልግሎት ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ እንዲህ ያለ ነገር ሲፈጠር ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማነጋገር እንዴት ጉዳቱን መቀነስ እንደሚቻል በውይይት ማስተካከያ ማድረግ ይቻላል፡፡ ከዚህ በኋላም እንዳይደገም መመካከሩ ግድ ይላል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ቴክኖሎጂውን ለማስፋፋት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ዘመናዊ አገልግሎትን ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት ላይ እንቅፋት ሊፈጥር ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ቴክኖሎጂው እየተገጠመ ያለው በትላልቅ ተሽከርካሪዎች ላይ ነው፡፡ በታክሲዎችና ሌሎችም ተሽከርካሪዎች ላይ ለምንድን ነው ሲዘወተር የማይታየው?  ምርቶችን በሚያከፋፍሉትስ ረገድ ቴክኖሎጂው ምን ዓይነት ድጋፍ መስጠት ይችላል?

አቶ ሰለሞን፡- ቴክኖሎጂው በመንግሥት መደገፍ አለበት፡፡ በከተማ ታክሲዎችም ሆነ በአውቶብሶች ብሎም በሁሉም ላይ ገጥሞ መሥራቱ ብዙ ጠቀሜታ አለው፡፡ ጂፒኤስ የሚሰጠው መረጃ በርካታ ነገሮችን ያቃልላል፡፡ አንድ ተሽከርካሪ አደጋ ቢያደርስ የአደጋውን መንስዔ ለማወቅ የሚደረጉ ምርመራዎችን ለማፋጠን ይረዳል፡፡ ምክንያቱም ጂፒኤስ የተገጠመለት ተሽከርካሪ በምን ያህል ፍጥነት ይሽከረከር እንደነበር በቀላሉ ታውቃለህ፡፡ መረጃውንም በሰነድ አትሞ ማውጣት ይችላል፡፡ ሁሉንም የጉዞ ታሪክ ያስቀምጣል፡፡ ከሕግ አንፃር ድጋፍ ይሰጣል፡፡ መንግሥትን ይጠቀማል፡፡ ዋናው የእኛ ዓላማም ይኼው ነው፡፡ ጂፒኤስ ሲባል እኮ መኪናውን ብቻ አይደለም የምትቆጣጠረው፡፡ መኪናዎቹ ሲንቀሳቀሱ ይዘውት የማሄዱትንም ምርት ነው፡፡ ለምሳሌ መድኃኒት ስታከፋፍል ለማን ሰጡ፣ እንዴት ሰጡ የሚለውን ሁሉ ታያለህ፡፡ የዕርዳታ ድርጅት ዕርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎቹ በትክክል ለተረጂው ስለማድረሳቸው ለመቆጣጠር የሚቻልበት አንዱ መንገድ እኮ ይህ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ ብዙዎች ግን ስለ ቴክኖሎጂው ዕውቀት የላቸውም፡፡ ፍራቻም አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ቴክኖሎጂው ይህንን ያህል ጠቀሜታ ካለውና የትኛውንም ወገን ከጠቀመ ተገልጋዮች ለምን አላፈራም? ለአገልግሎቱ የሚጠየቀው ዋጋ መብዛት ምክንያት ሊሆን ይችላል?

አቶ ሰለሞን፡- ነፃ ገበያ ስለሆነ ሁላችንም ተወዳድረን ነው ዋጋ የምንሰጠው፡፡  ብዙ ግን ከሚሰጠው ጥቅም አንፃር ክፍያው አነስተኛ ነው፡፡ ዋናው ነገር ቴክኖሎጂውን ከሸጥን በኋላ የምንሰጠው ድኅረ አገልግሎት ነው፡፡ ደንበኛህን መጠበቅ መቻል አለብን፡፡ ያለውን በደንብ ስለያዝነው ህልውናችንን ማቆየት ችለናል፡፡ እንደ መሣሪያው ዓይነት ዋጋውም ይለያል፡፡ ለአንድ ተሽከርካሪ የሚገጠሙ ጂፒኤስ ከ5,000 እስከ 8,000 ብር ይጠይቃል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የወጣበትን ተሽከርካሪ በዚህ ዋጋ መጠበቅ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ባለፈው ጊዜ ለሦስት ወር ያህል የጂፒአርስ ኔትወርክ ሲቆም ገቢያችን መቀነሱ ብቻ ሳይሆን፣ ተገልጋዮች ንብረታቸውን ለመቆጣጠር አለመቻላቸው ጎድቷቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በቴሌኮም ኔትወርክ መቋረጥ ብቻም ሳይሆን ከዚህ ውጪ ባሉ ጉዳዮች አገልግሎቱ ሊቋረጥ የሚችልባቸው ሌሎች መንስዔዎች የሉም? የአገልግሎቱ ሽፋንስ ምን ይመስላል?

አቶ ሰለሞን፡- ከቴሌኮም ኔትወርክ ውጭ ከሆነ የተቋረጠው ችግሩ የእኛ ይሆናል፡፡ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል ኔትወርክ አለ፡፡ አሁን እኮ ኦሞ ሸንኮራ ፋብሪካ ላይ ጂፒኤስ ተገጥሞ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በዚያ መስመር መኪኖቻቸው ላይ ጂፒኤስ ያስገጠሙ ድርጅቶች እንደልብ መቆጣጠር ችለዋል፡፡ ኔትዎርኩ ባይኖር ኑሮ ንብረታቸውን መቆጣጠር አይችሉም ነበር፡፡ ይህ መልካም ነገር ነው፡፡ ቴክኖሎጂውን እንዴት እንጠቀምበት የሚለውን ማሰብ አለብን፡፡ ተሽከርካሪዎቻቸውን ሩቅ ቦታ ያሰማሩ ድርጅቶች ንብረታቸውን ያለ ችግር መቆጣጠር ችለዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ መኪኖች ከተከለለላቸው ቦታ ውጭ ሲወጡም ሆነ ሲገቡ ባለንብረቱ ወዲያው መረጃ የሚያገኝበት አገልግሎት ተፈጥሯል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ለአንድ ፕሮጀክት ሥራ የተላከ መኪና ከፕሮጀክቱ አጥር ውጭ ሲወጣ የሚያሳየውን መረጃ ይዘህ ወዲያውኑ ተመለስ ማለት ትችላለህ፡፡ ከዚህ ሥፍራ ውጭ ተሽከርካሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ የሚያደርግ ፕሮግራም ከጫንክ በዚያ መሠረት ስለሚሠራ የሚፈጠር ችግር አይኖርም፡፡ ተሽከርካሪው የመጨረሻው ፍጥነት ወሰን 80 ኪሎ ሜትር መሆን አለበት ካልክና አሽከርካሪው ከ80 ኪሎ ሜትር በላይ በሰዓት እየነዳ ከሆነ፣ ከተቀመጠለት ፍጥነት በላይ መጓዙን የሚገልጽ ሪፖርት ይደርስሃል፡፡ ሌላው ተሽከርካሪን ለመጠገን፣ ጎማ ለመቀየር ስትፈልግ፣ ይህንን መቼ እንደምታደርግ ለሶፍትዌሩ በምትሰጠው መረጃ መሠረት ጊዜው ሲደርስ ይጠቁምሃል ማለት ነው፡፡ አስታዋሽ ነው ማለት ነው፡፡ መኪናህ ለስንት ሰዓት ቆሞ እንደነበር ሁሉ ይነግርሃል፡፡ ኢንሹራንስ ኩባንያዎችም ጂፒኤስ ለተገጠመላቸው ተሽከርካሪዎች የመድን ዋጋ ይቀንሳሉ፡፡ ምክንያቱም ጂፒኤስ የተገመለት ተሽከርካሪ አደጋ የማድረስ ዕድሉ ካልተገጠመለት መኪና ያነሰ በመሆኑ፣ እንዲህ ላሉት ተሽከርካሪዎች የሚያስከፍሉትን ዓረቦን ቅናሽ አለው፡፡  

ሪፖርተር፡- ጂፒኤስ ስለተገጠመለት ብቻ የኢንሹራንስ ክፍያው ይቀንሳል ማለት ነው?

አቶ ሰለሞን፡- አዎ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህንን አሠራር ለመተግር እየተሞከረ ነው፡፡ እነዚህን ተሽከርካሪዎች ኢንሹራንስ ኩባንያዎች መከታተል የሚችሉበት ዕድል አላቸው፡፡ አደጋ ቢደርስ ስለአደጋው ሙሉ መረጃ እንዲኖራቸው ያግዛቸዋል፡፡ አደጋው እንዴት ደረሰ የሚለውን ለማወቅ ይረዳቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የሚሩበት የመረጃ ሥርዓት ክፈትት ነበረበት፡፡ አሁን ግን በማስረጃ የተደገፈ መረጃ ስለሚኖራቸው የተሽከርካሪውን ታሪክ በቀላሉ አግኝተው መረጃውን ያጠናቅራሉ፡፡ ይህንን ሥራ በመድን ድርጅቶች ለመተግበር ሒደቶች ተጀምረዋል፡፡ ከኢትዮጵያ መድን ድርጅት ጋር የጀመርነው ሥራም አለ፡፡ በነገርህ ላይ ለባንኮችም ይጠቅማቸዋል፡፡ ገንዘባቸውን ሲያንቀሳቅሱ በቀላሉ ሊቆጣጠሩ ይችላሉ፡፡ የገንዘቡን ፍሰት ከማዕከል ሆነው ያለ ችግር መቆጣጠር ይችላሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች