ከአንድ ዓመት በፊት ለፈረንሣይ መንግሥት ይሠሩ ነበር፡፡ ሥልጣናቸውን በቅርቡ ለሚያስረክቡት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ኦላንዴ የኢኮኖሚ አማካሪም ነበሩ፡፡ ለፈረንሣይ የኢኮኖሚ ሚኒስትርም ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከ15 ቀናት በፊት ፈረንሣያውያን ፕሬዚዳንታቸውን ለመምረጥ ባደረጉት የመጀመሪያ ዙር ምርጫ፣ የቅርብ ተቀናቃኛቸውንና የቀኝ አክራሪ ፓርቲ ብሔርተኛዋን ማሪን ለፔንን አሸንፈው፣ በአውሮፓ ኅብረት ላይ የተጋረጠውን የመበታተን ሥጋት አቅልለው ነበር፡፡ ፈረንሣያውያኑ እሑድ ሚያዝያ 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ባደረጉት የማሳረጊያ ምርጫ ደግሞ፣ የአገሪቱን የፕሬዚዳንትነት መንበር ለመቆናጠጥ ከሕዝባቸው ይሁንታን አግኝተዋል፡፡
የ39 ዓመቱ ኢማኑኤል ማክሮን ከ66 በመቶ በላይ የምርጫ ድምፅ በማግኘት ለአገሪቱ ፕሬዚዳንትነት የተመረጡ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንታዊ ቃለ መሃላቸውንም ግንቦት 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ይፈጽማሉ፡፡
እ.ኤ.አ. በ1767 ተወልዶ በ1821 የሞተው የፈረንሣይ የጦር መሪና የመጀመሪያው ንጉሥ ናፖሊዮን ቦናፓርት በኋላ ወጣቱና መልከ መልካሙ የፈረንሣይ መሪ የተባሉት ማክሮን፣ ‹‹ኤን ማርቼ›› የተባለውን ፓርቲያቸውን ካቋቋሙ ያስቆጠሩት የዓመት ዕድሜ ቢሆንም፣ መልካም ዝናንና ገጽታን ማትረፍ ችለዋል፡፡
ኤን ማርቼ ፓርቲ 577 ዕጩዎችን በሰኔ ወር ለፓርላማ ምርጫ እንደሚያሳትፍ ያሳወቀ ሲሆን፣ ከእነዚህ 50 በመቶ ያህሉ ከሲቪል ማኅበረሰቡ ይውጣጣሉ ተብሏል፡፡ ሃምሳ በመቶው ድርሻ ደግሞ ለሴቶች ይሰጣል፡፡ በኤን ማርቼ ዓርማ ሥር የሚወዳደሩ ዕጩዎች ከአውራ ፓርቲ ያላቸውን ግንኙነት ማቋረጥ የማይጠበቅባቸው ሲሆን፣ ለሁለት ፓርቲዎች በአንዴ መወዳደር ግን አይችሉም፡፡ የአውሮፓ መፈራረስን ይታደጋሉ ለተባሉት ማክሮን የጀርመኗ መራሒተ መንግሥት አንገላ መርከል የማክሮንን ማሸነፍ፣ ‹‹የአውሮፓ ኅብረትን የማስቀጠል ዘመቻ የሚያጠናክር መሪ›› ሲሉ ሲገልጹ፣ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው በፈረንሣይና በሩሲያ መካከል የተፈጠረውን አለመተማመን በጋራ ለመፍታት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በፈረንሣይ የካፒታሊስት ርዕዮተ ዓለም አውጋዦች ደግሞ ማክሮንን ተቃውመው ሠልፍ ወጥተዋል፡፡ ሆኖም ማክሮንን ከለፔን ጋር አወዳድረው የጻፉ የፖለቲካ ተንታኞች፣ ማክሮንን አዎንታዊ ምልከታ (ፓዘቲቭ) ሲሏቸው ለፔንን አሉታዊ ናቸው ብለው ፈርጀዋቸዋል፡፡ እንደ ምሳሌም ማክሮን በንግግሮቻቸው ሁሉ አዎንታዊ መልዕክቶችን ሲያስተላልፍ ለፔን ደግሞ በስደተኞች፣ በአውሮፓ ኅብረትና በሥርዓቱ ላይ ነቀፋ መሰንዘራቸው ለውድቀት ዳርጓቸዋል ብለዋል፡፡
የማክሮን ፖሊሲዎች
ማክሮን ፈረንሣይን ወደፊት ያራምዳሉ፣ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በቀጣይ ይሠራሉ ያሏቸውን የፖሊሲ መነሻዎች አስቀምጠዋል፡፡ ቢቢሲ ማክሮን ለፈረንሣይ ብሔራዊ መታደስን ያመጣሉ የሚሏቸውን የፖሊሲ አቅጣጫዎች አስፍሯል፡፡
ኢኮኖሚ
ገበያ መር የሆነና ሉላዊነትን (ግሎባላይዜሽን) የሚያቀነቅን ኢኮኖሚን በፈረንሣይ ለማስፈን ይፈልጋሉ፡፡ በአገሪቱ የወደቁ ቢዝነሶችን የማይደግፉ ሲሆን፣ የሚንገዳገዱትንና ለሠራተኞቻቸው ደመወዝ መክፈል ያልቻሉት ላይ በማነጣጠር ድጋፍና ሥልጠና የሚያደርግ ፖሊሲ እንደሚያሰፍኑም ቃል ገብተዋል፡፡
ስልሳ ቢሊዮን ዩሮ የበጀት ቁጠባ እንዲኖር በማስቻልም በአውሮፓ ኅብረት የተቀመጠውን ከጠቅላላ የምርት ገቢ ሦስት በመቶ ጉድለት ገደብ ጠብቀው የአገሪቱን ኢኮኖሚ እንደሚመሩ ይጠበቃል፡፡ ለመሠረተ ልማት፣ በኢንቨስትመንት፣ ለዲጂታል ፈጠራና ለአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት 50 ቢሊዮን ዩሮ የሚመድቡ ሲሆን፣ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ቃል የገቡትን የኮርፖሬሽን ታክስ ቅነሳ አሁን ካለበት 33.3 በመቶ ወደ 25 በመቶ ዝቅ ያደርጋሉ ተብሏል፡፡
ሠራተኞች
የሠራተኞችን የመግዛት አቅም ለማጠናከር፣ በየወሩ ለማኅበራዊ ዋስትና የሚከፍሉትን ገንዘብ እንዲቀንስ ያደርጋሉ፡፡ በፈረንሣይ በወር 2,200 ዩሮ የተጣራ ደመወዝ የሚያገኝ ግለሰብ በዓመት 500 ዩሮ ለማኅበራዊ ዋስትና የሚከፍል ሲሆን፣ ማክሮን ይህ ገንዘብ መቀነስና የሕዝቡ የመግዛት አቅም መጠናከር እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡ ድርጅቶች በሳምንት 35 ሰዓታት መሥራት የሚችሉበትን ዕድል ማመቻቸት፣ የጡረታ ዕድሜ ባለበት 62 እንዲቆይና የጡረታ ሥርዓቱ እንዲሻሻልም ፍላጎታቸው ነው፡፡
አውሮፓ
ማክሮን በአውሮፓ ኅብረት መጠናከር የሚያምኑ ቢሆንም፣ አንዳንድ መሻሻሎች እንዲደረጉ ይፈልጋሉ፡፡ ከኅብረቱ አባል አገሮች ውስጥ 19 ያህል የሚገበያዩበት ዩሮ ነው፡፡ እነዚህ አገሮች በኅብረቱ ውስጥ የተለየ በጀት፣ የገንዘብ ሚኒስትርና ፓርላሜንት እንዲኖራቸውም ይፈልጋሉ፡፡ እንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት ከመውጣቷ ጋር ተያይዞም፣ የኅብረቱ የገበያ ሕግ በሁሉም አገሮች ላይ ተፈጻሚ መሆን አለበት የሚል አቋም ይዘዋል፡፡ የአውሮፓ ኅብረት በኅብረቱና በካናዳ መካከል እንዳለው የንግድ ስምምነት ሁሉ፣ ሌሎች ነፃ የንግድ ስምምነቶችን እንዲያደርግም በኅብረቱ ውስጥ የአሠራር መሻሻሎችን የሚደግፉ ፖሊሲዎች መውጣት አለባቸው ይላሉ፡፡
የውጭ ግንኙነት
ማክሮን ከተቀናቃኛቸው ከለፔን በተሻለ የውጭ ግንኙነታቸውን መልካምና በመቻቻል ላይ ያተኮረ ማድረግ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ሩሲያን በተመለከተ፣ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ባላት አለመግባባት የተጣለባትን ማዕቀብ ይደግፋሉ፡፡ ላለፉት ስድስት ዓመታት በእርስ በርስ ጦርነት በምትታመሰውና ሩሲያና አሜሪካ ፅንፍ ይዘው ሰላሟን ያደፈረሱባትን ሶሪያን የሚመሩት በሽር አል አሳድ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ድርድር ከመጀመሩ በፊት ስለፈጸሙት ወንጀል መጠየቅ አለባቸው ብለውም ያምናሉ፡፡ የውጭ ዕርዳታን በተመለከተ ለአፍሪካ የሚደረገው ዕርዳታ እንዲጨምር የሚፈልጉ ቢሆንም፣ አገሮች የራሳቸውን የመከላከያ አቅም በራሳቸው መገንባት አለባቸው ይላሉ፡፡
የስደተኞች ጉዳይ
ማክሮን በስደተኞች ላይ ያላቸው አቋም እንደ ጀርመኗ መራሒተ መንግሥት አንገላ መርከል ነው፡፡ ስደተኞችን የሚያገል ፖሊሲ አይኖራቸውም፡፡ ሆኖም የአውሮፓ ኅብረት ድንበሮችን የሚጠብቁ አምስት ሺሕ የልዩ ኃይል አባላት መመደብ እንዳለባቸው ይገልጻሉ፡፡ የፈረንሣይን ዜግነት ለማግኘት ደግሞ በፈረንሣይኛ ቋንቋ አጠቃቀም እጅግ በጣም ጥሩ የሚል ደረጃ ማግኘትን ዋናው መሥፈርት የሚያደርጉ ሲሆን፣ ሁሉም የሃይማኖት መሪዎችም የፈረንሣይን ዓለማዊ እሴት አስመልክቶ ጥልቅ ሥልጠና እንዲሰጣቸውም ያደርጋሉ ነው የተባለው፡፡
መከላከያና ደኅንነት
በፈረንሣይ አሥር ሺሕ አዳዲስ የፖሊስ አባላት እንዲመለመሉ ማድረግ፣ በአፍሪካ የወታደር ካምፕ አስፈላጊነትን መከለስ፣ እ.ኤ.አ. በ2025 ከአገሪቱ ጠቅላላ ምርት ሁለት በመቶውን ለኔቶ (የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት) ለመመደብ፣ ለአውሮፓ ኅብረት መከላከያ ኃይል የመከላከያ ፈንድ እንዲኖር፣ የጋራ የመከላከያ ፕሮጀክትና ይህንን የሚመራ ቋሚ የኅብረቱ ዋና ጽሕፈት ቤት እንዲመሠረት እንደሚያደርጉ ተገልጿል፡፡
ትምህርትና የአካባቢ ጥበቃ
በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በተደጋጋሚ በማክሮን ሲነሳ የነበረው አጀንዳ የገጠር ትምህርት ቤቶች ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ በአገሪቱ ልዩ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል በሚባሉ አካባቢዎች በአንድ ክፍል ውስጥ አንድ አስተማሪ 12 ተማሪዎችን ብቻ እንዲያስተምር የሚያደርጉ ሲሆን፣ በትምህርት ቤት ግቢ ተማሪዎች የሞባይል ስልክ ይዘው መገኘትም አይፈቀድላቸውም፡፡ 18 ዓመት ሲሞላቸው በተማሪ 500 ዩሮ ያስወጣል የሚባለውን ‹‹ካልቸራል ፖስ›› ብሔራዊ ማንነታቸውን የሚያውቁባቸው ክህሎቶች ማግኘት ይችላሉ፡፡ ለትምህርት ቤቶች ከሚሰጡ ምግቦች ገሚሱ የተፈጥሮ ሆነው አገር ውስጥ እንዲመረቱና ፈረንሣይን አረንጓዴ ቴክኖሎጂን በማራመድ መሪ ማድረግም ከፖሊሲ አቅጣጫዎቻቸው ይመደባሉ፡፡
ፖለቲካ
ማክሮን ወደ ፖለቲካው ዓለም ከተቀላቀሉ የዓመት ዕድሜ ቢኖራቸውም፣ ተቀባይነትን አግኝተዋል፡፡ በሕዝባቸው ከመመረጥ አልፈውም የአውሮፓ ኅብረትን ለመበታተን የተነሳውን የፖለቲካ ውዥንብር በመመረጣቸው ብቻ ረገብ አድርገዋል፡፡ ለዘብተኛው ማክሮን፣ ከኅብረቱ በዘለለም በአገራቸው ተቀባይነትን ያገኘ የፖለቲካ ማዕበል አስነስተዋል፡፡ ለፔንን የመረጡና ማክሮንን የሚቃወሙ ወጣቶች ማክሮንን ‹‹ኒዮ ሊበራል›› በማለት የኢኮኖሚ ማሻሻያዎቻቸውን አይቀበሉም፡፡ ሆኖም ማክሮን ሆስፒታሎችን ሳይጨምር የመንግሥት ሠራተኞችን በ120 ሺሕ፣ በፓርላማ ያሉትን የፓርላማ ምክትሎችን እንዲሁም ሴናተሮችን በአንድ ሦስተኛ የመቀነስ ዕቅድ አላቸው፡፡ የፓርላማ አባላትም አማካሪ ሆነው እንዳይሠሩ ማድረግም ዓላማቸው ነው፡፡