Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በምልክት ወይስ በዜማ እንግባባ?

እነሆ መንገድ። ከአዲሱ ገበያ ወደ ፒያሳ ልንንደረደር ነው። ወያላው ያለ ከልካይ ያሻውን ይዘላብዳል፡፡ “ምን አፍሽን ታሾይብኛለሽ? ሺሻ መሰልኩሽ?” ይላታል ራሱ ጎትጉቶ ሦስተኛው ረድፍ ላይ ቦታ የሰጣትን ጭምት። “ሲያልፍም አይነካኝ። ሙያህን መዘገብህ ነው? የጨዋ ልጅ ነኝ ብታውቀኝ፤” ስትለው ተበሳጭታለች። “ኧረ እናንተ ልጆች በፈጣራችሁ ተው? ደግሞ ብላችሁ ብላችሁ ይኼን ምናምንቴ ነገር መሰዳደቢያ ታደርጉት?” መሀል መቀመጫ ላይ ጥቁር ባርኔጣ ከደፋ ጎልማሳ አጠገብ የተቀመጠች  ወይዘሮ ትገላግላለች። “ታዲያ በዚህ በሠለጠነ ዘመን ሙዝ፣ ፓፓያ፣ እያልን እንሰዳደብ? ለወረትና ለዓመል እንኳ ፍራፍሬ አንበላ፣ ቅጠል እንጂ. . .” ይላል ጎልማሳው። “ታዲያ ይኼ መሠልጠን ነው? መሰይጠን ነው እንጂ፤” ወይዘሮዋ ታቀባብላለች። “ግምገማ አልተሰበሰብንም አርፋችሁ ተቀመጡ፤” ወያላው አፄ በጉልበቱ ነገር ነው። “ደግሞ ብለህ ብለህ ወደ እኛ አፍ ዞርክ?” ሲለው ጎልማሳው ወያላው ተገላመጠ።

“ወንድ፣ ወንዱ ላይማ ዝም ትላለህ። ቆይ ብቻችንን እንገናኝ፤” ብሎ ደግሞ ሾፌሩ የወያላውን ቀልብ ይገፈዋል። ይኼን ካለ በኋላ ሬዲዮን ይከፍታል። ሰዓቱ የዜና ነው። “አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በየአካባቢያቸው ያልተከደኑ የፍሳሽ ቱቦዎች የጤናና የአካል ጉዳት እያደረሱባቸው እንደሆነ ተናገሩ. . .” ብሎ ዜና አንባቢው፣ “የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽም የነዋሪዎቹን አስተያየት ሙሉ ለመሉ እንደሚጋራ አስታውቋል. . .” ሲል መጨረሻ ወንበር የተቀመጡ ወጣቶች የአረረ ማሽላ ዓይነት ሳቅ ሳቁ። “ኧረ እኛም እንሳቅ፤” ሲላቸው ጎልማሳው፣ “አትሰማም እንዴ? አሁን እስኪ ማን ይሙት ያልተከደኑ ቱቦዎችና ጉድጓዶች የተከሰቱት አሁን ነው? ስንት ፆም ይዘን አልፈሰክንም?” ሲል ጎልማሳው ፈገግ ብሎ፣ “ይኼንንስ ማን አየብን? ቢያንስ ውጤቱን ትተህ አፋችን አንድ እየሆነ መምጣቱን አመስግን፤” ብሎ ጠቀሰው። ‘የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የአፍ ነገር ሲሆን አይሠራም ማለት ነው’ ያለውን ተሳፋሪ ወያላው መንጥሮ ማውጣት ቢችል ያለጥርጥር ይወርድ ነበር። ወይ አፍና አፈኛው ዘንድሮ!

ጉዟችን ተጀምሯል። ተሳፋሪው አፍ አፉን የሚለውና የሚያይበት በዝቶ በዝምታ ይናጣል። ዓይን ተራውን ጣራና ጌጡን ያማትራል። ይኼኔ አንድ ጥቅስ አነበብን። ‘ሥራ ለፈታ ሰው ያንን ቲቪ አውሰው፤’ ይላል። “እኔ እኮ እዚህ አገር በሰው ምርጫና ዓይን ዕጣ የሚያወጣው አልበዛባችሁም?” ትላለች አንዷ። “ዓይቶ ማለፍ እያለና ሰምቶ መቻል ሳለ አንቺስ ምን ነዳጅ ያስጨርስሻል? ያውም ጠፍቶ ላልጠፋ ነዳጅ ለመሠለፍ?” ይላታል ከጎኗ። ጎልማሳው ደግሞ፣ “ሲቸግር ምን ታድርግ? ይኼው አሁን እኔ የምጓዘው ለሽምግልና ነው። ድምፃቸው የማይሰማ የትዳር አጋሮች ናቸው። ስንቱን ክፉ ጊዜ ያሳለፉ። ካልጠፋ ነገር በምን ተጣሉ አትለኝም? በዚህ በመከረኛው ቲቪ፡፡ ራት አላት። እሺ አለችው። እሺ ብላው ቆማለች። ደግሞ ራት ሲል ሄዳ ወጡን ብቻ አመጣች። ደግሞ በዚያው ቆማ ቀረች። እሱ ርቦታል። ያልፈጠረበትን ተንስቶ በጥፊ መታት ይኼው ልጆቿን ትታ ትናንት ማታ እንደወጣች አደረች፤” ሲል ተሳፋሪው ወደ አለመደማመጥ ባህሉ ተጣደፈ።

 “ደግ አደረጋት፤” ሲል አንዱ፣ “ምን ማለት ነው ደግ አደረገ? እሱ ወጥና እንጀራ ለማቅረብ አንሶ ነው? ነውር አይደለም እንዴ? ያውም በዚህ በሠለጠነ ጊዜ?” ትላለች ነገር ቆስቋሻ። ከሾፌሩ ጀርባ ያሉት ደግሞ፣ “ምን ማለት ነው በዚህ ጊዜ ማለት? መጽሐፍ ሚስት ፈቃዷ ወደ ባሏ ነው አይልም እንዴ?” ብሎ ነገር ሲያከር፣ “እሱስ ይውደዳት፣ እንደሚሰበር እንቁላል ይንከባከባት እንጂ ካሻው ያቅምሳት፤›› ይላል ብሎ ከጎኑ ያሉትን ሰቅዞ መያዝ። ታክሲያችን በተደበላለቀ ቁጭት ስትናጥ በአንዴ ለዛዋ ጠፍቶ እጅ እጅ አለች። ሰው የዓኑን ነበር? የእጁን አያጣም የሚባለው?

መስኮት ተከፍቶባቸው የሚታገላቸውን ንፋስ ለመከላከል በአሳር የሚጠበሱ አዛውንት ጨዋታ ያነሳሉ። “አዳሜ እንዲህ የሆድሽን አውጥተሽ እያራገፍሽ የመናገር ነፃነት ታፍኗል እያልሽ ‹አሳይለም› ትጠይቂያለሽ! ወዬውልሽ እያንዳንዳሽ! በፍርድ ቀን የምትመልሽውን አዘጋጂ!” አሉ። “እኔ የሰማሁት ግን የመጻፍ እንጂ የመናገር ነፃነት ችግር አለ ሲባል አይደለም፤” አለች እዚያው ቅርባቸው። “የተጻፈ ሕይወት እየኖራችሁ ማነው አትጻፉ ያላችሁ በእስጢፋኖስ?” አዛውንቱ  ነገሩን ማጠጠርና ማዋዛት ይዘዋል። “ምነው አባት ሕገ ሰማይና ሕገ መንግሥት ከተለያዩ ቆዩ እኮ፤” ሲላቸው ደግሞ ያ አጭሩ ነገር ጫሪ፣ “እሱንማ መርጣችሁ ነዋ። የሰው መንግሥት ድሮም ወጉ የሰው ነው። ምነው ግን የዛሬ ልጆች ይኼ ይኼ ማስተዋል ርቋችሁ ከእባብ እንቁላል የዶሮ ጫጩት ትጠብቀላችሁሳ? ደግሞ ይኼንንም ፌስቡካችሁ ላይ ለቅልቁና አነካኩኝ አሉዋችሁ፤” ሲሉ ተሳፋሪው ሳቀ።

ጎልማሳው ዘወር ብሎ፣ “ዘመኑ የመነካካት ነው አባት። ሳይነካኩ መኖር ከብዷል፤” ሲላቸው ደግሞ፣ “ኧረ እኔስ የከበደኝ ሌላ ነው፤” ብለው ልብ አንጠልጥለው ዝም አሉ። “ይንገሩና!” ጎልማሳው ወተወታቸው። “አትኖረው ይመስል ምኑን ልንገርህ?” አሉት። “እሱን እኮ ነው የምልዎት፤” ሲላቸው፣  “ምን ይላል ሰውዬው? የራሴን ሐሳብ መልሰህ እየነገርከኝ ነው ‘እሱን እኮ ነው የምልዎት’ የምትለኝ? አዲስ ሐሳብ ሳታፈልቁ አዲስ ራዕይ ሳትቀርፁ ነው ታዲያ ማይኩ የጥቂቶች ብቻ ሆነ ብላችሁ የምትጮሁት? ለመቃወም ለመቃወምማ ሰይጣንም ይቃወማል እኮ? ቀናነትን በጠማማነት ለማሸነፍ የመረጠው የትግል ሥልት ግን የት አደረሰው? የትም!” እያሉ ያሻቸውን ነካክተው ጠያቂና ሞጋቾቻቸውን ዝም አሰኙ። መቼም ዕድሜ የጠገበ ሰውና ሥርዓት ዝም የሚያሰኝበት ነገር አያጣም!

ጉዟችን ቀጥሏል። ወያላው በሞባይሉ ሒሳብ እያሰላ መልስ ያድለናል። “ኧረ ይቆጥርብሃል ብዙ አትጠቀም፤” ይለዋል አንዱ። ወያላው፣ “እኔን ነው?” ይጠይቃል። “ለአንተም ለሞባይልህም የተላለፈ መልዕክት ነው። ቴሌ ካልጻፈው በቃ መልዕክት አናነብም አይደል?” ይላል መጨረሻ አካባቢ ሌላው። “ምነው የእናንተ ቤት አከራይ ቴሌ ነው እንዴ መብራት አጥፉ ብሎ የሚልክባችሁ?” ጎልማሳው ነገሩን ወዳመጣው ተሳፋሪ ዞሮ ጠየቀ። “እሱስ ለጨዋታ አልኩት እንጂ ሁላችንም በየቤታችን መብራት እልም ሲል አድብቶ ነው፤” ማለት። “አድብቶ ስትል?”  ከጎኔ ያለችው በጥያቄ ማፋጠጥ። “እንጀራ ልንጋግር ስንል፣ ገና ቁሌት ስናቁላላ፣ ሞባይላችን ቻርጅ አድርጉኝ ከማለቱ ነዋ. . .” አላት። “ይቅርታ አድርግልኝ አሁን ከጠቀስካቸው ነገሮች ሁሉ አድብቶ የሚያስብል ነገር አላገኘሁም፤” አለው ከወደ ጋቢና። “እንዴ መብላት የህልውና ማገር እንደሆነ ለማስመስከር ተደራጅተን እናብስል? ዘንድሮ እኮ የተናጠል መብት አላዋጣም ጎበዝ፤” አለ ሰውዬው።

“ስንቱ የመብራት መቆራረጥ ንግዱንና ሥራውን እያስተጓጎለበት፣ ግፋ ቢል ፌስቡክ ከፍቶ የሚፈዝበት ስልኩ ቻርጅ ሲጨርስ መብራት ሄደብኝ ብሎ ሰው የአገሩን ደካማ ጎን አጋልጦ ይሰጣል?” ስትለኝ ከጎኔ ሰውዬው ሰምቷት ኖሮ፣ “እሱስ ልክ ነሽ። ከመብራት መቆራረጡ በላይ እርስ በርሳችን የጋራ ችግራችንን በተመለከተ የአቋም መዋዠቅና መቆራረጥ እያለ እኔም ሰው አገኘሁ ብዬ ይኼን መናገር አልነበረብኝም፤” ብሎ በነገር ጎሸማት። እንዲህ ተፋጠን መሽቶ እየነጋ የኃይል መቆራረጥ ችግር በአንድም በሌላ ካላቆራረጠን እንላቀቃለን ታዲያ? ‘ደግሞ ይኼን ሰምታችሁ መስመሩን ቆራርጡት አሉዋችሁ’ ሲሉ የምንሰማቸው ወይዘሮዋን ነው!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ወይዘሮዋና ጎልማሳው በአንድ አንድ ተዛምደው ስለጥቁሩ ባርኔጣ ይነጋገራሉ። “ምነው የቅርብ ሰው ነው?” ስትል ወይዘሮዋ ሐዘን ላይ መስሏት ጎልማሳውን ትጠይቃለች። “የለም። ማንም አልሞተም። ብቻ ወሬ የሚገለው በዛ። በሆነ ባልሆነው ባልተጨበጠ ትርክት ገደል የሚገባው ላቀ፤” ካላት በኋላ፣ “እና ይኼ እኔ የጀመርኩት አዲስ ምልክት ነው። የሰው ልጅ አዕምሮን የመሰለ አስገራሚ ነገር ተሠርቶ ተሰጥቶት በተለይ በተለይ እኛ ዘንድ ሲሆን የምንጠቀምበት የሚያመነጨውን አመክንዮ ሳይሆን ስሜቱን ብቻ ነው። ለዚህ ነው የእስካሁኑ ይበቃል፣ የኑሯችን ከልና ደመና ምንጩ ጭንቅላታችንን ልክ እንደዚህ ጥቁር ኮፍያ የተኮፈሰበት የጥመት አስተሳሰብ ነው ለማለት ነው፤” ብሎ ኮራ ብሎ እንደ መደላደል ሲያደርገው፣ “ወይ አማርኛ። በደቦ እያስጨፈለቀ ገደለን እኮ? እኛ እኛ እያልን በፍረጃ የምንገጫጨው እኮ ከከተማችን የትራፊክ አደጋ ባሰ፤” ትላለች ከወዲያ።

መጨረሻ ወንበር ያሉት ወጣቶች ደግሞ በአንድ ድምፅ ‘ላይክ አድርገነዋል’ ብለው ጎልማሳውን ጫር ሲሉት፣ “እንደ ሰሜን ኮሪያ የማያጠፉትን እሳት የሚጭሩ ዘንድሮ መግቢያ ቀዳዳቸውን አውቀነው፤” ብላ ከጋቢና ሌላው ታስተጋባለች። ወያላው “መጨረሻ” ብሎ በሩን ሲከፍተው ከሐሳብ ይልቅ ስሜት የሚሰጠውም የማይሰጠውም ጭፈራና ዘፈን ብቻ ጎላ ብሎ በሚደመጥበት ጎዳና ሿ ብለን ፈሰን ትርምሱን ተቀላቀልን። የተቀላቀለው በዝቶ ኩልል ባዩ ኩሉን መጠበቅ አቅቶት ያልሆነውን ሲሆን፣ በመመሳሰል ጎዳና የምናትመው አሻራ አስጨፍልቆ ሊያፈራርደን ደግሞ ሌላ ፌርማታ ይጠራናል። በምልክት ወይም በዜማ ካልተግባባን ምን ቀርቶልን ይሆን? መልካም ጉዞ!

 

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት