Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርፌዴሬሽኖችና የፌደራል መንግሥቱ ዋና ከተሞች

ፌዴሬሽኖችና የፌደራል መንግሥቱ ዋና ከተሞች

ቀን:

በኃይለየሱስ ታዬ (ዶ/ር)

የፌዴሬሽን ቅርጽ ያለው የፌደራል ሥርዓት የሚከተሉ አገሮች የአስተደዳር መዋቅራቸው ሥልጣንን በመከፋፈል ላይ የተመሠረተ ከመሆኑ ጋር ተያይዞና የሥልጣን ክፍፍሉም የጋራና የተናጥል ሥልጣኖችን ያማከለ በመሆኑ፣ ፌዴሬሽኖቹ ቢያንስ ከአንድ በላይ መንግሥታት ያቀፉ ናቸው፡፡ በመሆኑም የፌደራል መንግሥቱን ጨምሮ እያንዳንዱ መንግሥታት የየራሳቸው መንግሥታት መቀመጫ ወይም ዋና ከተማ ይኖራቸዋል፡፡ ስለሆነም ፌዴሬሽኖች ብዙ የሆኑ ማዕከላት የሚፈጠሩባቸውና  የባለብዙ ማዕከላት ባህሪ የተላባሱና ሁሉም መንግሥታት በየአካባቢያቸው ትልልቅ የአስተዳደር፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ማዕከላት የመፍጠር ዕድልን የሚሰጥ፣ ከአንድ ማዕከል አስተሳሰብና የልማት አቅጣጫ ወደ ባለብዙ ማዕከላት አስተሳስብና የልማት አቅጣጫ የሚያመራ የአስተዳደር ሥርዓት ነው፡፡

ይህ እደተጠበቀ ሆኖ የጋራ ሥልጣናቸው ዋና መገለጫና ማዕከል የሆነው የፌደራል መንግሥቱን ዋና ከተማ ወይም መቀመጫ የሚሆን ቦታን፣ የአስተዳደር ሁኔታ የመሳሰሉ ጉዳዮችን የመወሰን ሁሉንም የፌዴሬሽኑ አባል መንግሥታት የሚመለከት ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም የፌደራል ሕገ መንግሥቱ በሚፀድቅበት ወቅት ከፍተኛ ውይይት ተደርጎበትና የፌዴሬሽኑን ባህሪና ሕገ መንግሥቱ ያስቀመጠውን ራዕይ በሚያመላክት መንገድ፣ የፌደራል መንግሥቱ መቀመጫ በአዲስ መልክ እንዲቆረቆር ይደረጋል፡፡ ወይም ደግሞ በተለያዩ አግባቦች ቀደም ሲል የነበሩ ከተሞች በፌደራል መንግሥቱ ዋና ከተማነት እንዲቀጥሉ ይደረጋል፡፡

እስካሁን በፌደራል መንግሥታት ዋና ከተሞች አመሠራረትና አስተዳደር ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶች ስፋት ያላቸው ሲሆኑ (ለምሳሌ ናግል 2013፣ ጊሊላንድ 2013፣ አንድሪው 2013 ሁሉም እ.ኤ.አ.)፣ ዝርዝር የፌደራል ዋና ከተሞች አመሠራረት፣ እያንዳንዱ ከተሞች ሲመሠረቱ የነበሩ ነባራዊ ሁኔታዎች፣ ማዕከል ያደረጓቸውን መነሻዎች፣ የአስተዳደራዊ ወሰናቸውን ያገኙበት አግባብ፣ የተከተሉዋቸው አደረጃጀቶች፣ የሕዝቦችን ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎና የፌደራል ሥርዓቱን ከማጠናከርና የፌደራል ይዘቱን ከማንፀባረቅ አኳያ የሄዱበት አግባብ ሰፊ ትንታኔና ቦታም ስለሚጠይቅ፣ በቀጣይም በቀጣይ ወደ ተግባር እንደሚገባ ከታሰበው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 49/5 አኳያ በቀጣይ በየደረጃው ይኖራሉ ተብለው በሚገመቱት ውይይቶች የመጻፍና የመወያይት ዕድሉ ይኖራል የሚል ታሳቢ በማድረግ፣ ይህ ጽሑፍ በፌዴራል መንግሥታት ዋና ከተሞች/መቀመጫዎች አደረጃጀት ዙሪያ መሠረታዊ በሆኑ መነሻ ጉዳች ላይ በመወሰን የቀረበ ነው፡፡   

በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች አሁን በዓለም ላይ የሚገኙ ፌዴሬሽኖች የፌዴራል መንግሥታቱን ዋና ከተሞች አስተዳደራዊ አደረጃጀት በሦስት ዋና ዋና ሞዴሎች ይፈርጇቸዋል፡፡

የመጀመሪያው ሞዴል የፌዴራል ዲስትሪክት ሞዴል ሲሆን ይህ ሞዴል ዋሽንግተን ዲሲ፣ አቡጃ፣ ብራዚሊያ፣ ካንቤራ፣ ቦኖ ሳይረስ፣ ካራካስ፣ ኳላ ላምፑር፣ ሜክስኮ ሲቲ፣ ኒው ዴህሊና አዲስ አበባ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የሚከተሉት የአስተዳደር ሞዴል ነው፡፡ የፌደራል መንግሥቱ ዋና ከተማ በራሱ እንደ ሌሎቹ የፌዴሬሽኑ አባል መንግሥታት እኩል የሆነ መንግሥት ያለው የከተማ መንግሥት (City State) ሳይሆን፣ ወይም በአንድ የክልል መንግሥት አስተዳደር ሥር ሳይሆን  ለፌደራል መንግሥቱ በቀጥታ ተጠሪ ሆኖ የከተማ አስተዳደሩ የራሱ መተዳደሪያ ቻርተር ኖሮት የሚተዳደር ነው፡፡ የፌደራል ዋና ከተማው ያረፈበት ቦታ ወሰንም በሚገባ ተወስኖና ታውቆ በፌደራል መንግሥቱ በባለቤትነት ተይዞ የሚተደዳር ነው፡፡ በፌደራል መንግሥት ዋና ከተማው የሚኖሩ የከተማው ነዋሪዎችም ዴሞክራሲዊ በሆነ አግባብ ራሳቸውን በራሳቸው በየደረጃው የሚያስዳደሩበት አግባብ የሚዘረጋበትና  በፌደራል ደረጃም እንደማንኛውም የአገሪቱ ዜጋ በተወካዩቻቸው አማካይነት በታችኛው ምክር ቤት (በሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት) ውክልና የሚያገኙበትን ሥርዓት ያስቀምጣሉ፡፡

 በላይኛው ምክር ቤት በብዙዎች ፌዴሬሽኖች ውክልና የሌላቸው መሆኑ አንዱ የአደረጃጀቱ ድክመት እንደሆነ ይተቻል፡፡ ይህ አደረጃጀጀት የፌደራል መንግሥቱ የጋራ በሆኑ ሥልጣኖች ዙሪያ ለሚያከናውናቸው ተግባራት አመቺ በሆነ መንገድ ከማንኛውም አባል የክልል መንግሥታት ጣልቃ ገብነት አንፃራዊ ነፃነት ኖሮት፣ የፌደራል መንግሥቱን ዋና ከተማ ወይም መቀመጫ በማደራጀትና ዋና ከተማውን ፌደራላዊ  የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ፣ የባህላዊና የኢኮኖሚዊ ይዘት እንዲላበስ ያደርጋል፡፡ የሁሉም የፌደራል አባል መንግሥታና ሕዝቦች ማዕከል እንዲሆን ለማስቻል ሰፊ ዕድል የሚሰጥ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ ለባለብዙ ብሔር ለሆኑ ፌዴሬሽኖች በአንፃራዊነት ተመራጭ ተደርጎ ይታያል፡፡

በፌዴሬሽኖች የፌደራል መንግሥቱ ዋና ከተሞች ከተዋቀሩባቸው ሌላው ሞዴል የከተማ መንግሥት (City State ) ሞዴል ነው፡፡ ይህ ሞዴል የፌደራል መንግሥቱ ዋና ከተማ የሆኑ ከተሞች አንድ ራሳቸውን የቻሉና የፌዴሬሽኑ እኩል አባል መንግሥታት ሆነው የሚደራጁበት ነው፡፡ አንዳንዴ በተሟላ ሁኔታ ባይሆንም ሌሎች የፌደሬሽኑ አባል መንግሥታት ሥልጣንና ኃላፊነት ይኖራቸዋል፡፡ በርሊን፣ ብራስልስ፣ ሞስኮና ማድሪድ ይህ ዓይነት አደረጃጀት ካላቸው የፌደራል መንግሥታቱ ዋና ከተሞች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በከተማ መንግሥታት ክልል ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች እንደ ማንኛውም በሌሎች የፌዴሬሽኑ አባል መንግሥታት ክልል ዉስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው የማስተዳደርና በጋራ ጉዳዩችም ላይ የመሳተፍ ዴሞክራሲያዊ መብታቸው የተረጋገጠ ነው፡፡

 በአንዳንድ እንደ ብራስልስ ባሉ የከተማ መንግሥታት በከተማው የሚኖሩ የተለያዩ ማኅበረሰቦች ባህላዊ መብታቸውን የሚተገብሩበት ዕድል በተለያዩ ማኅበረሰባዊ አደረጃጀቶች ይመቻችላቸዋል፡፡ ከዚህም በዘለለ የአውሮፓ ኅብረት መቀመጫ በመሆኑ ይህም ያለው አንድምታ በከተማው አጠቃላይ አደረጃጀትና አሠራር ላይ ተገቢው ቦታ ይሰጠዋል፡፡ ይህ አደረጃጀት በፌደራል ዋና ከተማው ለሚኖሩ ሕዝቦችና ሕዝቦቹ ለሚያዋቀሩት የራስ አስተዳደር የበለጠ አንፃራዊ ነፃነት የሚሰጥ ነው፡፡ የፌደራል መንግሥቱ በከተማው ላይ ያለው ወሳኝነት ዝቅ ያለ በመሆኑ፣ የፌደራል መንግሥቱ  የጋራ ሥልጣኑን በተገቢው መንገድ ለማስኬድ በከተማው ዙሪያ ለሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች መሰናክሎች ሊገጥሙት የሚችሉበት አጋጣሚዎች ሊኖሩ ቢችሉም፣ ተቋማዊ በሆነና በአግባቡ በተደራጀ የመንግሥታት ግንኙነት የሚያጋጥሙ ችግሮችን እያቃለሉ መሄድ የሚቻልበት አግባብ ይታያል፡፡

ሌላው በፌደራል ዋና ከተሞች አደረጃጀት አግባብ የሚታየው ሞዴል በአንድ የፌዴሬሽኑ አባል በሆነ መንግሥት ሥር ያለ የፌደራል መንግሥቱ መቀመጫ ነው፡፡ በዚህ አደረጃጀት ሥር ያሉ የፌደራል መንግሥቱ መቀመጫዎች በክልል መንግሥታቱ ሥር ካሉ የከተማ ማዘጋጃ ቤቶች የተለየ አደረጃጀት የሌላቸው ናቸው፡፡ ተጠሪነታቸውም በዋናነት ለፌዴሬሽኑ አባል ለሆነውና ከተሞቹ ለሚገኙበት የክልል መንግሥት ነው፡፡ በከተሞቹ የሚኖረው ሕዝብም በክልሉ ከሚገኙ ሌሎች ከተሞች እንደሚኖረው ሕዝብ ተመሳሳይ የሆነ የአካባቢያዊ አስተዳደርና በክልልና በፌደራል ደረጃ ውክልና ይኖረዋል፡፡ የዚህን መሰል አደረጃጀት በመከተል በምሳሌነት መጠቀስ የሚችሉት በርን፣ ኦቶዋና ኬፕታውን/ፕሪቶሪያ ናቸው፡፡ በአደረጃጀታቸው በመሀላቸው የተወሰነ ልዩነት ቢኖርም፣ እነዚህ ከተሞች ምንም እንኳን ለፌዴሬሽኑ አባል ለሆነ የክልል መንግሥት ተጠሪ ቢሆኑም የፌደራል ሥራዎችን ከማሳለጥ አኳያ ከፌደራል መንግሥት የበጀት ድጎማ የሚያገኙበት አግባብ ሊበጅ ይችላል፡፡  

በእነዚህ ከተሞች ላይ የፌደራል መንግሥቱ ለሚያከናውነው ተግባራት ሙሉ በሙሉ ከተሞች በሚገኙበት የፌዴሬሽኑ አባል መንግሥት ይሁንታ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የፌደራል መንግሥቱ ዋና ከተማውን ወይም መቀመጫውን የአገሪቱን ፌደራላዊ ባህሪ ባገናዘበ መንገድ ለመምራት የማይችልበትና ከተማዋ በምትገኝበት የክልል መንግሥት በጎ ፈቃድ እንዲንቀሳቀስ የሚገደድበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ምንም እንኳን ፌደራላዊ ሥርዓት በባህሪው ትብብርንና በጎ ፈቃድን መሠረት ያደረገ ቢሆንም፣ ይህኑ የማይቀርና የሚያጋጥም ተግዳሮት በተሳለጠና ተቋማዊ በሆነ የመንግሥታት ግንኙነት መፍታት የሚቻልበት አግባብ ፈጥሮ መንቀሳቀስ እየተለመደ መምጣቱ ይታወቃል፡፡

ከላይ በዝርዝር ለማብራራት እደተሞከረው እስካሁን በፌደራል ዋና ከተሞች ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶች በዓለም ላይ ያሉ የፌደራል ዋና ከተሞች ከሦስቱ ሞዴሎች አኳያ ለመፈረጅ የሞከሩ ቢሆንም፣ የሁሉም ከተሞች አደረጃጀት በሞዴሎቹ ውስጥም ሆነው ያለውና አንድ ናቸው ተብሎ ሊወሰድ አይችልም፡፡ ከተሞች ሲመሠረቱ ከነበረው ነባራዊና ኅሊናዊ ሁኔታ፣ እንዲሁም ፌዴሬሽኖች ሊመሠረቱ ያስቻሏቸውን መሠረታዊ መነሻ ሐሳቦችና ፌዴሬሽኖቹ ሲመሠረቱ ገዥ በሆነው የጋራ ሰነዳቸው ያስቀመጡትን የወደፊት ራዕይ መሠረት ባደረገ መንገድ የተደራጁ ሲሆን፣ በየጊዜው ከሚያጋጥሙ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ጋር ተያይዞ ከአንዱ ወደ ሌላ ሞዴል ሽግግር ያደረጉ ከተሞችም እንዳሉ ይታወቃል፡፡

ስለሆነም ሰሞኑን በማኅበራዊ ሚዲያዎች የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 49/5 ወደ ተግባር እንዲገባ ተዘጋጀ ተብሎ ይፋ በተደረገውና በመንግሥት ዕውቅና ባልተሰጠው ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ፣ የተለያዩ ጫፎችን የረገጡ ሐሳቦች እየተንሸራሸሩ ነው፡፡ በመሆኑም በቀጣይ የኢፌዴሪ መንግሥት ይህን አንቀጽ ወደ ተግባራዊ አፈጻጸም ለማስገባት በሚያደርገው የማስፈጸሚያ አዋጅ ዝግጅት በተለያዩ ደረጃዎች ሰፊ ውይይቶች ማድረግ አስፈላጊ መስሎ ስለሚታይ፣ የአገራችን የፌደራላዊ ሥርዓት ልዩ ባህሪያትና በዓለም ላይ ያሉ ጠቃሚ ተሞክሮዎችን መሠረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

 በኢፌዴሪ አንቀጽ 49 እንደተደነገገው የአዲስ አበባን ከተማ የፌደራል መንግሥቱ ዋና ከተማነት፣ እንዲሁም የሁሉም አባል ክልሎች ማዕከልነትና በከተማው የሚኖረውን ማኅበረሰብ በሕገ መንግሥት ማዕቀፍ ራሱን በራሱ የማስተዳደርና በጋራ ጉዳዮች ላይም እንደ አግባቡ የመሳተፍ ዴሞክራሲያዊ መብቱን ሲያስከብር፣ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በከተማዋ ላይ ያለውን ልዩ ፍላጎት ተመጋጋቢነት በሚያረጋግጥና የፌዴራል ሥርዓቱን ይበልጥ በሚያጠናክር መልኩ መተግበር ተገቢ ስለሚሆን፣ ለቀጣይ ይኖራሉ ተብሎ ለሚገመቱ ውይይቶች ውስን አስተዋጽኦ ለማድረግ ይህ አጭር ጽሑፍ  ቀርቧል፡፡

             ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በፌዴራሊዝም ጥናት ረዳት ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ወይም [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡      

      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...